Monday, May 20, 2024

ሰላማዊ የፖለቲካ ትግልና ፈተናው

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) የፖለቲካ ኦፊሰር የአቶ በቴ ኡርጌሳን አሟሟት በተመለከተ እሑድ ሚያዝያ 6 ቀን 2016 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ ሒደቱን በቅደም ተከተል ይገልጻል፡፡

በመቂ ከተማ ግራዝማች አበበ ከሚባለው እንግዳ ማረፊያ (መኝታ) ቤት በድንገት በመጡ የመንግሥት ፀጥታ ኃይሎች መያዛቸውን፣ የፀጥታ ኃይሎቹ አቶ በቴን እየጎተቱና እየደበደቡ ሲወስዷቸው እሳቸው ግን በሕግ አምላክ አትምቱኝ፣ በሥርዓት ያዙኝ እያሉ ሲጮሁ ነበር ይላል፡፡ ይህን ሁኔታ በቦታው ሆኖ በዓይኑ ያየው የመኝታ ቤቱ የበር ጠባቂ ታፍኖ ከተወሰደ በኋላ የደረሰበት አለመታወቁን ኦነግ በመግለጫ ይገልጻል፡፡ በቦታው የነበሩ የዓይን ምስክሮች አቶ በቴን ዩኒፎርም የለበሱና የታጠቁ የመንግሥት የፀጥታ ኃይሎች ከሆቴሉ አውጥተው በመኪና ጭነዋቸው መሄዳቸውን መመስከራቸው በኦነግ መግለጫ ውስጥ ተካቷል፡፡ መኪናውን የከተማው ቆሻሻ መድፊያ ወደ ሆነ ቦታ እየነዱ እንደወሰዱትም የዓይን እማኞች ማረጋገጣቸውን ኦነግ ያብራራል፡፡

ቦታው ሲደርሱ አቶ በቴ ከመኪና አውርደው እጃቸውን ወደኋላ ጠምዝዘው እንዳሰሩ መግለጫው ያትታል፡፡ በበርካታ ጥይት ተኩሰው በመምታት እንደገደሏቸውም ይገልጻል፡፡ የፀጥታ ኃይሎቹ በዚህ መንገድ አቶ በቴን ከገደሏቸው በኋላ፣ ጅብ ወይም አውሬ አስከሬናቸውን እንዲበላው እዚያው የቆሻሻ መጣያ ቦታ አካባቢ ጥለውት መሄዳቸውንም ይህ የኦነግ መግለጫ ያብራራል፡፡ ይህን ሁኔታ በርቀት የተመለከቱ ሰዎች የፀጥታ ኃይሎቹ ከሄዱ በኋላ ቦታው ላይ ደርሰው አስከሬኑን ባይጠብቁት ኖሮ፣ አስከሬኑ በአውሬ ተበልቶ ማንነቱ ሳይታወቅ ይቀር እንደነበር በኦነግ መግለጫ ተዘርዝሯል፡፡

የኦነግ የፖለቲካ ኦፊሰር የአቶ በቴ ሰሞነኛ ግድያ ከዚህ በተጨማሪ በብዙ መንገዶች ሲገለጽ ሰንብቷል፡፡ ይሁን እንጂ ይህ አጋጣሚ በኢትዮጵያ ሰላማዊ ፖለቲካ ጉዳይ ላይ ጥያቄ እንዲነሳ እየጋበዘ ነው፡፡

ከሰሞኑ የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት (መኢአድ)፣ የኢትዮጵያ ሕዝባዊ አብዮታዊ ፓርቲ (ኢሕአፓ)፣ የአማራ ግዮናዊ ንቅናቄ፣ እንዲሁም እናት ፓርቲ በጋራ  በሰጡት መግለጫ በኢትዮጵያ ያለው የሰላማዊ ፖለቲካ እንቅስቃሴ ከባድ ፈተና እንደተጋረጠበት ገልጸው ነበር፡፡

ሰላማዊ የፖለቲካ ትግልን የመረጡ የፖለቲካ ፓርቲዎች በአገሪቱ ለሕግ የበላይነት መስፈን፣ ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት መፈጠር፣ ለሕዝቦች ደኅንነትና መብቶች መጠበቅ፣ ለአገር ሉዓላዊነት መከበር፣ ችግሮች በውይይትና በንግግር እንዲፈቱ ለማስቻል፣ ሰላም እንዲሰፍንና ሕጋዊ ተጠያቂነት ያለበት ሥርዓት እንዲኖር ያላቸው አስተዋጽኦ እጅግ ከፍተኛ መሆኑን ይኼው የአራቱ ፖለቲካ ድርጅቶች መግለጫ ይዘረዝራል፡፡

ይሁን እንጂ በሰላማዊ መንገድ የሚታገሉ የፖለቲካ  ድርጅቶች ላይ ከፍተኛ ጫናና እንግልት እየደረሰ ነው ይላል፡፡ የኢሕአፓ ሊቀመንበር ዝናቡ አበራ (ረዳት ፕሮፌሰር) ቢሯቸው በሥራ ላይ እንዳሉ፣ የመኢአድ የማዕከል አደራጅ አቶ ጫንያለው ዘየደ ከመኖሪያ ቤታቸው መያዛቸውን የሚገልጸው የአራቱ ፓርቲዎች መግለጫ የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮቹና አባላቱ የእስር አያያዝም ሆነ ለፍርድ የማቅረብ ሒደት ሕጋዊ አካሄድን የተከተለ አለመሆኑን ያስረዳል፡፡ በሰላማዊ ፖለቲካ ታጋዮች ላይ እየደረሰ ነው የሚሉት እስራትና ወከባ ለሰላማዊ ፖለቲካ ብቻ ሳይሆን፣ ለአገር አይጠቅምም ይላሉ አራቱ ድርጅቶች በዚሁ መግለጫቸው፡፡

በሰላማዊ የፖለቲካ ትግል ለመራመድ ቆርጠው ወደ ትግል ሜዳው የገቡ የፖለቲካ ድርጅቶች ይገጥመናል የሚሉት እንግልትና መሰናክል መክበዱን፣ በቅርቡ ከጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ጋር ውይይት ያደረጉ ተፎካካሪ የፖለቲካ ድርጅቶች ፈተና ሆኖብናል ብለው ሲጠይቁ ተደምጠው ነበር፡፡

የፖለቲካ ምኅዳርን የማስፋት ጉዳይን ደጋግመው ሲጠይቁ የተደመጡት የፖለቲካ ፓርቲዎቹ ከቢሮ ይሟላልን ጀምሮ በጀት አነሰን የሚሉ ጥያቄዎችን ሲያቀርቡ ነበር፡፡ ጠቅላላ ጉባዔ ለማካሄድ እንኳ እንደተቸገሩ ሲናገሩም ተደምጠዋል፡፡ ሐሳብና ፕሮግራሞቻቸውን በነፃነት ለሕዝብ ለማቅረብ የሚችሉበት መንገድ መገደቡንም ደጋግመው ከመግለጻቸው ባሻገር፣ የሐሳብ ብዝኃነት የሰፈነበት የፖለቲካ ሥርዓት አለመኖሩንም ተናግረዋል፡፡

ከዚህ በተጨማሪም የተመጣጣኝ ምርጫ ሥርዓት እንዲዘረጋ በተደጋጋሚ ሲጠይቁ ተደምጠዋል፡፡ ገዥው ፓርቲ በአመዛኙ የመንግሥትና የአገር ሀብትን በመጠቀም ጭምር ለምርጫ፣ ለመደራጀትና ለፓርቲ ማጠናከሪያነት ሲያውል እንደሚታይ በማስታወስ ተቃዋሚዎች በተናጠል የመንግሥትን ሀብትና መዋቅር ከሚያንቀሳቅስ ኃይል ጋር በመፎካከር ለማሸነፍ እንደሚቸገሩ መግለጻቸው አይዘነጋም፡፡

የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤትን ፓርቲዎች ቢፈጥሩም፣ ነገር ግን ሕጋዊ ዕውቅና አላገኘም የሚል ጥያቄም አንስተዋል፡፡ በበርካታ አጋጣሚዎች የፖለቲካ ፓርቲዎች በነፃነት ሰላማዊ ሠልፍ ወይም ተቃውሞ ማካሄድ እንደተከለከሉም ደጋግመው ሲናገሩ ማዳመጥ አዲስ ነገር አይደለም፡፡

የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ሰብሳቢ አቶ ደስታ ዲንቃ፣ በአሁኑ ጊዜ  የፖለቲካ ምኅዳር ጥበት በስፋት መኖሩን ይናገራሉ፡፡ ተቃዋሚዎች በነፃነት የመደራጀትና የመንቀሳቀስ ችግር እየገጠማቸው መሆኑንም ይገልጻሉ፡፡ አቶ ደስታ የፖለቲካ ፓርቲዎች እንቅስቃሴ ገደብ እየገጠመው ያለው በገዥው ፓርቲም ሆነ በሌላ ሳይሆን በራሱ በመንግሥት እንደሆነም ያስረዳሉ፡፡

‹‹ፖሊስ የመንግሥት የፍትሕ ተቋም አካል እንጂ የፓርቲ ተወካይ አይደለም፡፡ በተለያየ እርከን የአስተዳደር በደል የሚፈጽሙ የተለያዩ የአስተዳደር አካላት የመንግሥት አስፈጻሚዎች እንጂ የፖለቲካ ተወካዮች አይደሉም፡፡ ከሚሊሻ ጀምሮ እስከ ላይኛው እርከን ባለው የመንግሥት አካል ያሉ አስፈጻሚዎች በተፎካካሪ የፖለቲካ ድርጅቶች ላይ የሚፈጽሙት ወከባ በቀጥታ ከመንግሥት ጋር የተገናኘ ነው፤›› በማለት ያብራራሉ፡፡

እሳቸው እምነት የፖለቲካ ምኅዳሩ የታፈነውና የጠበበው በመንግሥት መዋቅሮች ዕርምጃ በመሆኑ፣ መንግሥት በቢሮክራሲው የሚፈጸመውን አፈና ካላቆመ በስተቀር ሰላማዊ የፖለቲካ ትግል በኢትዮጵያ መፈተኑ ይቀጥላል፡፡

በቅርቡ የኢትዮጵያን ሰላማዊ የፖለቲካ ምኅዳር መጥበብ በሚመለከት መግለጫ ያወጣው ሂዩማን ራይትስ ዎች የተቃውሞ እንቅስቃሴ ማድረግ ፈተና እየሆነ መክበዱን ይፋ አድርጎ ነበር፡፡ ‹‹ማንም ላለመታሰሩ እርግጠኛ አይደለም›› (No one Appears Safe from Arbitrary Arrest) በማለት የፖለቲካ ከባቢ አየሩን የገለጸው ድርጅቱ፣ በወቅቱ ከአንድ የፈረንሣይ ጋዜጠኛ ጋር ቃለ መጠይቅ አድርገዋል በሚል ታስረዋል የተባሉትን ሟቹ የአቶ በቴን ጉዳይ እንደ ምሳሌ አድርጎ ያቀርበዋል፡፡

የሂውማን ራይትስ ዎች መግለጫ ሲቀጥልም በፓርላማው የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) ተወካዩ አቶ ክርስቲያን ታደለን ጨምሮ፣ አምስት የተቃዋሚ ፖለቲከኞች መታሰራቸውን ይገልጻል፡፡

በኢትዮጵያ በአሻሚ ሁኔታ መታሰር እንደጨመረ የሚገልጸው ይህ መግለጫ የኢትዮጵያ አጋር የሆኑ ደርጅቶች፣ ተቋማትና አገሮች ይህን የፖለቲካ ምኀዳር ጥበትና ሰላማዊ የፖለቲካ እንቅስቃሴ መገደብ እንዲያወግዙትም በይፋ ይጠይቃል፡፡

ይህ መግለጫ ከወጣና የአቶ በቴ መታሰር ዜና ከተሰማ ከአንድ ወር በኋላ በሰላማዊ የፖለቲካ ትግል የሚታወቁት ግለሰቡ በትውልድ ቦታቸው በመቂ ተገድለው መገኘታቸው፣ የሰላማዊ ፖለቲካ ትግል በር በኢትዮጵያ ከመጥበብ ወደ መዘጋት እየሄደ ነው የሚል ስሞታ አስነስቷል፡፡ በርካታ አስተያየት ሰጪዎች፣ ፖለቲከኞች፣ የፖለቲካ ድርጅቶች ከአቶ በቴ ግድያ በኋላ በሰጧቸው መግለጫዎች ኢትዮጵያ እንደ እሳቸው ያሉ ሰላማዊ ፖለቲከኞች የሚገደሉባት ከሆነች ለሌሎች የሰላማዊ ፖለቲካ ኃይሎች ዋስትና መስጠት ከባድ እንደሆነ ሲናገሩ ተደምጠዋል፡፡

መንግሥት የፖለቲካ ምኅዳሩን አጠበበ፣ እንዲሁም ሰላማዊ የፖለቲካ እንቅስቃሴ በኢትዮጵያ ፈተና ሆነ ከሚለው ስሞታ እኩል በሰላማዊ የፖለቲካ እንቅስቃሴ ስም ወዳልተፈለገ የፖለቲካ መንገድ የገቡ ኃይሎች መኖራቸው ፈተና ሆኗል የሚለው ወቀሳ  በመንግሥት በኩል ተደጋግሞ ይደመጣል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) አባሎቻችን ታሰሩብን የሚለውን የተቃዋሚዎች ጥያቄ በመለሱበት ወቅት፣ መንግሥት ይህንን ወደ ማድረግ የገባው ተገዶ እንደሆነ ሲናገሩ ተደምጠው ነበር፡፡ መንግሥታቸው ወደ ሥልጣን በመጣበት ወቅት ‹‹ሳናጣራ አናስርም›› የሚል ቃል ገብቶ እንደነበር በማስታወስ፣ ‹‹እኔ ይህንን የተናገርኩት በጊዜው ሁሉም በሰላማዊ መንገድ ብቻ የሚንቀሳቀስ ስለመሰለኝ ነበር፡፡ በሒደት ስናይ እኩይ የፖለቲካ ዓላማ ያላቸው እንዳሉ ተረዳን፡፡ ስለዚህ ሳናጣራ አናስርም በሚል ለቀን አገር አደጋ ላይ ከምንወድቅ እስክናጣራ ማሰሩ ተገደን የገባንበት ምርጫ ነው፤›› ብለው ነበር፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዚሁ ጊዜ የፖለቲካ ምኅዳርን የተመለከተ አስተያየት የሰጡ ሲሆን፣ ‹‹የሲቪክ ስፔሱ በጣም ሲጠብም ሆነ በጣም ሲሰፋ ችግር አለው፤›› ማለታቸው አይዘነጋም፡፡

በሌላ በኩል መንግሥት ለሰላማዊ ፖለቲካ ከፈጠረው ፈተና ባልተናነሰ በሰላማዊ ፖለቲካ እንንቀሳቀሳለን የሚሉ ኃይሎችም ቢሆን በዚህ ረገድ ችግር ሲፈጥሩ እንደሚታዩ የሚወቅሱ አሉ፡፡ አንዳንዶች ሰላማዊ የፖለቲካ ሥልትን ወይም በተፎካካሪ ፓርቲነት መደራጀትን ለግል ጥቅም ማጋበሻነት ያውሉታል የሚለው ወቀሳ ጎልቶ ይደመጣል፡፡ በፓርቲ ስም ከምርጫ ቦርድ ገንዘብ ለመሰብሰብ አንዳንዶች ይጠቀማሉ የሚል ወቀሳም ይቀርባል፡፡ የሰላማዊ ፖለቲካው በአንድ ወገን የሚፈጠር ብቻ ሳይሆን ከየአቅጣጫው በሚመጣ ችግር መፈተኑን ብዙዎች ይስማሙበታል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -