Sunday, May 19, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

እኔ የምለዉሰው መሆን ምንድን ነው? ቅርስና ማኅበራዊ ፍትሕ

ሰው መሆን ምንድን ነው? ቅርስና ማኅበራዊ ፍትሕ

ቀን:

በሱራፌል ወንድሙ (ዶ/ር)

  1. ዳራ

ከጎራዎች፣ ከመፈራረጅ፣ ነገሮችን ከማቅለልና ከጊዜያዊ ማለባበስ ወጥተን ስለሕዝቦቻችን የተሻሉና ዘለቄታዊ ሕይወቶች ስንል በወግና በሀቅ ለመመካከር ነው ሐሳቤን የምሰነዝረው። “ለልማት” የተባለውም ለጥፋት እንዳይሆን። በአሁኑ ጊዜ በሚስተዋለው “የኮሪደር ልማት” ጉዳይ “ማኅበራዊ ቅርሶች ይጠበቁ” ማለታችን፣ ‘ለምን ድሆች ሻል ያለ ቦታ አገኙ’ የሚል “የቅንጡ” አሊያም “ውስብስብ ሁኔታዎችን ያለመገንዘብ” መስሎ መቅረቡ ትልልቅ ጥያቄዎቻችንን ያቀጭጫልም፣ ይደብቃልም። እናም የሚከተሉትን ሐሳብ ማጥሪያ ነጥቦች በማቅረብ ነው ይህንን በባህላዊ ቅርስና በማኅበራዊ ፍትሕ ዙሪያ የሚያጠነጥን ጽሑፌን የምጀምረው። በጥሞና እንድትከታተሉኝና በጋራ እንድናስብ በትህትና እጋብዛችኋለሁ።

  • በአዲስ አበባ በተወሰኑ ሥፍራዎች የጀመረውና ስትራቴጂ በተሞላው ሁኔታ (የሕዝብ ቁጣ እንዳይቀሰቀስ ይመስላል) ራሱን ቀስ በቀስ እየገለጠ ያለው የመንግሥት አካሄድ ፒያሳን በማፍረስ በመጀመሩ፣ የሕዝቡ ምላሽ ከዚያ ለመነሳት ተገዷል። ሆኖም ችግሩ የመላ አዲስ አበባ ብቻ ሳይሆን ከሌሎች ክልሎች ከተሞች፣ እንዲሁም ከአገሪቱ አጠቃላይ ሁኔታና ከዓለም አቀፍ ግንኙነቶች ጋር እንደሚተሳሰር መገንዘብ ያሻል። እናም ውይይታችን በዚያ ልክ እንጂ በፒያሳና ለነዋሪዎች የተሻለ መፀዳጃ ቤት በመስጠትና ባለመስጠት፣ ወይም ባፈጀ የቁሳዊ ቅርስ ትርክት ውስጥ ተቀርቅሮ ሊዘልቅ አይችልም፣ አይገባምም፡፡
  • ኢትዮጵያ የገባችበትን አገራዊና ዓለም አቀፋዊ ፈተናና አጣብቂኝ በግልጽ ከሕዝብ ጋር ተማክሮ አገራዊ መፍትሔ ማምጣቱ ነው የሚበጀን። መንግሥት ለተፈናቃዮች በአስቸኳይ የቀበሌ ቤቶችንም ሆነ ኮንዶሚኒየም ሊያከፋፍል የተገደደው በዚህ ችግር ውስጥ ሆኖ፣ የአዲስ አበባ ሕዝብ የሚኖሩባቸውን ሠፈሮች ለውጭና ለአገር ውስጥ ሀብታሞች ለመስጠት እየተገደደ ስለሆነ፣ ወይም ሐሳቡን ያድነኛል ብሎ ስላመነበት ይሆናል (ለዚያውም ተፈናቃዮቹ በሙሉ ቤት ሳያገኙ፣ ቤት ቁጥር ሳይኖራቸው ከተማዋን ተጠግተው ለብዙ ዘመን የኖሩ ብዙ ሰዎች ሜዳ ላይ ተጥለው፣ ብዙዎች የነበራቸውን ሀብት እያጡ፣ በጋራ አክሲዮን ገንዘብ አጠራቅመው በኖሩበት ቦታ እናልማ ቢሉም መብቶቻቸውን ተነፍገው በድንገትና በፍጥነት ከሠፈርና ከከተማቸው እንዲለቁ ተዋክበዋል። ይኼ ሁሉ በአገሪቱ ላይ አንዳች ሸክም እንዳለ ነው የሚያሳየው)፡፡
  • ሌላው ትልቅ ጥያቄ ደግሞ ለምንድን ነው የአዲስ አበባ ነዋሪዎች በኖሩባቸው ቦታዎች የተሻለ ቤት ሊሠራላቸው፣ ሕይወታቸው በሒደትም ቢሆን ከመሠረቱ ሊለወጥላቸው ያልቻለው የሚል ነው። ለሃምሳና ከዚያ በላይ ዓመታት ከኖሩበት ሥፍራ ሳይነቀሉ በከተማቸው ሊኖሩ ይገባል ከሚል መነሻ፡፡ ይህ አሁን በደረስንበት የሰብዓዊነትና የነፃነት ጥያቄ ከተማዬ የእኔ ነች፣ ከኖርኩበት ቦታ ሳልነቀል ከብዙኃኑ ጋር ልኑር የሚል ብቻ ሳይሆን ሰው መሆኔ ታውቆ የዓለም አቀፍም ሆነ የአገር አቀፍ ከበርቴዎች በዘር፣ በብሔር፣ በፆታ፣ በሃይማኖትና በአካል ጉዳተኝነቴ ሳያገሉኝ፣ ማኅበራዊ ፍትሕን ባማከለና እኛነትን ማዕከል ላይ ባስቀመጠ ሁኔታ በጋራ እንልማ የሚል ጥያቄ ነው፡፡
  • መንግሥት ከኖሩበት ለተፈናቀሉት ሰዎች ቤት ሰጥቻችኋለሁ ቢልም፣ በሄዱበት አካባቢ ምን ሠርተው እንደሚኖሩ ምንም ያቀደላቸው ነገር የለም። በድሮ ሠፈሮቻቸው ቢያንስ የዕለት ጉርሶቻቸውን አድነው የሚበሉባቸው መሠረቶችን ገንብተው ነበር፡፡
  • በዚያ ላይ የምንነጋገረው ከዚህ በፊት በነበሩ መንግሥታት ሁሉ ስለተረሱ ደሃ ሕዝቦች መሆኑን መዘንጋት የለብንም። የሚበጀው ትኩረት ሊሰጠው ከሚገባው የአገሪቱ ሥር የሰደደ ችግርና ዓለም አቀፍ ከበርቴነት ጋር አስተሳስረን፣ ሰፊውን ሕዝብ የሚባጅ መፍትሔ ይዞ መምጣት ነው። ሐሳቡ በከባድ ድህነትና ዓለም አቀፋዊ ጫና ውስጥ ስንኖር፣ ረቂቅ ድርድራችንን ለማካሄድ የምንጠቀምበት ረዥም ግብ ተደርጎ ሊወሰድ ይገባል። የተገዥ ተገዥዎችም ብንሆን ነፃነትን በምትገባን ልክ እያለምናት መንቀሳቀሱ እንደሚጠቅም ስለፍትሕ የሚያስቡና የሚታገሉ ሰዎች ይመክራሉ፡፡
  • ለይስሙላና ባልጠራ ጽንሰ ሐሳብ “ሰው ተኮር ልማት” እየተባለ ቢለፈፍም ልክ ከዚህ በፊት በገበሬዎች ላይ ሲደረግ እንደነበረው፣ መሬቱ እንጂ ሕዝቡ እንዳልተፈለገ የሚታወቀው፣ በድንገትና በአንድ ጊዜ፣ ለዚያውም በሙስሊሞችና በኦርቶዶክስ ክርስቲያኖች የፆም ፀሎት ወቅት፣ በአስፈሪ ዘመቻ እንደ ጦርነት በከተማው ሕዝብ፣ በሀብት ንብረቶቻቸው እንዲሁም በቁሳዊና መንፈሳዊ ቅርሶቻቸው ላይ በመዘመቱም ነው።
  • የችግሩን ስፋት ስናየው፣ አገራዊ ውይይቶች በተለያዩ ርዕሶች፣ በተለያዩ ሥፍራዎች ቀጣይነት ባለው መልኩ ማካሄድ እንዳለብን እንገነዘባለን። ይህንን ብዬ ወደ ተነሳሁበት የሰውነት፣ የቅርስና ማኅበራዊ ፍትሕ ርዕስ እመለሳለሁ።
  1. መግቢያ

“ሰው ተኮር ልማት እያካሄድን ነው” የሚል ዲስኩር እየሰማን፣ እዚያው በዚያው ሰዎች ተሸብረው ከመኖሪያቸው፣ ከከተማቸው ሲነቀሉ፣ ባህላዊ ቅርሶቻቸው ሲፈራርሱ ስናይ “ሰው መሆን ምንድን ነው?” ብለን ለመጠየቅ እንገደዳለን። ይህ ጽሑፍ ከተማን ከተማ የሚያሰኘው የሰው ልጆችን ተለዋዋጭ ቁሳዊና መንፈሳዊ ባህሎች እንዲሁም ታሪካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ፍላጎቶቻቸውን ባገናዘበ ሁኔታ፣ በኖሩባቸው ሥፍራዎች አቅፎ ማሳደግ መቻሉ እንደሆነ ለማሳየት ይሞክራል። የባህላዊ ቅርስ ጉዳይ እነዚህን ሐሳቦች ተንተርሶ ብቻ ሳይሆን፣ ለእነዚህ እሴቶችም ሲባል ሰፋ ተደርጎ ነው መተንተን ያለበት። በአሁኑ ጊዜ ስለባህላዊ ቅርስ እንድንነጋገር ያስገደደንም፣ ታይቶ በማይታወቅ ኃይል የመጣው “የኮሪደር ልማት” ጉዳይና ድርጊት ነው። በአዲስ አበባ በልማት ስም እየተካሄደ ያለው ሰፊ ፈረሳ፣ ብዙ የአገሪቱን አጠቃላይ ኢፍትሐዊነቶች የሚያመላክት እንደሆነና አገራዊና ዓለም አቀፋዊ አንድምታው ከፍ ያለ እንደሆነ መገንዘቡ ወሳኝ ይሆናል ማለት ነው። እናም እንዲህ ስል እከራከራለሁ። ከተማን በዘለቄታ ከተማ አድርገው በኅብር ሊያኖሩት የሚችሉት የሰዎች የዕለት ተዕለት ባህሎቻቸውና ፈጠራዎቻቸው፣ እንዲሁም ማኅበራዊ ፍትሕ ሆነው ሳለ፣ የአዲስ አበባ ነዋሪዎች በኮሪደር ልማት ስም እየተጠረጉ፣ ለብልጭልጭ ሰማይ ጠቀስ ፎቆችና ለማይታወቁ የአገር ውስጥና የውጭ አገር ሀብታሞች ተላልፈው እየተሰጡ ነው። እነዚያ ሀብታሞች ደግሞ በአገራችን ላይ ተጨባጭ የኢኮኖሚ እሴት የሚፈጥሩ ሳይሆኑ፣ በጨበጣ ውርርድ (Speculation) በሁላችን ነገ ወይም ተስፋ ላይ እየቆመሩ፣ የደሃ ሀብታችንን ወደ ፈለጉበት ቦታ የሚያሸሹበት ነው የሚሆኑት። ይህ ሥልት በብሔር ስም የሚነግዱ ባለገንዘቦችንና የውጭ ከበርቴዎችን ይጠቅም እንደሆን እንጂ፣ የትኛዋንም የኅብረተሰብ ክፍልና ማንኛውንም ብሔር አይምርም። ከተሞችን ከውስጥ ማፈናቀሉ የቆየ ችግር ቢሆንም የአሁኑ ደግሞ መጠንና ስፋቱ፣ የውስጡን ችግር ከማባባስ አልፎ፣ ወደ ጎረቤት የገበሬ መሬቶችም እየፈሰሰ ማስጨነቁ የማይቀር ነው።

- Advertisement -

ስለከተማ በጥልቅ የሚያስቡ ተንታኞች ነገሩን የሚያማልል “ዕንቁ ከተማን” እጨብጣለሁ ብሎ (የማያዛልቅ ቁሳዊነትን ለማትረፍ ልንለው እንችላለን) ነፍስያን ለሰይጣን አሳልፎ ለመስጠት እንደ መዋዋል (Faustian Bargain) ይቆጥሩታል:: ይልቁንም የድህነታችንን ሁኔታና የገባንበትን ፈተና በቅጡ ላጤነ ሰው፣ ነገሩ በታላቁ ደራሲና አሳቢ ሃዲስ ዓለማየሁ ቋንቋ “እሾህ የሚያስጨብጥ የመኖር ፍላጎት” ሊባል ይችላል። እሾሁን እንዴት እንዳይገድለን እናድርገው? እንዴትስ ጋሬጣውን እንለፍ? እንደምንስ የሕይወትን አበባ መልካም መዓዛ በእኩልነትና በጋራ እናሽትት? ነፍስያችንን ሳንሸጥ እንዴት የጋራ ሕልሞቻችን እንቅረፅ፣ እንዴትስ እንጨብጣቸው? የከተማ ነፍስያ የሚለካው በነዋሪዎችና በባህላዊ ቅርሶቻቸው እንደሆነ ዘመኑ የደረሰበት በሂስ የተሞላ ጥናት (Critical Heritage Studies) እና የፀረ ቅኝ ግዛት ዕውቀት (Decolonization of Heritage) ይነግሩናል። አይደሉም እነዚህ የጥናት መስኮች ይቅሩና አንድ ወጥ የአውሮፓን አመለካከት በዓለም ላይ ይጭናል የሚባለው የተባበሩት መንግሥታት የትምህርት፣ የሳይንስና የባህል ድርጅት-ዩኔስኮ (UNESCO) እንኳን የሚመሰክረው እውነት እየሆነ መጥቷል። ነገር ግን የአዲስ አበባ ሕዝብ መኖሪያዎች፣ ከእነ ባህል አሻራዎቻቸውና ማኅበራዊ ትስስሮቻቸው ከዚህ ቀደም ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ እየተጠረጉ ነው፣ ገና በስፋት ይጠረጋሉ። በቅርቡም እንደሰማነው ተመሳሳይ አካሄድ በድሬዳዋም ሊቀጥል ነው። ስለዚህም የዘመኑን በሂስ የተሞላ የቅርስ ጥናትና የፀረ ቅኝ ግዛት ዕውቀት ሐሳቦችን ከማኅበራዊ ፍትሕ ጥያቄዎች ጋር አያይዤ በማስረዳት፣ በኢትዮጵያ ቅርስ ባለሥልጣን መግለጫ ላይ ሂሳዊ ምልከታዬን አቀርባለሁ።

3. ባህላዊ ቅርስና ማኅበራዊ ፍትሕ፣ የሐሳብ ትንተና

3.1 ሂሳዊ ያልሆነ የቅርስ አረዳድ

የኢትዮጵያ የቅርስ ባለሥልጣን ቅርስን የሚረዳበትና መመዘኛ ነድፎ የሚተገብርበት ዕውቀት፣ ከሃምሳና ከስልሳ ዓመታት በፊት ተጠየቅ የተነሳበት ነው። ከሃምሳ ዓመታት በፊት ገዥ ሐሳብ ተደርጎ ይወሰድ የነበረውና አሁንም ርዝራዡ እንደ ኢትዮጵያ ባሉት አገሮች መሬት ነክሶ የሚገኘው የቅርስ ብያኔ፣ ጠባብ፣ አቅላይ (Reductionist)ና አግላይ (Discriminatory) ነው። በሂሳዊ የቅርስ ጥናት ውስጥ ተንታኞች የሆኑት ኪናን ጀንትሪና ላውራጄን ስሚዝ በ2001 ዓ.ም. ባሳተሙት ጥናታዊ ጽሑፍ የሚሉትን በምሳሌነት ላንሳ። ያረጀና ያፈጀ የሚባለው የቅርስ አመለካከት አፅንኦት የሚሰጠው ለቁሶችና ቁሶቹ በቅርሶቻቸው ይሸከማሉ ለሚላቸው “ፈጠራዊና ሳይንሳዊ” “እሴቶች” ነው። ቅርሶቹንም በመጠበቅና ለቀጣዩ ትውልድ በማስተላለፍ በኩል የቅርስ ኤክስፐርቶች የሚሰጡት ከፖለቲካ ሐሳብ የራቀ “ተጨባጭ” የሚባል ምዘና ዋነኛው ጉዳይ ነው ብሎ ያምናል። ይህ አስተሳሰብ ቅርስን በቁስ ብቻ እንደሚለካ፣ ቅርሶች የተለየ የላቀ ፈጠራና ሳይንሳዊነት አላቸው ብሎ እንደሚያስብ፣ ሕዝብን ከባህሎቹ ነጥሎ ኤክስፐርቶችን በዋናነት እንደሚሾም ልብ ልንል ይገባል። በዚያው ልክ ደግሞ አስተሳሰቡ ኤክስፐርት ነን ባዮቹን የፍትሕና ዴሞክራሲ ጉዳይ የማይመለከታቸው አስመስሎ ከማቅረቡም ባሻገር፣ የፖለቲካ ተላላኪዎች ሊሆኑ እንደሚችሉም ይደብቅብናል።

በአጠቃላይ የድሮው አስተሳሰብ ቅርስን በዋናነት ብቻ ሳይሆን በብቸኝነት እንደ ቁስ (ሐውልት፣ ቅርፃ ቅርፅ፣ ሕንፃና ‘ትልልቅ’ የሚባሉ የሥነ ጥበብ ሥራዎች) የሚወስድና የኤክስፐርትን መመዘኛ አስፈላጊ ነው ብሎ የሚያምን፣ ምዘናውንም የቅርስ ማስተዳደሪያ ሥርዓት (Heritage Management System) የማዕዘን ድንጋይ አድርጎ የሚወስድ ነው። ለዚያ ነው ላውራጄን ስሚዝ በ1998 ዓ.ም. ይህንን ዓይነቱን አስተሳሰብ “ሐውልታዊ/ቅርፃ ቅርፃዊ ቅርስ” (Moneumental Heritage) ስትል የጠራችው። የዚህ ጊዜ ያለፈበት ነው ወይም ዘመናችንን አይባጅም ተብሎ የሚታሰበው ዕውቀት መሠረቱ አውሮፓ በተለይም ፈረንሣይ ሆኖ እናገኘዋለን።

3.2 ዘመነ አብርሆት፣ የፈረንሣይ አብዮትና ቅርስ

የሐውልታዊ ቅርስ አስተሳሰብ በዋናነት የአውሮፓን የዘመነ አብርሆት ገዥ ፍልስፍና (Hegemonic Idea of Enlightenment) የተሸከመ ነው። ዘመነ አብርሆት ትልልቅ ሐውልቶች፣ የሥነ ጥበብና ሥነ ጽሑፍ ሥራዎች እንዲፈጠሩና እንዲጠበቁ፣ በሙዚየም እንዲሰበሰቡና እንዲጎበኙ፣ የተለየ (የቡርዧ) የውበት ጣዕም እንዲፈጠርም ምክንያት ሆነ። ምንም እንኳን በ19ኛው መቶ ክፍለ ዘመን እየነገሠ ቢመጣም፣ የቅርስ ጥበቃ ሐሳብ በቀጥታ የሚያያዘው ከ18ኛው ክፍለ ዘመን ዓብይ ክስተቶች ጋር ነው። በተለይም የፈረንሣዩ አብዮት ከ1781 እስከ 1791 ዓ.ም. በተከሰተ ወቅት የተካሄዱት የሐውልት ፈረሳዎችና የሕንፃ ዘረፋዎች እንዲሁም ያበቃለት የተባለው የቀድሞውን አገዛዝ (Ancien Régime) ፊውዳላዊ የባህል ውጤቶች በአጠቃላይ የማፈራረስና የመጥረግ ዘመቻ (Vandalism) ናቸው የቋሚ ቅርስ/ሐውልት ጥበቃ (Monument Historique) ሐሳብ እንዲስተጋባ ምክንያት የሆኑት። ዛሬ ፈረንሣይ በቅርስ ጥበቃ ግንባር ቀደም ነኝ እንድትልና ለብዙ ጊዜያትም የሷን ሐሳብ በዩኔስኮም በኩል በቀሪው ዓለም ላይ እንድትጭን ያስቻላት ታሪክ ሥሩ የሚመዘው ከዚያ ሁኔታ ውስጥ ነው። ያ አውሮፓዊ የቅርስ አስተሳሰብ ዋነኛ ዓላማው፣ ‘ቁሳዊ የፈጠራ ሥራዎችና ዓለም አቀፋዊ የሥነ ውበት እሴትን የሚያንፀባርቁ፣ የታሪክና የሥነ ጥበብ ምስክሮች ስለሆኑ በመንግሥት ጥበቃ ሊደረግላቸው ይገባል’ የሚል ነው። ለብዙ ዘመናት አውራ የቅርስ ጥበቃ መመዘኛ ሆኖ የቆየው አካሄድ ኃያልነቱን ተቀዳጅቶ የኖረው፣ ዘመናዊ መንግሥታት ቁሶችን በብሔራዊ ደረጃ በቅርስነት ጠብቆ የማቆየት ሐሳብን አንዱና ዋነኛው የመንግሥትነት መገለጫ ባህሪያቸው አድርገው በመውሰዳቸውም ነው። ሆኖም አስተሳሰቡ በብዙ መልኩ ችግሮች ነበሩበት። ለዚያም ነው የተለያዩ አስተሳሰቦች በሒደት እየፈተሹት የሄዱት።

የተለየ የቅርስ አረዳድ በተለያዩ አካባቢዎች ሲስተጋባ ቆይቷል። በሁሉም አካባቢ ተመሳሳይ መረዳቶች ላይ ተደርሷል ተብሎ ባይገመትም። ለምሳሌ ራሱ ዩኔስኮ የአውሮፓን ሐውልቶችን፣ ቅርፃ ቅርፆችን፣ ኪነ ሕንፃዎችን ብቻ የማምለክና እነሱን ዓለም አቀፍ መሥፈርት በሚል ብቸኛ፣ እንዲሁም ዋነኛ መመዘኛዎች አድርጎ የመውሰዱ ሐሳብ እያደር ተሸርሽሮ ዛሬ አዳዲስ መረዳቶችን እያስተጋባ ይገኛል። እነዚህ ሐሳቦች ታዲያ በትግል የመጡ ናቸው። እንደ አውሮፓ ያሉ ትልልቅ የሚባሉ ሐውልቶችና ኪነ ሕንፃዎች ሳይሆኑ፣ በሌሎች መረዳቶች የምናደንቃቸውን ቅርሶች በባለቤትነት የያዙ የዓለማችን ደቡባዊ ክፍል ሕዝቦች ናቸው ትግሉን ያቀጣጠሉት። በተለይም ኋላቀር እየተባሉ ሲንጓጠጡና በዓለም አቀፍ ቅርስን የማስመዝገብ ሒደት ውስጥም ያለውን ፉክክር መቋቋም ያልቻሉት ብዙ ታግለዋል። በየአገራቸውም ውስጥ ገሸሽ በመደረጋቸው ምክንያት በእስያ፣ በደቡብ አሜሪካና በአፍሪካ የሚኖሩ ማኅበረሰቦች ያደረጓቸው ትግሎች ናቸው፣ እንደ ዩኔስኮ ያሉትን ድርጅቶች የቅርስ ሐሳባቸውን እንዲያስተካክሉ የገፏቸው (ትግሉ ገና ብዙ ርቀት መጓዝ ቢቀረውም)። እናም ቅርስ የሐሳብ አድማሱ ሰፍቶ ብዝኃ ባህልን፣ አገር በቀል የባህል መገለጫዎችንና የተገፉ ማኅበረሰቦችን ማንነቶች ማቀፍ ጀመረ። ቅርስ ወይም ባህላዊ ቅርስ ከትናንት ወደ ዛሬ የሚተላለፉልንን ወግና ልማዶች ማለትም ቁሳዊና ቁሳዊ ባልሆነ መንገድ የምንወርሳቸውን ሐውልቶች፣ ቅርፃ ቅርፆች፣ ኪነ ሕንፃዎችና ትልልቅ የጥበብ ሥራዎች ብቻ ሳይሆን ሌሎች ፈጠራ የተመላባቸውን ዕውቀቶችንና ተግባሮችን፣ ሐሳቦችንና ትውስታዎችን (Ideas and Memories) ጭምር እንዲያጠቃልል ሆነ። ማለትም የተለያዩ አገር በቀል የቤት አሠራሮች (ጭቃ ቤቶችን ጨምሮ)፣ አስተራረሶች፣ ዘፈኖች፣ የምግብ ዓይነቶችና ምግብ ቤቶች/የመመገቢያ ሥፍራዎች፣ ቋንቋዎች፣ ጭፈራዎች፣ እሬቻዎች፣ እንዲሁም አያሌ የሰው ልጆች ራሳቸውን የሚገልጡባቸው መንገዶች ሁሉ የባህላዊ ቅርስ አስተሳሰብ አካላት መሆን ጀመሩ።

3.3. ሂሳዊ የቅርስ ጥናት (Critical Heritage Studies)

ከላይ የተመለከትናቸው አስተሳሰቦች ከዚያ በፊት የነበረውን ጠባብ አመለካከት የሚያሰፉ ቢሆኑም፣ በ1990ዎቹ መጀመሪያ ላይ “ሂሳዊ የቅርስ ጥናት” (Critical Heritage Studies) በሚል መጠሪያ መታወቅ የጀመረው የምርምር ዘርፍ የቅርስን አስተሳሰብ የበለጠ ድንበሩን ማስፋት ቻለ። መሠረታዊ ጥያቄዎቹን በመለወጥ ጭምር ቅርስን የታሪክ፣ የፖለቲካ፣ የባህል፣ የማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ክስተት አድርጎ መውሰድ ጀመረ። ሂሳዊ የቅርስ ጥናት ባህላዊ ቅርስን የትናንት ጉዳዮችን ለዛሬ የተሻለ ሕይወት ማስገኘት ይቻል ዘንድ፣ በመቀራረብ ሳናቋርጥ ድርድር እንደምናደርግበት እንቅሰቃሴ የመውሰዱን ሐሳብም አዳበረው። በዋናነት ደግሞ ማንነትን፣ ትውስታዎቻችንንና ለምንኖርባቸው ቦታዎች ያሉንን ስሜቶች (Sense of Space) ቁልፍ ሚና ካላቸው የኃይል ግንኙነቶች ጋር አያይዘን መመልከት እንዳለብን አሳሰበ። የእኩልነት መዛባቶችን እንድናጤንና ቅርስን ከማኅበራዊ ፍትሕ ጉዳዮች ጋር እንድናቆራኝ ሐሳቦችን አፍታታ። ይህ ሰፊ ሂሳዊ ምልከታ ኅብረተሰብንና ቅርስን ረግተው እንደሚቀመጡ ቁሳቁሶችም ሆነ ሥነ ውበታዊና መንፈሳዊ እሴቶች መመልከቱ የትም አያደርስም አለ። ይልቁንም በቅራኔዎች የተሞሉ ትርክቶችንና ፖለቲካዊ ጥያቄዎችን ከዕለት ሕይወት ጋር በማያያዝ፣ ሕዝብን በዘለቄታ ንቁ ታሳታፊ ማድረግ እንደሚጠበቅብን ሕይወቶችን በጥልቀት እያጠና አስተነተነ (ይኼኔ ነው ታዲያ የከተማ ውስጥ ቅርሶችን ጉዳይ ስናነሳ ጉዳዩ በመቶ ሥሌት ስናደርግ አብዛኛው ቅርስ የተባለ ሁሉ ቅርስነትን አያሟላም፣ በዚያም በኩል እነከሌን ኮንዶሚኒየም ውስጥ አስገብተናቸዋል፣ ስለዚህ ዝም በሉ ከሚል ጠባብ ክርክር መውጣት የምንችለው)፡፡

የሂሳዊ ጥናት ፈላስፎች ኋላ ቀር የሚባለው የቅርስ አረዳድ አንድ ወጥ መመዘኛ አውጥቶ ውሳኔ የማሳለፍ ሥልጣንን ማዕከል ያደረገ ሐሳብን (Authorised Heritage Discourse – AHD) የሚንተራስ ስለሆነ፣ መንግሥታዊ የቅርስ አስተሳሰቦች የነበሩትን ማኅበራዊ መዛነፎች ያስቀጥላሉ። እንደ ኢትዮጵያ ባሉ ብዙም ለቅርስ የሚሟገቱ ራስ ገዝ ሕዝባዊ ድርጅቶች ስለሌሉና ያሉትም በመንግሥት ጫናና ማስፈራራት የተገደቡ እንቅስቃሴዎች ውስጥ ስለሆኑ፣ ባህላዊ ቅርሶች በማንነት ጥያቄዎች ለተወጠረችውና አያሌ ግጭቶችን እያስተናገደች ላለችው ኢትዮጵያ ሕዝቦቿን የማወያያ፣ ከራሷ ጋር የመምከሪያ ዕድል ተነፍገው አሉ። እንኳንስ እንደዚያ ላለ ዕድል ሊበቁ ቀርቶ፣ እንዲሁም ለሚቀጥለው ትውልድ ለመተላለፍ ታላቅ ፈተና ተጋርጦባቸዋል። ምክንያቱም ቅርስና ልማት በሁለት ፅንፎች ላይ የተቀመጡ ሐሳቦች ተደርገው፣ ስለባህላዊ ቅርስ ያነሳ ሁሉ በልማት አደናቃፊነት ይቆጠራል። በዚህ መሀል ስንትና ስንት የጋራ ባህላዊ፣ ማንነታዊ፣ ታሪካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ጥቅሞች ልናገኝባቸው የምንችላቸውን ባህላዊ ቅርሶች (የቁስ፣ የመንፈስ፣ የሥነ ውበት፣ የሐሳብ፣ የቋንቋ፣ የትውስታ፣ የታሪክ፣ የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚ ዕድሎች) አገሪቱን በማይመጥንና የገባንባቸውን ፈተናዎች በሚያቀል ሁኔታ እያባከናቸው ነው።

3.4. የፀረ ቅኝ ግዛት አስተሳሰብና የአፍሪካ ቅርሶች

ባለፈው ዓመት ታኅሳስ ወር ላይ አግነስ ሺኒንጋያምዌ የተባለች የመስኩ ተመራማሪ ‹‹የቅርስ አያያዝ ሥርዓትን ከቅኝ ግዛት አስተሳሰብ ማላቀቅ›› በተሰኘ ጥናቷ እንደገለጸችው፣ አፍሪካም ሆነች ሌሎች ዓለማት ቅርስን የሚረዱበትንና የሚይዙበትን መንገድ ከሥሩ መፈተሽ እንዳለባቸው አስረድታለች። አግነስ የናሚቢያን ቅርስ አያያዝ ቀረብ ብላ ስታጠና እንዳየችው ምዕራባዊ ቅርስን የተመለከቱ አስተሳሰቦች፣ ሌሎች የቅርስ አረዳዶችን እንዳናይ አድርገውን፣ በአፍሪካ ቅርስ አያያዝ ላይ ብዙ ችግሮችን እየፈጠሩ ነው ስትል ትሞግታለች። ከእሷም በፊት ቦሊንና ንኩሲ የተባሉ አጥኚዎች የሩዋንዳን ችግሮች በመፈተሽ፣ የየአገሩ ማኅበረሰቦች ስለቅርስ ያላቸውን አመለካከት ዕርባና ቢስ የሚያስመስለውንና ከላይ ወደ ታች ሕዝቡንና ባህሉን የሚጫንን ርዝራዥ የቅኝ ግዛት አስተሳሰብ አጋልጠዋል። ያም አስተሳሰብ የአፍሪካን የቅርስ አያያዝ በትልቁ ተፅዕኖ እያደረገበት በመሆኑ ልንታገለው እንደሚገባ አስረድተዋል።

በ2011 ዓ.ም. ለኅትመት በበቃውና የቅርስ አያያዝ በአፍሪካ ተቆርቋሪው ማነው? (Managing Heritage in Africa: Who Cares?) በተሰኘው መጽሐፋቸው መግቢያ ምዕራፍ ላይ ቺሪኩሬ፣ ዲያኮንና ንዴሬ ኅብረተሰቡን በቅርስ ሐሳብ አረዳድና አያያዝ ላይ ጠንካራ ተሳትፎ እንዲኖረው ማድረግ፣ ራሱን የቻለ የፀረ ቅኝ አገዛዝ ዕሳቤ ነው ሲሉ ያስረዳሉ። ለምን ቢባል ‘የነጮች ዕውቀት ነው ዓለምን ሁሉ መዳኘት ያለበት’ የሚለው አስተሳሰብ ሕዝብን፣ በተለይ ደግሞ እንደ ምዕራባውያኑ ዓይነት ሥልጣኔና ቅርስ የላቸውም ብለው የሚያስቡትን ሕይወትና ባህል ገሸሽ ስለሚያደርጉ ነው (ለምሳሌ የኢትዮጵያ ቅርስ ባለሥልጣን የአዲስ አበባን ቅርሶች መመዝገብ የጀመረው የውጭ ኪነ ሕንፃ ባለሙያዎች የሠሩትን ከመቁጠር እንጂ ከአገር በቀሎቹ አይደለም)። በአንድ ወጥ ምዕራባዊ አስተሳሰብ (በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ) የተጠመቁ “ኤክስፐርቶችን” መሥፈርት አውጪና መዛኝ በማድረግ፣ ሕዝቡን ከቅርስ ባለቤትነትም ሆነ ጠባቂነት አውጥቶ መጣሉ አሁንም ፈተና ሆኖ ቀጥሏል። ሶንያ አታላይ የተባለችው ተመራማሪ፣ የቅኝ ግዛት ከመምጣቱ በፊት፣ ማኅበረሰቦች የራሳቸውን ባህላዊ ቅርስም ሆነ ታሪክ ሲያስተዳድሩ፣ ሲመረምሩ፣ ሲማሩ፣ ሲያስተምሩና ሲጠብቁ የኖሩት ራሳቸው እንጂ፣ ቅኝ ገዥዎቹም ሆኑ በእነሱ አምሳል የተቀረፁት የየአገሩ ኤክስፐርት ተብዬዎች አይደሉም ትለናለች። ሆኖም ግን የአገር ውስጥ ሐሳቦች ሁሉ ነፃ አውጪዎች ናቸው ማለት ስህተት ላይ እንደሚጥል እነዚህን አስተሳሰቦች የሚያራምዱ አሳቢዎች ያስጠነቅቃሉ። በእርግጥም በአንድ አገር ውስጥም የተዛነፉ የታሪክ፣ የባህልና የፖለቲካ ታሪኮች እንደመኖራቸው፣ የፀረ ቅኝ አገዛዝ የባህል ቅርስ ግንዛቤና ተግባር በሂስ የተሞላ ንግግርን ማዕከል ላይ ማስቀመጥም አለበት።

4. ቅርስ ጥበቃ ወይስ አፍራሽ ግብረ ኃይልነት?

እነዚህን የቅርስ አስተሳሰባችንን አድማስ የሚያሰፉ ምልከታዎች ካየን በኋላ፣ በቅርቡ በኢትዮጵያ ቅርስ ባለሥልጣን የተሰጠውን መግለጫ በምሳሌነት መመልከቱ አግባብ ነው። ዳይሬክተሩ ከተናገሯቸው ብዙ ነገሮች ውስጥ የሚከተለው ይገኝበታል፡

<< አዲስ አበባ ላይ ብዙ ቅርሶች አሉ። ሐውልቶችም አሉ፣ ሌሎች አደባባዮች አሉ፣ ከእምነት ተቋማት ጋር ተያይዞ እንደ ቅርስ የተያዙ አሉ፣ በየተቋማቱ ደግሞ አገልግሎት የሚሰጡ ያሉ ብዙ ቅርሶች አሉ። ከእነዚያ ውስጥ ትልቅ አወዛጋቢ የነበረው የከተማ ሥነ ሕንፃ ቅርስ ነው። መመርያችንን ስንመለከተው የከተማ ሥነ ሕንፃ ቅርስን በጥቅሉ ያስቀምጣል እንጂ (ከአዋጁ በመነሳት) በእያንዳንዱ ከፋፍሎ አያስቀምጥም። [ይኼ] ሁሉ ለየብቻው መታየት አለበት ነው። በየትም አገር እንደሚደረገው የሥነ ጥበብ ቅርስ ለመባል አንድ ቅርስ መሥፈርቱ ምንድን ነው? አንድ ሁለት ተብሎ ወጥቶ በእነዚያ ተመዝኖ ነው መመዝገብ ያለበት። እ … እ … እ … የማይዳሰስ የባህል ቅርስ ካልን እሱም መሥፈርት ይወጣለታል። አንደኛው በእኛም አገር በሌላም አገር አጨቃጫቂ የሚሆነው ከተሞች የልማት ማዕከል ስለሆኑ ከተሞች በየጊዜው እየለሙ ስለሚሄዱ ከተማ ላይ ያለ የሥነ ሕንፃ ቅርስን መሥፈርት ማውጣት ነው። ለዚህ መመርያው ላይ የተቀመጠው አንድ ቅርስ ማለት የሰው ልጅ በኪነ ጥበብ፣ በፈጠራ፣ በሳይንስ በባህል፣ ያካበተው የሠራውና ከትውልድ ወደ ትውልድ መተላለፍ ያለበት የሚለው ጥቅል አይገልጸውም። ስለዚህ ከ2014 ዓ.ም. ጀምረን መመልከት የጀመርነው ምንድነው? የከተማ ሥነ ሕንፃ ቅርስ ማለት (Urban Building Heritage) በዚህ መሥፈርት አውጥተን መንቀሳቀስ አለብን፣ ለምን ቢባል ብዙ ከልማት ጋር ተያይዘው አጨቃጫቂ ጉዳዮች ስለነበሩ፣ ፍርድ ቤትም ያደረሱን ጉዳዮች ስለነበሩ፣ እነዚህን የግድ ዕልባት መስጠት አለብን፣ ወደፊት ደግሞ የምንመዘግበውና የምንከባከበው ነገር፣ እንደዚሁ ከመሬት ተነስተን በጥቅል መሥፈርት ሳይሆን በተመዘነ መሥፈርት መሆን አለበት ነው። ይኼን ስናደርግ የሦስት አገሮችን ተሞክሮ ነው የተመለከትነው። አንደኛ የስዊትዘርላንድን፣ ሁለተኛ ጃፓን፣ እንደገና ደግሞ ረጅም ታሪክ ከሌላቸው የካናዳን… እነዚህን እንደ መነሻ አድርገን በመውሰድ ለእኛ የሚሆኑትንና ኢንተርናሽናሊ እንደ ስታንዳርድ የሚወሰዱትን በመውሰድ፣ ከእኛ ነባራዊ ሁኔታ ጋር ደግሞ ማስማማት ነው። እሱ በባለሙያዎች በደንብ ተመክሮ በማኔጅመንት ፀድቆ መጨረሻ ላይ የሚኒስትር መሥሪያ ቤቱ በቱሪዝም ሚኒስቴር በኩል ታይቶ፣ ፀድቆ 2015 ዓ.ም. ተግባር ላይ የዋለ ነው። በዚህ መመሪያ መሠረት እንግዲህ የከተማ ቅርስ ብለን፣ የምንወስደው ከመቶ የሚመዘን መሥፈርት አለው። >>

አቶ አበባው አያሌው፣ የቅርስ ጥበቃ ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር በዚህ ገለጻ ውስጥ ፍንትው ብሎ እንደሚታየው ኢትዮጵያ ያረጀና ያፈጀን ብቻ ሳይሆን፣ ቀደም ሲል ምን ያህል በቅኝ አገዛዝ አስተሳሰብ እንደ ተለወሰ እንዲሁም እንደ ተሞገተ ያወሳንለትን ሐሳብ ይዘው ነው የምናገኘው። ምክንያቱም ቅርስ በዋናነት የተበየነው በቁስነት ነው። መግለጫው ምንም እንኳን በጨረፍታ መንፈሳዊ ቅርሶች አሉ ቢሉም፣ እነሱም የኤክስፐርት መሥፈርት ወጥቶላቸው መመዘን አለባቸው ነው የሚለው። በሌላ መግለጫቸው ዋና ዳይሬክተሩ በቃልና በክዋኔ ሲወርዱና ሲዋረዱ የመጡ የኪነ ጥበብ ሥራዎችን በቅርስነት እንደማይዟቸው ተናግረዋል። እንዲያም ሆኖ ይህንን መግለጫ ሙሉውን የተከታተለ ሰው ቅርስ ቁስ ብቻ ነው እየተባለ እንደሆነ ነው የሚረዳው። አንገብጋቢ ነው ብለው ያወሱትም ጉዳይ የከተማ ሥነ ሕንፃ ቅርስ ነው። በሚገርምና በሚያሳዝን ሁኔታ አንገብጋቢነቱን የሚያያይዙት፣ ለቁሶቹም አሳቢ በመሆን አይደለም። በተለይ በዚህ ሰዓት የተናገሩት አንበሳ መድኃኒት ቤትን በምሳሌነት አንስተው ስለሆነ፣ የሕንፃዎቹ የቀድሞ ባለቤቶች፣ ሕዝቡና የቅርስ መብት ተሟጋቾች ቅርስ ነው እያሉ ፍርድ ቤት ድረስ ያመላልሱናል ለማለት ነው። በኋላም መፍትሔ አድርገው ያስቀመጡት፣ ይፍረስና ለትውስታ ያህል ስሙ በብረት ላይ ተጽፎ አንድ ቦታ ላይ ይተከል የሚል ነው። ሌሎች አገሮች ቅኝ ግዛታዊ የሚባሉት መሥፈርቶች ራሳቸው መፈተሽ አለባቸው፣ ምክንያቱም አስተሳሰቡ ሰፊ የባህል ቅርስ ሀብቶችን እንዳናካትትና እንዳንጠብቅ አድርጎናል እያሉ እንደሚከራከሩ አይተናል። የእኛዎቹ ግን “አልሚዎች” የተባሉ ነጋዴዎች በራሳቸው ፈቃድ ቡልዶዘር እያሰማሩ በሚያፈርሱበትም ሁኔታ ውስጥ ተርፈው የተመዘገቡትንም ቅርሶች መፍረስ አለባቸው እያሉ ይከራከራሉ። የቅርስ ባለሥልጣን ሳይሆን አፍራሽ ግብረ ኃይል ነው እንዴ ያለን? የሚያሰኘን ይኼ ነው።

ከዚህም ባሻገር ባለሥልጣኑ ይህንን የቁስና የመሥፈርት ጉዳይ ዓለም አቀፍ መመዘኛ በማለት ለራሱ ዕውቀትና ተግባር ላቅ ያለ ደረጃ ሊያጎናፅፍ ይሞክራል። ቀደም ሲል እንዳየነው ይህ ዓለም አቀፍ ምዘና የሚለው አስተሳሰብ አውሮፓ ተኮር የሆነ ነው። ይህ ማለት አውሮፓዊ የሆነ ሁሉ ክፉ ነው ለማለት አይደለም። እኛን ሊገልጽ የማይችልና የሚንቀን፣ ራሱን የሚያዋድድና በዓለም ላይ እንደ ብቸኛ መመዘኛ በሌሎች ላይ የሚጫነውን አስተሳሰብ ነው አውሮፓ ተኮር የምንለው። ለዚያም ነው የአፍሪካ፣ የእስያና የደቡብ አሜሪካ፣ እንዲሁም የተለያዩ አኅጉራት ነባር ማኅበረሰቦች ተቃውመውት ሕዝባቸውን መሀከል ላይ እያስቀመጡና ምክክርን በመፍትሔነት እያመጡ ያሉት።

የኢትዮጵያው አውራ የቅርስ አረዳድ ራሱን ላቅ ለማድረግ ልምድ ወሰድኩ የሚለው ደግሞ፣ በታሪክና በባህል ከሚመሳሰሉንና የትግል አጋሮቻችን ሊሆኑ ከሚገባቸው አገሮች ሳይሆን፣ ገና ረጅም ርቀት ሊጓዙ ከሚገባቸው ከካናዳ፣ ከስዊዘርላንድና ከጃፓን ነው። በባህል ቅርስ ረገድ ሕዝቦቻቸውን ነፃ ለማውጣት ከሚተጉት ተሞክሮዎች አለመቅዳቱ አስተሳሰባችንን ምን ያህል መፈተሽ እንዳለብን ያመላክተናል። በተጨማሪም ባለሥልጣኑ አምስት መመዘኛ መሥፈርቶችን አውጥቼ ለእያንዳንዳቸው መሥፈርቶች ንዑስ መመዘኛዎች ነድፌና የተለያዩ ነጥቦችን በመቶኛ አሥልቼ፣ በመጨረሻም ከመቶ ደምሬ ነው የምለካቸው ብሏል። የሚደንቀው መመዘኛዎቹ ቅርስ ተብለው የሚመዘገቡ ነገሮች እጅግ ያነሱ ብቻ ሳይሆኑ፣ ከእነ ጭራሹ እንዳያኖሩም ታስቦ የተሠራ ወጥመድ ነው የሚመስለው። ምነው ቢሉ መመዘኛዎቹ ቀደም ሲል በተነጋገርነው መሠረት አላስፈላጊ ከመሆናቸውም በላይ፣ እንዳሉ እንኳን እንያቸው ቢባል ቅርሶችን በቁስ ብቻ ወደ መለካት እንዲወርድ፣ ብሎም በቁስነት የተመዘገቡት ቅርሶችም ቢሆኑ በአንድ መመዘኛ ቢያልፉ እንኳን በሌላኛው እንዲያም ካልሆነ በሦስተኛውና በአራተኛው መመዘኛ እንዲወድቁ የሚያደርጉ ናቸው። እንዲያም በማድረግ መንግሥት ቅርሶቹን እንዲያፈርሳቸው መንገዱን ያመቻቻሉ። የማይጨበጡ የሚባሉትን መንፈሳዊ፣ ዕውቀታዊና ጥበባዊ ቅርሶች ደግሞ ፈጽሞ ከምዘናም ውጭ በማድረግ፣ መፍረሳቸውም እንዳይታይ፣ እንዳይሰማ እየሆነ ነው። በሕዝብ ባህላዊ አኗናር፣ በመንፈሳዊና ቁሳዊ ሀብቶቻቸው ላይ ፈረሳ እንዲካሄድ በሙያ ስም ሕግ የሚያቆም ፀረ ባህል የዕውቀት ሥርዓትና ተግባር ነው እየተካሄደብን ያለው።

መግለጫው በአንድ በኩል እኔ ይህንን መመርያ አጥንቼ ያሰናዳሁት የዛሬ ሁለት ዓመት ነው ይላል (መመርያዬ ከአሁኑ የልማት ኮሪደር ፈረሳ ጋር አይገናኝም ለማለት)። በሌላ በኩል ደግሞ እንዲህ ይላል፡፡ ‹‹የኮሪደሩ ልማት ከመጣ በኋላ የግድ መሥራት ያለብን ምንድን ነው? እነዚህን ቅድሚያ ሰጥተን መገምገም አለብን፣ የጋራ ከአዲስ አበባ ባህልና ቱሪዝም ኪነ ጥበባት ቢሮና ከእኛ ባለሙያ እንዲሁም ደግሞ መካከለኛው አመራርም፣ ከፍተኛው አመራርም ያለበት አንደ እኛ የመስክ ጉብኝት ነው የተደረገው። ቦታዎቹን እንያቸው፣ የልማቱ ሁኔታና ፀባይ ምንድነው? ምክንያቱም ሰፊ ቦታ የሚያካትት ነው፤››፡፡  እዚህ ጋ ጥሩ መረጃ ነው ባለሥልጣኑ የሰጠን። የኮሪደር ልማቱና ከተማን ለመጥረግ የመጣበት ሰፊ ዘመቻ (“የልማቱ ሁኔታና ፀባይ” የተባለው) ከፍተኛ መሆኑን ነው የምናየው። እንኳንስ ሕዝቡን መመርያዬን ከሁለት ዓመታት በፊት አሰናድቻለሁ ያለውን የቅርስ ባለሥልጣንም ሳያማክር ድንገት ከተፍ ነው ያለበት ዘመቻው። ለዚያ ነው ቀድሞ ሳይማከር፣ በፈረሳው መሀል የቅርስ ቆጠራና ስረዛ ውስጥ የገባው። ሕዝብንም ቅርስንም ያላገናዘበው ልማት ለፈረሳው የ“ዕውቀት ሽፋን” እንዲሰጠው ብቻ ነው ባለሥልጣኑን የጠራው። ለዚያም ነው ባለሥልጣኑ እንዲህ ያለው፡፡ ‹‹አራዳ ክፍለ ከተማ የአዲስ አበባ እምብርት ከሆኑት አንዱ ነው። ሁለት ቦታዎችን እንግዲህ መነሻ አድርገን ብንወስድ ከቤተ መንግሥቱ ውጪ ያለውን የፍልውኃ አካባቢ፣ የአራዳና ፒያሳ አካባቢ፣ እዚያ ላይ ወደ 147 ቤቶች በቅርስነት ተመዝግበው ነው የነበር። እነዚህ መቶ አርባ ሰባቱ ሁሉ መሥፈርት ያሟላሉ? ቅርስ ናቸው ወይ? ሌላ ጉዳይ ነው እሱ፤››፡፡ ተመልከቱ እንግዲህ። ዋናውን ጉዳይ “ሌላ ጉዳይ ነው እሱ” ይላል መግለጫው። በልማት ስም ግለሰብ ባለሀብት ነን ባዮችን የልብ ልብ እየሰጠ ቅርሶችን እያፈረሰ ብዙ ተቃውሞ በሚደርስበት የኢሕአዴግ ዘመን እንኳን፣ ቅርስ ናቸው ተብለው በተመዘገቡት አያሌዎቹ የሕዝብ ሀብቶች ላይ ነው የቅርስ ጥበቃ ባለሥልጣን እንዲፈርሱ የኤክስፐርትነት ሽፋን የሰጠባቸው። መንፈሳዊ ሀብቶች ለሚባሉት የከተማው ነዋሪዎች ታሪክ፣ ትውስታ፣ ማኅበራዊ መስተጋብር፣ የኢኮኖሚ ሁኔታ መሻሻል ሊፋለም የሚገባው ባለሥልጣን በስንት ጭንቅና ጥብ ተመዝግበው የቆዩትን ቅርሶቻችንን ነው እንዲፈርሱ በአዋቂነት ስም አብሪ ጥይት ያስተኮሰባቸው።

ሌላ ምሳሌ ላምጣ። የአዲስ አበባ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ኃላፊዎች አይፈርስም ብለው ቃላቸውን በአደባባይ የሰጡለትን የሀገር ፍቅር ቴአትር የጀርባ ክፍል ባለሥልጣኑ አሳዛኝ ምክንያት በመስጠት ነው ያስፈረሰው። አቤቱታችንን ለአዲስ አበባ ባህልና ቱሪዝም ሰዎች በየአቅጣጫው ባደረስን ሰዓት አገር ፍቅር በአካል ተገኝተው፣ የጀርባውን ሕንፃ ታሪካዊነት ገምግመው ነበር የቀደመ ውሳኔያቸውን የቀለበሱት። ማለትም የቅኝ ገዥዎች መኖሪያና ኢትዮጵያውያን የነፃነት ታጋዮችን መግረፊያ የነበሩት ሕንፃዎች የሚሸከሙትን የኋላ ታሪኮች፣ ቀጥሎ በመጡት የነፃነትና የድል ማግሥት የባህልና ጥበብ ተጋድሎዎች በመመዘን ነበር የሀገር ፍቅር ቴአትር አንድ ክፍል የሆነው ሕንፃ አይፈርስም ያሉት። በኋላ ግን የቅርስ ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር በአጃቢ አገር ፍቅር ገብተው ሕንፃውን አይተው፣ ‹‹ይኼማ 20 በመቶም አያሟላም›› ብለው ዕቃዎቻቸውን በበነጋው እንዲያወጡ ነበር ትዕዛዝ ሰጥተው የሄዱት። መዛኝ ብቻ ሳይሆኑ አፍራሽም ስለሆኑ። በመግለጫቸውም ላይ ‘ዜሮ ፐርሰንትም አያሟላም’ ብለዋል።

እንግዲህ ትውስታን፣ የባዕድ ወራሪን ግፍና የወገንን የነፃነት ተጋድሎን ታሪክ እላዩ ላይ በአሻራነት በመመዝገቡ ሊመዘን የሚገባውን ሥፍራ ነው፣ ‹‹የሥነ ሕንፃው ስታይል›› እዚህ ግባ የሚባል አይደለም ብለው እንዲፈርስ ትዕዛዝ ያስተላለፉበት። ስለሐኪም ወርቅነህም ቤት ኢትዮጵያ በታሪኳ በግንባር ቀደምትነት ልትመዘግባቸው የሚገባቸው ሰው መሆናቸውንና የሁላችንንም ዓለም አቀፋዊ ትግል ታሪክ የሚሸከሙ ተምሳሌት እንደሆኑ በስፋት ብናስረዳም፣ ቤታቸው ከመቶ ዓመት በላይ የሆነው መሆኑን ብንናገርም የእሳቸውም ቤት ከመፍረስ አልዳነም። ‘ከድህነት ተላቆ ራሱን ያልቻለ ሕዝብ ነፃ ሕዝብ ነኝ ማለት አይችልም… በዕውቀት ራሱን ነፃ ያላወጣ ሕዝብ፣ መሠረተ ልማት ቢገነባም የሚጠቀሙበት የውጭ በዝባዥ ኃይሎች ናቸው’ የሚሉትን ጭብጦች በኢኮኖሚ ትንተና የዛሬ መቶ ዓመት ለአገራቸው ሕዝብና መንግሥት ያስጨበጡትን የገብረ ሕይወት ባይከዳኝንም ቤት ቅርስ አይደለም ብለው አስፈረሱት። ዕውቁ ዓለም አቀፍ የኢትዮጵያ የነፃነት ተፋላሚው አብዲሳ አጋ የታሰረበትንም እስር ቤት እንዲፈርስና ቅርሱ ከታሪክ እንዲፋቅ ፈረዱበት (አዲሱን የዲጂታል ቴክኖሎጂ ተጠቅመው ቀድሞውኑ ሊፈርሱ ባይገባቸውም፣ ከቶውኑ ተረስተው መቅረት የለባቸውም ብለው የሚፋለሙ ወጣቶች በዚህ ረገድ እየሠሩ ያሉትን ባለሙያዎች ከልቤ አደንቃለሁ)። ብቻ መሥፈርት ተብለው የመጡትም መሥፈርቶች ቅርሶች በአንዱ ቢያልፉ በሌላኛው እንዳያልፉ የሚያደርጉ ወጥመዶች ናቸው። እውነተኛው ጉዳይ ሌላ ቦታ ነው የተደበቀው። ከተማን ከእነ ሰው፣ ከእነ ቅርሱና ሕይወቱ በአንድም ይሁን በሌላ መልኩ አፍርሶ፣ ያለውንም ሀብት አሳጥቶ፣ ለቀጣይ ድህነት አሳልፎ ሰጥቶ፣ ለውጭና ለአገር ውስጥ የናጠጡ ሀብታሞች መሸጥ ነው ዓላማው። እነዚህን ውስብስብ ሁኔታዎች አገናዝበን የአሁኑንና ያለፈውን ሕይወታችንን መተንተን፣ ሌሎች ሕልሞችን እያለምን፣ የተሻሉ ዓለማትን ለማስገኘት መሥራት እንጂ ሌላ “የሰውነት ሕይወት” አማራጭ የለንም።

መውጫ

በአገራችን በፖለቲካ ቅኝ ግዛት ሥር አለመውደቃችንንና ለዚያም የከፈልናቸውን መስዋዕትነቶች ማውሳቱ ተገቢ ሆኖ ሳለ፣ ዛሬም የቅርስና የሙዚየም ሐሳባችንን የቀነበብንበት ሐሳብ፣ ምዕራባዊና ቅኝ ግዛታዊ መሆኑን አውቀን የእጅ አዙር ቅኝ አገዛዝን መፋለም ይጠበቅብናል። እናም ቅርስን በቁስ ብቻ ሳይሆን ጥበባትንም በሚያቅፉ መንፈሳዊ መገለጫዎቹም ጭምር መረዳት ይገባናል። አልፈንም የሕዝቡን አኗናር በዚሁ የቅርስ አረዳድ ውስጥ ማካተትና ማኅበረሰቦችን ማዕከል ላይ አስቀምጠን ማሳተፍ፣ እነዚህን ሁሉ አስተሳሰቦችም ሰብዓዊነትን በሚያከብርና በማኅበራዊ ፍትሕ በሚያንፅ መንገድ ዳግም ማሰብ ይጠበቅብናል። አስበንም በሕዝብ ላይ መሸፈጥ ሳይሆን፣ ውግንናችንን ከሕዝብ ጋር ለሕዝብ በማድረግ፣ በጋራ ልናስብና ልንሠራ ግድ ይለናል።

አሁን ለገባንባቸው ፈተናዎች አንድ መውጫ ቀዳዳ ወይም መፍትሔ የሚገኘው የሠራተኞችን፣ የድሆችን፣ የወጣቶችን፣ የሕፃናትን፣ የሴቶችን፣ የአካል ጉዳተኞችን፣ የአረጋውያንን፣ የተለያዩ እምነት ባለቤቶችን፣ የተለያዩ ብሔሮችን፣ የቅይጥ ማንነት ባለቤቶችን፣ የሥራ አጦችንና የሌሎችንም የኅብረተሰብ አካላት ከቀሪዎቹ የአገሪቱ ክፍሎች ማለትም ከገበሬዎችና አርብቶ አደሮች አጠቃላይ የኑሮ ሁኔታ፣ የአሁን ችግሮችና የባህላዊ ቅርስ (የሰውነት) ጥያቄዎች ጋር በማስተሳሰር ነው ብዬ አምናለሁ። ያም ብቻ ሳይሆን በታሪካዊ ሁኔታዎች አስገዳጅነት የማናመልጣቸውን ዓለም አቀፍ የኃይል ግንኙነቶችን በጥንቃቄ መመርመር እንደሚያሻን ማስመር አለብን። እኛ ባልነው መንገድ ካልተጓዛችሁ የሚሉትንም ሆነ አብረናቸው ብንሆን ልንበለፅግ እንችላለን ብለን ያመንናቸውን ታሪካዊ ዓለም አቀፍ ኃይሎች፣ በአጭርና በረዥም ጊዜ ጥበብ የተመላ ድርድር (Tactical Negotiation) ልንቀርባቸው ነው የሚገባን። እንዲሁም ብዙኃኑን ከነባህላዊ ነፍስያቸው ጭዳ ከሚያደርግ የጊዜያዊ ትርፍ ሥሌት በራቀና ፍትሕ ተኮር በሆነ የመላ ኢትዮጵያ፣ የአፍሪካና የዓለም ግፉአን ኅብረት (Critical Pan-African and South-South Solidarity) ዙሪያ መለስ ትግል ማድረግም ያሻናል ብዬ አስባለሁ።    

ሳምንት ተያያዥ በሆነ ጉዳይ በተለይም በከተማ የመኖርን መብት እንደ ነፃነት ጥያቄ ለመተንተን በሌላ ጽሑፍ እመለሳለሁ። የዓለም አቀፍ የከተሜነት ታሪኮችንና በጉዳዩ ላይ ያሰቡ ሰዎችን ጥናቶች ይዤ አዲስ አበባንና ኢትዮጵያን የተመለከቱ ሐሳቦቼን ላጋራችሁ ቃል እገባለሁ።

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ በኢሜይል አድራሻቸው ezopaddis@gmail.com ማግኘት ይቻላል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

በሥጋ ላይ አላግባብ እየተጨመረ ያለውን ዋጋ መንግሥት ሊቆጣጠረው ይገባል

በአገራችን የግብይት ሥርዓት ውስጥ ኢኮኖሚያዊ ያልሆኑ ወይም ያልተገቡ የዋጋ...

ኢትዮጵያን የተባበረ ክንድ እንጂ የተናጠል ጥረት አይታደጋትም!

ኢትዮጵያ በአሁኑ ጊዜ ከምትገኝበት ውጥንቅጥ ውስጥ የምትወጣበት ዕድል ማግኘት...

የፖለቲካ ቅኝቱ የሕዝባችንን ታሪካዊ ትስስር ለምን አያከብርም?

በንጉሥ ወዳጅነው የዓብይ አህመድ (ዶ/ር) መራሹ የ2010 ዓ.ም. የለውጥ መንግሥት...

ዛሬም ኧረ በሕግ!

በገነት ዓለሙ በዚህ በያዝነው ሚያዝያ/ግንቦት ወይም ሜይ ወር ውስጥ የተከበረው፣...