Monday, May 20, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ዜናየኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት አድልኦ እየፈጸመ ነው የሚል ቅሬታ ቀረበበት

የኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት አድልኦ እየፈጸመ ነው የሚል ቅሬታ ቀረበበት

ቀን:

  • አገልግሎቱ ቅሬታውን አስተባብሏል

የኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት ዜጎች ሊያሟሏቸው የሚገቡ መረጃዎችን ይዘው ቢቀርቡም፣ በቀለማቸው ተለይተው አገልግሎቱን ከማግኘት የሚከለከሉበት ተቋም መሆኑን በመግለጽ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል ቅሬታቸውን አቀረቡ፡፡

ዓርብ ሚያዝያ 18 ቀን 2016 ዓ.ም. የዘጠኝ ወራት ዕቅድ አፈጻጸሙን ያቀረበው አገልግሎቱ፣ በተለይ ከቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል የሚመጡ ዜጎች በቀለማቸው ምክንያት አገልግሎቱን ከማግኘት እየተከለከሉ መሆናቸውን፣ በምክር ቤቱ የሕግና ፍትሕ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አባል አቶ ሙባረክ ኤሊያስ ቅሬታ አቅርበዋል፡፡

‹‹ሌሎች ዜጎች ብቻ ሳይሆኑ የክልሉ ካቢኔ አባላት ሳይቀሩ የአገሪቱ ዜጎች እንዳልሆኑ በሚገልጽ ስሜት፣ አገልግሎቱን ሳያገኙ እንዲመለሱ ተደርገዋል፤›› ያሉት አቶ ሙባረክ፣ ከፍተኛ እንግልት እየደረሰባቸውም ነው ብለዋል፡፡

- Advertisement -

አገልግሎቱን ተደራሽ ለማድረግ በአሥራ ሦስት ክልሎች ድጋፍና ክትትል እየተደረገ መሆኑን፣ ነገር ግን ውጤታማነቱ ጥያቄ የሚፈጥር ነው ብለዋል፡፡ የአገልግሎቱ ቅርንጫፍ መሥሪያ ቤቶች ቢከፈቱም አገልግሎት እየሰጡ አለመሆናቸውን አቶ ሙባረክ አስረድተዋል፡፡ 

በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል ባለው የፀጥታ ችግር ምክንያት ባለፉት አምስት ዓመታት የየብስ ትራንስፖርት አለመኖሩን፣ በዚህም ምክንያት ዜጎች ፓስፖርት ፍለጋ ለከፍተኛ ወጪ እየተዳረጉ መሆናቸውን አስረድተዋል፡፡

ከዚህ ቀደም በተቋሙ ከፍተኛ የሆነ የአሠራር ብልሹነት በመኖሩና ከአመራር ጀምሮ ያሉ ሠራተኞቹ በሙስና ተዘፍቀዋል ብለው ባለፈው ዓመት መገባደጃ በአዲስ አመራሮች እንዲተኩ መደረጉ ይታወሳል፡፡ በ2015 ዓ.ም. መጨረሻ የተሾሙት ዋና ዳይሬክተሯ ወ/ሮ ሰላማዊት ዳዊት፣ በቋሚ ኮሚቴው አባል የተነሳው ጥያቄ የተፈጠረው በምን አጋጣሚ እንደሆነ እንደማያውቁ ገልጸው፣ የተባለው ዓይነት አሠራር በተቋማቸው እንደሌለ በመግለጽ ቅሬታውን አስተባብለዋል፡፡

‹‹በድንበር አካባቢ ካሉ ቦታዎች የሚመጡ ዜጎች ይዘውት የሚመጡትን ማስረጃ ማረጋገጥ ስላለብን የልደት ካርድ፣ በተጨማሪም መታወቂያ እናያለን፡፡ ባለሙያው ማስረጃው ሕጋዊ መስሎ ካልታየው ተጨማሪ ማስረጃዎችን የሚጠይቀው ክፍል እንዲሄድ ይደረጋል፤›› ብለዋል፡፡

ሁሉም ሰው አገልግሎቱን ማግኘት ያለበት በሚያቀርበው መረጃ መሠረት ሊሆን እንደሚገባ ገልጸው፣ ‹‹በቀለም ተመርጦ አገልግሎት ይሰጣል›› የሚለው ግን ትክክል አይደለም በማለት ተከራክረዋል፡፡ የዳይሬክተሯ ምላሽ ያልተዋጣላቸው አቶ ሙባረክ በበኩላቸው ማስረጃ ማቅረብ ካስፈለገ ማቅረብ እንደሚችሉ በመግለጽ፣ የአሠራር ችግር ካለ እናስተካክላለን መባል ሲገባው፣ ‹‹በእኛ በኩል ዕውቅና የለም›› የሚለው ተቀባይነት የለውም ብለዋል፡፡

‹‹ማስረጃ ከቀበሌና ከክልል ተሰጥቷቸው ሱዳናዊ ናችሁ ተብለው አገልግሎቱን ተከልክለዋል፣ ይህም ዜጎቻችንን ያስከፋ ተግባር ነው፤›› ሲሉም አክለዋል፡፡   

‹‹የአባትና የእናት እንዲሁም የትምህርት ሰነድ ሲጠየቁ እንደሌላቸው የሚገልጹ ዜጎች በመኖራቸው ተጨማሪ ምርመራዎች ማድረግ ያስፈልጋል፤›› ሲሉ የአገልግሎቱ ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ቢቂላ መዝገቡ ተናግረው፣ ይህ ሒደት ጊዜ እንደሚወስድና አንዳንዶችም የውጭ አገር ዜጎች ሆነው እንደሚገኙ አስረድተዋል፡፡

ባለፉት ዘጠኝ ወራት ከ700 ሺሕ በላይ ፓስፖርቶችን ለተገልጋዮች ማድረስ መቻሉን የተቋሙ የሥራ ኃላፊዎች የገለጹ ሲሆን፣ ከአንድ ዓመት በላይ ሳይታተሙ የቀሩ ውዝፍ ኅትመቶችን በማሳተም 65 በመቶ ተገልጋዮች ፓስፖርታቸውን እንዲወስዱ መደረጉን አመላክታል፡፡

በተጨማሪም ለፓስፖርት ኅትመት የሚወጣውን የውጭ ምንዛሪ ለማስቀረት በሚቀጥለው ዓመት በአገር ውስጥ ማሳተም እንደሚጀመር አስታውቀዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

በሥጋ ላይ አላግባብ እየተጨመረ ያለውን ዋጋ መንግሥት ሊቆጣጠረው ይገባል

በአገራችን የግብይት ሥርዓት ውስጥ ኢኮኖሚያዊ ያልሆኑ ወይም ያልተገቡ የዋጋ...

ኢትዮጵያን የተባበረ ክንድ እንጂ የተናጠል ጥረት አይታደጋትም!

ኢትዮጵያ በአሁኑ ጊዜ ከምትገኝበት ውጥንቅጥ ውስጥ የምትወጣበት ዕድል ማግኘት...

የፖለቲካ ቅኝቱ የሕዝባችንን ታሪካዊ ትስስር ለምን አያከብርም?

በንጉሥ ወዳጅነው የዓብይ አህመድ (ዶ/ር) መራሹ የ2010 ዓ.ም. የለውጥ መንግሥት...

ዛሬም ኧረ በሕግ!

በገነት ዓለሙ በዚህ በያዝነው ሚያዝያ/ግንቦት ወይም ሜይ ወር ውስጥ የተከበረው፣...