Monday, May 27, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ስምምነት ሊደረስበት ያልቻለው የኢትዮጵያና የአይኤምኤፍ ድርድር

spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

ኢትዮጵያ የገጠማትን ከፍተኛ የማክሮ ኢኮኖሚ መዛባት ለማስተካከል በፅኑ የሚያስፈልጋትን የውጭ ብድር ወይም የገንዘብ ድጋፍ ለማግኘት ለዓለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም (አይኤምኤፍ) እና ለፓሪስ ክለብ አበዳሪ አገሮች ጥያቄ አቅርባ ድርድር ከጀመረች ከሁለት ዓመት በላይ ቢቆጠሩም አሁንም መንገዶቹ አልጋ በአልጋ ሊሆኑላት አልቻሉም።

ኢትዮጵያ ከገጠማት የውጭ ምንዛሪ አጣብቂኝ ለመውጣት የዓለም አቀፉን የገንዘብ ተቋም ጠቀም ያለ ብድር ማግኘት የምትሻ ቢሆንም፣ በአሁኑ ወቅት ያለባት አጠቃላይ የውጭ ዕዳ መጠን ተጨማሪ የውጭ ብድር ለማግኘት የሚያስችል አለመሆኑ ፍላጎቷን ለመፈጸም አዳጋች አድርጎባታል።

ይህንን የውጭ ዕዳ አጣብቂኝ ለመቅረፍ በማሰበም የቡድን 20 አበዳሪ አገሮች ባመቻቹት የብድር ማቅለያ ማዕቀፍ ለመጠቀም ያቀረበችው ጥያቄ ደግሞ በተለይ አሜሪካና ቻይና ከብድር ጋር በተያያዘ የገቡበት ፖለቲካዊ ተቃርኖ ሳቢያ መፍትሔ የማግኘት መንገዱን አርዝሞባታል። 

አሜሪካና ሌሎቹ የቡድን 20 አገሮች ባስቀመጡት የዕዳ ጫና ውስጥ ለገቡ አገሮች ያለባቸውን ብድር የወለድ ምጣኔና የመክፍያ ጊዜ ለማሻሻል፣ ለማራዘም ወይም የእፎይታ ጊዜ ለመስጠት የሚያስችል ጂ20 ኮመን ፍሬምወርክ (የቡድን 20 የጋራ ማዕቀፍ) የተሰኘ የብድር ማቅለያ ማዕቀፍ ያስቀመጡ ቢሆንም በዕድሉ መጠቀም የሚፈልጉ አገሮች ከቡድን 20 አባል ካልሆኑ አገሮች በዋናነትም ከቻይናና ከሌሎች የግል አበዳሪዎች ባገኙት ብድር ላይም ተመሳሳይ የዕዳ ማቅለያ ማግኘት እንደሚገባቸው አስገዳጅ ቅድመ ሁኔታ አስቀምጠዋል።

የዚህ ቅድመ ሁኔታ መሠረታዊ ዓላማ የዕዳ ማቅለያ ሥርዓቱ ፍትሐዊ እንዲሆን ማድረግ ሲሆን፣ ይኸውም ቻይናና ሌሎች የግል አበዳሪ ተቋማት ተመሳሳይና ተመጣጣኝ የዕዳ ማቅለያ የማይሰጡ ከሆነ ከፍተኛ ዕዳ ውስጥ የገቡ አገሮች ከቡድን 20 አገሮች የሚያገኙትን የዕዳ ማቅለያ ከሌሎች አገሮች በዋናነትም ከቻይናና ከግል አበዳሪ ተቋማት ለወሰዱት ብድር መክፈያ ያደርጉታል የሚል ሥጋት እንደሆነ መረጃዎች ያመለክታሉ። ኢትዮጵያ ከአውሮፓ ባንኮች የተበደረችው አንድ ቢሊዮን ዶላር ላይ መከፈል የሚጠበቅባትን 33 ሚሊዮን ዶላር ወለድ ከጥቂት ወራት በፊት ከመክፈል የታቀበችውም በዚሁ የቡድን 20 አገሮች የዕዳ ማቅለያ መርህ ላለመውጣት እንደሆነ የገንዘብ ሚኒስቴር በወቅቱ አስታውቆ ነበር።

በመሆኑም የቡድን 20 አገሮች ከላይ በተገለጸው መልኩ ከቻይና በተገኘው ብድር ላይ ተመጣጣኝ የሆነ ማሻሻያ እንዲደረግበት ግዴታ ማስቀመጣቸው ኢትዮጵያ የጠየቀችውን የዕዳ ማቅለያ ለማግኘት የተራዘሙ ዓመታትን ደጅ እንድትጠና አድርጓታል።

ከዓለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም የጠየቀችውን ብድር ለማግኘትም በሁኔታዎች ከታጀቡ መሰናክሎች ጋር መገዳደርን ደቅኖባታል።

የአይኤምኤፍ የኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክተር ጁሊ ኮዛክ እንደሚሉት፣ ኢትዮጵያ እያጋጠሟት ያሉትን ጉልህ ተግዳሮቶች ማለትም የምግብ ዋስትናን፣ የሰብዓዊ ፍላጎቶችን፣ ግጭት በተካሄደባቸው አካባቢዎች የመልሶ ግንባታ ለማካሄድና ከፍተኛ የዋጋ ንረትን ለማቃለል፣ እንዲሁም የአገር ውስጥ የኢኮኖሚ ማሻሻያ አጀንዳዎችን ለመደገፍ የገንዘብ ድጋፍ ጥያቄ ለአይኤምኤፍ አቅርባለች። የገንዘብ ድጋፍ ጥያቄው አጠቃላይ ዓላማ የኢትዮጵያን ከፍተኛ የኢኮኖሚ አቅም በተሟላ መንገድ ጥቅም ላይ ለማዋል ያለመ እንደሆነም ይገልጻሉ።

ጥያቄውን መሠረት በማድረግም የአይኤምኤፍ ልዑክ ባለፈው ጥቅምት ወር በአዲስ አበባ ተገኝቶ የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ ፕሮግራምና የተጠየቀውን ፕሮግራም የሚያጠናክሩ ማሻሻያዎችን እንዴት እንደሚደግፍ ከአገሪቱ ባለሥልጣናት ጋር ውይይት አድርጎ ነበር። በጥቅምት ወር በተካሄደው ውይይት ግን ስምምነት ላይ መድረስ አልተቻለም። 

በጥቅምት ወር የተካሄደውን ውይይት አስመልክቶ በወቅቱ መረጃ የሰጡት የአይኤምኤፍ የኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክተር ጁሊ ኮዛክ፣ ‹‹በውይይቱ ጥሩ መግባባት ተፈጥሯል። ነገር ግን ውይይቱ በቀጣይም የሚካሄድ ይሆናል። ምናልባትም በጥቂት ጊዜ ውስጥ የአይኤምኤፍ ልዑክ ወደ አዲስ አበባ እንደሚጓዝ ይጠበቃል›› ብለው ነበር።

ነገር ግን በጥቂት ጊዜ ውስጥ ይካሄዳል የተባለው ሁለተኛ ዙር ድርድር እንደተባለው አልሆነም። ወደ አዲስ አበባ ይጓዛል የተባለው የአይኤምኤፍ ቡድንም በተባለው ፍጥነት ወደ ኢትዮጵያ አልመጣም። ይሁን እንጂ የአይኤምኤፍ ቡድን ዘግይቶም ቢሆን በመጋቢት ወር መጨረሻ ላይ በአዲስ አበባ ተገኝቶ ከኢትዮጵያ ባለሥልጣናት ጋር ተወያይቷል። ነገር ግን በመጋቢት ወር በተካሄደው ድርድርም ሁለቱ ወገኖች ስምምነት ላይ መድረስ አልቻሉም።

በመጋቢት ወር መጨረሻ በተካሄደው ወይይት ላይ የተሳተፈውን የዓለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም የባለሙያዎች ልዑክ የመሩት በአልቫሮ ፒሪስ በወቅቱ የተካሄደውን ውይይት አስመልክቶ በሰጡት መግለጫም፣ ‹‹የአይኤምኤፍ ቡድን ቀደም ሲል በተደረጉት ውይይቶች ላይ በመነሳት የኢትዮጵያ ባለሥልጣናትን የኢኮኖሚ ፕሮግራም እንዴት መደገፍ እንደሚቻል በማረጋገጥ ረገድ ትልቅ መሻሻል የታየበት ውይይት ተርጓል፤›› ብለዋል። 

አክለውም ውይይቱ በሚያዝያ ወር በአሜሪካን አገር በሚካሄደው የአይኤምኤፍና የዓለም ባንክ የጋራ የስፕሪንግ ስብሰባ ወቅት እንደሚቀጥል ተናግረው ነበር።

ይሁን እንጂ ባለፈው ሳምንት በተካሄደው የአይኤምኤፍና የዓለም ባንክ የጋራ ስብሰባ ወቅት የተደረገው ድርድርም ውጤት አላመጣም።

‹‹አሁንም ልዩነቶች አሉ። ድርድሩ ግን ቀጥሏል›› ሲሉ አይኤምኤፍን በመወከል በኢትዮጵያ የገንዘብ ድጋፍ ጥያቄ ዙሪያ የሚደራደሩት አልቫሮ ፒሪስ ባለፈው ሳምንት በዋሽንግተን በተካሄደው የአይኤምኤፍና የዓለም ባንክ የስፕሪንግ ስብሰባ ወቅት ለጋዜጠኞች ተናግረዋል። 

አክለውም፣ ‹‹መጠነኛ ጥርጣሬ ቢኖረኝም ልዩነቶቹ እንደሚፈቱ ተስፋ አለኝ። ውይይቶች የሚወስዱትን ጊዜ እንደሚወስዱም መታወቅ አለበት፤›› ብለዋል። ነገር ግን አሁንም መፈታት ያለባቸው ልዩነቶች ምን እንደሆኑ ዝርዝር መግለጫ ከመስጠት ተቆጥበዋል።

የኢትዮጵያ የፋይናንስ ሚኒስትርና የማዕከላዊ ባንክ ገዥ ከአይኤምኤፍና ከዓለም ባንክ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች ጋር በዋሽንግተን ተገናኝተው በኢትዮጵያ እየተካሄዱ ያሉ የኢኮኖሚ ማሻሻያዎችን በተለይም ‹‹የውጪ ምንዛሪ መዛባትን ለማስተካከልና ኢኮኖሚውን ነፃ ለማድረግ የተጀመሩ ተግባራትን በተመለከተ መወያየታቸውን የኢትዮጵያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ሐሙስ ዕለት በሰጠው መግለጫ አስታውቋል። ‹‹ባለሥልጣናቱ አይኤምኤፍና የዓለም ባንክ የኢትዮጵያን ታላቅ የኢኮኖሚ መርሐ ግብር መደገፍ በሚችሉበት ሁኔታ ላይ ተወያይተው ተስማምተዋል›› ሲል መግለጫው ገልጿል።

ኢትዮጵያ ከዓለም ባንክ የጠየቀችውን የገንዘብ ድጋፍ በተመለከተ ሮይተርስ የጠየቃቸው የዓለም ባንክ ቃል አቀባይ ወደፊት ስምምነት ላይ እንደሚደረስ ብሩህ ተስፋ እንዳላቸው ገልጸዋል። ነገር ግን ወደዚህ ስምምነት ለመድረስ የሚቀሩ በርካታ ጉዳዮች መኖራቸውንና ቀሪ የተባሉት ጉዳዮች ዝርዝርም እየተጠናቀቀ መሆኑን ገልጸዋል።

ድርድሩን ምን አከበደው?

ኢትዮጵያ ከአይኤምኤፍ የምትፈልገው የፋይናንስ ፍላጎት 3.5 ቢሊዮን ዶላር ሲሆን፣ ከዓለም ባንክም 3.5 ቢሊዮን ዶላር የፕሮግራም ድጋፍ ለማግኘት መጠየቋን መረጃዎች ያመለክታሉ። ከዚህም በተጨማሪ ከቡድን 20 የዕዳ ማቅለያ ማዕቀፍ በመጠቀም 3.5 ቢሊዮን ዶላር የዕዳ ክፍያ እፎይታ ለማግኘት አቅዳለች።

አይኤምኤፍን በመወከል በኢትዮጵያ የገንዘብ ድጋፍ ጥያቄ ዙሪያ የሚደራደሩት አልቫሮ ፒሪስ መጠኑን ባይናገሩም በኢትዮጵያ የፋይናንስ ፍላጎት ላይ በሰፊው እንደተስማሙ ባለፈው ሳምንት ገልጸዋል። ነገር ግን የተጠየቀውን የገንዘብ ድጋፍ ለማግኘት አሁንም ገና የሚቀራት ቁልፍ ጉዳይ አለ።

መረጃዎች እንደሚያመለክቱት ኢትዮጵያ ከአይኤምኤፍ የጠየቀችውን የገንዘብ ድጋፍ እስካሁን ለማግኘት ያልቻለቸው የገንዘብ ተቋሙ ኢትዮጵያ የመገበያያ ገንዘቧን (ብር) የመግዛት አቅም እንድታዳክም በመፈለጉ ነው። በአሁኑ ወቅት አንድ ዶላር ከአገሪቱ ይፋዊ የዶላር ምንዛሪ ተመን በ50 በመቶ በላይ ብልጫ በጥቁር ገበያ እየተመነዘረ ሲሆን፣ የኢትዮጵያ መንግሥት የብር የመግዛት አቅምን በማዳካም ከኦፊሴላዊ የብር የምንዛሪ ተመኑ ከጥቁር ገበያ ተመን ጋር የተዋሃደ እንድታደርግ መጠየቋን ሪፖርተር ያነጋገራቸው ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው ምንጮች ይገልጻሉ። 

የአይኤምኤፍ ተደራዳሪው አልቫሮ ፒሪስ ግን የገንዘብ ተቋሙ እንዲህ ያለ (የብርን የመግዛት አቅም የማዳከም) ቅድመ ሁኔታ ማስቀመጡን አላረጋገጡም፣ ሆኖሞ ተቋሙ ብዙውን ጊዜ ተለዋዋጭና በገበያ ላይ የተመሠረተ የውጭ ምንዛሪ ተመን ሥርዓትን እንደሚደግፍ አስታውቋል።

የኢትዮጵያ ባለሥልጣናት የብርን የመግዛት አቅም በማዳከም የውጭ ምንዛሪ መዛባትን ማስተካከል እንደሚገባቸው የሚገነዘቡ ቢሆንም ይህንን ዕርምጃ መውሰድ አሁን በአገሪቱ ካለው ከፍተኛ የዋጋ ግሽበት፣ የምርት ፍላጎትና አቅርቦት አለመጣጣምና ከውጭ ዕዳ ክምችቷ አንፃር የሚያስከትለው ጉዳት የከፋ ይሆናል የሚል ሥጋት አላቸው። በመሆኑም የብር የመግዛት አቅምን የማዳካም አስፈላጊነት ላይ በመሠረታዊነት በማስማማት አፈጻጸሙን ግን በአንድ ጊዜ ሳይሆን በሒደት ለማድረግ አቋም መያዛቸውን ምንጮች ይገልጻሉ።

ዓለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም ግን የብር የመግዛት አቅምን በአንድ ጊዜ በማዳካም በውጭ ምንዛሪ ላይ ያለውን መዛባት በተሟላ ሁኔታ ማዳከም ይገባል የሚል አቋም እንደተያዘ የሚገልጹት ምንጮች፣ ለዚህም በመከራከሪያነት የሚቀርበው የኢትዮጵያ መንግሥት በመጀመሪያው አገር በቀል የኢኮኖሚ ሪፎርም የተጠቀሰውን የውጭ ምንዛሪ መዛባት በተራዘመ ሒደት ለማስተካከል አቅዶ ሳያሳካ መቅረቱን ነው።

የኢትዮጵያ መንግሥት እ.ኤ.አ. ከ2019 እስከ 2022 ተግባራዊ ባደረገው የመጀመሪያው አገር በቀል የኢኮኖሚ ሪፍርም ፕሮግራም ላይም የውጭ ምንዛሪ መዛባትን ለማስተካከል ዕቅድ ይዞ ነበር። በዚህ የኢኮኖሚ ሪፎርም ፕሮግራም የውጭ ምንዛሪ መዛባትን ለማስተካከል ተይዞ የነበረው ግብ መሠረታዊ ማጠንጠኛም በኦፊሳላዊ የብር የምንዛሪ ተመንና በጥቁር ገበያው የምንዛሪ ተመን መካከል ያለውን ልዩነት በማጥፋት ተመሳሳይ ወይም አንድ ዓይነት የምንዛሪ ተመን (Unified exchange rate) እንዲኖር ማድረግ ነበር። 

የፖሊሲ ጥናት ኢንስቲትዩት Assessment Report of the Homegrown Economic Reform Agenda በሚል ርዕስ የመጀመሪያውን አገር በቀል የኢኮኖሚ ሪፎርም ፕሮግራም አፈጻጸም ገምግሞ የግኝት ሪፖርቱን ከጥቂት ወራት በፊት ይፋ ያደረገ ሲሆን፣ ኢንስቲትዩቱ ባደረገው የአፈጻጸም ግምገማም፣ መንግሥት ተግባራዊ ባደረገው የመጀመሪያው አገር በቀል የኢኮኖሚ ሪፎርም ምሰሶዎች መካከል አንዱ የነበረው የውጭ ምንዛሪ መዛባትን የማስተካከል ጉዳይ ሳይሳካ መቀርቱን ይገልጻል።

የግምገማ ሪፖርቱ እንደሚያስረዳው፣ ብሔራዊ ባንክ የውጭ ምንዛሪ መዛባትን ለመቅረፍ በአገር በቀል የኢኮኖሚ ሪፎርም ትግበራው ወቅት የብርን የመግዛት አቅም በፍጥነት በማዳከም ሚዛናዊ ዋጋውን የጠበቀ እውነተኛ የምንዛሪ ተመን ላይ ለመድረስ ግብ ጥሎ ነበር። ይህንን ለማሳካትም ብሔራዊ ባንክ የብርን የመግዛት አቅም በዕቅድ ዘመኑ ሦስት ተከታታይ ዓመታት በፍጥነት ለማዳከም (ዲቫልዩ ለማድረግ) ግብ አስቀምጦ ነበር። በዚህም መሠረት፣ በመጀመሪያው ዓመት ማለትም እ.ኤ.አ. በ2020 መጨረሻ ላይ አንድ ዶላር በ34.7 ብር እንዲመነዘር፣ በ2021 መጨረሻ ላይ 40.9 ብር እንዲመነዘር፣ በ2022 መጨረሻ ላይ 45.8 ብር እንዲመነዘር ለማድረግ፣ በመጨረሻም እ.ኤ.አ. በ2024 ላይ በኦፊሳላዊ የውጭ ምንዛሪ ተመንና በጥቁር ገበያው ተመን መካከል ያለውን ልዩነት ወደ ዜሮ በማምጣት በሁለቱም ገበያዎች አንድ ዶላር የምንዛሪ ተመን በ52 ብር እንዲሆን ለማድረግ ብሔራዊ ባንክ አቅዶ እንደነበር የፖሊሲ ጥናት ኢንስቲትዩት የግምገማ ሪፖርት ያስረዳል።

ከዚህም ባለፈ በብሔራዊ ባንክ የአገሪቱን የውጭ ምንዛሪ ክምችት በከፍተኛ ደረጃ በማሳደግና በማቅረብ የውጭ ምንዛሪ ሥርዓቱ በገበያ የሚመራ ለማድረግ እንዲሁም ካስቀመጠው የውጭ ምንዛሪ ተመን ፍኖተ ካርታ ጋር ጥብቅ የገንዘብ ፖሊሲን አቀናጅቶ በመተግበር የዋጋ ንረትን ወደ ነጠላ አኻዝ ለማውረድ ግብ ጥሎ እንደነበር የግምገማ ሪፖርቱ ያስረዳል።

‹‹ይህ ግን ከላይ እንደተገለጸው ተግባራዊ ሊሆን አልቻለም፤›› የሚለው የግምገማ ሪፖርቱ፣ በኦፊሳላዊውና በጥቁር ገበያው መካከል ያለውን የምንዛሪ ተመን ልዩነት ዜሮ በማድረግ አንድ ውጥ ወይም የተቀናጀ የምንዛሪ ተመን ሥርዓት የመፍጠር ግብን ማሳካት ባለመቻሉ በገንዘብ ፖሊሲ ሪፎርም ፍኖተ ካርታው የተቀመጡ ሌሎቹ ግቦችም ተግባራዊ መሆን እንዳልቻሉ ከግምገማ ሪፖርቱ ለመረዳት ተችሏል።

መንግሥት ከአቋሙ በመንሸራተት የአይኤምኤፍን ቅድመ ሁኔታ ተቀብሎ የብር የመግዛት አቅምን ያዳክም ይሆን ወይስ በአቋሙ በመጽናት ፈተናውን በራሱ መንገድ ለመሻገር ይወስናል የሚለው በቀጣዩቹ ጥቂት ወራት የሚታወቁ ይሆናል።

የሪፖርተር ምንጮች እንደሚሉት የኢትዮጵያ መንግሥት የዓለም አቀፍ የገንዘብ ተቋሙ ያስቀመጠውን ቅድመ ሁኔታ በመቀበልና ባለመቀበል ቅርቃር ውስጥ ገብቷል። ኢትዮጵያ የገባችበትን አጣብቂኝ የበለጠ አስቸጋሪ እንደሚያርገው ከቡድን 20 የዕዳ ማቅለያ ማዕቀፍ ተጠቃሚ ለመሆን ከአይኤምኤፍ ጋር ስምምነት ላይ መድረስ አንዱ ቅድመ ሁኔታ መሆኑ ነው ሲሉ ምንጮቻችን አስረድተዋል።

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች