Monday, May 27, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ልናገር‹‹የኋላው ከሌለ የለም የፊቱ››

‹‹የኋላው ከሌለ የለም የፊቱ››

ቀን:

በአክሊሉ ባሻዬ

በቅድሚያ መጋቢት 13 ቀን 2016 ዓ.ም. ለንባብ በበቃው ሪፖርተር ዕትም ‹ልናገር› ዓምድ ሥር በተረፈ ወርቁ (ዲ/ን)፣ ‹‹እንደ ዓድዋው ሁሉ አገራችን የአትሌቲክስ ቤተ መዘክር/ሙዚየም ያስፈልጋታል›› በሚል ርዕስ የጻፉትን ጽሑፍ እንደ አንድ የስፖርተኛ ቤተሰብና በአገሩ ታሪክ የሚኮራ ግለሰብ አለማድነቅ፣ አገሩን እንደማይወድ ዜጋ ያስቆጥርብኛል፡፡

ወደ ዋናው ነጥቤ ሳመራም የዚህ ጽሑፍ አቅራቢ ይህን ጽሑፍ ለመጻፍ የተነሳሁበት ዋናው ዓላማዬ የጸሐፊውን ጽሑፍ ለመተቸት ሳይሆን፣ ጸሐፊው በሪፖርተር ዕትም ልናገር በሚለው ዓምድ ሥር የጻፉትን የታሪክ ፍሰት በተመለከተ ጥቂት ማስተካከያ ለማድረግ በማሰብ ነው፡፡

- Advertisement -

እንደ ጸሐፊው ዕይታ መጋቢት 13 ቀን 2016 ዓ.ም. ለንባብ በበቃው ሪፖርተር ዕትም፣ በሻምበል አበበ ቢቂላ አሀዱ የተባለው የኢትዮጵያውያን የኦሊምፒክ የድል ብሥራት ሌሎች በርካታ ጀግኖችን ወልዷል፡፡

ዋሚ ቢራቱ፣ ማሞ ወልዴ፣ ምሩፅ ይፍጠር፣ በላይነህ ዴንሳሞ፣ ገዛኸኝ አበራ፣ ገብረ እግዚአብሔር ገብረ ማርያም፣ ጀግናው ሻለቃ ኃይሌ ገብረ ሥላሴ፣ ቀነኒሳ በቀለ፣ ስለሺ ስኅን፣ ፋጡማ ሮባ፣ አልማዝ አያና፣ ወዘተ በዓለም አደባባይ የአገራችንን የኢትዮጵያን ስም በክብር እንዲጻፍና ሰንደቅ ዓላማዋም በድል እንዲውለበለብ ያደረጉ የሁልጊዜም ጀግኖቻችን መሆናቸውን፣ ሁሉም ኢትዮጵያዊ የሚመሰክረው ሀቅ ነው፡፡ የዚህ ጽሑፍ አቅራቢም የምስማማበት ነው፡፡

ጸሐፊው የኦሊምፒክ የድል ብሥራት በሚል የአትሌቶች መዘርዝር መነሻ ጽሑፍ ሥር በኢትዮጵያ አትሌቲክስ ተፅዕኖ ፈጣሪ አትሌቶቻችንን ሲዘረዝሩ፣ በየትኛውም የኦሊምፒክ አትሌቲክስ ቡድን ውስጥ ያልተካተቱ አትሌቶች ተጠቅሰዋል፡፡ በተቃራኒው ለኢትዮጵያ የረዥም ርቀት ሩጫ መሠረት የጣሉና በታላቁ የኦሊምፒክ መድረክ የተሳተፉ እንደ ሃምሳ አለቃ ባሻዬ ፈለቀና ወታደር ገብሬ ብርቄ የመሳሰሉ ታላላቅ የአትሌቲክስ ፈር ቀዳጆችን ገሸሽ ያደረገ መሆኑ መታረም ያለበት መሆኑ ሳይታለም የተፈታ ነው፡፡

ምንም እንኳን የዚህ ጽሑፍ አቅራቢ በሻምበል አበበ ቢቂላ አሀዱ የተባለው የወርቅ ሜዳሊያ በማራቶን ከኢትዮጵያም አልፎ ከአፍሪካ የመጀመሪያው የወርቅ ባለሜዳሊያ አትሌት መሆኑን እስማማለሁ፡፡ ይሁን እንጂ ለጀግናው አትሌት ሻምበል አበበ ቢቂላ አገሩን በኦሊምፒክ ውድድር እንዲያስጠራ ተምሳሌት የሆኑት እ.ኤ.አ. በ1956 ወይም በ1948 ዓ.ም. በሜልቦርን ኦሊምፒክ ኢትዮጵያን ወክለው የተሳተፉት፣ የመጀመሪያው ኢትዮጵያዊ ማራቶን ሯጭ ሃምሳ አለቃ ባሻዬ ፈለቀና ጓደኞቻቸው መሆናቸውን ሊዘነጋ አይገባም፡፡ ጸሐፊውም ከተለያዩ የታሪክ ዶሴዎች ተመልክተው ይህንን ጽሑፍ ጽፈው ቢሆን ኖሮ የመጀመሪያው ኢትዮጵያዊ ማራቶን ሯጭ ታሪክ ጋ መድረስ ይችሉ ነበር የሚል እምነት አለኝ፡፡

ይህንን በማስረጃ ለማረጋገጥ ጀግናው አትሌታችን ሻምበል አበበ ቢቂላ ከሮም ድል በኋላ እንደተናገረው፣ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ለሻምበል አበበ ቢቂላ 60ኛ ዓመት የሮም ኦሊምፒክ የአስደናቂ የባዶ እግር የማራቶን ድልና ከሜልቦርን እስከ ሪዮ ዴጄኔሮ የኦሎምፒክ ባለድል የሆኑ አትሌቶችን ለመዘከር በተዘጋጀው የመታሰቢያ መርሐ ግብር ከተዘጋጀው መጽሔት ላይ የሠፈረውን የታሪክ ምስክርነት ማየት ይገባል፡፡

መጽሔቱ እንደሚያትተው፣ እ.ኤ.አ. በ1956 የሜልቦርን ኦሊምፒክ ኢትዮጵያን የወከሉት አትሌቶች በቡድን ሆነው ከጀርባቸው በትልቁ “ኢትዮጵያ” የሚል ጽሑፍ የተለጠፈበት ቲሸርት ለብሰው በአዲስ አበባ ጎዳናዎች ላይ ልምምድ ሲያደርጉ የተመለከተውና ስለጉዳዩ በሚገባ ካጣራ በኋላ፣ ‹‹እኔም እንደ እነሱ አገሬን መወከል አለብኝ›› በሚል ተነሳሽነት ነበር አበበ ቢቂላ ወደ ሩጫው ዓለም የተቀላቀለው፡፡

አበበ ቢቂላ ከአገሩ አልፎ ለዓለም የሚተርፍ ብቃት እንዳለው ወዲያውኑ የተረዱት በትውልድ ፊንላንዳዊና በዜግነት ስዊድናዊው ሻለቃ ኦኒኒስካን ዘመናዊ ልምምድ ያስጀመሩት በቶሎ ነበር የሚለውን የዚህን መጽሔት የታሪክ ምስክርነት መመልከቱ፣ የአገራችን የአትሌቲክስ ስፖርት ታሪክ እንደ ዱላ ቅብብሎሽ ከትውልድ ወደ ትውልድ እየተሸጋገረ አሁን የደረስንበት ደረጃ መድረሱን ያሳየናል፡፡

የአገራችን የአትሌቲክስ ድል አንዱ ለአንዱ ፋና ወጊ እየሆነ ከሜልቦርን ኦሊምፒክ ጀምሮ እስካሁን ትውልድ ድረስ እንደ ዱላ ቅብብሎሽ በመተካካት የአገራችን የአትሌቲክስ ድል እየጎመራ በመሄድ ላይ የሚገኝ መሆኑን ለማሳየት ያህል፣ ሻምበል አበበ ቢቂላ የሜልቦርን ኦሊምፒክን ወክለው ዝግጅት ሲያደርጉ የነበሩ አትሌቶች በቡድን ሆነው ከጀርባቸው በትልቁ ኢትዮጵያ የሚል ጽሑፍ ተለጥፎበት ባያይ ኖሮ፣ ምናልባትም ሻምበል አበበ ቢቂላን በስፖርቱ መስክ ውስጥ ባላየነው ነበር፡፡

ሻምበል ምሩፅ ይፍጠርም ጀግናው አትሌታችንን አበበ ቢቂላን ባያይ ኖሮ በሞስኮ ኦሊምፒክ በ5‚000 እና በ10‚000 የወርቅ ሜዳሊያ ባላመጣ ነበር፡፡ እንዲሁም የምንጊዜውም ድንቅ አትሌታችን ሻለቃ አትሌት ኃይሌ ገብረ ሥላሴ የሻምበል ምሩፅን ድል ባይሰማ ኖሮ፣ የዓለማችን ድንቅ አትሌት ባልሆነና ኢትዮጵያን በዓለም አደባባይ ባላስተዋወቀ ነበር፡፡

ከዚህ በተጨማሪ አንደኛ አትሌት ሻለቃ ባሻ ዋሚ ቢራቱ ሩጫ እንዴት እንደጀመሩ በ1978 ዓ.ም. ታትሞ ለንባብ በበቃው በጦር ኃይሎች መጽሔት ላይ እንደተጻፈው፣ ሩጫን የወደዱት አገር ቤት እያሉ ነው፡፡ ብቻ ያኔ የማረካቸው ሩጫ ሳይሆን የሯጩ ቁመና ነበር፡፡ አገር ቤት ሆነው አንድ የማራቶን ሯጭ ፎቶግራፍ ያያሉ፡፡ ከዚያ አረማመዱንና አቋሙን ተመልክቼ እኔም ሩጫ ብጀምር ከዚህ ፎቶግራፉን ከማየው ሰውዬ የተሻለ እሆናለሁ በማለት ለመሮጥ በ1945 ዓ.ም. በጦር ሠራዊት ውስጥ ይቀጠራሉ፡፡

አትሌት ሻለቃ ባሻ ዋሚ ቢራቱ ስማቸውን ላለመጥራት የፈለጉት ፎቶግራፉን ከማየው ሰውዬ ያሉት የመጀመሪያው ኢትዮጵያዊ የኦሊምፒክ ማራቶን ሯጭ ሃምሳ አለቃ ባሻዬ ፈለቀን ነው፡፡ በዚህ ታሪካዊ መጽሔት ምስክርነት ባሻዬ ከጀግናው አትሌት ሻምበል አበበ ቢቂላ በተጨማሪ፣ ለአትሌት ሻለቃ ባሻ ዋሚ ቢራቱ አርዓያ (ፈር ቀዳጅ) መሆናቸውን መገንዘብ ይቻላል፡፡

ሁለተኛ አትሌት ሻለቃ ባሻ ዋሚ ቢራቱ ስፖርት ከጀመሩበት ከ1945 ዓ.ም. ጀምሮ ባሻዬ በ1948 ዓ.ም. 16ኛውን ኦሊምፒያድ በሜልቦርን ኦሊምፒክ ተሳትፈው እስከተመለሱ ድረስ፣ በየዓመቱ በሚካሄደው የጦር ኃይሎች ውድድር ላይ የባሻዬን እግር ተከትለው ሁለተኛ ሆነው ከመግባት ውጪ አንድም ቀን ባሻዬን በማራቶንም ሆነ በ15 ኪሎ ሜትር ሩጫ አሸንፈው የማያውቁ መሆናቸውን በራሳቸው አንደበት ጥቅምት 5 ቀን 2001 ዓ.ም. በወጣው ሪፖርተር ዕትም ከሰጡት ቃለ መጠይቅ መረዳት ይቻላል፡፡

በነገራችን ላይ ሻለቃ ባሻ ዋሚ ቢራቱ በተለያዩ የዓለም አቀፍ ውድድሮች ኦሊምፒክን ሳይጨምር መሳተፍ ቢችሉም፣ የሜልቦርን ኦሊምፒክና የሮም ኦሊምፒክ ለመሳተፍ ከሄዱት የልዑካን ቡድን ውስጥ ተካተው የነበረ ቢሆንም፣ በጤና ጉዳይ በታሪካቸው ኢትዮጵያን ወክለው በማራቶን በኦሊምፒክ ውድድር ያልሮጡ መሆናቸው ሊሰመርበት ይገባል፡፡

ስለሆነም በሪፖርተር ጋዜጣ ላይ ሃምሳ አለቃ ባሻዬ ፈለቀ የመጀመሪያው ኢትዮጵያዊ ማራቶን ሯጭ መሆናቸውን ተዓማኒነት ካላቸው የመረጃ ምንጮች አረጋግጬ የጻፍኩትን ይህን ጽሑፍ እንደምታስተናግዱልኝ አምናለሁ፡፡

ይህ በአትሌቲክስ ዘርፍ አኩሪ ታሪካችንን ሳይሰረዝና ሳይሸራረፍ ለቀጣይ ትውልድ እንዲተላለፍ ከማንም በላይ በተለይም፣ አገራችን እንደ ዓድዋው ሁሉ የአትሌቲክስ ቤተ መዘክር/ሙዚየም ያስፈልጋታል በማለት ትልቅ ሐሳብ ያነሱት ተረፈ ወርቁ (ዲ/ን) እንደ እሳቸው የታሪክና ቅርስ ባለሙያ ከሆነ ኢትዮጵያዊ ዜጋ ቀጣይ ትውልድ እንዲማርበት የማድረግ ከፍተኛ የታሪክ አደራቸውን እየተወጡ ነውና ይበል የሚያሰኝ ነው፡፡

መንግሥትም ይህን ጥያቄ ከግምት ውስጥ በማስገባት በአዲስ አበባ ዕምብርት በመሀል ፒያሳ የኢትዮጵያና የአፍሪካ/የመላው ጥቁር ሕዝብ ድል ለሆነው ለታላቁ የዓድዋ ድል መታሰቢያ ቤተ መዘክር/ሙዚየም እንደገነባው ሁሉ፣ በዓለም አደባባይ የአገራችንን ስምና ሰንደቅ ዓላማ ከፍ ላደረገውና አሁንም እያደረገ ላለው አትሌቲክስ ቤተ መዘክር/ሙዚየም የመገንባቱ ነገር በደንብ ቢታሰብበት እላለሁ፡፡

የአትሌቲክስ ፌዴሬሽን፣ ፌዴሬሽኑን እየመሩ ያሉት ጀግናዋ አትሌታችን ረዳት ኮሚሽነር ደራርቱ ቱሉ፣ እንደ ጀግናው ኃይሌ ገብረ ሥላሴ ያሉ በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚታወቁ ጀግኖች አትሌቶቻችን በአንድነት ሆነው ይህን ‹የአትሌቲክስ ሙዚየምን› የመገንባት ጉዳይ ወደ ተግባር የሚለወጥበትን እንቅስቃሴ ያደርጉ ዘንድ እኔም አደራ እላለሁ፡፡ አበቃሁ፡፡

ለአገራችን ሰላምን፣ ፍቅርንና አንድነትን ተመኘሁ!

ቸር እንሰንብት!!

ከአዘጋጁ፡- ጸሐፊው የመጀመሪያው ኢትዮጵያዊ ማራቶን ሯጭ የሃምሳ አለቃ ባሻዬ ፈለቀ ልጅ ሲሆኑ፣ ጽሑፉ የእሳቸውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን በኢሜይል አድራሻቸው Newake33@gmail.com ማግኘት ይቻላል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የፋይናንስ ኢንዱስትሪው ለውጭ ባንኮች መከፈት አገር በቀል ባንኮችን ለምን አስፈራቸው?

የማይረጥቡ ዓሳዎች የፋይናንስ ተቋማት መሪዎች ሙግት ሲሞገት! - በአመሐ...

የምርጫ 97 ትውስታ!

በበቀለ ሹሜ      መሰናዶ ኢሕአዴግ ተሰነጣጥቆ ከመወገድ ከተረፈ በኋላ፣ አገዛዙን ከማሻሻልና...

ሸማቾች የሚሰቃዩት በዋጋ ንረት ብቻ አይደለም!

የሸማች ችግር ብዙ ነው፡፡ ሸማቾች የሚፈተኑት ባልተገባ የዋጋ ጭማሪ...

መንግሥት ከለጋሽ አካላት ሀብት ለማግኘት የጀመረውን ድርድር አጠናክሮ እንዲቀጥል ፓርላማው አሳሰበ

የሦስት ዩኒቨርሲቲዎች ፕሬዚዳንቶች በኦዲት ግኝት ከኃላፊነታቸው መነሳታቸው ተገልጿል አዲስ አበባ...