Friday, May 24, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

እኔ የምለዉልንዘነጋው የማይገባንና የዘነጋነው የአፍሪካ ቀን

ልንዘነጋው የማይገባንና የዘነጋነው የአፍሪካ ቀን

ቀን:

በአሮን ሰይፉ

የሰው ዘር መገኛ የሆነችውና የቀደምት ሥልጣኔዎች ባለቤት የሆነችው አፍሪካ በተለያዩ የታሪክ ዑደቶች ውስጥ ያለፈች አኅጉር ናት፡፡ በረዥሙ የአፍሪካ ታሪክ ውስጥ ታላላቅ ሥልጣኔዎችን፣ የንግድ ልውውጦችን፣ የትምህርትና የባህል በረከቶቿ እንደሚነሳው ሁሉ በአሥር ሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ወጣት አፍሪካውያንን ለባርነት አትላንቲክ ውቅያኖስን አቋርጠው ወደ አውሮፓና አሜሪካ መጫናቸው፣ እንዲሁም በአውሮፓውያን ቅኝ ግዛት ሥር የመውደቅ ጨለማ ጊዜያትንም አሳልፋለች፡፡

እ.ኤ.አ. በ1884/85 በታሪክ የአፍሪካ ቅርምት ተብሎ በሚታወቀው የበርሊን ጉባዔ አውሮፓውያን አፍሪካን በቅኝ ለመያዝ ተከፋፈሉ፣ ኢትዮጵያ ዓድዋ ላይ ወራሪውን ጣልያንን ድል ነስታ፣ እንዲሁም ላይቤሪያ ከአሜሪካ ወደ አፍሪካ በተመለሱ ጥቁሮች የተመሠረተች አገር በመሆኗ ሁለቱ ብቻ ሲቀሩ መላ አፍሪካን አንድ በአንድ በቅኝ ግዛት መዳፋቸው ውስጥ አስገቡ፡፡ ይህ ወቅት አፍሪካ የራሷን ሥልጣኔና ነፃነት ያጣችበትና የአውሮፓውያን የጉልበትና የጥሬ ዕቃ ማግኛ ሥፍራ ብቻ እንድትሆን አድርጓል፡፡ የአፍሪካ ከራሷ ሐዲድ በመውጣት ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ጉዳዮቿ የአውሮፓውያኑን ጥቅም በማማከል ይወሰን ስለነበር አፍሪካ በችግር አዙሪት ውስጥ እንድትዳክር አድርጓል፡፡

- Advertisement -

አፍሪካን ከቅኝ አገዛዝ ነፃ ለማውጣት መላ አፍሪካውያን እልህ አስጨራሽ ትግል አድርገዋል፡፡ ሚሊዮኖችም ለዚህ ቅዱስ ዓላማ ሕይወታቸውን ሰውተዋል፡፡ ከጋና እስከ ሱዳን፣ ከአልጄሪያ እስከ ናሚቢያ፣ ከኮንጎ እስከ ሞዛምቢክ  በአራቱም የአፍሪካ ማዕዘናት የተስፋፋው የነፃነት ትግል በጊዜ ሒደት ፍሬ እያፈራ በተለይ በ1950ዎቹና 60ዎቹ በርካታ የአፍሪካ አገሮች ነፃነታቸውን መቀዳጀት ችለዋል፡፡

አፍሪካውያን ነፃነታቸውን ማግኘት ሲጀምሩ የተፈጠረው መላ አፍሪካን ነፃ የማውጣት ተስፋና ጉጉት፣ ነፃዎቹ የአፍሪካ አገሮች እየተሰባሰቡ እንዲመክሩ አስችሏል፡፡ ይሁን እንጂ የአፍሪካውያን መሰባሰብ አንድ ወጥ መሆን አልቻለም፡፡ የካዛብላንካ ቡድን በመባል የሚታወቀው አንደኛው ቡድን አፍሪካ አንድ አገር መሆን ይገባታል የሚል አቋም የነበረው ሲሆን፣ ሁለተኛውና የሞኖሮቪያ ቡድን የሚባለው የአፍሪካ አንድ አገርነት በሒደት የሚመጣ ሆኖ ነፃ አገሮቹ ለጋራ ዓላማ በጋራ መቆምን የሚጠይቅ ነበር፡፡ የሁለቱ ቡድኖች አለመግባባት በቅኝ ግዛት ሥር እየማቀቁ ላሉ አፍሪካውያን ጥሩ ዜና አልነበረም፡፡

እ.ኤ.አ. በሜይ 1963 ይህ የአፍሪካ በሁለት ጎራ መሠለፍን ሊያስቀርና አፍሪካን በአንድ ድምፅ እንድትናገርና በአንድነት ለመቆም ማስቻልን ዓላማ ያደረገ ጉባዔ በኢትዮጵያ አስተናጋጅነት በአዲስ አበባ ተካሄደ፡፡ የአፍሪካ ብሥራትም ተበሰረ፡፡ በሁለት ቡድኖች የተከፋፈሉት ነፃዎቹ የአፍሪካ አገሮች በአንድነት በመቆም ከቅኝ አገዛዝ መውጣት ያልቻሉትን አፍሪካውያን ነፃ ለማውጣት እ.ኤ.አ. ሜይ 25 ቀን 1963 የአፍሪካ አንድነት ድርጅትን ይፋ አደረጉ፡፡ ይህች ታላቅ ቀን ‹‹የአፍሪካ ቀን›› በመባል በአፍሪካና በመላው ዓለም ለመታወቅ በቃች፡፡ ለዚህች ታሪካዊ ቀን ዕውን መሆን የኢትዮጵያ ሚና በእጅጉ የላቀ እንደነበር ዘለዓለም የሚዘከር ሆኖ፣ በወቅቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር የነበሩትና ለአፍሪካ አንድነት ድርጅት ምሥረታ ታላቅ አስተዋጽኦ ያበረከቱት አቶ ከተማ ይፍሩ እ.ኤ.አ. በ1991 ለአሜሪካ ድምፅ ሬድዮ ላይ በሰጡት ቃለ ምልልስ፣ ‹‹አንድ ነገር ኢትዮጵያ ለአፍሪካ አደረገች ብንል አንዱና ዋናው የአፍሪካ አንድነት ድርጅት መቋቋም ነው፤›› በማለት ገልጸውታል፡፡  

የአፍሪካ ቀን በአፍሪካና በመላው ዓለም ያለው አከባበር

የአፍሪካ ቀን በአፍሪካ ታሪክ ውስጥ ታላቁ ቀን ነው ቢባል ማጋነን አይሆንም፡፡ ከቅኝ ግዛት ቀንበር መላቀቅ ያቃታቸው አፍሪካውያን ባሉበት የተስፋ ዜናን የሰሙበት፣ የነፃነትን አየር የሚተነፍሱ አፍሪካውያንም በአንድነት ለአንድ ዓላማ መሠለፍን ያስቻለ ታላቅ ቀን ነው፡፡ አንድነቱም ተስፋ ብቻ ሆኖ አልቀረም፡፡ የነፃነት ትግሉን በማፋፋም መላ አፍሪካ ነፃ እንዲወጣ የዲፕሎማሲና ወታደራዊ ትግሉን አስተባብሮ ለድል እንዲበቃ አድርጓል፡፡ ይህ የታሪክ እውነታ ነው የአፍሪካ ቀን በአፍሪካና ጥቁሮች በሚኖሩባቸው የዓለማችን ክፍሎች በደማቅ እንዲከበር ያደረገው፡፡

