Wednesday, June 19, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

መንግሥት ለአገር ውስጥ ነጋዴዎች የሰጠውን ከለላ በማንሳቱ ሸማቹ ይጠቀማል!

ኢኮኖሚ ቀመስ ከሆኑ ሰሞናዊ አበይት ክስተቶች መካከል አንዱ እስካሁን ለኢትዮጵያውያን ብቻ ተገድበው የቆዩ አራት የቢዝነስ ዘርፎች ለውጭ ኩባንያዎች ክፍት መደረጋቸውን የሚደነግግ ሕግ ይፋ መደረጉ ነው፡፡ በዚህ ድንጋጌ መሠረት ለኢትዮጵያውያን ብቻ የተቀፈዱት የጅምላና ችርቻሮ ንግድ፣ እንዲሁም የወጪና ገቢ ንግድ ከዚህ በኋላ የውጭ ኩባንያዎችም የሚሳተፉበት ይሆናል፡፡

መመርያው ይፋ ከሆነ በኋላ በተለያዩ ባለሙያዎችና የኅብረተሰብ ክፍሎች በዚህ መመርያ አስፈላጊነትና ሊኖረው ይችላል ተብሎ በሚገመተው ተፅዕኖ ዙሪያ ሐሳባቸውን እየሰነዘሩ ነው፡፡ በዚህ አጭር ጊዜ ውስጥ ከተሰጡ አስተያየቶች መረዳት የሚቻለው እነዚህ በኢኮኖሚ ውስጥ ከፍተኛ ድርሻ ያላቸው የቢዝነስ ዘርፎች ለውጭ ኩባንያዎች ክፍት መሆናቸው ብዙዎች የሚስማሙበት መሆኑን ነው፡፡

በተለይ በእጅጉ የሚተቸውንና በተለያዩ መንገዶች ተሞክሮ ከመሻሻል ይልቅ እየባሰ የመጣውን የግብይት ሥርዓት ለማስተካከል በእነዚህ ቢዝነሶች ውስጥ የውጭ ኩባንያዎች እንዲገቡ መፈቀዱ ለውጥ ሊያመጣ ይችላል ተብሎ መታመኑ ነው፡፡

እነዚህ የቢዝነስ ዘርፎች በአገሬው ቢሠሩና የውጭ ኩባንያዎች ባይገቡባቸው የሚመረጥ ቢሆንም የግብይት ሥርዓቱ ከመሻሻል ይልቅ ከድጡ ወደ ማጡ እየሆነ መምጣቱ እንዲሁም በእነዚህ ዘርፎች የተሰማሩ የአገር ውስጥ ባለሀብቶች ቅጣ ያጣ የትርፍ ህዳግ ሸማቹን ማኅበረሰብ ማሰቃየቱ መንግሥት ወደዚህ ዕርምጃ እንዲገባ አስገድዶታልም ማለት ይቻላል፡፡

በአስመጪና ላኪነት ዘርፍ ላይ ያለው የተበላሸ አሠራር በዚሁ የሚቀጥል ከሆነም እንደ አገር ጉዳቱ የሚያመዝን በመሆኑ አማራጮችን መጠቀም ግድ በማለቱ  የተሰወደ ዕርምጃ ስለመሆኑ የሚገልጹም አሉ፡፡

በጅምላና በችርቻሮ ንግድ ውስጥ ያለው እጅግ የበዛ የተበለሻሸ አሠራርና አብዛኛዎቹ የፍጆታ ዕቃዎች አይነኬ በሚባሉ ጥቂት ኩባንያዎችና ግለሰብ ነጋዴዎች በሞኖፖል የተያዙ መሆናቸው ማኅበረሰቡን ላልተገባ የዋጋ ጭማሪ ዳርጓል፡፡ በመሆኑንም ቢያንስ ሸማቹን ለመታደግ እንዲህ ያሉ ሕጎች እንኳንም መጡ የሚያስብል ነው፡፡

ከሰሞኑ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ አሃዛዊ መረጃ እንዳመለከተውም ከአገሪቱ ባንኮች አብዛኛውን ብድር የሚወስዲት በጣት የሚቆጠሩ ነጋዴዎችና ኩባንያዎች ናቸው፡፡ ብድር ለጥቂቶች ብቻ ይሰጥ ከነበረ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ተበዳሪዎቹ በእነዚህ አራት የቢዝነስ ዘርፎች ላይ የተሰማሩ ግለሰቦች መሆናቸው አያጠራጥርም፡፡

ስለዚህ የአገሪቱን ቢዝነስ የሚያሽከረክሩት ጥቂቶች መሆናቸውንና ንግዶችን በሞኖፖል መያዛቸው ዋጋን እንደፈልጉ እንዲወስኑ፣ የግብይት ሥርዓቱን እንዲዘውሩ ዕድል ይሰጣቸዋል፡፡ ይህንንም እያደረጉ ነበር ወደሚለው መደምደሚያ ይወስደናል፡፡

በተለያዩ አጋጣሚዎች ስንናገር እንደነበረው በአንዳንድ ቢዝነሶች ላይ አዳዲስ ተዋንያን እንዳይገቡ ክልከላ ጭምር ይደነገግ እንደነበር ማስታወስ ተገቢ ነው፡፡

በቢዝነሳችን ሌላ አይገባም ተብሎ በተሻለ ሊሠሩ የሚችሉ ኩባንያዎችንና ግለሰብ ነጋዴዎችን በማሰነካከል ወደዚያ ሥራ እንዳይገቡ የሚያደርጉ ስውር እጆች የአገሪቱን የግብይት ሥርዓት አበለሻሽተዋል፡፡

እንዲህ ያሉ ያልተገቡ ተግባራት በገበያ መርህ የሚደረግን ነፃ ውድድርን የሚፃረር፣ መሆናቸው አብዛኛውን ኅብረተሰብ ተጠቃሚ የሚያደርግ የውድድር ሥርዓት እንዳይሰፍን እንቅፋት መሆናቸው አይጠረጠርም፡፡ በመሆኑም እንዲህ ያሉ ብልሽቶችና ሌሎች ተያያዥ የሆኑ በርካታ የግብይት ሥርዓቱ መገለጫ የሆኑ ሕመሞችን ለማከምና ወደ ትክክለኛው መንገድ እንዲራመድ እንዲህ ያሉ ውሳኔዎችን ጨከን ብሎ መተግበር ሊያስከትል ይችላል ተብሎ ከሚገመተው ተፅዕኖ በላይ ጥቅሙ ጎልቶ ሊታይ ይችላል፡፡

‹‹ገበያው እየተመራ ያለው በደላላ ነው›› ተብሎ በግልጽ በሚነገርበት ድርጊቱም በተግባር ፈጦ በሚታይበት አገር በደላላ ከሚመራ ቢዝነስ ለመላቀቅ እንደ አማራጭ በግብይት ውስጥ ሕግና ሥርዓትን ጠብቀው የሚሠሩ ተዋንያኖችን ማበርከት ነው፡፡ ለዚህም አንዱ አማራጭ ከአገሬው ሌላ ገበያውን ሊያረጋጉ የሚችሉ በውድድር የሚያምኑ ተቋማትን መጋበዝ ለትችት የሚያበቃ ነገር የለውም፡፡

መንግሥት እንዲህ ያሉ የቢዝነስ ዘርፎች ሌሎች እንዳይሳተፉበት ከለላ ሲያደርግ መቆየቱ የማይካድ ሲሆን ዘርፉን ዝግ አድርጎ መቆየቱም ቢሆን ጥቅም እስካላመጣ ድረስ ለምን እንዲህ አደረገ ብሎ ለመውቀስ እጅግ ሊከብድ ይችላል፡፡ በአግባቡ ካልሠራችሁ የውጭ ኩባንያዎችን ማምጣት ቀላል እንዳልሆነ በአገር መሪ ደረጃ ማሳሰቢያ ሲሰጥ የነበረው ዛሬ ብቻ ስላልነበር አንድ ቀን ይህ እንደሚመጣ ሳይታለም የተፈታ ጉዳይ ነበር፡፡

ይህም ባይሆን ወደ ዓለም ንግድ ድርጅት ሲገባ ደግሞ በግድ የተዘጉ በሮች መከፈታቸው አይቀርምና ውጤት ያልተገኘባቸው አንዳንድ አላስፈላጊ የሆኑ ከለላዎችን በማንሳት አብዛኛውን የሚጠቅም መንገድ መከተል ተገቢ ነው፡፡

ይህ ማለት ግን አገሬው ሊሠራ የሚችላቸውን ሥራዎች ሁሉ ለውጭ እየሰጡ የአገር ውስጥ ኩባንያዎች ይዳከሙ ማለት እንዳልሆነ ሊሰመርበት ይገባል፡፡ ውጤቱ ማዳከም መሆን የለበትም፡፡ ከውጭ ተወዳዳሪዎች እንዲመጡ የተወሰነውን ያህል የአገሬውን ነጋዴ ማበረታታትና ማጠንከር ጎን ለጎን ሊሠራበት ይገባል፡፡

ለግብይት ሥርዓቱ ብልሽት ምክንያት የሆኑትን አካላት በመለየት በአግባቡ ሊሠሩ የሚችሉትን የአገር ውስጥ አምራችና ነጋዴዎች ወደ መስመር እንዲገቡ የውድድርን ትርጉም እንዲረዱ፣ ትርፋማነት ማለት ሸማቹን መበዝበዝ ማለት እንዳልሆነ በማሳወቅ እንዲሠሩ መደረግ አለበት፡፡

እንዲህ ያለው መመርያ ተፅዕኖው እንዲቀንስ በተለይ በአምራች ዘርፎች ላይ ያሉ ኩባንያዎች ውድድሩ እንዳያበረታባቸው ሊፈጠር በሚችለው የገበያ ውድድር ጥሩ ተወዳዳሪ ሆነው እንዲዘልቁ ከወዲሁ አቅማቸውን እንዲያጎለብቱ ማድረግ ይገባል፡፡

የአገራችን አምራቾች ተወዳዳሪ መሆን ካልቻሉ ሊጎዱ የሚችሉበት ዕድል ሰፊ ነው፡፡ እንዲገቡ የተፈቀደላቸው የውጭ ኩባንያዎች የአገር ውስጥ አምራቾች የሚያመርቷቸውን ምርቶች በቀላሉ ማቅረብ የሚችሉበት ዕድል ስለሚኖር አገር በቀለ ኩባንያዎች ላይ ሊፈጥር የሚችለውን አደጋ ከግመት በማስገባት ይህንን ሥጋት ለመቀነስ ከወዲሁ ማሰብና መሥራት  ግድ ይላል፡፡

በስመ የውጭ ኩባንያዎች የሚሆነውንም የማይሆነውንም ምርት በማስገባት የሸቀጥ ማራገፊያ እንዳንሆን የመቆጣጠሪያ ስልት እስካልተበጀ ድረስ ለበጎ የታሰበው ሌላ አደጋ ይዞ ሊመጣ ይችላል፡፡

ከዚህ ባሻገር እነዚህ የውጭ ኩባንያዎች እንዲገቡ የሚፈለግበት አንዱና ዋነኛ ምክንያት ሸማቹን ምን ያህል ይታደጉታል? የአቅርቦትና ፍላጎቱ መካከል ያለውን ልዩነት በማጥበብ ረገድ አቅማቸው ምን ያህል እንደሆነ መመዘንና ይህንንም የሕጉ አካል ማድረግ በኋላ ከሚፈጠር እሰጥ አገባ ያድናል፡፡

ጉዳዩ ከአገር ሉዓላዊነት ጋር የሚያያዝ ጭምር በመሆኑ ለውጭ የኩባንያዎች የተፈቀዱት እነዚህ ዘርፎች አገርን ሊጎዱ እንዳይችሉ ባልተገባ መንገድ የአገር ውስጥ አምራቾችን እንዳይጫኑ ሕጉን ተከትሎ የሚወጡ መመርያዎች በጥንቃቄ ሊቀረፁ ይገባል፡፡

እስከዚያው ድረስ ንግድ ኅብረተሰቡን እንወክላለን የሚሉ ተቋማት እንዲህ ያሉ ወሳኝ ጉዳዮችን አይተውና ጥናት አድርገው የንግድ ኅብረተሰቡ የማይጎዳበትን መንገድ ማመላከት ሥራቸው የመሆኑን ያህል የበኩላቸውን ሊያደርጉ ይገባል፡፡

እነዚህ ተቋማት ከዚህ የበለጠ ብርቱ ጉዳይ ሊኖራቸውም አይገባም፡፡ ስለሆነም በዚህ ጉዳይ ላይ መድረክ አዘጋጅተው ሊፈጠሩ የሚችሉ ዕድሎችንና ሥጋቶችን በሚገባ ለአባሎች ማስገንዘብ አለባቸው፡፡

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት