Sunday, May 19, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

አደይ አበባ ብሔራዊ ስታዲየም ግንባታን ያቋረጠው ተቋራጭ 419 ሚሊዮን ብር እንዲመልስ ተደረገ

spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

የአደይ አበባ ብሔራዊ ስታዲየምን ግንባታ ተረክቦ ሲያከናውን ከነበረው የቻይና ኮንስትራክሽን ዲዛይን ኮርፖሬሽን ጋር ፕሮጀክቱ ከተቋረጠ በኋላ፣ ከተከፈለው ቅድመ ክፍያ ተቀናንሶ 419 ሚሊዮን ብር ቀሪ ገንዘብ መመለሱ ተገለጸ፡፡

የባህልና ስፖርት ሚኒስቴር የ2016 በጀት ዓመት የዘጠኝ ወራት ዕቅድ አፈጻጸም ሪፖርት ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሚያዝያ 17 ቀን 2016 ዓ.ም ባቀረበበት ወቅት እንደተገለጸው፣ የአደይ አበባ ስታዲየም ግንባታ ምዕራፍ አንድ ተጠናቆ የምዕራፍ ሁለት ግንባታ አፈጻጸም ከነባሩ ተቋራጭ ጋር የውል ማቋረጥ ከተደረገ በኋላ፣ የሳይትና የማቴሪያል ርክክብ መደረጉን ሪፖርቱ ያሳያል፡፡

ረዥም ጊዜ በወሰደው የርክክብ ሒደት 183 ሚሊዮን ብር የሚገመት ንብረት ማስመለስ መቻሉን እንዲሁም የተሠሩ ሥራዎችን በጥንቃቄ ቴስት በማስደረግና በሚሰጡ አስተያየቶች መሠረት ጥራቱን የማየት ሥራና፣ ከተከፈለው ቅድመ ክፍያ ተቀናንሶ 419 ሚሊዮን ቀሪ ገንዘብ እንዲመልስ መደረጉ ተገልጿል፡፡

ለተሠሩ ሥራዎችና ለግንባታ ግብዓት ቁሳቁሶች የክፍያ ሰርተፊኬት ከተዘጋጀ በኋላ፣ ሥራውን ለማስቀጠል ኮንትራቱን ሎት በሎት ከፋፍሎ ለመሥራት እንዲቻል ሥራዎችን የመለየት፣ የሥራ ዝርዝርና የጨረታ ዶክመንቶች የማዘጋጀት ሥራዎች መሠራቱ ተጠቅሷል፡፡

በጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) አማካይነት በአጋርነት ከውጭ በተገኘ የፋይናንስ ድጋፍ ለማሠራት ድጋፍ ሰጪዎቹ በራሳቸው ሎት አንድን ለመሥራት የባለሙያዎች ቡድን በመላክ የሳይት ጉብኝትና አጠቃላይ የግንባታ ሒደቱን በተመለከተ ሰፊ መረጃና ገለጻ መሰጠቱ በሪፖርቱ ተገልጿል፡፡

ወደ አገራቸው ከተመለሱ በኋላ ለ‹‹ኤም ኤች›› አማካሪ ድርጅት ባስተላለፉት መልዕክት የውስን ጨረታ ግዥ እንዲፈጸም የሚል በመሆኑ አማካሪ ድርጅቱ ራሱ አምስት ዓለም አቀፍ ተቋራጮችን በመጋበዝ የቴክኒክና የፋይናንሽያል ፕሮፖዛላቸውን እንዲያቀርቡ አስደርጎ ግምገማውንም ራሱ አከናውኖ ከአምስቱ ኮንትራክተሮች ውስጥ ሁለቱን በመጣል የሦስቱን ድርጅቶች ፕሮፖዛሎች ለለጋሹ አካል ከላከ አራት ወራት መሆኑን በሪፖርቱ ተጠቅሷል፡፡

የአጋር ባለሙያዎችም አማካሪ ድርጅቱ የላከላቸውን የሦስቱ ድርጅቶች ፕሮፖዛሎችን ለረጅም ጊዜ ሲገመግሙ ከቆዩ በኋላ ለውሳኔ ለሚመለከተው ፋይናንሰር አስረክበው ውሳኔ እየተጠባበቁ እንደሆነ በቃል ተገልጿል ተብሏል፡፡

ይሁንና የስታዲየሙ ሎት አንድ ሥራ መጀመር በመዘግየቱ በጠቅላይ ሚኒስትሩ በተሰጠው አቅጣጫ በውስጥ አቅም ሥራውን ለማስጀመር በእንቅስቃሴ ላይ በመሆኑ በቀጣይ የአፍሪካ እግር ኳስ ዋንጫ ጨዋታን ወደ ኢትዮጵያ ለማምጣት አቅጣጫ ተቀምጦ እንቅስቃሴ መጀመሩ ተገልጿል፡፡

ለዚህም ከሚያስፈልጉ ዝግጅቶች አንዱ ፋሲሊቲዎችን አሟልቶ መገኘት በመሆኑ በሚቀጥሉት አራትና አምስት ዓመታት ደረጃቸውን የጠበቁ ቢያንስ ስድስት ስታዲየሞች እንደሚያስፈልጉ ተጠቅሷል፡፡

የአፍሪካ ዋንጫ ጨዋታውን ወደ ኢትዮጵያ ለማምጣት የባህልና ስፖርት፣ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴርና ትምህርት ሚኒስቴር የበላይ ኃላፊዎች ያቀፈ ኮሚቴ ተቋቁሞ የዝግጅቱ ፍኖተ ካርታ ተሠርቶ አስፈላጊውን ዕቅድ በማርቀቅ ላይ መሆኑንና ዕቅዱን ለማሳካት ስታዲየሞቹን በጥራት መገንባት ትኩረት እንደሚሰጠው ተገልጿል፡፡

ምክር ቤቱም በዚህና በሌሎችም አስፈላጊውን ዕገዛ እንዲያደረግ በመጠየቅ የነባሩ አዲስ አበባ ስታዲየም የዕድሳት ሥራ የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን (CAF) በሰጠው መሥፈርት መሠረት ከመጠነኛ የስታንዳርድ ሥራ በስተቀር ተጠናቅቆ ለውድድር ዝግጁ መደረጉ ተጠቅሷል።

ከስታዲየሙ ሥራ በተጨማሪ የአትሌቲክስ መሮጫ ትራክን ለመዘርጋት ኮንትራክተሩ ከውጭ ባለሙያ ጋር ስምምነት አድሮጎ ትራኩን በማስመጣት ላይ መሆኑንና የውጭ ባለሙያ ድርጅቱ የኮንትራት ውል ከገባ በኋላ ዕቃዎቹን ከቀረጥ ነፃ ለማስገባት ጥያቄ አቅርቦ ተገቢ ጥያቄ ባለመሆኑ ተቀባይነት አለማግኘቱ ተገልጿል፡፡

በመሆኑም በውሉ መሠረት እንደሚሠራ በመጠበቅ ቀሪው የስታዲየሙ የምህንድስና ሥራዎች፣ የሜዳ ሌቭል ሥራና ሳር ተከላ፣ የVIP እና ቪቪአይፒ ወንበሮችን የመግጠም ሥራ፣ የቪቪ አይፒ ሎውንጅ፣ ባለ 48 ካሬ ስክሪን ተከላ የማታ መብራት ፍለድ ላይት፣ የተጨዋቾች መልበሻ ክፍሎች፣ 13 የደጋፊ መፀዳጃ ክፍሎች፣ የቬይፕና ቪቪ አይ ፒ መፀዳጃ ክፍሎች፣ ለቪአይፒ መውጫና መውረጃ ሊፍት፣ ሚዲያ ሩም፣ የካፍ ኦፊሻል ክፍሎች፣ የመሳሰሉት በማጠናቀቅ ሜዳው ጫወታዎችን ማስተናገድ ጀምሯል ተብሏል፡፡

በቅርብ ጊዜም ብሔራዊ ቡድኑ ከሌሴቶ ብሔራዊ ቡድን ጋር የወዳጅነት ጨዋታዎች የተደረጉበት መሆኑን ተገልጿል፡፡

በአጠቃላይ በግዥ ከሚገቡ አንዳንድ ዕቃዎች በስተቀር የግንባታ ሥራው በተያዘው ዕቅድ ተጠናቆ አገልግሎት እንዲሰጥ በማስጀመር ስታዲየሙን የተሻለና የበለጠ ማራኪ ለማድረግ ከስታዲየሙ ውጪም ተጨማሪ የላንድስኬፕና የአጥር ሥራዎችም በቀጣይ እንደሚሠሩ በሪፖርቱ ተጠቅሷል፡፡

ይኼውም ውጫዊ ገጽታውን ከተማውን በሚመጥን ደረጃ በቀጣይ በስታዲየሙ ዙሪያ የኮሪደር ልማቶች እንደሚሠሩ ተገልጿል፡፡

በሌላ በኩልም ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ በአገሪቱ በአሁኑ ወቅት በዓለም አቀፍ ደረጃ የስፖርቱ ትልቅ ፈተና እየሆነ እየመጣ ነው በሚል የገለጸው፣ አበረታች ቅመሞችን ወይም ዶፒንግን በመጠቀም ያልተገባ ውጤት የማስመዝገብና የማጭበርበር ችግርን በመከላከልና በመቆጣጠር ረገድ፣ ዓለም አቀፉን የፀረ ዶፒንግ ሕግና ስታንዳርድ መሠረት ባደረገ መልኩ የኢትዮጵያ ብሔራዊ የፀረ አበረታች ቅመሞች ባለሥልጣን በየደረጃው ሰፊ የትምህርትና ሥልጠና ፕሮግራሞች እንዲሁም የሕዝብ ንቅናቄና የግንዛቤ ማስጨበጫ ተግባራቶች እየተከናወኑ ሲሆን፣ በበጀት ዓመቱ በባለፉት ዘጠኝ ወራቶች ለ3.1 ሚሊዮን ማኅበረሰብ ተሳታፊዎችን ግንዛቤያቸውን ለማሳደግ፣ ለማስተባበር፣ ድጋፍና ክትትል ለማድረግ ታቅዶ ለ2.5 ሰዎች ግንዛቤ ማስጨበጥ መቻሉን በሪፖርቱ ተገልጿል፡፡

በተመሳሳይ በተለያዩ የስፖርት ዓይነቶች የአበረታች ቅመሞች ምርመራ በውድድር ጊዜና ከውድድር ውጪ ለ700 አትሌቶች ምርመራና ቁጥጥር ለማድረግ ታቅዶ ለ583 አትሌቶች የደምና ሽንት ምርመራ የተደረገ ሲሆን፣ የዕቅዱን 83 በመቶ ማከናወኑን ጠቅሷል፡፡

የአደይ አበባ ስታዲየም ጉዳይን በተመለከተ፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩ የገቡበት ጉዳይና በዓለምም ከፍ የሚያደርግ ሥራ በመሆኑ፣ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ በይበልጥ መከታተል እንደሚገባው የጤና፣ ማኅበራዊ ልማት ባህልና ስፖርት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ወ/ሮ ወርቀሰሙ ማሞ አሳስበዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች