Sunday, May 19, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

‹‹በአሁኑ ወቅት ከ21 ሚሊዮን በላይ ሕዝብ ሰብዓዊ ዕርዳታ ይፈልጋል›› አቶ አበራ ሉሌሳ፣ የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማኅበር ምክትል ጸሐፊ

የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማኅበር ላለፉት 89 ዓመታት በመላ አገሪቱ የሰብዓዊነት አገልግሎት ሲሰጥ ቆይቷል፡፡ በድርቅ፣ በበሽታና በግጭት ምክንያት ለተጎዱ ወገኖች የምግብ፣ የመጠለያ፣ የመድኃኒትና የ24 ሰዓት ነፃ የአምቡላንስ አገልግሎት በመስጠት ኅብረተሰቡን እያገዘና እየደገፈ ይገኛል፡፡ በተጨማሪም በጤና፣ በንፁህ መጠጥ ውኃ አቅርቦት፣ እንዲሁም በግጭት ምክንያት የወደሙ መሠረተ ልማቶችን በመጠገን በኩል ተሳትፎው የጎላ ነው፡፡ ማኅበሩ እያከናወናቸው ስላለው ሰብዓዊ ተግባራት፣ በግጭቶች አካባቢ እየገጠመው ስላለው ተግዳሮትና በቀጣይ ሊሠራቸው ስላቀዳቸው ተግባራት የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማኅበር ምክትል ጸሐፊ የሆኑትን አቶ አበራ ሉሌሳን የማነ ብርሃኑ አነጋግሯቸዋል፡፡

ሪፖርተር የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማኅበር ከተቋቋመለት ዓላማ አንፃር እያከናወናቸው ያሉ ተግባራት ምን ይመስላሉ?

አቶ አበራ፡- የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማኅበር ኢትዮጵያ ውስጥ ካለው ሰብዓዊ ፍላጎት አንፃር ዘርፈ ብዙ ሥራዎች እየሠራ ይገኛል፡፡ በድርቅና በግጭት ምክንያት ለተጎዱ ወገኖች አጠቃላይ የምግብና ምግብ ነክ ያልሆኑ ነገሮች በማቅረብ ይደግፋል፡፡ በተጨማሪም በንፁህ መጠጥ ውኃ አቅርቦት፣ በሥነ ንፅህና፣ በግጭት ምክንያት የተጎዱ መሠረተ ልማቶችን የመጠገን ሥራ ያከናውናል፡፡ በሌላ በኩል የጤና ዘርፉን ለማገዝ ለኅብረተሰቡ መድኃኒቶችን በተመጣጣኝ ዋጋ በማቅረብ ላይ ነው፡፡ ከውጭ አገሮች ወደ አገራችን ለሚመለሱ ወገኖችም ድጋፍ በማድረግ ላይ ይገኛል፡፡ በአጠቃላይ በኢትዮጵያ ውስጥ ባሉ የሰብዓዊ ፍላጎቶች ላይ በመመርኮዝ የተለያዩ ሥራዎችን ይሠራል፡፡

ሪፖርተር፡- ማኅበሩ ሰብዓዊ አገልግሎቱን ተደራሽ በማድረግ ረገድ፣ ከበጎ ፈቃደኞችና ከቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤቶቹ ጋር ያለው ጥምረት እንዴት ይገለጻል?

አቶ አበራ፡- ማኅበሩ የተለየዩ የሰብዓዊ ተግባራትን በሚያከናውንበት ጊዜ በመላ አገሪቱ ካሉ በጎ ፈቃደኞች፣ አባላትና ከክልል ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤቶች ጋር በመቀናጀት ነው፡፡ ከዋና ጽሕፈት ቤት ጀምሮ እስከ ወረዳና ቀበሌ ድረስ የሚዘልቅ መዋቅር አለ፡፡ በዚህ ውስጥ ወደ 2‚500 ሠራተኞች አሉ፡፡ እነዚህም በተለያዩ ሥራዎች ኅብረተሰቡን የሚያግዙ የቋሚ ሰዓት (ደመወዝ ተከፋይ) ሠራተኞች ናቸው፡፡ በበጎ ፈቃደኝነት ደረጃ የሚያገለግሉ ከ200 ሺሕ በላይ የሚሆኑ ወገኖች ያሉን ሲሆን፣ እነርሱም ጊዜያቸውንና ዕውቀታቸውን ለሰብዓዊ አገልግሎት በነፃ እያቀረቡ የሚገኙ ናቸው፡፡ አባሎቻችንም ወደ 6.7 ሚሊዮን ይደርሳሉ፡፡ እነኚህ የማኅበሩ አባላት በየዓመቱ የአባልነት ክፍያ የሚከፍሉ ሲሆን ከእነሱም የሚገኘው ገንዘብ ለተጎዱ ወገኖች ድጋፍ እየዋለ ይገኛል፡፡

ሪፖርተር፡- ማኅበሩ በርካታ ሰብዓዊ ተግባራትን እያከናወነ እንደሚገኝ ይታወቃል፡፡ ለእነዚህ ተግባራት መከወኛ የገቢ ምንጩ ምንድነው?

አቶ አበራ፡- ማኅበሩ ለሚያከናውናቸው ሰብዓዊ አገልግሎቶች አብዛኛው ምንጩ ከውጭ ለጋሽ ድርጅቶች ነው፡፡ የአውሮፓ ቀይ መስቀል ጽሕፈት ቤት፣ የዓለም አቀፍ ቀይ መስቀል ኮሚቴ፣ የዓለም አቀፍ ቀይ መስቀልና ቀይ ጨረቃ ፌዴሬሽን ይረዱናል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ የተለያዩ ዓለም አቀፍ ለጋሽ ድርጅቶች፣ ለምሳሌ ዩኤስኤይድ (USID)፣ የእንግሊዝ፣ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅትና የአውሮፓ ኅብረት ለምንተገብራቸው ፕሮጀክቶች ገንዘብ የሚያቀርቡልን ናቸው፡፡ በመሆኑም የማኅበሩ ትልቁ የገቢ ምንጭ ከዓለም አቀፍ ድርጅቶች የሚገኝ ድጋፍና ዕርዳታ ነው፡፡ በሁለተኛ ደረጃ ከአገር ውስጥ ከአባሎቻችን በየዓመቱ የምንሰበስበው የአባልነት መዋጮ ነው፡፡ ከግል የአባልነት ክፍያ በተጨማሪም የተለያዩ ድርጅቶችም ያግዙናል፡፡ ለምሳሌ ኢትዮ ቴሌኮም አጭር የጽሑፍ መልዕክት 9400 ትብብር አድርጎልናል፡፡ ይህም አንድ ዓመት አካባቢ ሆኖታል፡፡ በዚህም ከመቶ ሺሕ በላይ ሰዎች ለሰብዓዊነት በቀን አንድ ብር በመክፈል ማኅበሩን ያግዛሉ፡፡ የተለያዩ አገር በቀል ድርጅቶችም በየዓመቱ ከሚከፍሉት የአባልነት ክፍያ በተጨማሪ በተለያዩ አካባቢዎች ለምናከናውናቸው ፕሮጀክቶች ድጋፍ ያደርጉልናል፡፡ በአብዛኛው 99 ከመቶ የሚሆነው የገቢ ምንጭ የሚገኘው ግን ከውጭ ካሉ ለጋሽ ድርጅቶች ነው፡፡

ሪፖርተር፡- በምትሰጡት የሰብዓዊ አገልግሎት በዚህ ዓመት ምን ያህል የማኅበረሰብ ክፍሎች ጋር ደርሳችኋል?

አቶ አበራ፡- ባለፉት ስድስት ወራት ከሐምሌ 1 እስከ ታኅሣሥ 30 ቀን 2016 ዓ.ም.  ከ1.5 ሚሊዮን ሕዝብ በላይ ደርሰናል፡፡ ይህ የተለያዩ የዘመቻ ሥራዎችን ሳያካትት ነው፡፡ ይህ እንደኛ ትልቅ ቁጥር ቢሆንም ኢትዮጵያ ውስጥ አሁን ካለው የሰብዓዊ ፍላጎት አንፃር ሲመዘን ግን ትንሽ ሊባል የሚችል ነው፡፡ በአሁኑ ወቅት ከ21 ሚሊዮን ሕዝብ በላይ ሰብዓዊ ዕርዳታ ይፈልጋል፡፡ ለዚህ ሁሉ ሕዝብ የሰብዓዊ ድጋፍ ለማቅረብ እንዳንችል አቅም ገድቦናል፡፡ በቅርብ ዩኤን ኦቻ (የመንግሥታቱ ድርጅት) ባወጣው ሪፖርት መሠረት ለእነኚህ ወገኖች የሰብዓዊ ድጋፍ ለማድረግ ከሰባት ቢሊዮን ዶላር በላይ ያስፈልጋል፡፡ እንግዲህ እዚህ ቁጥር ውስጥ ነው ማኅበራችን እየተጫወተ የሚገኘው፡፡ ‹‹ኃምሳ ሎሚ ለአንድ ሰው ሸክሙ፣ ለኃምሳ ሰው ግን ጌጡ ነው፤›› እንደሚባለው፣ ማንኛውም ኢትዮጵያዊ አንድ ብር ለሰብዓዊ አገልግሎት ቢለግስ በርካቶች ጋ መድረስ ይቻላልና እጃቸውን እንዲዘረጉ በዚህ አጋጣሚ ጥሪ አቀርባለሁ፡፡ በመሆኑም በአገር ውስጥም ሆነ በውጭ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ጥሪያችንን ተቀብለው በኢትዮጵያ ቀይ መስቀል በኩል ወገኖቻችንን ቢረዱ፣ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ዜጎችን መታደግ ስለሚቻል በድጋሚ ለሰብዓዊነት እንዲፈጥኑ መልዕክቴን አደርሳለሁ፡፡

ሪፖርተር፡- ባለፉት ሦስትና አራት ዓመታት በአገሪቱ በነበሩ ግጭቶች በማኅበሩ ላይ የደረሱ ጉዳቶች ምን ይመስላሉ?

አቶ አበራ፡- ቀይ መስቀል ግጭት በሚከሰትባቸው ቦታዎች በሁሉም አለ፡፡ ማኅበሩ ከመርሁ አንፃር ለማንም አይወግንም፡፡ አያዳላም፡፡ ሁሉንም ወገኖች እኩል ይመለከታል፡፡ ይህንንም ዓላማ አንግበው ስታፎቻችንና በጎ ፈቃደኞቻችን በግጭት አካባቢዎች ራሳቸውን መስዋዕት አድርገው የሰብዓዊ አገልግሎት ይሰጣሉ፡፡ ይህ ሆኖ ባለበት በተለይም ባለፉት ሦስትና አራት ዓመታት በማኅበሩ ስታፎች፣ በጎ ፈቃደኞችና ንብረቶች ላይ ከፍተኛ ጉዳት ደርሷል፡፡ በርካታ ስታፎቻችንና በጎ ፈቃደኞቻችን ሞተዋል፣ ንብረቶቻችን በአንድ ወይም በሌላ መንገድ ተጎድተዋል፡፡ የተቃጠሉ፣ በጦር መሣሪያ የተመቱና የተዘረፉብን አሉ፡፡ እውነት ለመናገር ይኼ በጣም ያሳዝናል፡፡ ስታፎቻችንም ሆኑ በጎ ፈቃደኞቻችን በሥፍራው የሚገኙት የወገኖቻቸውን ሕይወት ለመታደግ ነው፡፡ ከዚህ አንፃር በሰሜኑ የአገራችን አካባቢ 12 በጎ ፈቃደኞቻችንና ስታፎቻችን ሞተዋል፡፡ በቅርብ እንኳ የዛሬ ሁለትና ሦስት ወራት አካባቢ ትግራይ ውስጥ አንድ የአምቡላንስ አሽከርካሪ ወላድን ለማምጣት እየሄደ ባለበት ሰዓት በተተኮሰ ጥይት ተመቷል፡፡ ንብረቶችም እየወደሙና እየተቃጠሉብን ነው፡፡ ይህ ለማኅበሩ ትልቅ አደጋና ሥጋት ነው፡፡ አንድ ሕይወት ለማትረፍ ሌላ ሕይወት መገበር ፈጽሞ ትክክል ሊሆን አይችልም፡፡ ከዚህ አንፃር በግጭት ውስጥ የሚገኙ አካላት የቀይ መስቀልንና የሰብዓዊ አገልግሎት የሚሰጡ ተቋማትን ሚና ተረድተው ትብብር ማድረግ ይጠበቅባቸዋል፡፡ የሰብዓዊ አገልግሎትን ተደራሽ ከማድረግ አንፃርም መንገዶች ክፍት መሆን አለባቸው፡፡ ዓለም አቀፍ የቀይ መስቀል ሕጎችና መርሆች ሊከበሩ ይገባል፡፡

ሪፖርተር፡- ቀይ መስቀል አሁን እያከናወናቸው ካሉ ተግባራት በተጨማሪ ሌሎች ሊሠራቸው ያቀዳቸው ተግባራት ይኖራሉ?

አቶ አበራ፡- ማኅበሩ አሁን እየሰጠ ከሚገኘው የሰብዓዊ አገልግሎት በተጨማሪ በሕዝቦች መካከል ቅራኔ ተወግዶ ሰላማዊ አገር ትኖረን ዘንድ የሚሠራቸው ሥራዎች ይኖራሉ፡፡ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በአገራችን እየታዩ ያሉ አዝማሚያዎች ጥሩ አይደሉም፡፡ ሥር የሰደደ ጥላቻ እየተፈጠረ ይገኛል፡፡ በመሆኑም የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማኅበር ከሚያራምደው ዓላማና ከተሰሚነቱ አንፃር የኅብረተሰቡን መስተጋብር በጠበቀ መልኩ በጋራ የመኖር ታሪኩን የማስቀጠል፣ ሕዝብ ለሕዝብ ተቀራርቦ እንዲነጋገርና ችግር ካለም በውይይት እንዲፈታ ለማድረግ አቅዶ በመንቀሳቀስ ላይ ይገኛል፡፡ በተጨማሪም ወጣቶችና ትምህርት ቤቶችን ማዕከል ያደረገ የአመለካከት ለውጥ እንዲመጣ ትኩረት አድርጎ ይሠራል፡፡ ከዚህ ጋር ተያይዞ የሰብዓዊነት ትምህርት ቤት (School of Humanity) በማቋቋም ወጣቶችን በሰብዓዊነት፣ በአብሮነትና በመቻቻል እሴት አሠልጥኖ ለማስመረቅ የሚያስችል እንቅስቃሴ በማድረግ ላይ ይገኛል፡፡ ትምህርት ቤቱም የቀይ መስቀል መርሆችን ባካተተ መልኩ ሥርዓተ ትምህርቱ ተዘጋጅቶ ከ2017 ዓ.ም. ጀምሮ ተማሪዎችን ተቀብሎ ለማስተማር በዝግጅት ላይ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ማኅበሩ በተለያዩ ክልሎች በርካታ ፕሮጀክቶችን እየተገበረ ይገኛል፡፡ ከእነዚህ ፕሮጀክቶች መካከል ስካይ በርድ ፕሮግራም ይገኝበታል፡፡ በዚህ ፕሮጀክት የሚከናወኑ ተግባራት ምንድናቸው?

አቶ አበራ፡- ስካይ በርድ ፕሮጀክት በውኃ፣ በጤናና በሴቶች ላይ ትኩረት የሚያደርግ ነው፡፡ ከኦስትሪያ ቀይ መስቀልና ከኦስትሪያ ኤምባሲ በሚያገኘው የገንዘብ ድጋፍ በኢትዮጵያ፣ በዑጋንዳና በሩዋንዳ በመጪዎች አምስት ዓመታት ተግባራዊ የሚሆን ነው፡፡ አሁን ሊተገበር የታቀደው ስካይ በርድ ፕሮጀክት ሁለተኛው ምዕራፍ ሲሆን፣ የመጀመሪያው ምዕራፍ ባለፉት አምስት ዓመታት በቤኒሻንጉል ጉሙዝ፣ ኦሮሚያ አማራና ደቡብ ክልሎች ተግባራዊ ተደርጎ ጥሩ አፈጻጸም የተገኘበት ነው፡፡ በእነዚህ አካባቢ የሚኖሩ የማኅበረሰብ ክፍሎችንም በተለያዩ የማኅበራዊ ዘርፎች ተጠቃሚ ሆነዋል፡፡ የስካይ በርድ ምዕራፍ ሁለት የትግበራ ፕሮግራም በሲዳማ፣ በአርሲና በኢሉአባቡር ተግባራዊ የሚደረግ ነው፡፡ ይህም የሴቶችን የውኃና የንፅህና ችግር ለመቅረፍ ታሳቢ ያደረገ ነው፡፡ አብዛኞቹ የኢትዮጵያ ሴቶች በተለይም በገጠራማው የአገራችን ክፍሎች ንፁህ የመጠጥ ውኃ ለማግኘት የሚቸገሩ ናቸው፡፡ በመሆኑም የዚህ ፕሮጀክት ዓላማ ሴቶች በአቅራቢያቸው የውኃና መሠረታዊ የንፅህናና ሳኒቴሽን አገልግሎት እንዲያገኙ የሚያደርግ ነው፡፡ በተጨማሪም ፕሮጀክቱ ከውኃ፣ ከንፅህናና ሳኒቴሽን ባሻገር ድንገተኛ የሕክምና አገልግሎት/ኤመርጀንሲ ሜዲካል ሰርቪስ ላይ ትኩረት ያደርጋል፡፡ በስካይ በርድ ፕሮጀክት የመጀመሪያ ትግበራ ምዕራፍ ወደ 210 ሺሕ የሚጠጉ የማኅበረሰብ ክፍሎችን መድረስ ተችሏል፡፡ በመሆኑም ይህ የኅብረተሰቡን ችግር የቀረፈና ውጤት የተመዘገበበት ፕሮግራም መቀጠልና መስፋት እንዳለበት በመታመኑ፣ በቀጣዮቹ አምስት ዓመታት ሁለተኛው የትግበራ ምዕራፍ እንዲተገበር ሆኗል፡፡

ተዛማጅ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች ለማግኘት

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች


ተዛማጅ ፅሁፎች

ኤስ ኦ ኤስ እና ወርቅ ኢዮቤልዩ

ኤስኦኤስ የሕፃናት መንደሮች በኢትዮጵያ እ.ኤ.አ ከ1949 ዓ.ም. ጀምሮ የቤተሰብ እንክብካቤ ላጡ ሕፃናት ቤተሰባዊ አገልግሎት ሲሰጥ የቆየው የዓለም አቀፉ ኤስኦኤስ የሕፃናት መንደሮች ፌደሬሽን አካል ነው፡፡...

የግንባታ ኢንዱስትሪዎች የሚገናኙበት መድረክ

የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ በኢንቨስትመንት፣ በማኑፋክቸሪንግ፣ በኢንዱስትሪ ልማትና በኤክስፖርት የሚመራ ዕድገትን እንዲያስመዘግብ ታልሞ የተነደፈና በአብዛኛው በማደግ ላይ ባለው የግንባታው ዘርፍ ላይ ያተኮረ ነው፡፡ ይህ ዘርፍም ወደ...

ከጎዳና ከማንሳት ራስን እስከማስቻል የሚዘልቀው ድጋፍ

ጎዳና ተዳዳሪነትን ለማስቀረት መንግሥታዊና መንግሥታዊ ያልሆኑ ተቋማት ለዓመታት ሠርተዋል፡፡ ከችግሩ ስፋት አንፃር ሙሉ ለሙሉ መፍትሔ ባያገኝለትም፣ የጎዳና ተዳዳሪዎችን ለመለወጥ በሚሠሩ ሥራዎች ዕድሉን አግኝተው ራሳቸውን...