Tuesday, May 21, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ስፖርትየመምረጫ መሥፈርት ክፍተት ሳይኖር መመሪያን የመተግበር ክፍተት ለምን?

የመምረጫ መሥፈርት ክፍተት ሳይኖር መመሪያን የመተግበር ክፍተት ለምን?

ቀን:

በቴክኖሎጂም ሆነ በኢኮኖሚያዊ አቅማቸው ላቅ ባለ ደረጃ ላይ የሚገኙ አገሮች  ከሚያዘጋጇቸው ስፖርታዊ ክንውኖች መካከል በየአራት ዓመቱ የሚከናወነው የኦሊምፒክ ጨዋታ በቀዳሚነት ይጠቀሳል፡፡

በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ምክንያት ተስተጓጉሎ የነበረው የቶኪዮ 2020 ኦሊምፒክ የተካሄደው ከሦስት ዓመት በፊት ሲሆን፣ ቀጣዩን የ2024 ኦሊምፒክን የተረከበችው ከሦስት ወር በኋላ የምታስተናግደው ፓሪስ ናት፡፡

በፓሪስ ኦሊምፒክ ለመካፈል ብሔራዊ ኦሊምፒክ ኮሚቴዎችና የተለያዩ ፌዴሬሽኖች ያጭዋቸውን አትሌቶች ማሳወቅ ጀምረዋል፡፡ ከነዚህም መካከል ኢትዮጵያ ትገኝበታለች፡፡ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን በመካከለኛና በረዥም ርቀት እንዲሁም በዕርምጃ ሚኒማ ያመጡትን በዝርዝሩ አካትቷል፡፡ ይሁን እንጂ በዝርዝሩ ውስጥ  የማራቶን ተወዳዳሪዎች የሉበትም፡፡

- Advertisement -

የማራቶን አትሌቶች ዝርዝር የት ነው?

ኢትዮጵያ በፓሪስ ኦሊምፒክ  ውጤት ከምታስመዘግብባቸው ውድድሮች መካከል ማራቶን ይጠቀሳል፡፡ ይሁንና በዚህ ወቅት በውድድሩ አገሪቱን ወክለው የሚወዳደሩት አትሌቶች እነማን ይሆኑ? የሚለው በጊዜያዊነት እንኳ አለመታወቁ ማነጋገሩ አልቀረም፡፡

ከማራቶን ምርጫ ጋር ተያይዞ ‹‹መምረጫ መሥፈርቱ›› ላይ ያላቸውን ሥጋት ከወዲሁ የሚገልጹ አትሌቶችና አሠልጣኞች አሉ፡፡

ቅሬታ አቅራቢዎቹ ለዚህ ሥጋታቸው ምክንያት የሚሉት ደግሞ ከሦስት ዓመት በፊት የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ብቻ ምክንያት በማድረግ፣ በፌዴሬሽኑ የተደረገው ሕግና መመርያን ባልተከተለ አግባብ በአገር ውስጥ በተደረገ ማጣሪያ የማራቶን አትሌቶች የተመረጡበትን አሠራር ነው፡፡

ይሁን እንጂ፣ ከ2024 የፓሪስ ኦሊምፒክ ዝግጅትና ምርጫ ጋር ተያይዞ የተዘጋጀ መመርያ ስላለ የሚፈጠር አንዳችም ሥጋት እንደማይኖር የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ዋና ጸሐፊ አቶ ዮሐንስ እንግዳ ይናገራሉ፡፡ ፌዴሬሽኑ በተለይ የማራቶን ብሔራዊ አትሌቶችን ዝርዝር ከወዲሁ ከመግለጽ የተቆጠበው ሙያዊና አሳማኝ በሆነ ምክንያት እንደሆነ ጭምር ያስረዳሉ፡፡

በማራቶን በርከት ያሉ አትሌቶች የኦሊምፒክ ሰዓት (ሚኒማ) በማሟላት ላይ ይገኛሉ፡፡ በዚህ ረገድ በቅርብ በተደረጉ ውድድሮች የኦሊምፒክና የዓለም ሻምፒዮኑ ቀነኒሳ በቀለን ጨምሮ ቁጥራቸው በርከት ያሉ አትሌቶች አስፈላጊውን የኦሊምፒክ መግቢያ ሰዓት አሟልተው ቀጣዩን ምርጫ በመጠባበቅ ላይ ይገኛሉ፡፡

የዓለም አትሌቲክስ በወርቅ ደረጃ ከሚያስቀምጣቸው የማራቶን ውድድሮች መካከል በለንደን ማራቶን ቀነኒሳ በቀለ ውድድሩን ሁለተኛ ሆኖ ቢያጠናቅቅም ሰዓቱ ግን 2፡04.11 መሆኑ ብቻ ሳይሆን፣ በራሱ የተያዘውን በማራቶን ዕድሜያቸው ከ40 ዓመት በላይ ሆነው የተወዳደሩ አትሌቶች ክብረ ወሰንን ዳግም መስበሩ ነው፡፡ 

በለንደን ማራቶን የአሸናፊነት ዕድሉን ባታገኝም እስካሁን የዓለም የማራቶን ክብረ ወሰንን በስሟ አስመዝግባ ያለችው ትዕግሥት አሰፋ ሁለተኛ ሆና በማጠናቀቅ ያስመዘገበችው ሰዓት 2፡16.23 መሆኑ ሌላው ተጠቃሽ ሆኗል፡፡

በተመሳሳይ በቦስተን ማራቶን ሲሳይ ለማ 2፡06.17 በማስመዝገብ አንደኛ ሆኖ ቢያጠናቅቅም፣ የቦስተን ማራቶን ከመካሄዱ ከአራት ወራት በፊት በደቡብ ኮሪያ ዴጉ  የማራቶን ውድድርን ከ2፡02 በታች ማጠናቀቁ ይታወሳል፡፡ በሮተርዳም ማራቶን ብርሃኑ ለገሰ 2፡05.16 የገባበት ሰዓት ነው፡፡ በሴቶች አሸቴ በከሪ 2፡19.30 በመግባት አንደኛ ሆና ያጠናቀቀችበት ሰዓትም ይጠቀሳል፡፡

በፓሪስ ማራቶን ሙሉጌታ ኡማ 2፡05.33 በመግባት አሸናፊ ሲሆን፣ በሴቶች መስተዋት ፍቅርና እናት ጥሩሰው 2፡20.45 እና 2፡20.48 አንደኛና ሁለተኛ ሆነው አጠናቀዋል፡፡

ብሔራዊ ፌዴሬሽኑ ለ2024 ፓሪስ ኦሊምፒክ በተለይም የማራቶን ብሔራዊ አትሌቶች ምርጫን በተመለከተ በመመርያው በግልጽ እንደተመለከተው፣ ከነሐሴ 2015  እስከ ሚያዝያ ወር 2016 መጨረሻ ድረስ በተከናወኑ ማናቸውም የማራቶን ውድድሮች የዓለም አትሌቲክስ በሚሰጠው ደረጃ ልክ (የወርቅ፣ የብርና የነሐስ) ራሱን የቻለ የነጥብ አሰጣጥ ሥርዓት በመመርያው ተካትቷል፡፡

መመርያው ከቀነ ገደቡ በፊት ተወዳድረው ሰዓት ያላቸውን አያካትትም ያሉት ኃላፊው፣ ‹‹በተጠቀሰው ጊዜ ውስጥ እንኳ ሆኖ የውድድር ድግግሞሽ ካለ መሥፈርቱ አይቀበለውም፤›› በማለት የመመርያውን ጥንካሬና ግልጽነት ያብራራሉ፡፡

መመርያው በዚህ ልክ የተዘጋጀና ያለ ከሆነ ኦሊምፒክና የዓለም ሻምፒዮና  በሚኖሩበት ጊዜ ከምርጫ ጋር ተያይዞ ችግሮች ለምን ይፈጠራሉ? ሲል ሪፖርተር የጠየቃቸው የፌዴሬሽኑ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ዮሐንስ እንግዳ እንዲህ መልሰዋል፡፡

‹‹መመርያው ምርጫን በሚመለከት ጥርት ያለና ግልጽ ነው፡፡ ለምን ከተባለ የግል ውድድሮች ማለትም እንደ ለንደን፣ ቦስተን፣ ኒውዮርክ፣ በርሊንና ሌሎችም የዓለም አትሌቲክስ በወርቅ፣ በብርና በነሐስ ደረጃ ከፋፍሎ እንደሚሰጠው ነጥብና ደረጃ ሁሉ አንድ አትሌት በዋና በዋና ማራቶኖች ላይ የሚያስመዘግበው ውጤት ብቻ ሳይሆን፣ በኦሊምፒክና በዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ላይም የሚያስመዘግበውን ውጤት ጭምር እየለየ ራሱን የቻለ ነጥብ የሚሰጥበት አግባብ አለው፡፡››

ችግሩ ታዲያ እንዴት ሊፈጠር ቻለ? ለሚለው ግን መልስ ከመስጠት ተቆጥበዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

በሥጋ ላይ አላግባብ እየተጨመረ ያለውን ዋጋ መንግሥት ሊቆጣጠረው ይገባል

በአገራችን የግብይት ሥርዓት ውስጥ ኢኮኖሚያዊ ያልሆኑ ወይም ያልተገቡ የዋጋ...

ኢትዮጵያን የተባበረ ክንድ እንጂ የተናጠል ጥረት አይታደጋትም!

ኢትዮጵያ በአሁኑ ጊዜ ከምትገኝበት ውጥንቅጥ ውስጥ የምትወጣበት ዕድል ማግኘት...

የፖለቲካ ቅኝቱ የሕዝባችንን ታሪካዊ ትስስር ለምን አያከብርም?

በንጉሥ ወዳጅነው የዓብይ አህመድ (ዶ/ር) መራሹ የ2010 ዓ.ም. የለውጥ መንግሥት...

ዛሬም ኧረ በሕግ!

በገነት ዓለሙ በዚህ በያዝነው ሚያዝያ/ግንቦት ወይም ሜይ ወር ውስጥ የተከበረው፣...