Tuesday, May 21, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ኪንና ባህልለዩኔስኮ የማስመረጫ ሰነድ ዝግጅት እየተደረገለት ያለው ‹‹ፊላ››

ለዩኔስኮ የማስመረጫ ሰነድ ዝግጅት እየተደረገለት ያለው ‹‹ፊላ››

ቀን:

ቀደምትና ታሪክ ጠገብ እንደሆነ በሚወሳለት በደቡብ ኢትዮጵያ በጋርዱላ የሚገኘው የዲራሼ ብሔረሰብ፣ ልዩ በሆኑት ባህላዊ የሙዚቃ መሣሪያዎቹና ጨዋታዎቹ ታዋቂ ነው፡፡ በቀዳሚነት የሚወሳው ከአገር አልፎ ባህር ማዶ ድረስ ዕውቅናን ያገኘው ‹‹ፊላ›› የሚባለው ባህላዊ የሙዚቃ መሣሪያ ነው፡፡

‹‹ፊላ እና ሌሎች ሙዚቃዊ ጥበባት በጋርዱላ ዲራሼ›› በተሰኘው መጽሐፋቸው አቶ ፍሬው ተስፋዬ ኦዳይቴ እንደገለጹት፣ ፊላ ሦስት መሠረታዊ ትርጉሞች አሉት፡፡ ፊላ ሙዚቃን፣ ውዝዋዜንና የሙዚቃ መሣሪያን ይወክላል፡፡ በሙዚቃ መሣሪያነቱ ከ24 እስከ 32 በሚደርሱ ከአንድ ሜትር እስከ አምስት ሳንቲ ሜትር አማካይ ቁመት ባላቸው ቀርከሃና ሸንበቆ የሚበጁ በአንድ በኩል ክፍት፣ በሌላው በኩል ድፍን የሆኑ የትንፋሽ መሣሪያዎች ስብስብ ነው፡፡  

የትንፋሽ መሣሪያው ፊላ የሙዚቃ ስልቱ እንዲማረክ ያደረገው አብሮነታቸውና ብዙ በመሆናቸው ነው፡፡ በአፋቸው ከያዙት ቀርከሃ መሰል ነገር የሚወጣው ድምፅ የተለያየ ነው፡፡ በቁጥር 20 እና ከዚያ በላይ የሆኑ ሰዎች ክብ ሠርተው በአፋቸው የያዙት የትንፋሽ መሣሪያ በተጨማሪ የሰውነታቸውና እጅግ የሚያምረው የእግራቸው እንቅስቃሴ ቀልብ ይስባል፡፡

- Advertisement -

ለእነርሱ የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴያቸው በመሆኑ በመካከላቸው አንዱም ቅደም ተከተሉን የሚስት የለም፡፡ የትንፋሽ መሣሪያውን የእግራቸው እንቅስቃሴ ሲጨመርበት ልዩ ድባብ ይፈጥራል፡፡ ፊላ የትንፋሽ መሣሪያ ብቻ አይደለም ውዝዋዜውም ጭምር እንጂ፡፡

ይህን የብዙዎችን ቀልብ የሚስበው ፊላ ከተያያዥ ትውን ጥበባት ጋር ባንድነት ይበልጥ በምርምር የሚታወቅበት፣ በሒደትም ለዩኔስኮ የማስመረጫ ሰነድ ዝግጅት ለማከናወን ‹‹በዲራሼ ብሔረሰብ ባህላዊ የሙዚቃ መሣሪያ (ፊላ) እና ተያያዥ ትውን ጥበባት›› በሚል መሠረተ ሐሳብ በ2015 ዓ.ም. የአራትዮሽ የመግባቢያ ሰነድ ስምምነት መፈረሙ ይታወቃል፡፡

የዚሁ ተቀፅላ የሆነ በጋራ ምርምር ለማከናወን በተዘጋጀ ረቂቅ የትልመ ጥናት ሰነድ ላይ ምክክር መካሄዱን የኢትዮጵያ ቅርስ ባለሥልጣን አስታውቋል፡፡

ባለሥልጣኑ ከአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ፣ ከደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የባህልና ቱሪዝም ቢሮና ከጋርዱላ ዞን የባህልና ቱሪዝም መምሪያ ጋር በመተባበር ሚያዝያ 12 ቀን 2016 ዓ.ም. በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ በተዘጋጀ መድረክ በረቂቅ የትልመ ጥናት ሰነድ ላይ የሚመለከታቸው አካላት በተገኙበት ምክክር አካሂዷል፡፡

በምክክር መድረኩ ላይ የኢትዮጵያ ቅርስ ባለሥልጣን የቅርስ ምርምር መሪ ሥራ አስፈጻሚ ታደለ ሰሎሞን (ዶ/ር)፣ የዲራሼ ብሔረሰብ የበርካታ ባህልና እሴቶች እንዲሁም በትውልዶች ቅብብል የደረጀ የቅርስ ሀብቶች ባለቤት መሆኑን በተለይም፣ ዋነኛ መገለጫ የሆነውን የባህላዊ ሙዚቃ መሣሪያ ፊላና ተያያዥ ትውን ጥበባት፣ ለማጥናትና ለመሰነድ ባለሥልጣኑ የሚጠበቅበትን ኃላፊነትና ድርሻ ይወጣል በማለት አጽንኦት ሰጥተው ገልጸዋል፡፡

ከጋርዱላ የፈለቀው የፊላ ጨዋታ

በጋርዱላ ኅብረተሰብ ዘንድ እጅግ ተወዳጅ የሆነው የሙዚቃ መሣሪያ ዳንስ (ውዝዋዜ) ፊላ ነው፡፡ የፊላ ጨዋታ ታሪካዊ አመጣጥ የተለያየ መላምት ቢኖረውም፣ እስካሁን ይኼ ነው የሚባል ተጨባጭ መረጃ እንደሌለ ይወሳል፡፡

ፊላ በደቡብ ኢትዮጵያ ለሚገኙት የጋርዱላ ማኅበረሰቦች የደም ሥራቸው ጭምር ነው፡፡ ከልጅነት እስከ ዕውቀት በአካባቢው የሚኖሩ ሁሉ ያልተጫወተ አለ ለማለት ያስቸግራል፡፡ አራቱም የጋርዱላ ማኅበረሰቦች በአገር ልብሳቸው አሸብርቀውና ደምቀው ነው ፊላን የሚጫወቱት፡፡ ለብዙ ሰዓታት ሲጫወቱ ላየ አይደክማቸውም ሊል ይችላል፡፡ ነገር ግን ‹‹ጨቃ›› የሚባል ባህላዊ መጠጣቸውን እየተጎነጩ በብርታት ጨዋታውን ለረዥም ሰዓታት ይጫወታሉ፡፡

ፊላን የሚጫወቱት የደራሼ፣ የኩስዬ፣ የሞሴዬና የማሾሌ ብሔረሰቦች ናቸው፡፡ የሙዚቃ መሣሪያቸው የሚሠራው ከቀርከሃና ከሸንበቆ ሲሆን፣ በአማካይ ከአንድ ሜትር እስከ አምስት ሳንቲ ሜትር የሚደርስ ቁመት፣ በአንድ በኩል ክፍት፣ በሌላኛው ደግሞ ድፍን የሆነ የሙዚቃ መሣሪያ ነው፡፡ የሙዚቃ መሣሪያው ብዛቱ አነስተኛ የሚባለው 24 ሲሆን፣ አንዳንድ ጊዜ ስምንት ተመሳሳይን በመጨመር 48 የሚደርስበት ጊዜ አለ፡፡ 24ቱም ለፊላ ለሙዚቃ የተሰናዱት የሙዚቃ መሣሪያዎቹ ሁሉም የተለያዩ ድምፅ ያወጣሉ፡፡

የፊላው ብዛት የሚወስነው በካሳንታ/ቶንቶለያ (ትልቁ ፊላ) ቁመት ታይቶ ነው፡፡ የመጀመርያው ፊላ ቁመቱ ረዥም ከሆነ ትንሿ (ፊንት/ፈንቲያ) ድረስ ብዙ ፊላዎችን መሥራት እንደሚችሉ ብዙዎች ይናገራሉ፡፡ የተለያየ 24 ድምፅ የሚያወጣው ይህ የሙዚቃ መሣሪያ በሦስት ዋና ዋና ደረጃዎች ማኅበረሰቡ እንደሚመድበው ፍሬው ተስፋዬ በጻፉት ‹‹ፊላና ሌሎች ሙዚቃዊ ጥበባት በጋርዱላ ደራሼ›› ላይ ሠፍሯል፡፡

የሙዚቃ ባለሙያዎች እንደሚጠሩት ሦስት መሠረታዊ (ቤዞች) ድምፆች ይኖራቸዋል፡፡ እዚህ ድምፆች ከ24ቱ ስምንት ስምንት ሆነው ከሳንታ (ወፍራም ድምፅ)፣ አታንትያ (መካከለኛ ድምፅ) እና ፍትፍታ (ቀጫጭን/ቀጭን ድምፅ) በማለት ይመድቧቸዋል፡፡

ፊላ በሚሠራበት ጊዜ በባለሙያ (ስለአሠራሩ ዕውቀት ያላቸው አባት) ተመርጠው ይገመግማሉ፡፡ ለዚህ ዝግጅት ተብሎ እያንዳንዱ ድምፅ ላይ ፍተሻ ተደርጓልና አንዱ ቀዳሚና ተከታይ መሆኑን በጥንቃቄ ተከትለው ይሠራሉ፡፡ ወፍራም ድምፅና መካከለኛ ድምፅ የሚያወጣው ከቀርቀሃ የሚሠራ ሲሆን፣ ፍት ፍታዎች (ትናንሾቹ) ደግሞ ከሸንበቆ ይዘጋጃሉ፡፡ በሙዚቃ አመዳደብ ፊላ የትንፋሽ መሣሪያ ነው የሚሉ የአካባቢው ነዋሪዎች እንግዶች በአንድ ጊዜ መልመድ እንደሚከብዳቸው ይናገራሉ፡፡

የፊላ ሙዚቃን የአካባቢ ሰው ሲጫወት አይደለም ለማኅበረሰቡ ቀርቶ አዲስና እንግዳ ለሆኑ ሰዎች ለጆሮ ማራኪ ብሎ የሚነሽጥ የሙዚቃ ሥልት ነው፡፡ ፊላ የሙዚቃ መሣሪያ ብቻ አይደለም፡፡ ከፊላ ሙዚቃ መሣሪያ ጋር የሚቀርበው ልዩ ውዝዋዜ እጅግ ውበት የተላበሰ ነው፡፡ ውዝዋዜውን የሚመራው በፊላ ተጫዋቾች ውስጥ በሚገቡ ሦስት መሪዎች ሲሆን፣ ከመሀል አንደኛው ወጥቶ ከመሪ በኋላ በመመለስ ሌላኛውም እንዲሁ እየገባ፣ እየመራና እያሳየ ሙዚቃና ዳንሱን ያጣጡፉታል፡፡

የፊላን ጨዋታ እጀግ ማራኪ እንዲሆን ካደረጋቸው መካከል የፆታ እኩልነት የሚንፀባረቅበት በመሆኑም ጭምር ይመስላል፡፡ በዚህ ጨዋታ ሴቷ ከወንዱ እኩል መሪ ሆና ታስጨፍራለች፣ ብሎም ሴቶች ሲጫወቱት እጅግ ማራኪና የብዙዎችን ቀልብ የሚስብ ያደርገዋል፡፡ ከዚህ ባሻገር የፊላ ጨዋታ የሚጫወቱት ከሕፃናት ጀምሮ እስከ አዋቂ ድረስ ይጫወታሉ ማለት ድፍረት አይሆንም፡፡

ፊላን ለየት የሚደርገው መተሳሰብን፣ አንድ የመሆን፣ አንዱ የሌላውን ማክበር የሚንፀባረቅበት እንደሆነ የጊዶሌ ከተማ መሰናዶ አሳይቷል፡፡ ለምሳሌ ሁለት የተለያዩ የፊላ ተጫዋች ቡድኖች ቢኖሩና ቦታው ጠባብ ቢሆን እንኳን በጨዋታው እርስ በርስ ሲጋጩ አይታይም፡፡    

በፊላ የሙዚቃ መሣሪያ የሚወጣው ድምፅ ብቻ ሳይሆን አስገራሚ የሚያደርገው በእግሮቻቸው የሚወጡት/መሬቱን እየረገጡ) ድምፅ ብሎም ቡድኑ (እኩል) ሲጫወቱ ማየት ቀልብ የሚስብ ሥልተ ውዝዋዜ አላቸው፡፡ በፊላ ጨዋታ ጦር (ሉዳ) ሰበቃና ጋሻ፣ የሴቶች እልልታ፣ ሌላታ (ሌላኛው የትንፋሽ ሙዚቃ መሣሪያ) በመታጀብ ጨዋታው እንዲደምቅ ሚናቸው ከፍተኛ እንደሆነ ይነገራል፡፡ ሌላት ሙዚቃውና ጨዋታው እንዲደምቅ ከማድረግ ባሻገር፣ ከአንዱ ምዕራፍ ወደ ሌላኛው ምዕራፍ ሲሸጋገር ሌላት የያዘው ሰው እርሱን በመንፋት እንዲሸጋገሩ የሚያግዝ የሙዚቃ መሣሪያ ነው፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ኅብረተሰቡ ለስብስብ፣ ለሥራ ዘመቻ፣ ደቦ ሲኖር፣ ለሠርግና ለሌሎችም ግልጋሎቶችን የሚሰጥ የትንፋሽ መሣሪያ ነው፡፡

ፊላን አንዳንዶች ሲገልጹት ፍቅር፣ መተሳሰብ፣ መተጋገዝ፣ አንዱ ለሌላው ጋሻ፣ የብዝኃነት የሚያሳይ እንደሆነ ነው፡፡ ሌሎች ደግሞ ፊላ ለጋርዱላ ማኅበረሰብ የደም ሥር፣ ኅብረታቸውን የሚገልጹበት፣ በተረት እንደሚባል ‹‹50 ሎሚ ለ50 ሰው ጌጡ›› እንደሆነ ሁሉ ፊላ በአንድ ግለሰብ ለመጫወት አዳጋችና ብዙዎች የሚቀበሉት በመሆኑ ትስስርን የሚያሳይ ነው ይሉታል፡፡

ገሚሱ ደግሞ ጥላቻን ያስወገደ፣ ጀግንነትን፣ አብሮነትን የሚሳይ በመሆኑ ለጋርዱላዎች ፊላ የጀርባ አጥንታቸው ቢባል አያስደፍርም ይላሉ፡፡ ፊላን የሚጫወቱ ቡድኖች ፊታቸው በደስታ ያበራ፣ ድካምና መዛል የማይታይባቸውና አንዱ ለሌላው ያለውን ጥልቅ ፍቅር የሚገልጹበትም ጭምር ነው፡፡

ፊላን ሲጫወቱ ግለኝነትና እኔነት የማይታሰብ ነው፡፡ ምክንያቱም ፊላ የጥቂቶች፣ ፊላ የግለሰብ ሳይሆን የብዙዎች በመሆኑ ነው፡፡ ጨዋታው ያማረው የብዙ ሰዎች ስብስብ በመሆኑና በእያንዳንዱ ሰው የተዋሃደ ለጨዋታው የተፈጠሩ እስኪመስሉ ድረስ ኅብረት ስላላቸው ጭምር ነው፡፡ የሙዚቃ ሥልቱ የሚሰለች አይደለም፡፡ ዘመናዊ ሙዚቃዎች በወረት ልናዳምጣቸው እንችል ይሆናል እንጂ ቀጣይነቱ ያጠራጥራል፡፡ ነገር ግን የፊላ ጨዋታ ለዘመናት ጋርዱላዎች ሲጫወቱት የዘለቁ ማኅበረሰቦች ናቸው፡፡ ዛሬ ታይቶ ነገም የአዲስ የሚሆን የሙዚቃ ሥልት እንደሆነ የጋርዱላ አባቶች ይናገራሉ፡፡

ኢትዮጵያ በዓለም አቀፉ የባህል ተቋም ዩኔስኮ ካስመዘገበቻቸው የማይዳሰሱ ቅርሶች ተርታ፣ ድንቁን ባህላዊ የሙዚቃ መሣሪያና የጭፈራ መገለጫ የሆነውን ፊላ እንዲሠለፍ ለማድረግ የዲራሼ ወረዳ ባህልና ቱሪዝም ጽሕፈት ቤት በጊዶሌ ከተማ ለሁለተኛ ጊዜ ባሰናዳው የፊላ ፌስቲቫል ላይ እንደሚተጋ መግለጹ አይዘነጋም፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

በሥጋ ላይ አላግባብ እየተጨመረ ያለውን ዋጋ መንግሥት ሊቆጣጠረው ይገባል

በአገራችን የግብይት ሥርዓት ውስጥ ኢኮኖሚያዊ ያልሆኑ ወይም ያልተገቡ የዋጋ...

ኢትዮጵያን የተባበረ ክንድ እንጂ የተናጠል ጥረት አይታደጋትም!

ኢትዮጵያ በአሁኑ ጊዜ ከምትገኝበት ውጥንቅጥ ውስጥ የምትወጣበት ዕድል ማግኘት...

የፖለቲካ ቅኝቱ የሕዝባችንን ታሪካዊ ትስስር ለምን አያከብርም?

በንጉሥ ወዳጅነው የዓብይ አህመድ (ዶ/ር) መራሹ የ2010 ዓ.ም. የለውጥ መንግሥት...

ዛሬም ኧረ በሕግ!

በገነት ዓለሙ በዚህ በያዝነው ሚያዝያ/ግንቦት ወይም ሜይ ወር ውስጥ የተከበረው፣...