Sunday, May 19, 2024
- Advertisment -
- Advertisment -

ከአይኤምኤፍ ጋር የሚደረገው ድርድር ብቃትና ብልኃት ይታከልበት!

ሰሞነኛው የመንግሥትና የዓለም ገንዘብ ድርጅት (አይኤምኤፍ) በአሜሪካ የተደረገ ንግግር፣ የተለያዩ ዓውዶችንና ገጽታዎችን ተላብሶ ብዙ ሲባልበት ሰንብቷል፡፡ መንግሥት ከአይኤምኤፍም ሆነ ከሌሎች ድጋፍና ብድር ለማግኘት እያደረገ ስላለው ጥረት፣ የብርን የመግዛት አቅም የበለጠ እንዲያዳክም ጥያቄ እንደቀረበለትና ሌሎች ተያያዥ ነጥቦች በየተራ መነጋገሪያ ነበሩ፡፡ ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው እንደሚያስረዱት ደግሞ፣ እነ አይኤምኤፍ የመንግሥት ሥጋት ያጠላበት ወጪና አጠቃላይ የፋይናንስ ሥርዓቱ አስተዳደር እንደሚያሳስባቸው ነው፡፡ የምዕራባውያንን ጥቅም ለማስጠበቅና ለታዳጊ አገሮች ዕድገት ደንታ የላቸውም ተብለው የሚብጠለጠሉት የዓለም ባንክና አይኤምኤፍ፣ ዛሬ ሳይሆን ከበፊት ጀምሮ እነሱን ለተጠጋ ማንኛውም አገር በቅድመ ሁኔታ ላይ ተመሥርተው የሚፈልጉትን እንደሚሰጡ ወይም እንደሚነሱ የታወቀ ነው፡፡ ከእነዚህ ተቋማት ጋር የሚሠራ አገር ብቃትን ብልኃት ያካተተ ዝግጅት ከሌለው ጫና እንደሚደረግበት የሚጠበቅ ነው፡፡

መንግሥት ከአይኤምኤፍ ጋር ኢኮኖሚው ከገጠመው ተግዳሮት እንዲላቀቅ፣ ተጨማሪ የፋይናንስ ድጋፍ ለማግኘት ሲመክር ሰንብቷል፡፡ መንግሥት ለአይኤምኤፍ እ.ኤ.አ. ከ2022 ጀምሮ የምግብ ችግርን ለመቅረፍ፣ ለመልሶ ግንባታና ማቋቋሚያ፣ በየጊዜው ለሚያሻቅበው ከፍተኛ የዋጋ ንረትና ለውጭ ምንዛሪ እጥረት የድጋፍ ጥያቄ ሲያቀርብ ነበር፡፡ ጥያቄ እየቀረበባቸው ያሉ ችግሮች በየቦታው በሚፈጠሩ ግጭቶች፣ በድርቅና በዓለም አቀፍ ገበያ በምርቶችና በሸቀጦች ዋጋ ላይ በሚታየው ጭማሪ ምክንያት እየተባባሱ ነው፡፡ የአይኤምኤፍ ተወካዮች እ.ኤ.አ. ከመስከረም 2023 ጀምሮ በተከታታይ በኢትዮጵያ ጉብኝት በማድረግ፣ ከመንግሥት የሚመለከታቸው አመራሮች ጋር በኢኮኖሚ ሪፎርም ዕቅዶች ላይ ተወያይተዋል፡፡ ዕቅዶቹ በዋናነት እንዲያተኩሩ የተፈለገው የፋይናንስ መረጋጋት እንዲፈጠርና የአገሪቱን የዕድገት ዕምቅ አቅም ለመፈተሽ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ያለባት የውጭ ብድር ጫና የዕዳ ሽግሽግና ዕፎይታን አስፈላጊ ስለሚያደርግ፣ ዘለቄታ ያለው የፋይናንስ መረጋጋት ለመፍጠር ከአበዳሪዎች ጋር ውይይት መደረጉ ሌላው ጉዳይ ነው፡፡

ውይይቱ በሁለቱም ወገኖች ዘንድ ስለሚፈለግና የኢትዮጵያ መንግሥትም የአይኤምኤፍን ድጋፍ ስለሚሻ፣ ተጠባቂ የሚሆኑ መሠረታዊ ነገሮች እንዳሉ ይታሰባል፡፡ ከእነዚህም ውስጥ አይኤምኤፍ ከመንግሥት ስለበጀት ጉድለቶች፣ ስለወጪዎቹ፣ የፋይናንስ አስተዳደሩን ስለማሻሻል፣ ስለመንግሥት የልማት ድርጅቶች እንደገና መዋቀር፣ ፕራይቬታይዜሽንና መሰል ጉዳዮች ዝርዝር የወደፊት ዕቅዶቹን ለማወቅ ግፊት ማድረግ እንደሚፈልግ ነው የሚነገረው፡፡ የኢትዮጵያ ሁሉም አበዳሪዎች የዕዳ መክፈያ የዕፎይታ ጊዜ አስፈላጊነት ላይ አመኔታ እንዲኖራቸው አበክሮ እንደሚሠራ፣ በዚህም የኢትዮጵያ ዕዳ ሥጋት ፈጣሪ ሳይሆን በአግባቡ እንዲመራ ይረዳል እየተባለ ነው፡፡ መንግሥት በእነዚህና በሌሎች ተዛማጅ ጉዳዮች ላይ ከአይኤምኤፍ ጋር እየተግባባ ሲቀጥል፣ የአይኤምኤፍ ቦርድ የሚፈለገውን ብድርም ሆነ ድጋፍ ለመልቀቅ የሚያስችል ዕድል እንደሚፈጥር ይታሰባል፡፡ ከአበዳሪዎች ጋርም ተመሳሳይ ውይይቶች እንዲቀጥሉም ይፈለጋል፡፡ መንግሥት በዚህ ቁመና ላይ ለመገኘት ግን የቤት ሥራውን በአግባቡ ሠርቶ አደባባይ መውጣት ይጠበቅበታል፡፡

ኢትዮጵያ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የምዕራቡን ዓለም ለመገዳደር የተቋቋመውን ብሪክስ ብትቀላቀልም፣ አሁንም ከዓለም ባንክና ከአይኤምኤፍ ጋር የምታደርገው ግንኙነት በቀላሉ እንደማይበጠስ ግልጽ ነው፡፡ ለአገር ልማት አስፈላጊ የሆኑ ድጋፎችና ብድሮች ከእነዚህ ተቋማት መገኘት ሲኖርባቸው፣ እነሱ በሚያስቀምጡት ቅድመ ሁኔታ መሠረት የመንግሥት ወጪን መግራትም የግድ ነው፡፡ የተገኘን ማንኛውም ዓይነት ብድር በወቅቱ ለመመለስ የሚቻለው፣ ገንዘቡ በትክክል ሥራ ላይ ውሎ ውጤት ሲያስገኝ ነው፡፡ ለዚህ ደግሞ ጠንካራ የኢኮኖሚ ፖሊሲ የሚያስፈልግ ሲሆን፣ የመንግሥት አሠራርም በዓለም አቀፍ ደረጃ ተቀባይነት ያላቸው መመዘኛዎችን ማሟላት ይኖርበታል፡፡ ዓለም አቀፍ ተቋማት ኢኮኖሚው በአግባቡ ሲመራ፣ ፕሮጀክቶች ከሌብነት ሲፀዱ፣ ብድሮች በተቀመጠላቸው ጊዜ ሲከፈሉና ጫናዎችን በብቃት ለመቋቋም የሚያስችሉ ሥራዎች ሲከናወኑ እጅ በመጠምዘዝ የሚፈልጉትን ለማስፈጸም አይንቀሳቀሱም፡፡

መንግሥት ከእነ አይኤምኤፍ ጋር ሲያደርግ የነበረው ንግግርና የተደረሰበት ስምምነት ወይም አለመስማማት በቅርቡ የሚታወቅ ቢሆንም፣ ከበፊት ልምዶች በመነሳት ጉዳዩ ሲዳሰስ ሦስት ነገሮች ላይ ያርፋል፡፡ አንደኛው ዓለም አቀፍ ተቋማቱ የሚያበድሩት ገንዘብ ለአደጋ እንዳይጋለጥ ስለሚፈልጉ፣ እያንዳንዱን እንቅስቃሴ ለመቆጣጠር የሚያስችላቸው አሠራር እንዲዘረጋ ያሳስባሉ፡፡ ሁለተኛ የአገሪቱ የፋይናንስ ዘርፍ አስተዳደር ጤንነትን በመመርመር ማወቅ ይፈልጋሉ፡፡ በመንግሥት የሚከናወኑ ፕሮጀክቶች የገቢ ምንጫቸው ምን እንደሆነ ለማወቅ ማንኛውንም ዓይነት ጥረት ያደርጋሉ፡፡ በአሁኑ ንግግር በብዙዎች ትኩረት የተሰጠው የብርን አቅም በከፍተኛ መጠን ማዳከም (ዲቫሉዌሽን) ጉዳይ የመጠይቅ ዝርዝሮች ውስጥ እንደነበር ለመረዳት ተችሏል፡፡ እነዚህና ሌሎች መሰል ጉዳዮች በወፍ በረር ሲቃኙ ከመቼውም ጊዜ በላይ ጥንቁቅ መሆንን ይጠይቃሉ፡፡ ለዚህ ደግሞ መንግሥት ወገቡን ጠበቅ አድርጎ የቤት ሥራውን ማከናወን አለበት፡፡

ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ መድረኮች ንግግርም ሆነ ድርድር ስታደርግ የኢኮኖሚ ጥንካሬዋ፣ የማደግ ተስፋዋ፣ የፋይናንስ ዘርፉ በብቃት ስለመመራቱ፣ የመንግሥት በኢኮኖሚው ውስጥ ያለው ሚና በሕግና በሥርዓት መሆን አለመሆኑ፣ ለውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት አመቺ መደላድል መኖሩ፣ ከሌብነትና ከጎታችነት የፀዳ ቢሮክራሲ መኖር፣ ትክክለኛ የዋጋ ግሽበት አኃዛዊ መረጃ ማግኘት መቻል፣ የፀጥታ ችግርና የመሳሰሉት ከእነ መፍትሔያቸው በግልጽ እንዲታወቁ ትጠየቃለች፡፡ እዚህ ላይ ልብ ማለት የሚያስፈልገው አገሮች ከአይኤምኤፍ ጋር በሚያደርጉት ድርድር ቅድመ ሁኔታዎች መኖራቸው የተለመደ መሆኑን ነው፡፡ ከቅድመ ሁኔታ በመለስ ጠንካራ ተደራዳሪ በመሆን የሚፈለገውን ማግኘት የሚቻለው ግን፣ ከተደራዳሪው አካል ጋር የሚደረጉ ድርድሮችን ሊደግፉ የሚችሉ አሳማኝ ሥራዎችን በማከናወን ነው፡፡ መንግሥት ውስጡን በማጥራት ከአይኤምኤፍ ጋር የሚደረገው ድርድር ብቃትና ብልኃት ይታከልበት!         

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች

በሥጋ ላይ አላግባብ እየተጨመረ ያለውን ዋጋ መንግሥት ሊቆጣጠረው ይገባል

በአገራችን የግብይት ሥርዓት ውስጥ ኢኮኖሚያዊ ያልሆኑ ወይም ያልተገቡ የዋጋ...

ኢትዮጵያን የተባበረ ክንድ እንጂ የተናጠል ጥረት አይታደጋትም!

ኢትዮጵያ በአሁኑ ጊዜ ከምትገኝበት ውጥንቅጥ ውስጥ የምትወጣበት ዕድል ማግኘት...

የፖለቲካ ቅኝቱ የሕዝባችንን ታሪካዊ ትስስር ለምን አያከብርም?

በንጉሥ ወዳጅነው የዓብይ አህመድ (ዶ/ር) መራሹ የ2010 ዓ.ም. የለውጥ መንግሥት...

ዛሬም ኧረ በሕግ!

በገነት ዓለሙ በዚህ በያዝነው ሚያዝያ/ግንቦት ወይም ሜይ ወር ውስጥ የተከበረው፣...

በስድስተኛው ዙር ጠቅላላና ድጋሚ ምርጫ የሚሳተፉ ፓርቲዎች በገዥው ፓርቲ ላይ ተቃውሞ እያቀረቡ ነው

በ2013 ዓ.ም. ስድስተኛው ምርጫ ባልተካሄደባቸው ክልሎች በጠቅላላና በድጋሚ ምርጫ...
spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

ኢትዮጵያን የተባበረ ክንድ እንጂ የተናጠል ጥረት አይታደጋትም!

ኢትዮጵያ በአሁኑ ጊዜ ከምትገኝበት ውጥንቅጥ ውስጥ የምትወጣበት ዕድል ማግኘት ብትችል፣ ከበርካታ ታዳጊ አገሮች የተሻለ በዕድገት ጎዳና የመገስገስ እምቅ አቅም እንዳላት የሚያጠራጥር አይደለም፡፡ ይህንን የመሰለ...

የመግባቢያ አማራጮችን ተባብሮ መፈለግ ከጥፋት ይታደጋል!

በአሁኑ ጊዜ ሕዝብና አገርን ጤና የሚነሱ በርካታ ችግሮች በየቦታው እንደ አሸን ፈልተዋል፡፡ ችግሮቹ ከመጠን በላይ እየተለጠጡ ቅራኔዎች ሲበረክቱ ሰከን ብሎ ከመነጋገር ይልቅ፣ የጉልበት አማራጭ...

አገርን ከቀውስ ውስጥ ማውጣት ብሔራዊ አጀንዳ ይሁን!

የአገራቸው መፃኢ ዕድል የሚያሳስባቸው በአገር ውስጥም ሆነ በውጭ የሚኖሩ ወገኖች፣ በየቀኑ የሚሰሟቸው ማቆሚያ ያጡ ልብ ሰባሪ የግጭትና የጦርነት ዜናዎች እንቅልፍ ይነሷቸዋል፡፡ በዚህም ምክንያት ማንኛውም...