Friday, May 24, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ዜናአቶ ታዬ ደንደአ የፀረ ሰላም ኃይሎችን መደገፍ ወንጀል ክስ ተመሠረተባቸው

አቶ ታዬ ደንደአ የፀረ ሰላም ኃይሎችን መደገፍ ወንጀል ክስ ተመሠረተባቸው

ቀን:

የቀድሞ ሰላም ሚኒስትር ደኤታ አቶ ታዬ ደንደአ የፀረ ሰላም ኃይሎችን በመደገፍና የጦር መሳሪያ ይዞ መገኘት ወንጀል ክስ ተመሠረተባቸው።

በፍትሕ ሚኒስቴር የተደራጁና ድንበር ተሻጋሪ ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ዓቃቤ ሕግ አቶ ታዬ ላይ ሦስት ክሶችን ያቀረበው፣ በፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 1ኛ ሕገ መንግሥትና ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓት ላይ የሚፈጸሙ የወንጀል ጉዳዮችን በሚመለከተው ችሎት ሲሆን፣ በ1996 ዓ.ም. የወጣውን የወንጀል ሕግ አንቀጽ 251(ሐ) እና አንቀጽ 257(ሰ) ድንጋጌንና የጦር መሳሪያ አዋጅን ተላልፈዋል በሚል ነው፡፡

አቶ ታዬ የሰላም ሚኒስትር ደኤታ ሆነው ሲሠሩ የአገርን፣ የመንግሥትንና የሕዝብን ደኅንነት ማረጋገጥ ሲገባቸው፣ ፀረ ሰላም ኃይሎችን የሚደግፉ የፕሮፖጋንዳ መልዕክቶችን  በስማቸው በተከፈተ ማኅበራዊ ትስስር ገጽ ላይ  ሲያስተላልፉ ነበር ሲል ዓቃቤ ሕግ በክሱ ጠቁሟል፡፡

- Advertisement -

ተከሳሹ ፍቃድ ሳይኖራቸው የጦር መሳሪያ አዋጁን በመተላለፍ በታኅሳስ 1 ቀን 2016 ዓ.ም. ከሰዓት በፊት 5 ሰዓት ላይ በልደታ ክፍለ ከተማ ወረዳ 6 በሚገኝ መኖሪያ ቤታቸው ውስጥ በተደረገ ብርበራ አንድ ታጣፊ ክላሽንኮቭ የጦር መሳሪያ ከሁለት ካዝና 60 ጥይቶች ጋር መገኘቱን ዓቃቤ ሕግ በክሱ አብራርቷል፡፡

አቶ ታዬ በአራት ጠበቆቻቸው ተወክለው ችሎት ቀርበው ክሱ ከተነበበላቸው በኋላ ጠበቆቻቸው የዋስትና መብታቸው እንዲከበርላቸው ጥያቄ አቅርበዋል።

ዓቃቤ ሕግ የአቶ ታዬን የዋስትና ጥያቄ በመቃወም ለችሎቱ ባቀረበው ክርክር፣ ሰበር ሰሚ ችሎት ዋስትናን በልዩ ሁኔታ ሊከለክል የሚችልባቸው ነጥቦች እንዳሉና በተደራራቢ ክስ መከሰሳቸውንና የተከሰሱበት የሕግ ድንጋጌ ከፍ ያለ ቅጣት የሚያስቀጣ ከሆነ ዋስትና ሊያስከለክል ይችላል በማለት የዋስትና ጥያቄውን ተቃውሟል።

የተከሳሽ ጠበቆች በበኩላቸው ባቀረቡት ክርክር፣ ሰበር ሰሚ ችሎት ያስቀመጣቸው ዋስትናን ሊያስከለክሉ የሚችሉ ድንጋጌዎች፣ በደንበኛቸው ላይ የቀረበውን ክስ የሚመለከቱ አይደሉም ሲሉ መልስ ሰጥተዋል።

አቶ ታዬ ሕፃን ልጃቸውን ጥለው የታሰሩ መሆናቸውን ጠቅሰው በሕገ መንግሥቱ ተደንግጎ የሚገኘውን የሕፃናት መብት ታሳቢ ተደርጎ ዋስትናቸው ተከብሮ በውጭ ሆነው እንዲከታተሉ ጠይቀዋል።

አቶ ታዬ በቁጥጥር ሥር ሲውሉ በራሳቸውና በቤተሰባቸው ላይ የሰብዓዊ መብት ጥሰት እንደደረሰባቸው ለችሎቱ አስረድተዋል። ምርመራው ከተጠናቀቀ በኋል ዘግይቶ ክስ መቅረቡንም ተቃውመዋል።

ፍርድ ቤቱም አቶ ታዬ በአያያዝ ላይ ያቀረቡትን የመብት ጥያቄ በሚመለከት በጽሑፍ በዝርዝር ማቅረብ እንደሚችሉ አስታውቆ፣ የተጠየቀውን ዋስትና በሚመለከት መርምሮ ብይን ለመስጠት ለሚያዝያ 24 ቀን 2016 ዓ.ም. ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል።

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የማዳበሪያ አቅርቦትና ውጣ ውረዱ

በቅፅል ስሙ “The Father of Chemical Warfare” እየተባለ የሚጠራው...

የኢትዮጵያ ልማት ባንክ የትርፍ ምጣኔውን ከ70 በመቶ በላይ አሳደገ

ከሁለቱ መንግሥታዊ ባንኮች መካከል አንዱ የሆነው የኢትዮጵያ ልማት ባንክ...