Tuesday, May 21, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

- Advertisement -

ፌርማታ ፅሁፎች

ቀጣዩ “ስቴፕ”

ትኩስ ፅሁፎች

እንደ ቀነኒሳ አይነት ልእለ-ሰብ  ሰዎችን ስታይ  የእድሜ መገስገስ አያስፈራህም፤ እድሜ ሆይ መውጊያህ ወዴት አለ? ብለህ ትፎክራለህ ፤ 

“ቀነኒሳ አንበሳ“ ይላል  ጀግና አሞጋሹ ጀግና ቴዲ አፍሮ፤ አንበሳ በምን ዕድሉ ነው ቀነኒሳን የሚስተካከለው?  አንድን አንበሳ በሀያ ዓመቱ በአፀደ ሥጋ  አታገኘውም፤ ካገኘኸው   ጭርጭስ  ብሎ፥ ጎብጦ  ቁርበቱን እየላሰ ተኝቷል፤  ቀነኒሳ ግን  በአርባ ሁለት ዓመቱ ማራቶን ያሸንፋል፡፡

ዋናው ጥያቄ- ለዕድሜ ትገብራለህ ወይስ ዕድሜን ታስገብራለህ?” የሚል  ነው፡፡

ርግጥ ነው እኔ  በዚህ ዕድሜየ እንኳን ማራቶን ልሮጥ ውድድሩን  በቲቪ ጨርሶ ለማየት ራሱ አቅምና  ትግስት የለኝም፡፡  አንዳንድ ቀን፥ ከባለንጀሮቼ  ጋር  ኳስ  ለማየት እቀመጣለሁ፤  በተቀመጥኩበት ሶፋ ላይ አራት ዙር ግልግል እንቅልፍ (ናፕ) እተኛለሁ፡፡

በቀደም ከስንት ጊዜ በሁዋላ ጂም ሄድኩ፤  አሠልጣኙ ተቀብሎ ገና የሥነልቦና ምክር እንኳ  ሳይሰጠኝ  “ሀያ ጊዜ  ቁጭ ብድግ ሥራ“ አለኝ::  “ቁጭ ማለቱ ላይ ችግር የለብኝም  ብሮ!  ብድግ ማለቱ  ላይ ግን  እገዛህን እሻለሁ” ብየው ፥ ትንሽ ወልመጥ ወልመጥ አልሁ፤

ቀጠለና  አሥር ፑሽ አፕ አዘዘልኝ፤ አምስቱን ወገቡን እንደተመታ እባብ እየተቅመደምድሁ  ሠራሁ፤  በተረፈች፥ ጉልበቴ ምንጣፉን እየሳምኩ ተነሳሁ፤  በመጨረሻ ሳልፈልግ ፥በርከክ ብየ ለወጫጫ ተራራ ሰገድሁ፡፡ 

ማጠቃለያው ላይ፥   አምስት ኪሎ ድምቤል አሸከመኝ፡፡

ከዚያ መስታወት ፊት ቆሜ፥  ከክርኔ በላይ ያለውን ክንዴን ክፍል እየዳበስኩ ገመገምኩት፤ ብዙም ሳይቆይ አሰልጣኙ  ከተፍ  አለና፥ 

“አሁን አሟሙቀሀል፤ ቀጣዩ ስቴፕ ምን እንደሆነ ታውቃለህ?” ሲል ጠየቀኝ፥

“ቀጣዩ ‹ስቴፕ›ማ ንቅሳት እሚሠሩ ሰዎችን ማፈላለግ ነው  ዠለስ“

– በዕውቀቱ ሥዩም በማኅበራዊ ገጹ እንደከተበው

- Advertisement -
- Advertisement -

ተጨማሪ ለማንበብ

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች