Sunday, May 19, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ማኅበራዊየአዲስ አበባ ከተማ ፈቃድ ሰጪ ተቋማት ተናበው ስለማይሠሩ ነዋሪዎች እየተንገላቱ መሆኑ ተነገረ

የአዲስ አበባ ከተማ ፈቃድ ሰጪ ተቋማት ተናበው ስለማይሠሩ ነዋሪዎች እየተንገላቱ መሆኑ ተነገረ

ቀን:

በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የሚገኙ ተቋማት በማይመለከታቸው ሥራ ፈቃድ በመስጠታቸው፣ ቁጥጥር በማድረጋቸውና በመመርያ መሠረት ተናበው ባለመሥራታቸው ኅብረተሰቡን ለእንግልት እየዳረጉ መሆናቸው ተገለጸ፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ደንብ ማስከበር ባለሥልጣን ሚያዝያ 15 ቀን 2016 ዓ.ም. ላለፉት ዘጠኝ ወራት ያከናወናቸውን ተግባራት ከአጋር አካላት ጋር በመሆን የገመገመ ሲሆን፣ ከተነሱ አንኳር ጉዳዮችም ተቋማት በማይመለከታቸው እየገቡ ፈቃድ መስጠታቸውና ቁጥጥር ማድረጋቸው የሚለው ይገኝበታል፡፡

በመድረኩ ከተለያዩ ተቋማት የተወከሉ አካላትም ያጋጠሙ ችግሮችን በዝርዝር የተናገሩ ሲሆን፣ ከመልካም አስተዳደር  ጋር  የተያያዙ ችግሮችም ተነስተዋል፡፡ የቂርቆስ ክፍለ ከተማ ደንብ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ዳኜ ሄርጴሳ፣ ፈቃድ ሰጪ ተቋማት በመብዛታቸው ሕጋዊ ዕርምጃ ለመውሰድ መቸገራቸውን  አስረድተዋል፡፡

- Advertisement -

‹‹ፈቃድ ሰጪው  አካል በዛ፣ ሁሉም ተቋም ይመለከተኛል ነው የሚለው፤›› ያሉት አቶ ዳኜ፣ ባዛሮችን ጨምሮ የመንገድ ዳር ኩነቶችንና ሊሎች ፈቃድ ፈላጊዎችን  በተመለከተ የንግድ ቢሮ፣ የትራፊክ ቁጥጥር፣ የግንባታ ፈቃድና የሥራ ዕድል ፈጠራ ሁሉም ያለ ሥልጣኑ ያገባኛል ስለሚሉና በየፊናቸው ፈቃድ እንደሚሰጡ፣ ችግሩ እንዲስተካከል አቅጣጫ ቢቀመጥም ሊስተካከል አልቻለም ብለዋል፡፡

‹‹ሁሉም ተቋማት ግባቸው አንድ ሆኖ ሳለ በአንድ ጉዳይ ላይ እንዴት የተለያዩ  ተቋማት ፈቃድ ሊሰጡ ይችላሉ?›› ሲሉ አቶ ዳኜ ጠይቀዋል፡፡ ‹‹አንዱ ተቋም  የፈቀደውን ሌላው ሲሽረው ዜጎች ለተጨማሪ ወጪና ለከፍተኛ እንግልት እየተዳረጉ ናቸው፤›› ሲሉም ተናግረዋል፡፡

የግንባታ ፈቃድና ቁጥጥር ላይ ከፍተኛ ችግር እየገጠማቸው መሆኑን ሲያስረዱም፣ ‹‹ሥልጣናችንን ያላግባብ የምንጠቀም ከሆነ ሁላችንንም አዳጋ ላይ ነው የሚጥለን፡፡ ሥልጣናችን ገደብ አለው፣ ሁሉም ነገር በሕግና በመመርያ ሊሆን ይገባል፡፡ ዘው ብሎ ያለ መመርያ ፈቃድ መስጠት ተገቢ አይደለም፤›› ብለዋል፡፡

የግንባታና ቁጥጥር ባለሥልጣን ፈቃድ በሚሰጥበት ወቅትም ለደንብ ማስከበር በግልባጭ ሊያሳውቅ ይገባል ሲሉ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡

የእሑድ ገበያንም በተመለከተ አስተያየታቸውን የሰጡት አቶ ዳኜ፣ የእሑድ ገበያ ዋጋን ለማረጋገት ተብሎ የተቋቋመ ሆኖ ሳለ ከምግብ ፍጆታዎች ውጪ ያሉ እንደ ጫማና ልብስ ሲሸጡ ይስተዋላሉ ብለዋል፡፡ ‹‹ደንቦችም በተሰጣቸው ሥልጣን መሠረት ነጋዴዎችን ሲጠይቁ፣ ከንግድ ቢሮ ፈቃድ መውሰዳቸውን ያሳያሉ፣ ይህ የእሑድ ገበያ ከቋቋመበት ዓላማ አንፃር ሊታይና ወጥ አሠራር  ሊበጅለት  ይገባል፤›› ሲሉ አሳስበዋል፡፡ 

ከፈቃድ አሰጣጠጥ ጋር ተያይዞ  ምላሽ የሰጡት የደንብ ማስከበር ባለሥልጣን  ምክትል ኃላፊ ወ/ሮ አበባ እሸቴ፣ ‹‹አንዳንዴ ለባዛር፣ ለእሑድ ገበያና ለመሳሰሉት ፈቃድ ሰጪው ማን እንደሆነ አይታወቅም፤›› ብለዋል፡፡

በቅንጅት የመሥራት ችግር መኖሩን የተረዳው የከንቲባ ጽሕፈት ቤት የደንብ ማስከበር ባለሥልጣንን፣ የንግድ ቢሮና የትራፊክ ማኔጅመንትን ጠርቶ አቅጣጫ ቢሰጥም በተሰጠው አቅጣጫ መሠረት ተፈጻሚ አልሆነም ሲሉ አስረድተዋል፡፡

‹‹ሁሉም ፈቃድ ሰጪ ሆኖ ተቸግረናል የተባለው አስተያየት ትክክል ነው፣ እኛም ተቸግረናል፡፡ በቀጣይ ግን ሁላችንም ልንታገልበት ይገባል፤›› ብለዋል፡፡

‹‹የወረዳ ደንብ ማስከበር ሕገወጥ ዕርድ እየደገፉ ነው፣ አብዛኛዎቹ የኪራይ ሰብሳቢነት አስተሳሰብ አላቸው ብዬ አምናለሁ፣እርስ በርሳችን የማንደማመጥና የማንደጋገፍ ከሆነ ትክክል አይደለም፤›› ያሉት ደግሞ የአዲስ አበባ የቄራዎች ድርጅት ተወካይ ናቸው፡፡

በሌላ በኩል ሕገወጥ ናቸው ተብለው በጋራ እንዲታሸጉ የሚደረጉ ልኳንዳ  ቤቶችን በጎን በመሄድ ገንዘብ ተቀብለው የሚያስከፍቱ ስለመኖራቸው ተናግረው፣ ለዚህም ማሳያ ብለው ያቀረቡት ቀደም ሲል በአራዳ ክፍለ ከተማ ወረዳ 05 ውስጥ ከተለያዩ አካላት የተዋቀረው ኮሚቴ ተወያይቶ ያሸጋቸውን ቤቶች የወረዳው ደንብ ማስከበር ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ሥልጣኑን ተመክቶ ማስከፈቱን አስታውሰዋል፡፡

ተወካዩ ይኼንን ቢሉም፣ ‹‹ለሚፈጠረው ብልሹ አሠራር ተጠያቂዎቹ የቄራዎች ድርጅት ኃላፊዎችና ሠራተኞች ናቸው፤›› የሚል ምላሸ ከደንብ ማስከበር ጽሕፈት ቤት ተሰጥቷል፡፡ የድርጅቱ ሁለት ሠራተኞችም በሕገወጥ ዕርድ ሲሳተፉ ተይዘዋል ብሏል፡፡

ባለሥልጣኑ ከአጋር አካላት ጋር በመሆን በአዋኪ ድርጅቶችና በሕገወጥ ንግድ ላይ ወደ ኅብረተሰቡ በመግባት ሰፊ የግንዛቤ ማስጨበጥ ሥራ እየሠራና ከጥፋታቸው በማይመለሱት ላይ ዕርምጃ ቢወሰድም፣ ውጤቱ በሚፈለገው ልክ እንዳልሆነ ወ/ሮ አበባ ተናግረዋል፡፡ ለምን ችግሩ አልተቀረፈም በሚለው ላይ ሳይንሳዊ ጥናት እንዲደረግ በቅርቡ ውል መዋዋላቸውንም  አክለዋል፡፡

‹‹ቅጣት የመጀመሪያው ግባችን ባይሆንም፣ ደንብን ተላልፈው በተገኙ ከሁለት ሚሊዮን በላይ የመዲናዋ ነዋሪዎች ላይ የቅጣት ዕርምጃ ተወስዷል፤›› ያሉት ደግሞ፣  የደንብ ማስከበር ባለሥልጣን ዋና ኃላፊ አቶ ደሳለኝ ፉፋ ናቸው፡፡

በጋራ የሚታሸጉ ንግድ ቤቶችን ባለድርሻ አካላት በጋራ ተወያይቶ ችግሩን ከፈታ በኋላ በጋራ መከፈት ይኖርበታል ያሉት አቶ ደሳለኝ፣ በተለይ ማሸግና መክፈት የንግድ ቢሮ ኃላፊነት በመሆኑ ኃላፊነቱን በአግባቡ ሊወጣ ይገባል ብለዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

በሥጋ ላይ አላግባብ እየተጨመረ ያለውን ዋጋ መንግሥት ሊቆጣጠረው ይገባል

በአገራችን የግብይት ሥርዓት ውስጥ ኢኮኖሚያዊ ያልሆኑ ወይም ያልተገቡ የዋጋ...

ኢትዮጵያን የተባበረ ክንድ እንጂ የተናጠል ጥረት አይታደጋትም!

ኢትዮጵያ በአሁኑ ጊዜ ከምትገኝበት ውጥንቅጥ ውስጥ የምትወጣበት ዕድል ማግኘት...

የፖለቲካ ቅኝቱ የሕዝባችንን ታሪካዊ ትስስር ለምን አያከብርም?

በንጉሥ ወዳጅነው የዓብይ አህመድ (ዶ/ር) መራሹ የ2010 ዓ.ም. የለውጥ መንግሥት...

ዛሬም ኧረ በሕግ!

በገነት ዓለሙ በዚህ በያዝነው ሚያዝያ/ግንቦት ወይም ሜይ ወር ውስጥ የተከበረው፣...