Monday, May 20, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የውጭ ባለሀብቶች ለኢትዮጵያውያን ብቻ በተፈቀዱ የንግድ ዘርፎች እንዲገቡ የመወሰኑ ፋይዳና ሥጋቶች

spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አዓመድ (ዶ/ር) የውጭ ኩባንያዎች በጅምላና ችርቻሮ ንግድ እንዲሁም በገቢና ወጪ ንግድ ላይ ተሳታፊ እንደሆኑ የሚያስችል የሕግ ማሻሻያ እንደሚደረግ በገለጹ በሁለት ሳምንት ልዩነት ውስጥ ይህንኑ የሚፈቅድ መመርያ ወጥቷል፡፡

ለኢትዮጵያውያን ብቻ ይፈቀዱ የነበሩ የንግድ ሥራዎች ለውጭ ኩባንያዎች ቀስ በቀስ እየተከፈቱ ስለመሆናቸው አንድ ማሳያ ተደርጎ የተወሰደው ይህ ሕግ  በኢትዮጵያ የግብይት ሥርዓት ውስጥ ለውጥ ያመጣል ተብሎም ታምኖበታል፡፡

ሕጉ ለኢትዮጵያውያን ብቻ ተከልሎ የነበረውን የጅምላና ችግርቻሮ የንግድ ሥራ ለውጭ ኩባንያዎች በመፍቀድ ብቻ የተገደበ ሳይሆን በወጪና ገቢ ንግድ ላይም የውጭ ባለሀብቶች ተሳታፊ የሚሆኑበትን በር የሚከፍት በመሆኑ በአገሪቱ ኢኮኖሚ ውስጥ አዲስ አሠራር እንደሚፈጥር በጉዳዩ ዙሪያ ያነጋገርናቸው በተለያዩ ዘርፎች ላይ የተሰማሩ ባለሙያዎች ገልጸዋል፡፡

የውጭ ባለሀብቶች ለኢትዮጵያውያን ብቻ በተፈቀዱ የንግድ ዘርፎች እንዲገቡ የመወሰኑ ፋይዳና ሥጋቶች | Ethiopian Reporter | ሪፖርተር
አቶ ፈቃዱ ጴጥሮስ የሕግ ባለሙያ

የዚህ መመርያ ተግባራዊ መሆን የአገሪቱ የግብይት ሥርዓትን ለማስተካከል ከመርዳቱም በላይ አገሪቱ በወጪ ንግድ ዘርፍ ያላትን ተወዳዳሪነት ይጨምራል የሚል እምነት በመንግሥት በኩል ተይዟል፡፡

በጉዳዩ ላይ ያነጋገርናቸው የኢኮኖሚ ባለሙያው ቆስጠንጢኖስ በርሃ የውጭ ኩባንያዎች በችርቻሮ ንግድ ላይ እንዳይሰማሩ ቀድሞም ቢሆን መከልከሉ አግባብ አልነበረም ይላሉ፡፡

በችርቻሮ ንግድም ሆነ በፋይናንስ ዘርፉ የውጭ ኩባንያዎች እንዲገቡ የሚፈቅደው ሕግ እስካሁን መዘግየት እንዳልነበረበት ጠንከር ያለ እምነት ያላቸው ቆስጠንጢኖስ (ዶ/ር) የውጭ ኩባንያዎች በዚህ ዘርፍ መግባታቸው ጠቀሜታ የሚሰጥ መሆኑንም ያስረዳሉ፡፡

በተለይ በኢትዮጵያ የግብይት ሥርዓት ውስጥ ያለውን ውስብስብ ችግር መስመር እንዲይዝ፣ ሕጋዊ የግብይት ሥርዓት እንዲሰፍንና ለዋጋ መረጋጋት ጭምር የራሳቸው አስተዋጽኦ ይኖራቸዋል ብለዋል፡፡ አክለውም የአገራችን የግል ዘርፍ እንዲያድግ ልምድም እንዲቀሰምበት ያግዛል ብለዋል፡፡

የውጭ ኩባንያዎች በችርቻሮ ንግድ ላይ የመሰማራት ጉዳይ ለኢትዮጵያ አዲስ ቢመስልም መላው ዓለም እየተጠቀመበት መሆኑን የሚገልጹት የኢኮኖሚ ባለሙያው፣ በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ሳይቀሩ ባሉበት አገር በተለያዩ ችርቻሮ ንግድ ላይ ተሰማርው የሚሠሩ መሆናቸውን በማሳያነት ይጠቅሳሉ፡፡

የዚህ መመርያ መውጣትን በተመለከተ ያነጋገርናቸው የሕግ ባለሙያው አቶ ፈቃዱ ጴጥሮስ በበኩላቸው ይህ መመርያ መንግሥት ተስፋ ቆርጦ ያወጣው ሊሆን ይችላል የሚል  እምነት አላቸው፡፡

ይህንንም ሲያብራሩ ለአገር ውስጥ ባለሀብቶች ከለላ ሲሰጥ ራሳቸውን ጠቅመው አገርንም ይደግፋሉ ብሎ ቢሆንም፣ ከረዥም ዓመታት በኋላም ለውጥ ስላልመጣ አማራጭ ማፈላለግ ግድ ሆኖበታል ብለዋል፡፡

መንግሥት ለአገር ውስጥ ነጋዴ ከለላ ሲሰጥ ትልቁ ዓላማው የአገር ውስጥ ኢንዱስትሪ እንዲያድግ ጊዜ ለመስጠት ነው እንጂ ነገሩ እንደ ሸማች ከታየ በውድድር የሚያድግ ገበያ የበለጠ ጠቃሚ ነው ብለዋል፡፡

‹‹ለአገር ውስጥ ባለሀብቶች ከለላ ተሰጥቶ በቆየበት ጊዜያት ሁሉ የምርት ዋጋ እየጨመረ ነው፡፡ አዝመራ ገባም አልገባም የምርት ዋጋ በአብዛኛው እየጨመረ እንጂ እየቀነሰ አይደለም፡፡ ስለዚህ በዚህ ማኅበረሰቡ እየተጎዳ ነውና ገበያውን ልክፈትና ውድድር ኖሮ ከውድድሩ ኅብረተሰቡ ተጠቃሚ ይሆናል በሚል መንግሥት ውሳኔ ላይ መድረሱን ያመለክታል፤›› ሲሉ አቶ ፈቃዱ አስረድተዋል፡፡

ለዚህም መመርያውን መግቢያ በምሳሌነት ጠቅሰዋል፡፡ ‹‹እስካሁን የነበረውን ከለላ በመስጠት የተገኘ ጥቅም የለም፡፡ እንደውም ባልተገባ መንገድ ጥቅም ላይ ውሏል›› የሚል ይዘት ያለው መሆኑ በራሱ የሚጠቀመው ከለላ በመደረጉ ምንም ጥቅም ያልተገኘ መሆኑ ነው፡፡

መንግሥት የግብይት ሥርዓቱን ለማስተካከል ከዚህ ቀደም የወሰዳቸው ዕርምጃዎች እንዳልሰመሩ የሚገልጹ አንድ የንግድና ኢንቨስትመንት አማካሪ በበኩላቸው በገበያ ውስጥ ያለውን ክፍተት ለመሙላት መንግሥት እጁን አስገብቶ ለማስተካከል ያደረገውም ጥረት ያለመሳካቱ የግድ ሌላ አማራጭ መፈለግ ግድ ሆኖበታል ብለዋል፡፡

ከእነዚህ አማራጮች መካከል አንዱ የውጭ ባለሀብቶች በጅምላና ችርቻሮ ንግድ ላይ እንዲሰማሩ መፍቀድ እንደሆነም ተናግረዋል፡፡ መንግሥት የአገር ውስጥ ነጋዴዎችን ለመጠበቅ በጅምላና ችርቻሮ ንግድ ላይ የውጭ ባለሀብቶች እንዳይገቡ ሲከላከል የቆየ መሆኑን ያስታወሱት እኚሁ አማካሪ፣ አሁን ግን መንግሥት ሲፈራ ሲቸር ቆይቶ ዘርፉን ለውጭ ኩባንያ መክፈቱ ትልቅ ውሳኔ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ አሁን ካለው የአገሪቱ ፍላጎት አንፃር የግብይት ሥርዓቱ በተጨማሪ ተዋንያኖች ካልታገዘ የሚያስከትለው ጉዳት ቀላል አለመሆኑን የገለጹት ባለሙያው፣ አሁን በጥቂቶች የተያዘውን የጅምላና ችርቻሮ ንግድ ሥራ ተወዳዳሪ እንዲሆን በማድረግ ገበያን ማረጋጋት የሚቻልበት ዕድል ሰፊ መሆኑንም ሳያመለክቱ አላለፉም፡፡

መንግሥት ገበያን ለማረጋጋት በሚል ከፍተኛ ኢንቨስትመንት ያቋቋማቸው እንደ አለ በጅምላ ያሉ ተቋማት የሚፈለገውን ግብ ሳይመቱ የተሽመደመዱት በጅምላና ችርቻሮ ንግድ ውስጥ በሞኖፖል ከመያያዛቸው ጋር ተያያዘ ጭምር እንዲሆነ የሚገልጹት ባለሙያው፣ በዘርፉ የውጭ ኩባንያዎች ከገቡ ቢዝነሱ በተወዳዳሪነት ላይ የተመሠረተ አገልግሎት የሚሰጥበት ይሆናል የሚል እምነት እንዳላቸው ገልጸዋል፡፡

ዋናው ነገር በአዲሱ መመርያ የውጭ ኩባንያዎች በዚህ ቢዝነስ ላይ ሲሰማሩ በአስገዳጅነት የተቀመጡ ድንጋጌዎችንና አሠራሮችን በአግባቡ ስለማካሄዳቸው መቆጣጠር መቻል ነው በማለት አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡

አቶ ፈቃዱም እንዲህ ያሉ መመርያዎች በዋናነት የሚጠቅሙት ሸማቹን እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ በእነዚህ አራት ዘርፎች (የገቢ፣ የወጪ፣ ጅምላና ችርቻሮ ንግዶች) ከለላ ተሰጥቶ የመቆየቱን ያህል ውጤታማ መሆን አልተቻለም፣ ዓላማውንም አላሳካም ብለዋል፡፡ አሁን ከለላው በመነሳቱ የውጭ ኩባንያዎች ከፍተኛ መጠን ያለው ምርት በማምጣት በዝቅተኛ የትርፍ ምጣኔ እንዲያቀርቡ የሚያስችላቸው በመሆኑ ገበያውን የሚያረጋጋና ዋጋ የሚቀንስበት ዕድል እንደሚፈጠር አቶ ፈቃዱ ገልጸዋል፡፡

የውጭ ኩባንያዎች በኢትዮጵያ ገበያ ውስጥ መግባታቸው በአገር ውስጥ ተመሳሳይ ሥራ በሚሠሩ ነጋዴዎች ላይ ጫና ይፈጥራል የሚል መከራከሪያ የሚያቀርቡ ወገኖች አሉ፡፡ በተለይ አሁን በንግድ ሥርዓቱ ውስጥ የተፈጠረው ክፍተት ችግሩ የአገሬው ነጋዴ ሊሠራ ባለመቻሉ አይደለም የሚሉት ስሜ አይጠቀስ ያሉ አንድ የፋይናንስ ባለሙያ፣ የውጭ ኩባንያዎች መግባት የግብይት ሥርዓቱን ያሻሽላል በሚለው ሐሳብ ቢስማሙም የአገሬው ነጋዴ የውጭዎቹ ይሸፍኑታል የተባለውን የገበያ ክፍተት መሸፈን ያልቻሉበት ዋነኛ ምክንያት የውጭ ምንዛሪ እጥረትና ከዚሁ ጋር የተያያዙ ችግሮች በመኖራቸው ነው ይላሉ፡፡ በእርግጥ ብዙው ነጋዴ ያለውን የውጭ ምንዛሪ እጥረት ክፍተት ተጠቅሞ የሚፈጽመው ያልተገባ ተግባር ቢኖርም በአገሪቱ የሚታየው ብልሹ የግብይት ሥርዓት አንዱ መንስዔ የውጭ ምንዛሪ እጥረትና ከዚሁ ጋር የተያዘው ፖሊሲ እንደሆነ ያምናሉ፡፡ ነገር ግን እንደተባለው የውጭ ኩባንያዎች ወደ ኢትዮጵያ ገብቶ በችርቻሮ ንግድ ላይ መሳተፋቸው ገበያው ላይ ለውጥ እንደሚያመጣ የእርሳቸውም እምነት እንደሆነ ያመላክታሉ፡፡

እንደ ፋይናንስ ባለሙያው ማብራሪያ ከሆነ በችርቻሮ ንግድ ላይ የተሰማሩ የውጭ ኩባንያዎች ኢትዮጵያ እንዲገቡ መፈቀዱ አግባብ የመሆኑን ያህል አሁን ባለው የአገራችን የፋይናንስ ፖሊሲ በተለይም የውጭ ምንዛሪ  ተመን በገበያ ዋጋ የማይወሰን ከሆነ እነዚህ ኩባንያዎች ሊገቡ የሚችሉበት ዕድል ጠባብ እንደሆነ ያምናሉ፡፡

ከዚህ ቀደም ዎልማርት የተባለው የአሜሪካው ግዙፍ ኩባንያ ኢትዮጵያ እንዲገባ ከመንግሥት ጋር ስምምነት በማድረግ አንዳንድ ሥራዎች ከጀመረ በኋላ ተግባራዊ መሆን ካልቻለበቸው ምክንያቶች አንዱ የአገሪቱ የፋይናንስ ፖሊሲ የማይሠራ በመሆኑ ነው ሲሉ እኚሁ የፋይናንስ ባለሙያ አስታውሰዋል፡፡

ስለዚህ የውጭ ኩባንያዎች ይግቡ ሲባል የግዴታ የውጭ ባንክ መግባትና የውጭ ምንዛሪ ተመንን በገበያ ዋጋ እንዲወሰን ማድረግ ግድ የሚል መሆኑን ያመለክታሉ፡፡

ይህ ካልሆነ በችርቻሮ ንግድ፣ በጅምላ በወጪና ገቢ ንግድ ላይ የሚሳተፉ  የውጭ ኩባንያዎች ሊገቡ የሚችሉበት ዕድል ጠባብ ሊሆን እንደሚችል ያላቸውን ሥጋት ጠቁመዋል፡፡

ይህንኑ ሐሳባቸውን ለማጠናከር እንደ ምሳሌ ያነሱት ሌላ ነጥብ አሁን በባንኮች አንድ ዶላር 57 ብር እየተመነዘረ በትይዩ ገበያ (ጥቁር ገበያ) 120 ብር እየተመነዘረ ባለበት አሠራር ውስጥ ዘው ብለው ይገባሉ ማለት አስቸጋሪ ነው ብለዋል፡፡ ይህ የተዘበራረቀ ገበያ ባለበት ሁኔታ በሕጋዊ የገበያ ሥርዓት እንዴት ሊሠሩ ይችላሉ በማለትም መንግሥት ይህንን ሕግ ለመተግበር ያለው ብቸኛ አማራጭ የውጭ ምንዛሪ በገበያ ዋጋ እንዲተመን ማድረግ ነው በማለት ይሞግታሉ፡፡

ቆስጠንጢኖስ (ዶ/ር) በበኩላቸው የውጭ ችርቻሮ ነጋዴዎች በኢትዮጵያ ገበያ መግባት ተፅዕኖ ያሳርፋል በሚለው እንደማይስማሙ ከመግለጻቸው በተጨማሪ፣ የውጭ ምንዛሪ ተመኑ በገበያ ዋጋ ሳይወሰን እንዲሁም የውጭ ባንኮች ሳይገቡ በችርቻሮ  ንግድ ላይ የተሰማሩ የውጭ ኩባንያዎች ሊገቡ አይችሉም በሚለው ሐሳብ አይስማሙም፡፡

አሁን በመጣው መመርያ መሠረት የውጭ ኩባንያዎች ሊጠቀሙበት የሚችሉት ብዙ ዕድል እንዳለ ያምናሉ፡፡ የበለጠ እንዲሠሩ ግን እንደተባለው የፋይናንስ ፖሊሲውን ማሻሻል በተለይም የውጭ ምንዛሪ ተመንን በገበያ ዋጋ እንዲሆን መወሰን ያስፈልጋል ብለዋል፡፡

የውጭ ምንዛሪ ተመን በገበያ ዋጋ እንዲወሰን ማድረግ ግድ የሚሆነው የውጭ ኩባንያዎች እንዲገቡ ለማድረግ ብቻ ሳይሆን አጠቃላይ ኢኮኖሚውን ለመደገፍ ግድ ስለሚል ነው ብለዋል፡፡ አሁንም በአገራችን የሚካሄደው አጠቃላይ ግብይት የጥቁር ገበያ የምንዛሪ ዋጋን መሠረት በማድረግ መሆኑን የጠቆሙት ባለሙያው፣ ይህም ሕገወጥ ተግባራት እያስፋፋ በመሆኑ ጉዳዩ ከባድ ሊመስል ቢችልም ለዘለቄታው የሚያስፈልገው በገበያ ዋጋ መመራት ነው ሲሉ ተናግረዋል፡፡

የውጭ ምንዛሪን በገበያ ዋጋ እንዲመራ ማድረግ የዋጋ ንረትን እንደሚያስከትል ብዙዎች የሚስማሙበት ቢሆንም፣ እንደ ፋይናንስ ባለሙያው ትንተና ግን አሁን በገበያው ላይ የሚደረገው ግብይት ዋጋ እየተሰላ ያለው በጥቁር ገበያ በመሆኑ የሚፈራው የዋጋ ንረት ለተወሰኑ ጊዜያት ጫና ሊፈጥር ይችላል እንጂ ያን ያህል ጉዳት ያመጣል ብለው እንደሚያምኑም ገልጸዋል፡፡

ጫናው እንዳይበረታ ደግሞ መንግሥት አሁን ያለውን የውጭ ምንዛሪ ፍላጎት ሊመልስ የሚችል የውጭ ምንዛሪ አቅርቦት እንዲኖር ማድረግ እንደሚገባው ተናግረዋል፡፡

ለምሳሌ በገበያ ዋጋ የአንድ ዶላር ዋጋ 120 ብር ቢሆን ሰው ወደ ጥቁር ገበያው አይሄድም፡፡ በቂ የውጭ ምንዛሪ ክምችት ከተያዘ የውጭ ምንዛሪ ፈላጊው ተጨማሪ ዶላር ለማግኘት ወደ ባንክ እንጂ ወደ ጥቁር ገበያ የሚሄድበት ዕድል ያጠባል በመሆኑም መንግሥት የውጭ ምንዛሪ በገበያ ዋጋ እንዲወሰን ዕርምጃ ከመውሰዱ በፊት በቂ የውጭ ምንዛሪ ስንቅ ሊኖረው ይገባል ብለዋል፡፡

ትልቁ ችግር የውጭ ምንዛሪ በገበያ ሲወስን ከውሳኔው በኋላ የውጭ ምንዛሪ ፍላጎትና አቅርቦት ካልተጣጣመ ግን እንደገና የጥቁር ገበያው እንዲያንሰራራ ስለሚያደርግ ይህ እንዳይሆን በቂ ስንቅ ይዞ ውሳኔው ቢወሰን ጠቃሚ እንደሆነ ጠቅሰዋል፡፡

ቆስጠንጢኖስ (ዶ/ር) እንደሚሉት በተለይ የምንዛሪ ዋጋን በገበያ መወሰን ግድ ይላል፡፡ ‹‹ሌላውን ትተን የውጭን ምንዛሪ ዋጋ በገበያ ዋጋ ቢወሰን ከዳያስፖራው ብቻ ከ12 ቢሊዮን ብር ያላነሰ የውጭ ምንዛሪ ይገኛል የሚል ግምት አለኝ የሚሉት ቆስጠንጢኖስ (ዶ/ር) ይህም በአብዛኛው ከባንክ ውጭ ይላክ የነበረ ዶላር በሕጋዊ መንገድ እንዲገባ ያስችላል ብለዋል፡፡

ከዚህም ሌላ በጥቁር ገበያው መስፋፋት ምክንያት በከፍተኛ ሁኔታ እየተካሄደ ያለውን የኮንትሮባንድ ንግድ እንደሚያስቀር ተናግረዋል፡፡ ይህ ደግሞ በሕጋዊ መንገድ የሚደረግ የንግድ እንቅስቃሴን ስለሚያሳደግ የግብይት ሥርዓቱን መስመር ከማስያዝ ባሻገር የመንግሥትም የግብር ገቢ እንደሚያሳድግ ገልጸዋል፡፡

በተለይም የውጭ ምንዛሪ ተመንን በገበያ ዋጋ ለመወሰን አይኤምኤፍ ወደ 3.5 ቢሊዮን ዶላር ለማበደር መስማማቱንም አስታውሰዋል፡፡ ‹‹ይህ አገሪቱ ከምትፈልገው የውጭ ምንዛሪ እንፃር አነስተኛ ነው፡፡ ከእነሱ 10 እና 12 ቢሊዮን ዶላር የሚገኝ ከሆነና የውጭ ምንዛሪ ተመኑ በገበያ ዋጋ መወሰን ቢችል ሥጋቶችን በማስቀረት ውጤታማ መሆን ይችላል፡፡ ምንዛሪን በገበያ ዋጋ መወሰን ለምሳሌ በኪሳራ እየተሸጠ ያለውን የቡና የወጪ ንግድ በገበያ ዋጋ እንዲስተናገድ የሚያስችልና ሕገወጥ ተግባራትንም የሚከለክል ይሆናል›› ብለዋል፡፡

በመሆኑም በአንዴ የውጭ ምንዛሪ በገበያ ዋጋ እንዲሆን መወሰን ጫና አለው ቢባል እንኳን ጨከን ብሎ መግባቱ አዋጭ እንደሚሆን ገልጸዋል፡፡

የውጭ ኩባንያዎች በተለያዩ የኢንቨስትመንትና የንግድ ሥራዎች ውስጥ እንዲገቡ መፈቀዱን ጠቀሜታ በተመለከተ አቶ ፈቃዱ በሰጡት ተጨማሪ ማብራሪያ የውጭ ኩባንያዎች የራሳቸው የትርፍ ህዳግና ደንቦች አሏቸው፡፡

ይህ መሆኑ የግብይት ሥርዓቱ ሕግና ደንብን ተከትሎ እንዲጓዝ ያስችላል ብለዋል፡፡

በተለይ በከፍተኛ ደረጃ የመሥራት አቅም ያላቸው በመሆኑ ከእያንዳንዱ ምርት ላይ ሁለትና ሦስት እጥፍ ከማትረፍ ይልቅ ብዙ በማምጣት አነስተኛ ትርፍ በመያዝ የሚሠሩ በመሆኑ፣ ገበያ ውስጥ በተለይ ከውጭ የሚገቡ ምርቶች ላይ የበለጠ ውድድር እንዲኖር ያስችላሉ ብለዋል፡፡

እንደ  ሱፐር ማርኬት ያሉ አገልግሎቶች ላይም ጥራት ያለው ዕቃ በተመጣጣኝ ዋጋ የማቅረብ ልምድና አቅም ስለሚኖራቸው ሸማቹ እንደሚጠቁም፣ ነገር ግን እነዚህ ድርጅቶች ሠርተው ትርፋቸውን በውጭ ምንዛሪ ለመውሰድ መጠየቃቸው እንደማይቀር ገልጸዋል፡፡

በሌላ በኩል ግን እነዚህ ኩባንያዎች በዚህ መመርያ ይመጣሉ ወይ? የሚለው አጠያያቂ የሚሆንበትም ሁኔታ ሊኖር እንደሚችል ጠቁመዋል፡፡

ይህም አሁን ባለው የውጭ ምንዛሪ አስተዳደር ኢትዮጵያ ገበያ ውስጥ ገብተን መሥራት እንችላለን ወይ የሚል እንደሚሆን ጠቅሰዋል፡፡

‹‹አሁን ባለው ሁኔታም አትራፊ ሊያደርጋቸው ቢችልም ትርፋቸውን ይዘው  ለመውጣት ያለው የውጭ ምንዛሪ እጥረት ሊያሠራን ይችላል ወይ?›› የሚል ጥያቄ ማንሳታቸው አይቀርም›› የሚሉት አቶ ፈቃዱ ከአጠቃላይ ማክሮ ኢኮኖሚው አንፃር የእነሱ መግባት የውጭ ምንዛሪ ላይ ጫና አይፈጥርም ወይ? የሚለውም መልስ ሊያገኝ እንደሚገባ ጠቁመዋል፡፡

የውጭ ዜጎች በችርቻሮ ጅምላ ንግድ ላይ እንዲሰማሩ የሚፈቅደው አዲሱ መመርያ ከነዳጅ ማዳበሪያ ውጭ ሌሎች በአገር ውስጥ የሚመረትም ሆነ ከውጭ የሚመጡ ምርቶችን በጅምላና በችርቻሮ ለገበያ ማቅረብ የሚችሉበትን አሠራር የሚፈጥር ነው፡፡ ነገር ግን በዚህ ቢዝነስ የሚሰማራ የውጭ ባለሀብት ዘመናዊ ገበያን ለማደራጀት ሊያሟሉ የሚገባቸውን ድንጋጌዎች ያስቀምጣል፡፡

የችርቻሮ መደብሮቻቸው ምን ያህል በተለይ ማትረፍ እንደሚገባውና በየደረጃው የተቀመጡ መሥፈርቶችና የካፒታል መጠናቸው ምን ያህል መሆን እንዳለበት የሚደነግግም በመሆኑ አሁንም የአገር ውስጥ ኩባንያዎች ተወዳዳሪ የሚሆኑበት ሰፊ የገበያ ዕድል እንዳለም ያሰባሰብናቸው መረጃዎች ያመለክታል፡፡

ቆስጠንጢኖስ (ዶ/ር) እንደሚገልጹት ከሆነ ለተወሰኑ አስመጪና ላኪዎች ከለላ በማድረግ መቀጠል ስለማይቻል ገበያ እስካረጋጋና ኢኮኖማውን እስከጠቀመ ድረስ እንዲህ ያሉ ሕጎች ያስፈልጋሉ፡፡

አቶ ፈቃዱ በአራቱ ዘርፎች ላይ የውጭ ኩባንያዎች እንዲገቡ መፈቀዱ ቀስ በቀስ ብዙ ቢዝነሶች ለውጭ ኩባንያዎች ክፍት መሆናቸውን የሚያሳይ ነው ይላሉ፡፡

ከ2002 በፊት የነበረው የኢንቨስትመንት ደንብ የውጭ ኩባንያዎች ሊሠሩበት የሚችሉትን የኢንቨስትመንት ብቻ የሚጠቅስ ነው፡፡ ከ2002 በኋላ የወጣው ደንብ ደግሞ መሥራት የሚችሉበትን የቢዝነስ ዘርፍ የሚሸረሽር ስለነበር ከተዘረዘሩት ውጭ ሌሎቹን መሥራት እንደሚችሉ የሚደነግግ እንደነበር አስታውሰዋል፡፡

አሁን ደግሞ እነዚህን አራት የቢዝነስ ዘርፎች እንዲወጡ በማድረግ የውጭ ኩባንያዎች በችርቻሮ፣ በጅምላ በወጪና ገቢ ንግድ ላይ እንዲሰማሩ መፍቀዱ የውጭ ኩባንያዎች የሚሳተፉበት የቢዝነስ ዘርፍ በእጅጉ እየጨመረ መምጣቱን እንደሚያመላክት አስረድተዋል፡፡ ይህ ደግሞ በተለይ ለተገልጋይና ሸማች ጠቀሜታው የሰፋ ነው ይላሉ፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች