Tuesday, May 21, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

በኢትዮጵያ ተገማች ያልሆነ የታክስ አስተዳደር እንዲስተካከል ተጠየቀ

spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

በኢትዮጵያ የሚተገበረው ተገማች ያልሆነ የታክስ አስተዳድር እንዲስተካከል የአውሮፓ ኅብረት ጠየቀ፡፡

በኢትዮጵያ የሚገኘው የአውሮፓ የንግድ ምክር ቤት በኢትዮጵያ የግብር አስተዳደር ላይ ያተኮረ የፖሊሲ ሰነድ ሚያዝያ 17 ቀን 2016 ዓ.ም. ይፋ አድርጓል፡፡

በመድረኩ የተገኙት በኢትዮጵያ የአውሮፓ ኅብረት አምባሳደር ሮላንድ ኮቢያ፣  ኢትዮጵያ ከአውሮፓ ኅብረት በጣም ምቹ የሚባል፣ የንግድ ዕድል እያገኘች ቢሆንም፣ በኢትዮጵያ ያለው የታክስ አሠራር ተለዋዋጭና ሊገመት የማይችል ለኢንቨስተሮች የማይመች ስለመሆኑ አንስተዋል፡፡

የአውሮፓ ገበያ አሜሪካ ለኢትዮጵያ ከምትሰጠው የአጎዋ ነፃ የገበያ ዕድል በተሻለ፣ ምቹ የሚባል የንግድ አማራጭ ስለመሆኑ የሚናገሩት አምባሳደሩ፣ በኢትዮጵያ የተመረቱ ማናቸውም ምርቶች በነፃ ወደ አውሮፓ ገበያ ይላካሉ ብለዋል፡፡ በዚህ ዕድል ያለምንም ታክስና የጉምሩክ ቀረጥ እንዲሁም የመጠን ገደብ ሳይደረግ የኢትዮጵያ ምርት ወደ አውሮፓ ይገባል ብለዋል፡፡

‹‹የአውሮፓ ባለሀብቶች ለኢትዮጵያ ሁለተኛ ኢንቨስተሮች ናቸው›› ያሉት አምባሳደሩ፣ ያም ሆኖ ግን በርካታ መሰናክሎች እየታዩ ነው ብለዋል፡፡ በኢትዮጵያ መዋዕለ ንዋያቸውን እያፈሰሱ ባሉ የአውሮፓ ኢንቨስተሮች ላይ የሚተገበረው ተገማች ያልሆነ የታክስ አስተዳደር ከባድና ትልቅ ማነቆ ነው ብለዋል፡፡

ኢንቨስተሮች የማይወዱትና የሚጠሉት አሠራር ‹‹የታክስ አስተዳደደሩ ተገማች አለመሆኑን ነው›› ያሉት አምባሳደሩ፣ ብዙውን ጊዜ ኢንቨስተሮች በቀላሉ የገቡበትን ሁኔታ መለማመድ የሚችሉ ቢሆንም፣ በየቀኑና በየጊዜው የሚቀያየሩ ሁኔታዎችን መገመትና ማንበብ የማይችሉ ከሆነ ግን አደገኛ እንደሚሆን ተናግረዋል፡፡

አክለውም የታክስ አስተዳደሩ እየከበደና ለመገመት የሚያዳግት እየሆነ፣ ፍትሐዊ ያልሆነ አሠራር በበዛ ቁጥር፣ የውጭ ኢንቨስተሮችን ለመሳብም ሆነ ያሉትን ለማቆየት አስቸጋሪ ያደርገዋል ብለዋል፡፡

  አርነስት ኤንድ ያንግ የተባለው ድርጅት የኢንቨስትመንት ምቹነትን በተመለከተ ያከናወናቸውን ጥናቶች በመጥቀስ፣ በኢትዮጵያ እ.ኤ.አ. በ2021 የውጭ ኢንቨስትመንት እንዲቀንስ ካደረጉ ምክንያቶች ‹‹የመጀመሪያው የታክስ አስተዳደሩ ነው›› ያሉት አምባሳደሩ፣ ይህ ሁኔታ በኢትዮጵያ አሳሳቢ ጉዳይ ነው ብለዋል፡፡ 

የንግድ ምክር ቤቱ የቦርድ ሰብሳቢ ቤን ዲፕራቴሌ በውይይቱ እንደገለጹት፣ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ተገማች ያልሆነ የታክስ ሥርዓት አስተዳደር፣ የውጭ ምንዛሪ አቅርቦት እጥረት፣ የመሬት አቅርቦትና የጉምሩክ ቀረጥ ሥርዓቱ ለኢንቨስትመንት ሥራቸው ቁልፍ ማነቆ እንደሆነባቸው ተናግረዋል፡፡

በተጨማሪም አፋጣኝ መፍትሔ የሚፈልገው የሰላምና ደኅንነት ሁኔታ ተገማች አለመሆን፣ የኢንቨስተሮች መብት አለመጠበቅ ወሳኝ የሆነ የኢንቨስትመንት ጥያቄና ሌሎች የአውሮፓ ባለሀብቶንችም ለመሳብ ሊፈቱ የሚገባቸው ጉዳዮች መሆናቸውን ጠቅሰው አሳስበዋል፡፡

በሚያሳዝን ሁኔታ በፀጥታና ደኅንነት እንዲሁም በታክስ አሠራሩ ምክንያት ኢትዮጵያን መዳረሻ አድርገው ሲመለከቱ የነበሩና ወደ አገር ውስጥ የገቡ ባለሀብቶች ሌላ መዳረሻ እያማተሩ ነው ብለዋል፡፡

ምቹ የሆነ የታክስ አስተዳደር፣ ብቁ የሆነ የታክስ ዕውቀት፣ ቴክኒካዊ የታክስ አሠራር ብቃት መኖርና፣ ባለሙያዎች መልካም ሥነ ምግባርን የተላበሱ መሆን አለባቸው ብለዋል፡፡ አክለውም የታክስ ኦዲት ማንዋሉ በሸልፍ ላይ ቢኖርም፣ ልምድና ዕውቀት ያላቸው ባለሙያዎች ባለመኖራቸው የታክስ አስተዳደሩን አበላሽቶታል፡፡

የኢንቨስትመንት ኮሚሽነሯ ወ/ሮ ሐና አርዓያ ሥላሴ በበኩላቸው፣ እንደ አንድ ቁልፍ ኃላፊነት ያለበት የኢንቨስትመንት ተቋም፣ እንዲሁም አዳዲስ ኢንቨስተሮችን ለመሳብና ያሉትን ይዞ ለማቆየት ከባለሀብቶችና ከማኅበሮቻቸው ጋር በመነጋገር ያሉ ማነቆዎችን እንፈታለን ብለዋል፡፡

በተጨማሪም የሚነሱ ቅሬታዎችን መልስ ለመስጠት በኢትዮጵያ ካለው የአውሮፓ ንግድ ምክር ቤት ጋር አብረው እንደሚሠሩ አስረድተዋል፡፡ ከንግድ ዘርፍ ጋር በቅርብ በመሥራት ኢትዮጵያን ተመራጭ ለማድረግ እንደሚሠሩ የተናገሩት ኮሚሽነሯ፣ ታክስ አስተዳደር ላይ የሚነሱ ጥያቄዎችን መፍታትና የተሻለ ምኅዳር መፍጠር ትልቁ ሥራችን ነው ብለዋል፡፡

እ.ኤ.አ. በ2012 የተቋቋመው በኢትዮጵያ የሚገኘው የአውሮፓ የንግድ ምክር ቤት ከ180 በላይ የአውሮፓ ኢንቨስተሮችን ያቀፈ ነው፡፡ ምክር ቤቱ ይፋ ያደረገው የፖሊሲ ሰነድ፣ በአገሪቱ የታክስ አስተዳደር ሒደት ውስጥ የግሉ ዘርፍ የሚያጋጥሙትን ተግዳሮቶች በተለይም፣ ከግብር ሥርዓቱ ጋር የተያያዙ ችግሮችን ለመፍታት፣ የግብር አሠራር ወጥነትን ለማሻሻል፣ የሕጎችን የተሳሳተ ትርጓሜ ለማረምና የኩባንያዎችን የኦዲት አሠራር ለማሻሻል የሚረዱ ምክር ሐሳቦችን ይዟል፡፡

የቀረበው የፖሊሲ ሰነድ የፋይናንስ ሚኒስቴር፣ የገቢዎች ሚኒስቴርና የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽንና በሌሎች የተለያዩ የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች የሚወጡ የግብር መመርያዎች አለመጣጣም፣ በግብር ከፋዮች ዘንድ ግራ መጋባትን እንደሚፈጥሩ ያመላከተ ነው፡፡

በተጨማሪም በተደጋጋሚ በሚደረጉ አድካሚ ኦዲቶችና ወጥ ባልሆኑ የግምገማ ቴክኒኮች ምክንያት በአንድ ኦዲት ተቀባይነት ያገኘ ወጪ በሌላ ኦዲት ውድቅ የሚደረግበት ግልጽ ያልሆነ አሠራር መኖሩም ተጠቁሟል፡፡

 የግብር ኦዲተሮች ያልተገደበ ሥልጣን፣ ስለተለያዩ ኢንዱስትሪዎችና ዓለም አቀፍ የግብር ስምምነቶች ካላቸው የዕውቀት ውስንነት ጋር ተዳምሮ፣ የንግድ ሥራ ሒደቱን የበለጠ አስቸጋሪ አድርጎታል ተብሏል፡፡

በታክስ ተቋሙ ድረ ገጽ ላይ ስለታክስ  ወቅታዊ የግብር መረጃ ለማግኘት አዳጋች መሆንና የታክስ ኦዲትን ጥራት የሚቆጣጠረው ተቋም ማንነት ግልጽ አለመሆን እንደ ችግር ከተነሱት ጉዳዮች ጥቂቶቹ ናቸው፡፡

ኩባንያዎች በታክስ ጉዳይ ለኢትዮጵያ የፌዴራል ይግባኝ ሰሚ ኮሚሽን ቅሬታቸውን ለማቅረብ እንዲመለስላቸው የሚጠይቁትን የግብር መጠን ሃምሳ በመቶ በቅድሚያ እንዲያስቀምጡ መገደዳቸው፣ ያለባቸውን የገንዘብ ጫና አባብሶታልም ተብሏል፡፡

በግብር ኦዲት ወቅት የግብር ከፋዮችን ከዚህ ቀደም የግብር ክፍያን በአግባቡ የመክፈል ልምድ ያላገናዘበ አገልግሎት መስጠቱም እንደ ችግር ተጠቅሷል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች