Sunday, May 19, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

የሳምንቱ ገጠመኝየ ሳ ም ን ቱ ገ ጠ መ ኝ

የ ሳ ም ን ቱ ገ ጠ መ ኝ

ቀን:

እኔ የእዚህ ገጠመኝ ጸሐፊ በተለያዩ የመንግሥትና የግል ተቋማት በልዩ ልዩ ኃላፊነቶች ከ35 ዓመታት በላይ አገልግሎት የሰጠሁ ሲሆን፣ በትምህርት ዝግጅቴም ሁለት ዲግሪዎች (የመጀመሪያና ሁለተኛ) እና በተለያዩ አገሮች በርካታ ሥልጠናዎችን በመውሰድ ቁጥራቸው በርከት ያለ ዲፕሎማዎችና ሰርተፊኬቶች አግኝቻለሁ፡፡ በአገር ውስጥም ሆነ በውጭ በርካታ የሥራና የልምምድ ልውውጥ ጉዞዎች ከማድረጌም በላይ፣ የተለያዩ ዕውቀቶችና ልምዶች ያካበቱ ብዙ ታዋቂ ሰዎችን የማግኘት ዕድልም ነበረኝ፡፡ ይህንን ከላይ የተጠቀሰውን አነስ ያለ የማንነት መገለጫ ያቀረብኩት፣ አንባብያን ከታች ስለምነግራችሁ ጉዳይ መንደርደሪያ እንዲሆናችሁ ያህል ነው፡፡

ከትምህርት ቤት ጀምሮ እስከ ሥራ ዓለም ድረስ በርካታ ሰዎችን በመተዋወቄ ደስተኛና ተጠቃሚ የሆንኩትን ያህል፣ በየጊዜው በሚያጋጥሙኝ አላስፈላጊ ነገሮች ምክንያትም ማዘኔ አልቀረም፡፡ እንደሚታወቀው እኛ ኢትዮጵያውያን ከበፊት ጀምሮ ከምንታወቅባቸው መልካም እሴቶች መካከል እንግዳ ተቀባይነት፣ መንግሥትና ሕግ አክባሪነት፣ ፈሪኃ ፈጣሪና ጨዋነት ከብዙ በጥቂቱ ተጠቃሽ ናቸው፡፡ ልጆች ሆነን ስናድግም ቤተሰቦቻችን አጥብቀው እነዚህን እሴቶች እንድናክብር፣ በዋልጌነት አላስፈላጊ ድርጊቶችን ፈጽመን ስማቸውን በዕድር ጭምር እንዳናነሳ ያስጠነቅቁን እንደነበር ብዙዎች እናስታውሳለን ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ፡፡

ከተወሰኑ አሠርት ዓመታት ወዲህ አገራችን ውስጥ ለመልካም ምግባር ተቃራኒ የሆኑ ድርጊቶች ከመጠን በላይ እየታዩ ነው፡፡ አንድ ምሳሌ ላቅርብ፡፡ የዛሬ አሥራ ሁለት ዓመት ገደማ የምሠራበት መሥሪያ ቤት ውስጥ እጅግ በጣም የምናከብራቸው አለቃችን የጡረታ ጊዜያቸው ደርሶ በክብር ይሰናበታሉ፡፡ እሳቸውን በመተካት የተሾመው ሽቅርቅር ጎልማሳ ኃላፊነቱን ሲረከብ፣ የመጀመሪያ ሥራው የመሥሪያ ቤታችንን በጣም የተከበረ የሥራ ከባቢ ማበላሸት ነበር፡፡ ሰውዬው በየሥራ ክፍሉ የራሱን ሰዎች በኃላፊነት በመመደብ፣ በአንድ ጊዜ ሠራተኞችን እርስ በርስ የሚያጋጭ የወሬ ኔትወርክ ማደራጀት ጀመረ፡፡ በዚህ ኔትወርክ አማካይነት ሠራተኞችን ማበጣበጥ መደበኛ ሥራ በመደረጉ፣ ከሥራ ይልቅ ሌብነትና ወሬ የተቋሙ መለያ ሆነ፡፡

- Advertisement -

ብዙዎቻችን አማራጭ ስለነበረን ፈጣን ዕርምጃ እየወሰድን ተቋሙን ለቀቅን፡፡ ይኸው እስካሁን ያንን የመሰለ መሥሪያ ቤት እንዳይሆኑ ሆኖ አለ፡፡ ለብዙዎች አርዓያ የነበሩ አመራሮችና ባለሙያዎች የነበሩበት ያ መሥሪያ ቤት፣ በመንግሥት ውሳኔ ከሆነ ተቋም ጋር ተዳብሎ ስሙ ሳይቀር ተረስቷል፡፡ ከዚያ ግለሰቡ እንደ ልቡ ፈንጭቶበት ከብሮበት ከወጣ መሥሪያ ቤት ለቅቄ አንድ የግል ዘመናዊ ድርጅት አማካሪ ሆኜ ተቀጠርኩ፡፡ ያለኝን ዕውቀትና ልምድ ያለ ስስት ሰጥቼ ከፍ ያለ ደረጃ እንዲደርስ ለማድረግ ለሁለት ዓመታት ሠራሁ፡፡ እዚህ ደግሞ የድርጅቱ ባለቤት በድንገት ከዚህ ዓለም በሞት ሲለይ፣ ወራሽ ተብዬዎች ‹አላዋቂ ሳሚ› ሆነው አላሠራም ሲሉ ጥዬ ወጥቼ የራሴን አማካሪ ድርጅት ከፈትኩ፡፡

በዚህ ሁሉ ጉዞዬ የታዘብኩት ብዙ ቦታዎች ጨዋነት፣ ሥነ ምግባርና ሞራላዊ ከፍታዎች ከጊዜ ወደ ጊዜ እየወረዱ መሆናቸውን በሚገባ አይቻለሁ፡፡ የግሌን ድርጅት ለመክፈት እንቅስቃሴ ሳደርግ በየደረስኩበት ቦታ የምጠየቀው ጉቦ አንገሽጋሽ ነበር፡፡ የአሁኑን አላውቅም እንጂ ከፈቃድ ሰጪዎች እስከ ብቃት ምዘና ድረስ የነበሩ ግለሰቦች መከራ ነበር ያበሉኝ፡፡ ብዙዎቹ አወዳድሬ የምቀጥራቸው ሠራተኞች ከሥራ ይልቅ የሚገኘው ጥቅም ላይ ስለሚያተኩሩ፣ ምን ዓይነት ዘዴ ተጠቅመው እንደሚያጭበረብሩ እንጂ ልምድ ቀሰማ ደንታቸው አይደለም፡፡ አንዱን አንድ ጊዜ አንደኛው የንግድ ባንክ ውስጥ አግኝቼው ሥራ እንዴት ነው ስለው፣ ‹‹አንተ ጋ ደረቅ ጣቢያ ነበር፣ እዚህ ከገባሁ ወዲህ ግን የራሴን ቤትና መኪና አግኝቻለሁ…›› ሲለኝ ደንግጬ ነበር፡፡

ገና ከተመረቀ አምስት ዓመት ያልሞላው ጎረምሳ ምኑን ከምን አድርጎ ባለንብረት እንደሆነ ሊገባኝ አልቻለም፡፡ ባንኩን የመሠረቱ ባለአክሲዮኖች ብድር ለማግኘት መከራ እያዩ፣ ትናንት የተቀጠረ አንድ ተራ ሠራተኛ በዚህ ደረጃ ላይ ሲገኝ የባንኮቻችን ጉዳይ ቢያሳስበን አይፈረድብንም፡፡ አሥር ግለሰቦች ከ400 ቢሊዮን ብር በላይ መበደራቸው የሚነገርበት አገር ውስጥ፣ ለአገር ትልልቅ አስተዋፅኦዎች ሊያበረክቱ የሚችሉ ዜጎች ግን ድህነት ተፈርዶባቸው ተቆራምደው ይኖራሉ፡፡ የባንኮቻችን ጉዳይ ‹ተከድኖ ይብሰል› የሚባል ሳይሆን፣ በጥናት ላይ በተመሠረተ ፖሊሲ መገራት ይኖርበታል የሚል ጥብቅ አቋም አለኝ፡፡ ምክንያቱም የማማከር ሥራዬ ብዙ አስገራሚ ክስተቶችን እያሳየኝ ነውና፡፡

በክልል ያለውን ሁኔታ በቅጡ ባላውቀውም በአዲስ አበባ ከተማ ግን በወረዳ፣ በክፍለ ከተማ፣ በመሬት አስተዳደር፣ በግንባታ ፈቃድና በሌሎች ማዘጋጃ ቤታዊ አገልግሎቶች የሚስተዋለው መረን የለቀቀ ሌብነት መንግሥት በሕይወት አለ ወይ ያሰኛል፡፡ በፓስፖርትና በሌሎች ሰነዶች ፍለጋ የሚስተዋለው ቅጥ ያጣ አሠራር ምን ያህል የሞራል ዝቅታ ውስጥ እንዳለን ፍንትው አድርጎ ያሳያል፡፡ አንዲት የሥራ ባልደረባዬ ከአንድ ክፍለ ከተማ የዲጂታል ካርታ ለማግኘት እያየች ያለውን ፍዳ ስትነግረኝ፣ ድርድሩ በቀጥታ ካልሆነም በዋትስአፕ አማካይነት በደላላ አማካይነት ነው የሚሳለጠው፡፡ የከፈለ በፍጥነት ያገኛል፣ መብቴ ነው ብሎ ለማስከበር ትግል የሚሞክር ካለ የእንግልት ቡፌ ይገጥመዋል ነው ያለችኝ፡፡

እዚያ ቀበና ከኮከበ ጽባሕ ትምህርት ቤት ማዶ ያለው ሠፈር ውስጥ ያሉ ባለይዞታዎች፣ በወንዝ ልማት ፕሮጀክት አካባቢ በሦስት ወራት ውስጥ እንደሚነሱ ከተነገራቸው ሳምንታት ተቆጥረዋል፡፡ የተሻለ ቤት መሥሪያ መሬትና ጠብሰቅ ያለ ካሳ ማግኘት ከፈለጉ ግን፣ በ40/60 ክፍፍል በደላላ አማካይነት እንዲደራደሩ ግፊት እየተደረገባቸው እንደሆነ የነገረችኝ ይህችው ባልደረባዬ ናት፡፡ ከዚህ ቀደም ጠቅላይ ሚኒስትሩም ሆነ የከተማችን ከንቲባ የኮሪደሩም ሆነ የወንዝ ልማቱ ከሌብነት የፀዳ እንደሚሆን ደጋግመው ነግረውናል፡፡ ይህንን ግርድፍ መረጃ ይዘው ክትትልና ቁጥጥር በማድረግ የተጀመረውን የልማት ጉዞ ከሌቦች ያፅዱልን እላለሁ፡፡ የሞራል ዝቅጠት ላይ ካልተዘመተ አገራችን ከዚህ የባሰ መከራ እንደሚገጥማት አልጠራጠርም፡፡

(ዮርዳኖስ ጉዲና፣ ከሲግናል)

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

በሥጋ ላይ አላግባብ እየተጨመረ ያለውን ዋጋ መንግሥት ሊቆጣጠረው ይገባል

በአገራችን የግብይት ሥርዓት ውስጥ ኢኮኖሚያዊ ያልሆኑ ወይም ያልተገቡ የዋጋ...

ኢትዮጵያን የተባበረ ክንድ እንጂ የተናጠል ጥረት አይታደጋትም!

ኢትዮጵያ በአሁኑ ጊዜ ከምትገኝበት ውጥንቅጥ ውስጥ የምትወጣበት ዕድል ማግኘት...

የፖለቲካ ቅኝቱ የሕዝባችንን ታሪካዊ ትስስር ለምን አያከብርም?

በንጉሥ ወዳጅነው የዓብይ አህመድ (ዶ/ር) መራሹ የ2010 ዓ.ም. የለውጥ መንግሥት...

ዛሬም ኧረ በሕግ!

በገነት ዓለሙ በዚህ በያዝነው ሚያዝያ/ግንቦት ወይም ሜይ ወር ውስጥ የተከበረው፣...