ደቡብ አፍሪካ የሜይ ወርን የአፍሪካ ወር የሚል ስያሜን የሰጠች ሲሆን፣ በወሩ ውስጥ የአፍሪካን ታሪክ፣ የነፃነት ትግልና ብሩህ ተስፋ፣ ወዘተ ይዳሰሳሉ፡፡ ይህም ሆኖ የአፍሪካ ቀን ብሔራዊ በዓል ሆኖ አልታወጀምና የአገሪቱ ዋና የተቃዋሚ ፓርቲ መሪ የሆነው ጁሊየስ ማሌማ ፓርቲያቸው የአፍሪካ ቀንን ሲያከብር ለአባላቶቻቸው ባደረጉት ንግግር ይህን ብለዋል፡፡ ‹‹Africa Day is a celebration and recognition of Pan Africanism. We must not make a mistake comrades, and confuse this day to any other day. This day is a day when we celebrate our selves, this day is a day when we tell the whole world and those who care to listen that we are Africans and we are proud. …. But we must ask ourselves a question. Why is Africa Day not a public holiday in South Africa?››            

እንደ ዚምባቡዌ፣ ናሚቢያ፣ ማሊ፣ ዛምቢያ፣ ጋምቢያ፣ ሌሶቶ፣ ሞሪታኒያ ያሉ የአፍሪካ አገሮች የአፍሪካ ቀንን በብሔራዊ በዓልነት ያከብራሉ፡፡ ዋና መቀመጫውን በምሥረታ ቦታው ያደረገው የአፍሪካ ኅብረትም ሥራ ዝግ ሆኖ የሚከበር ቀን ነው፡፡ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት፣ በተለያዩ ዓለም አቀፍ ድርጅቶች፣ እንዲሁም በተለያዩ የዓለማችን ክፍሎች በተለያዩ የፌስቲቫልና የፓናል ዝግጅቶች ይከበራል፡፡

ከአፍሪካ ውጭ ያሉ አገሮች የአፍሪካ ቀንን ከአፍሪካ ጋር ያላቸውን ትስስር የሚያጠናክሩበት መድረክ አድርገው ይጠቀሙበታል፡፡ በተለይ የሪፐብሊክ ኦፍ አየርላንድ የአፍሪካ ቀን አከባበር ከሌሎች አገሮችም በተሻለ የሚጠቀስ ነው፡፡ ለ2024 የአፍሪካ ቀን አከባበር በመንግሥት ድረ ገጽ ላይ ያለ ከወራት በፊት የተቀመጠው ማስታወቂያ እንዲህ ይላል፡፡

“Africa Day is returning this May – and set to be bigger and better than ever!

Events will be held in every county in Ireland to mark the day that celebrates Ireland’s growing links with the continent of Africa. Irish Aid is working with local authorities all over Ireland to plan a series of events.”

ኢትዮጵያና የአፍሪካ ቀን አከባበር

አገራችን ኢትዮጵያ የአፍሪካ ቀን ተብሎ ለተሰየመው የአፍሪካ አንድነት ድርጅት ምሥረታ ያበረከተችው አስተዋጽኦ ከየትኛውም አገር የላቀ ነው፡፡ ይሁን እንጂ ለአፍሪካ ቀን ሌሎች አገሮች እንደሰጡት ክብር አልሰጠችም፡፡ ሌሎች የአፍሪካ አገሮች የአፍሪካ ቀንን ብሔራዊ በዓል አድርገው ሲያከብሩ፣ የአፍሪካ ሳምንትና የአፍሪካ ወር በማለት ሰይመው አፍሪካዊ ሥራዎች ላይ የተለየ ትኩረት ሲያደርጉ በኢትዮጵያ ግን የአፍሪካ ቀን ይህ ነው የሚባል አከባበር አይደረግም፡፡ አፍሪካ ዴይ ኢኒሼቲቭ በሜይ 25 ቀን  2023 ዓ.ም. 60ኛው የአፍሪካ አንድነት ምሥረታ በዓል (የአፍሪካ ቀን) 60 ኢትዮጵያውያን አርቲስቶች የተሳተፉበት የሥዕል ኤግዚቢሽን በአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን በማዘጋጀት፣ እንዲሁም በፓናል ውይይት የአፍሪካ ቀንን ሲያከብር የአፍሪካ ቀን በአገራችን ተገቢውን ትኩረት እንዲያገኝ የራሱ ሚና እንደሚኖረው ተስፋ በማድረግ ነበር፡፡ ወደ ታች ዝቅ ብዬ እንደማነሳው ከአንድ ወር በኋላ ለሚከበረው 61ኛው የአፍሪካ ቀን በዓል ዝግጅት እየያደረገ ይገኛል፡፡

የኢፌሪ አዋጅ ቁጥር 1209/2012

አተገባበሩን በምሉዕ አላየነውም እንጂ ሐምሌ 9 ቀን 2012 ዓ.ም. በአዋጅ ቁጥር 1209/2012 ‹‹የአፍሪካ ኅብረት ሰንደቅ ዓላማ፣ መዝሙርና የአፍሪካ ቀን አዋጅ›› የአፍሪካ ቀንን በክብር እንድናከብር ብቻ ሳይሆን እንደ አገር ሰፊ ማኅበራዊ፣ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታዎችን ሊያስገኝልን የሚችሉ ሥራዎችን እንድንሠራ የሚያግዘን ክፍሎች ያሉት አዋጅ ነው፡፡ የአዋጁን የተወሰነ ክፍል እንመልከት፡፡ የአዋጁ መግቢያ መርሆ እንዲህ ይላል፡፡ 

‹‹የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ሕገ መንግሥት አንቀጽ 86(5) ከሌሎች የአፍሪካ አገሮች ጋር በየጊዜው እያደገ የሚሄድ ኢኮኖሚያዊ ኅብረትና የሕዝቦች ወንድማማችነትን ማጎልበት የኢትዮጵያ የውጭ ግንኙነት መርሕ እንደሆነ በመደንገጉ፣ አገራችን ከአፍሪካ አገሮች ጋር ያላትን አጋርነት ለማሳደግ፣ ለፓን አፍሪካኒዝምና ለአፍሪካ የውህደት አጀንዳ ተግባራዊነት ያላትን ቁርጠኝነት ለማስቀጠል፣ እንዲሁም የኅብረቱ ኮሚሽን አስተናጋጅ አገርነት ሚናዋን ለመወጣት ከምታከናውናቸው ተግባራት በተጨማሪ የአፍሪካ ኅብረት ሰንደቅ ዓላማን ማውለብለብ፣ የአፍሪካ ኅብረት መዝሙርን ማዘመርና የአፍሪካ ቀን ታስቦ እንዲውል ማድረጉ አገራችን ለኅብረቱ ያላትን ቁርጠኝነት የሚያሳይ በመሆኑ፣ በአፍሪካ ኅብረት የመሪዎች ጉባዔ የኅብረቱ ሰንደቅ ዓላማና መዝሙር በአባል አገሮች እንዲውለበለብና እንዲዘመር፣ እንዲሁም የአፍሪካ ቀን እንዲከበር ያስተላለፈውን ውሳኔ በኢትዮጵያ ተግባራዊ ለማድረግ የሕግ ማዕቀፍ በማስፈለጉ፣ ይህን ስምምነት የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሰኔ 18 ቀን 2012 ዓ.ም. ባካሄደው መደበኛ ስብሰባ ያፀደቀው በመሆኑ፣ በኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ሕገ መንግሥት አንቀፅ 55(1) እና (12) መሠረት የሚከተለው ታውጇል፡፡››

የአዋጁን የኅብረቱን ሰንደቅ ዓላማ አሰቃቀልን በሚደነግገው የአዋጁ ክፍል ሁለት አንቀጽ 4/1 ላይ የትኞቹ ተቋማት የኅብረቱን ሰንደቅ ዓላማ እንደሚሰቅሉ እንዲህ ይደነግጋል፡፡

የኅብረቱን ሰንደቅ ዓላማ መውለብለብ የሚያግድ ከአቅም በላይ የሆነ ምክንያት ካላጋጠመ በስተቀር የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት፣ የፌዴሬሽን ምክር ቤት፣ የሚኒስትሮች ምክር ቤት፣ የክልል ቢሮዎች፣ የሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶች፣ የሌሎች አስፈጻሚ አካላት ጽሕፈት ቤቶች፣ በከፍተኛ የትምህርት ተቋማትን ጨምሮ በትምህርት ቤቶች፣ የአገር መከላከያ ተቋማት፣ አውሮፕላን ማረፊያዎች፣ የፖሊስና የጠረፍ ጥበቃ ተቋማት፣ የኢትዮጵያ ሚሲዮኖች፣ የአምባሳደሮች መኖሪያ ቤት ሕንፃዎች፣ እንዲሁም ከዓለም አቀፉ የባህር ላይ ሰንደቅ ዓላማ አጠቃቀም ደንቦች ጋር በተጣጣመ አኳኋን የኢትዮጵያ ንግድ መርከቦችና ጀልባዎች በየቀኑ የኅብረቱን ሰንደቅ ዓላማ ይሰቅላሉ፡፡

በአዋጁ ከተጠቀሱት ተቋማት ውስጥ የትኞቹ ተቋማት የኅብረቱን ሰንደቅ ዓላማ እየሰቀሉ እንደሆነ በእርግጠኛነት መናገር አልችልም፡፡ ይሁን እንጂ የዚህ ጽሑፍ የትኩረት አቅጣጫዬ በሆነው ትምህርት ቤቶች እየተሰቀለ እንዳልሆነ ይታወቃል፡፡ ነገር ግን አዋጁ ትምህርት ቤቶችን በተለየ የአሰቃቀሉን ሥነ ሥርዓት ጭምር በግልጽ ያስቀምጣል፡፡ የኅብረቱን ሰንደቅ ዓላማ የሚሰቀልበትና የሚወርድበትን ጊዜ በሚደነግግበት አንቀጽ 5 ይህን ይላል፡፡ 5/1  በዚህ አዋጅ አንቀጽ 4/1 በተጠቀሱት መሥሪያ ቤቶች የኅብረቱ ሰንደቅ ዓላማ ከጠዋቱ በ12 ሰዓት ተሰቅሎ ከምሽቱ 12 ሰዓት ይወርዳል፡፡ 5/3 የዚህ አንቀፅ ንዑስ አንቀጽ 1 ቢኖርም በትምህርት ቤቶች የኅብረቱ ሰንደቅ ዓላማ የሚሰቀለው ጠዋት ተማሪዎች ተሠልፈው ትምህርት ከመጀመሩ በፊት ይሆናል፡፡ የሚወርደውም ከምሽቱ 12 ሰዓት ይሆናል፡፡

በአዋጁ በግልጽ እንደተቀመጠው የአፍሪካ ኅብረት ሰንደቅ ዓላማና መዝሙር ከኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማና መዝሙር ጋር በትምህርት ቤቶቻችን በየቀኑ እንዲዘመርና እንዲውለበለብ ተደንግጓል፡፡ ይሁን እንጂ አዋጁን የማስፈጸም ኃላፊነት ያለበት የትምህርት ሚኒስቴር  አዋጁን ሳያስፈጽም አራት የትምህርት ጅማሮ መስከረሞች አልፈዋል፡፡ ተማሪዎቻችን በየዕለቱ የአፍሪካን ሰንደቅ ዓላማን መዝሙሩን እየዘመሩ ቢሰቅሉ፣ በብሔረሰባዊ ማንነት ተቧድኖ ወደ መጨራረስ እየመራን ያለውን ፖለቲካ ሊያርቁ የሚችሉ ራሳቸውን በአፍሪካዊ ማንነት ያነፁ ወጣቶችን ለማፍራት ቀላል ያልሆነ ሚና እንደሚኖረው ዕሙን ነው፡፡

ፖለቲካችን በብሔረሰባዊ ማንነት ታጥሮ እርስ በርስ በመተጋተግ የተኮላሸ በመሆኑ፣ በአፍሪካ ውስጥ ለሚሆኑ ጉዳዮች የፖለቲካ ልሂቃኖቻችን ብዙም ጉዳይ ያላቸው አይመስሉም፡፡ አንድ ዓመት ያስቆጠረው በጎረቤታችን ሱዳን ያለው የእርስ በርስ ጦርነት፣ ኮንጎንና ሩዋንዳን ወደ ጦርነት ሊከት የሚችለው የምሥራቅ ኮንጎ ግጭት፣ ጊኒ፣ ኒጀርና ቡርኪናፋሶ ከምዕራብ አፍሪካ አገሮች ኅብረት (ኤኮዋስ) ራሳቸውን ማግለልና የጋራ ተቋም መመሥረት በአፍሪካ አንድነት ላይ ሊፈጥረው የሚችለው ጉዳት፣ የአፍሪካ ኅብረት የሪፎርም አጀንዳዎች፣ ወዘተ በኢትዮጵያ የፖለቲካ ልሂቃን ዘንድ የረባ ትኩረት የላቸውም፡፡

የምሥራቅ አፍሪካ የኢኮኖሚ ማኅበረሰብ ውስጥ አገራችን ለምን አባል እንዳልሆነች፣ በፖለቲካችን ውስጥ አጀንዳ  እንዴት ሊሆን እንዳልቻለ የሚገርም ነው፡፡ የኢኮኖሚ ማኅበረሰቡ ኬንያ፣ ኡጋንዳ፣ ታንዛንያ፣ ሩዋንዳ፣ ቡሩንዲ፣ ደቡብ ሱዳን፣ ኮንጎና ሶማሊያን በአባልነት የያዘ ሲሆን፣ ወደ ኮንፌዴሬሽን ለማሳደግ ሥራዎች እየተሠሩ ይገኛሉ፡፡ የአፍሪካ ነፃ የንግድ ቀጣናን በተሟላ ሁኔታ ለመተግበር እየተቃረብን ባለንበት በዚህ ወቅት፣ የኢትዮጵያ የንግዱ ማኅበረሰብ የጋራ የንግድ ቀጣናን በበቂ ከተለማመዱት እንደ ምሥራቅ አፍሪካ የኢኮኖሚ ማኅበረሰብና የሌሎችም ቀጣናዊ የኢኮኖሚ ኅብረት አገሮች የንግድ ማኅበረሰብ ጋር እንዴት ሊወዳደሩ እንደሚችሉ አሳሳቢ ነው፡፡ 

በአጠቃላይ ፖለቲካችን ወደ ውስጥ ቁልቁል ያቀረቀረ በመሆኑ ከኢትዮጵያ ባሻገር ስላሉ ዕድሎችና ሥጋቶች የሚመለከት አልሆነም፡፡ የአፍሪካ ችግሮች ላይ እንደ ሌሎች አፍሪካውያን የድርሻችንን ኃላፊነት ለመወጣት የሚያስችል ቁመናና ሁኔታ ውስጥ ልንገኝ አልቻልንም፡፡ የፖለቲካችን አልፋና ኦሜጋ የኢትዮጵያን የፖለቲካ ሥልጣን መያዝ ላይ ብቻ ያጠነጠነ ሆነና እንደ አፍሪካዊ ማኅበረሰብ በአፍሪካ ጉዳዮች ንቁ ተሳታፊ መሆን አልቻልንም፡፡ የአፍሪካን አሥር በመቶ የሕዝብ ቁጥር መያዝ ብቻ ሳይሆን፣ የአፍሪካ ኅብረት መቀመጫ የሆነ አገር ለአፍሪካዊ ጉዳዮች ባዳ ሆኖ የአፍሪካ የፖለቲካና የኢኮኖሚ ነፃነት ትግል ስኬት ላይ የሚፈጥረው ውስንነት በቀላሉ የሚታይ አይደለም፡፡

አፍሪካዊ ማንነትን የተላበሰና በአፍሪካ የፖለቲካ፣ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች ላይ ኃላፊነቱን የሚወጣ የፖለቲካ ባህል የገነቡ አገሮች ገዥው ፓርቲም ይሁን የተቃዋሚ ፓርቲዎች፣ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ይሁን ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት በአፍሪካ ጉዳዮች ላይ ንቁ ተሳታፊዎች ናቸው፡፡ ደቡብ አፍሪካን ለአብነት እናንሳና ለአፍሪካ ቀን የሚሰጡትን ትኩረት በጨረፍታ እንመልከት፡፡

የደቡብ አፍሪካ መንግሥት ገዥ ፓርቲ የአፍሪካ ብሔራዊ ኮንግረስ (ANC) የአፍሪካ ቀንን በተለይዩ ፕሮግራሞች ያከብራል፡፡ ፕሬዚዳንቱን ጨምሮ የቀድሞ ፕሬዚዳንቶችም የፕሮግራሙ ታዳሚዎችና ንግግር አቅራቢዎች ናቸው፡፡ በተቃዋሚ ፓርቲ በኩልም ለምሳሌ የኢኮኖሚ ፍሪደም ፋይተርስ (EFF) የአፍሪካ ቀንን በየዓመቱ በደማቅ ሁኔታ ያከብራል፡፡ በተለይ እ.ኤ.አ. በ2022 የአፍሪካ ቀን ሲከበር የፓርቲው አባላት በመሪያቸው ጁሊየስ ማሌማ መሪነት በፈረንሣይ ኤምባሲ በመገኘት፣ ፈረንሣይ በቀድሞ የቅኝ ግዛቶቿ ላይ ያላትን ተፅዕኖ እንድታቆም የሚጠይቅና ጦሯን ከእነዚሁ የአፍሪካ አገሮች እንድታወጣ የሚጠይቅ ሰላማዊ ሠልፍ በማድረግ ነበር፡፡ መንግሥታዊ ባልሆኑ ተቋማትም በኩል በተለይ የቀድሞው የደቡብ አፍሪካ ፕሬዚዳንት ታቦ ምቤኪ ፋውንዴሽን የአፍሪካ ቀን ዓመታዊ ገለጻዎች (Annual Africa Day Lecture) ላለፉት 14 ዓመታት የተካሄደ ሲሆን፣ የቀድሞው የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ኃይለ ማርያም ደሳለኝ  እ.ኤ.አ. በ2019 በደቡብ አፍሪካ ዩኒቨርስቲ ውስጥ በተዘጋጀው የአፍሪካ ቀን ፕሮግራም ላይ ንግግር አቅራቢ እንደነበሩ እናስታውሳለን፡፡ የደቡብ አፍሪካን ልምድ ከአገራችን ጋር ማነፃፀሩን ብቻ ሳይሆን ምን እንማራለን የሚለው የሁላችንም ጥያቄ ይሁን፡፡

ፖለቲካችን ከኢትዮጵያ ተሻግሮ አፍሪካዊ ማንነትን ወደተላበሰ ፖለቲካ ቢሸጋገር እንደ አፍሪካዊ ማኅበረሰብ ለአፍሪካችን የምናበረክተው አበርክቶ እንደተጠበቀ ሆኖ፣ ለአገራችን የሚኖረው በረከት ዘርፈ ብዙ ነው፡፡ በዚህ ዙሪያ ከሰሞኑ በሌላ ጽሑፍ እመለስበታለሁ፡፡

ወደ ነጥቤ ስመለስ የትምህርት ሚኒስቴር በተለይም የሚኒስትሩ ብርሃኑ ነጋ (ፕሮፌሰር) ቁርጠኝነትና ተባባሪነትን በመመኘት ነው፡፡ የመጀመሪያው ከላይ በተጠቀሰው አዋጅ 1209/2012 መሠረት የአፍሪካ ኅብረት ሰንደቅ ዓላማ በትምህርት ቤቶች እንዲሰቀል፣ እንዲሁም መዝሙሩ እንዲዘመር የማድረግ ኃላፊነቱን ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ እንዲወጣ ነው፡፡ የአዋጁ መተግበር አፍሪካዊ ማንነቱን የሚያወድስ፣ በአፍሪካ ውስጥ ያሉትን ዕድሎች የሚያይና ተግዳሮቶቿን በአሸናፊነት እንድትወጣ የድርሻውን መወጣት የሚችል ዜጋ ለማፍራት ትልቅ ሚና ይኖረዋል፡፡  

ሁለተኛው የዘንድሮው የአፍሪካ ቀን አከባበር ነው፡፡ እንደሚታወቀው የአፍሪካ ኅብረት የ2024 መሪ ቃል ትምህርት ነው፡፡ ትምህርት የአኅጉራችን የትኩረት አቅጣጫ በሆነበት በዚህ ወቅት፣ የአፍሪካ ቀን በትምህርት ቤቶች ከእስከ ዛሬው የተለየ ዝግጅቶች ሊኖር እንደሚችል ይጠበቃል፡፡ ወትሮውንም ትምህርት ቤቶች ዋና የአፍሪካ ቀን የድምቀት ቦታዎች ናቸው፡፡ ትምህርት ቤቶቻችን ከመዝናኛነት ባሻገር ምንም ዓይነት ታሪካዊም ሆነ ትምህርታዊ ፋይዳ የሌላቸው ‹‹ከለር ዴይ፣ ኦልዲስ ዴይ፣ ክሬዚ ዴይ…፣ ወዘተ›› እያከበሩ የአፍሪካ ቀን አለማክበራቸው አሳዛኝ ነው፡፡ ይህን ታሪክ ለመቀየር የዘንድሮ የአፍሪካ ኅብረት የትኩረት አቅጣጫው ትምህርት መሆኑ የኢትዮጵያ ትምህርት ቤቶች የአፍሪካ ቀንን ማክበር እንዲጀምሩ ለማስቻል፣ ከዚህ የተሻለ ወቅትና ዕድል ያለ አይመስለኝም፡፡ የትምህርት ሚኒስቴር በሁሉም ክልሎችና የከተማ አስተዳደር የትምህርት ቢሮዎች በኩል የአፍሪካ ቀን በትምህርት ቤቶች እንዲከበር ጥሪ ቢያስተላልፍ ውጤቱ ለዘንድሮው የአፍሪካ ቀን በዓል ብቻ ሳይሆን፣ ለመጪዎቹም ዓመታት ተማሪዎቹ የአፍሪካ ቀን በየዓመቱ እንዲያከብሩና ስለአፍሪካ የተሻለ የማወቅ ዝንባሌ እንዲኖራቸው ያግዛል፡፡

አፍሪካ ዴይ ኢኒሼቲቭ የአፍሪካን ብዝኃነት፣ ባህል፣ ታሪክ፣ ሙዚቃና ዳንስ ከተማሪዎች ጋር ለማክበር ዝግጅት እያደረገ ይገኛል፡፡ ከዚያም ባሻገር ተማሪዎቹ ስለአፍሪካ ያላቸውን ዕውቀት የሚፈትሹበትና ለወደፊቱም ስለአፍሪካ የበለጠ ለማወቅ እንዲተጉ የሚያደርጉ የጥያቄና መልስ ውድድሮች ይኖራሉ፡፡ ትብብሩን ካገኘን የአፍሪካ ቀን የትውልድ ቦታውን የሚመጥን የአፍሪካ ቀን አከባበር ይኖረናል፡፡ አፍሪካዊ ማንነታችንን እያወደስን የአፍሪካ ቀንን በጋራ እናክብር!

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ በኢሜይል አድራሻቸው aronseifu@africadayinitiative.org ማግኘት ይቻላል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የማዳበሪያ አቅርቦትና ውጣ ውረዱ

በቅፅል ስሙ “The Father of Chemical Warfare” እየተባለ የሚጠራው...

የኢትዮጵያ ልማት ባንክ የትርፍ ምጣኔውን ከ70 በመቶ በላይ አሳደገ

ከሁለቱ መንግሥታዊ ባንኮች መካከል አንዱ የሆነው የኢትዮጵያ ልማት ባንክ...