Wednesday, June 19, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

ወደው አይስቁ!

ሰላም! ሰላም! የሰላም ነገር ሲነሳ አዛውንቱ ባሻዬ የነገሩኝ አይረሳኝም፡፡ እኔም ከተለያዩ የዘመኑ ሰዎች የቃረምኳቸው አስፈሪ ወጎች አሉ፡፡ ያኔ ነው አሉ በዚያ የአብዮቱ ዓመታት፣ ‹‹ሰላምን ከጠረጴዛ የማይፈልግ ከጦር ሜዳ እንዲያገኝ ይገደዳል…›› የሚባል መፈክር ነበር አሉ፡፡ ያኔ መፈክሩ ሁሉ ያስፈራ ነበር፡፡ ‹‹በፊውዳሊዝም፣ በካፒታሊዝምና በኢምፔሪያሊዝም መቃብር ላይ ሶሻሊዝም ያብባል…››፣ ‹‹ትግላችን ከአድኃሪያን ጋር ብቻ ሳይሆን ከተፈጥሮም ጋር ነው…››፣ ‹‹ዲሞን በዲሞትፈር…››፣ ‹‹በመራራው ትግላችን እናሸንፋለን አንጠራጠርም…›› እና መሰል ደም የሸተታቸው መፈክሮች ሰላም አደፍርሰው ስንቶች እንዳለቁ፣ ስንቶች ለእስርና ለሥቃይ እንደተዳረጉ፣ ስንቶች ለስደት ተዳርገው አገር አልባ ሆነው እንደኖሩ አይረሳም፡፡ እኔማ ያኔ እያልኩ የዚያን ዘመን ሰቆቃ አስታወስኩ እንጂ፣ አሁንም ከዚያ የማይተናነሱ በርካታ ዘግናኝ ነገሮች እንደተፀናወቱን አብረውን አሉ፡፡ ለማንኛውም ፈጣሪያችን ይሁነን እንጂ አያያዛችን ያስፈራኛል፡፡ ምሁሩን የባሻዬ ልጅ ሥጋቴን ሹክ ስለው፣ ‹‹አንበርብር ሁን ያለው ላይቀር መንጰርጰር አይገባም…›› እያለ በዓይኑ ጠቀስ አድርጎ ያሾፍብኛል፡፡ እስቲ ይሁና!

በቀደም ዕለት የእንጀራ ነገር እያንቀዠቀዠ የት ቢወስደኝ ጥሩ ነው፡፡ ከቦሌ መድኃኔዓለም በታች ካለው መብራት ዝቅ ብሎ ካለ አዲስ ሕንፃ ከደንበኛዬ ጋር ተቀጣጥረናል፡፡ እኔ ቀደም ብዬ ደርሼ አካባቢውን እየቃኘሁ ከአንድ ዘመናዊ ልብስ መደብር ፊት ለፊት ደርሼ መቆም፡፡ እጅግ ውብና የሚያማምሩ የወንድ ልብሶችና ጫማዎች ቀልቤን ስበውት ጎራ ማለት፡፡ እንደ ቦይንግ ድሪምላይነር የሚያንሳፍፍ የሚመስል ውብ ስኒከር ጫማ ላይ ዓይኔ አርፎ ቁጥሬን ስጠይቅ መኖሩ ተነገረኝ፡፡ አስተናጋጇ በትህትና ያንን ውብ ጫማ አምጥታ ፊቴ ስታቀርብ የበለጠ አማረኝ፡፡ አገላብጬ ካየሁ በኋላ ዋጋ ስጠይቅ በተሰጠኝ መልስ ደነገጥኩ፡፡ ከድንጋጤዬ የነቃሁት በቅርብ ርቀት ተከታታይ የተኩስ ድምፅ ሲሰማ ነበር፡፡ ለተወሰኑ ደቂቃዎች የተካሄደው ተኩስ ጋብ ሲል መደብሩ ውስጥ የነበሩት በሙሉ ወደ ውጭ ተሯሩጠው ወጡ፡፡ እኔ ግን አንድ መደገፊያ ያለው ወንበር ላይ ዘፍ ብዬ ቀረሁ፡፡ ድንገቴ በሉት!

ከአፍታ በኋላ ሁኔታዎች ተረጋግተው የመደብሩ ሠራተኞችም ሆኑ ገበያተኞች ሲመለሱ ወሬው ድብልቅልቅ ብሎ ነበር፡፡ ወጣቷ አስተናጋጅ በገንዘብ የተጣሉ ሁለት ጓደኛሞች ተታኩሰው ሁለቱም መሞታቸውን መስማቷን ስትናገር፣ ጎረምሳው አስተናጋጅ ፖሊስ መኪና የሰረቁ ሰዎችን እያሳደደ ተኩስ መክፈቱን ከታማኝ ምንጭ እንደሰማ ሲያስረዳ፣ ተጨባጭ መረጃ አለኝ ያለ አንድ ሽበት ወጋ ያደረገው ጥበቃ ደግሞ ተኩሱ የተካሄደው ባንክ ለመዝረፍ ታስቦ እንደነበር ሲተነትን እኔ ፈዝዤ እየሰማሁ ነበር፡፡ ያቺ ወጣት አስተናጋጅ ቀረብ ብላ፣ ‹‹ጋሼ ጫማውን ትወስደዋለህ ወይ ሌላ ላማርጥህ…›› ስትለኝ፣ ‹‹የእኔ ልጅ አንድ ጫማ በሃያ አምስት ሺሕ ብር ሲሸጥ የሰማሁት ገና ዛሬ ስለሆነ ይለፈኝ…›› ብያት ስወጣ፣ ‹‹የነተበ ካፖርትና ባርኔጣ አድርጎ የመጣ ምስኪን ሼባ ይገዛል ብለሽ ነው የምትቅለሰለሽው…›› እያለ ጎረምሳው አስተናጋጅ ሲፎትት ሰማሁት፡፡ አካባቢው ላይ ምን እየተከናወነ እንደነበረ ወጣ ብሎ አጣርቶ መረጃ ማግኘት የተሳነው ከንቱ፣ እኔን በምስኪንነት ፈርጆ ሲዛበትብኝ አልከፋኝም ነበር፡፡ ማን ደስ ይበለው ብዬ!

ከመደብሩ እግሬን እየጎተትኩ ከመውጣቴ በጉጉት የምጠብቀው ደንበኛዬ ከተፍ አለ፡፡ እሱ በዋናው ቦሌ መንገድ በኩል ስለመጣ ተኩሱን አስመልክቼ ጥያቄ ሳቀርብለት፣ ‹‹የምን ተኩስ ነው የምትለው…›› እያለ በጥያቄ ዓይን ሲመለከተኝ፣ ‹‹አካባቢው ለአፍታ ያህል እኮ በተኩስ ተሸብሮ ነበር…›› አልኩት፡፡ እሱ ግን ግራ በተጋባ ስሜት እያየኝ፣ ‹‹አንበርብር እኔ መሀል ቦሌን አቆራርጬ ስመጣ ከግሬደርና ከቡልዶዘር ጩኸት ውጪ ምንም አልሰማሁም…›› ብሎኝ ወደ ጉዳያችን አመራን፡፡ የሄድንበትን ጉዳይ ጨራርሰን ምሳ ለመብላት ጉዞ ጀመርን፡፡ መኪናው ውስጥ ያለውን ሬዲዮ ሲከፍተው የፖሊስ መግለጫ እየተሰማ ነበር፡፡ ከመግለጫው እንደተረዳሁት ሚሊኒየም አዳራሽ አጠገብ ፖሊስ ሲከታተላቸው ከነበሩ የፋኖ ሰዎች ጋር እጅ ለማሰጠት የተካሄደ ተኩስ ነበር፡፡ ለደንበኛዬ እዚያ የልብስና የጫማ መደብር ውስጥ የሰማሁትን ወሬ ብነግረው፣ ‹‹ከአንተ እኔ ያልተጣራ ወሬ ያልሰማሁት እሻል ነበር…›› ብሎ ሳቀብኝ፡፡ ጎበዝ የድሮ ሰዎች እኮ፣ ‹‹ማን ያርዳ የቀበረ ማን ያውራ የነበረ…›› ይሉት የነበረው አባባል እጅግ በጣም ትክክል ነው፡፡ ምድረ ወሬኛ አስቸገረ እኮ!

ባለፈው ሰሞን አንድ ፖለቲከኛ ባልታወቁ ሰዎች መገደላቸው ሲነገር ድብልቅልቅ ያለ ስሜት ነበር የተሰማኝ፡፡ አንደኛው ስሜቴ ለምን ይሆን የሰው ልጅ በሌላው ወገኑ ላይ እጁን የሚያነሳው የሚለው ሲሆን፣ ሁለተኛው ስሜቴ ደግሞ የፈለገው የፖለቲካ አቋም መለያየት ቢኖር ግድያ ድረስ ለምን ይኬዳል የሚል ነው፡፡ ሐሳብን በሌላ ሐሳብ መሞገትን የመሰለ መልካም ፀጋ እያለ ምን ያጋድለናል፣ ለምንስ ሞትን ቅርባችን አድርገን እንኖራለን፣ ከግድያና ከጭካኔ ድርጊቶች ውስጥ ወጥተን በሰላማዊ መንገድ ለመነጋገርና ለመፎካከር ለምን ወኔ አጣን፣ ወዘተ እያልኩ በደላላ ጭንቅላቴ ለማሰብ ብሞክር መልስ ማግኘት አልቻልኩም፡፡ ‹‹አንበርብር ከዚህ አዙሪት ውስጥ መውጫ መንገዱ አንድና አንድ ብቻ ነው…›› የሚለኝ ምሁሩ የባሻዬ ልጅ ነው፡፡ ‹‹ምን ይሆን እባክህ…›› እያልኩ ለምላሹ ሰፍ ስል፣ ‹‹ምን መሰለህ ሕግና ሥርዓት እንዲከበር ማድረግ ብቻ ነው…›› ሲለኝ የማይጨበጥና የማይዳሰስ ነገር ሆነብኝ፡፡ ይህንን ጉዳይ ብዙ ጊዜ ብዙ ተብሎበት አዳማጭ ጠፋ እኮ፡፡ እህህህ…!

የድለላ ሥራዬ ከአንዱ ጫፍ ወደ ሌላው እያሳደደኝ ስውል የማላየውና የማልሰማው ጉድ የለም፡፡ አንዲት ሴት ወይዘሮ ለዓመታት ይገለገሉባት የነበረውን ራቭፎር መኪናቸውን በዘመናዊው ቱሶን መለወጥ ፈልገው ይቀጥሩኛል፡፡ ሳህሊተ ምሕረት አካባቢ የሚገኘው የተንጣለለ ቪላቸው ስደርስ ሊሸጡት የፈለጉት መኪና ግቢው ውስጥ ቆሟል፡፡ የተንጣለለውን ግቢ አልፌ ከበረንዳው ስደርስ ወይዘሮዋ ቡና አስፈልተው አረግራጊ ወንበራቸው ላይ ተኮፍሰው ነበር፡፡ ሰላምታ ሰጥቻቸው ወንበር ቀርቦልኝ ከመቀመጤ ከተፎ የሆነች ለግላጋ ወጣት የእጅ ውኃ ይዛልኝ ቀረበች፡፡ የቡና ቁርስ እንድቀምስ ወይዘሮዋ እጄን እንድታጠብ ሲነግሩኝ ለመግደርደር እንኳ ጊዜ አልሰጡኝም፡፡ ይሁን ብዬ ለብ ባለ ውኃ እጄን ታጥቤ በቀረበልኝ ናፕኪን አደራርቄ ስጨርስ፣ አጠገቤ የቀረበው አነስተኛ ጠረጴዛ ላይ ከምሳ የሚያስንቅ ምግብ በየዓይነቱ ተደርድሯል፡፡ ሽሮው፣ ምሥሩ፣ አተር ወጡ፣ የቲማቲም ቁርጡ፣ ስልሱ፣ የሱፍና የተልባ ፍትፍቱ፣ ስልጆውና የተሰነገ ቃሪያው ከነጭና ከቀይ የጤፍ እንጀራ ጋር ተደረደረ፡፡ ሁለት ቁርጥ ነጭ እንጀራ ዘርግቼ ከየዓይነቱ ማባያ አወጣሁና መጉረስ ስጀምር፣ ‹‹የቀይ ጤፍ እንጀራውንም ብላ እንጂ ለጤና ጥሩ ነው…›› ሲሉኝ ወይዘሮዋ፣ ‹‹ማኛው ነጩ እንጀራ ይሻለኛል፣ ቀዩ እኛ ቤት በሽ ነው…›› ስላቸው፣ ‹‹ተው አቶ አንበርብር ተው…›› እያሉ ሳቁ፡፡ ይሳቁ እንጂ!

ከወይዘሮዋ ጋር መኪናውን ለማሻሻጥ የሚያስችል መረጃ ተለዋውጠን አመሥግኜ ስንለያይ ቅድመ ኮሚሽን ሸጉጠውልኝ ነበር፡፡ እናንተዬ እኔ ግን አንድ አልገባህ ያለኝ ነገር ቢኖር፣ ወጣቶቹ እንደ ትልልቆቹ እንዲህ ያለ ወዳጅነት ማሰንበቻ አለማወቃቸው ነው፡፡ ብዙዎቹ በቃ ሲያልቅ እንገናኝ እንጂ እስቲ ተፍ ተፍ በልበት ወይም በእነሱ ቋንቋ ‹በት በት በልበት› የሚል ቃል ከአፋቸው አይወጣም፡፡ አንዳንድ መልካም ወጣቶች መኖራቸውን አልዘነጋሁም፡፡ እንዲያውም አንድ ጊዜ ከአንድ ወጣት ኢንቨስተር ጋር ሥራ ያገናኘናል፡፡ ወጣቱ ኢንቨስተር እዚህ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ አሜሪካ ደግሞ ከአንድ ታዋቂ ዩኒቨርሲቲ በማዕረግ የተመረቀ መሆኑን ሰምቻለሁ፡፡ አቤት ጨዋነት፣ አቤት ትዕግሥት፣ አቤት ደግነት፣ አቤት በቃል መገኘት፡፡ እኔማ እንደ አንተ ዓይነቱን መንታ መንታ መውለድ ነበር ብዬ መርቄዋለሁ፡፡ የዘመኑ ወጣቶች እንዲህ ዓይነት ሰብዕና ቢላበሱ እኮ ማንም እንደፈለገ እየነዳ አይጫወትባቸውም ነበር፡፡ በአቋራጭ ሁሉንም ነገር ለመጨበጥ ሲባል እኮ ነው ብዙ ነገር የሚበላሸው፡፡ ወይ ነዶ!

ደላላ ወዳጆቼ ከሚሰባሰቡበት መደበኛ ቦታችን ስደርስ ወሬው በየዓይነቱ ተዘርግቷል፡፡ ግማሹ በመሬት ላይ የተጣለው ገደብ ቢነሳም ለምን ገዥና ሻጭ እንዳልተከሰቱ በሰፊው ይተነትናል፡፡ በኮሪደር ልማት ምክንያት የሚነሱ ባለይዞታዎች የሚፈልጉትን የሚከራይ ቤት ማግኘት ያልቻሉበት ሰበብ ይደረደራል፡፡ ከአሠሪና ሠራተኛ አገናኝ እስከ ሪል ስቴት ያለው መስክ በየፈርጁ እየተሰለቀ ብዙ ይባላል፡፡ በዚህ መሀል ስልኩ የሚቀሰቅሰው ደላላ እንደ አሞራ ክንፍ አውጥቶ መብረር እስኪቃጣው ድረስ በየአቅጣጫው ይፈተለካል፡፡ እኔ ግን ብዙ ነገሮች በአዕምሮዬ ውስጥ እየወጡና እየወረዱ እንደ ፈላስፋ ለማድረግ ይቃጣቸዋል፡፡ አንዳንዶቹ ከዚህ ዓለም ውጣ ውረድና እንግልት ጋር የተያያዘው ሥጋዊ ፍላጎት ሲሆን፣ በሌላ በኩል በዚህ በኩዳዴ ፆም ተግተው የሚፆሙና የሚፀልዩ እንደ አዛውንቱ ባሻዬ ያሉ ሰዎችን እያሰብኩ እደመማለሁ፡፡ ሥጋችንና ነፍሳችንን ማዋደድ ካልተቻለ የሚከተለው ጥፋትም ይታየኛል፡፡ በእኔ ደላላ አዕምሮ ውስጥ እንዲህ ዓይነት ነገሮች ሲመላለሱ ከአንድም ሦስት ዲግሪዎችን የያዙ ምሁራን እንዴት ይሆኑ እያልኩ መብሰልሰሌ አልቀረም፡፡ እንዲያ ነው እንግዲህ!

ወገኖቼ አንዳንዴ ግራ ግብት ሲለኝ ያው የምታውቁት ምሁሩ ወዳጄ ዘንድ ሄጄ ነው ውጥረቴን የማረግበው፡፡ እሱ ደግሞ ለእኔ መድኃኒቴ ነው፡፡ በቀልድም ሆነ በቁምነገር እያዋዛ፣ አንዳንዴም እያሾፈብኝ፣ ሌላ ጊዜም ለአዕምሮዬ ጠጠር ያለ ነገር እየሰጠና በተቻለው መጠን ዕይታዬ እንዲሰፋ እያገዘኝ ሰው አድርጎኛል፡፡ እኔም ስለማላሳፍረው ጥረቴ ያስደስተዋል፡፡ አዛውንቱ አባቱ መካሪዬ፣ ተቆጪዬ፣ አፅናኜ፣ የሥነ ምግባር መምህሬ በመሆናቸው እወዳቸዋለሁ፡፡ ውዷ ባለቤቴ የሕይወቴ ንግሥት ማንጠግቦሽም ሁለቱን ወዳጆቻችንን ከልብ ታከብራለች፣ ትወዳለች፡፡ አብሮ መኖር ትርፉ ይህም አይደል፡፡ ያለንን ተካፍለንና ተሳስበን በጉርብትና ለረጅም ዓመታት በመኖራችን እንደ ቤተሰብ ነው የምንተያየው፡፡ የቤተሰቦቻችንን፣ የጎረቤቶቻችንን፣ የአካባቢያችንን ማኅበረሰብ፣ የአገራችንንና የመላውን ዓለም ጉዳይ አንስተን ስንወያይ በፍፁም ጨዋነትና ቅንነት ስለሆነ ደስታችን ወደር የለውም፡፡ የማንግባባበት ሐሳብ ሲኖር እንኳ እየተሳሳቅን እንተላለፋለን፡፡ ሥልጣኔ በሉት!

እስኪ እንሰነባበት፡፡ ቀኑ ተገባዶ ምሽቱ ሲቃረብ የተለመደችዋ ግሮሰሪ ጎራ ማለታችን ስለማይቀር ለምሁሩ የባሻዬ ልጅ ደወልኩለት፡፡ እሱም ወጥሮ ከያዘው ሥራው ትንፋሽ ማግኘት ፈልጎ ኖሮ ‹ዋን ዋን› ለማለት ግሮሰሪ ተቃጠርን፡፡ ስደርስ ግሮሰሪያችን በተለመዱት ደንበኞች ጢም ብላለች፡፡ መቀመጫዬን ይዤ አንድ ያላበው ቢራ ከማዘዜ ምሁሩ ወዳጄ ደረሰ፡፡ የሁለታችንም በአንድነት ታዞ መጎንጨት ስንጀምር የሰሞኑ ወበቅ ነበር የግሮሰሪ ታዳሚዎች ወሬ፡፡ አንዱ ይህ የአምላክ ቁጣ ነው ሲል፣ ሌላው የአምላክ ቁጣ ሳይሆን የሰው ልጅ ክፋት ውጤት ነው ይላል፡፡ የአምላክ ቁጣ ነው የሚለው የሰው ልጅ የፈጣሪን ትዕዛዛት ጥሶ እንዳሻው መሆን ሲያምረው፣ ሊቋቋመው የማይችለው ሙቀት ይለቅበትና ሩሁን ያስተዋል እያለ ይተነትናል፡፡ ያኛው ደግሞ የሰው ልጅ የምድርን ሥነ ምኅዳር በአግባቡ መጠቀም ሲገባው፣ ከመጠን ያለፈ ጥፋት በመፈጸሙ ‹በግሎባል ዋርሚንግ እየተቀጣ ነው› ብሎ የበኩሉን ተናገረ፡፡ ከወዲያ በኩል ሞቅ ያለው የሚመስል ተራቢ፣ ‹‹ሁለታችሁም ተሳስታችኋል፣ ወበቁ የመጣው እዚህ አገር ፖለቲካችን ከመጠን በላይ በመቀቀሉ ነው…›› ብሎ ሲስቅ ወደው አይስቁ ሆኖብን አብረነው ሳቅን፡፡ መልካም ሰንበት! 

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት