Sunday, May 19, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ማኅበራዊየልብ ሕሙማን ሕፃናት ተስፋ

የልብ ሕሙማን ሕፃናት ተስፋ

ቀን:

ገና በዘጠኝ ወር ዕድሜዋ ነበር ለስቃይና ለእንግልት የተዳረገችው፡፡ ዕድሜዋ በሽታን ለመቋቋም ቀርቶ በዳዴ ለመሄድ እንኳን የበቃ ባለመሆኑ ጫናውን የከፋ አድርጎታል፡፡ በዚህ ዕድሜዋ የበሽታ ገፈት ቀማሽ መሆኗ ለወላጆቿ ግራ መጋባትን ፈጥሯል፡፡

ሐፍዛ አጁሉ በዘጠኝ ወር ዕድሜዋ የልብ ክፍተት በሽታ ተጠቂ እንደነበረች እናቷ ወ/ሮ አምላ አብደላ ነግረውናል፡፡ ከልብ ክፍተት በተጨማሪ በቶንሲል፣ በጉንፋንና በሳንባ ምች በሽታዎች ስትጠቃ መቆየቷን የሚናገሩት እናቷ፣ ልጃቸውን ከእነዚህ በሽታዎች ለማትረፍ ያልረገጡበት ቦታ እንደሌለ ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡

እሳቸው ምንም ዓይነት ሥራ እንደማይሠሩና የባለቤታቸውን እጅ ጠብቀው እንደሚኖሩ የሚናገሩት እኚህ እናት፣ የኑሮ ውድነት፣ የቤት ኪራይ፣ የምግብ ወጪ ተሸፍኖ ለልጃቸው ሕክምና የሚውል ገንዘብ እንደሚያጡና አንዳንድ ጊዜም የሰው እጅ ለማየት ይገደዱ እንደነበር ያስታውሳሉ፡፡

- Advertisement -

የመጀመሪያ ልጃቸው በእንደዚህ ዓይነት በሽታ መያዟ ድንጋጤ ፈጥሮባቸው እንደነበር፣ በአሁኑ ወቅት ልጃቸው ኢትዮ ኢስታንቡል ጠቅላላ ሆስፒታል በፈጠረላቸው ዕድል በነፃ የቀዶ ሕክምና ማድረግ መቻሏን ይገልጻሉ፡፡

ከዚህ በፊት ጥቁር አንበሳ ሆስፒታል በመሄድ ክትትል ያደርጉ እንደነበር ያስታወቁት እኚህ እናት፣ ከጥቁር አንበሳ ወደ ኢትዮጵያ የልብ ማዕከል ሄዳ መታከም እንደምትችል ተነግሯቸው ወደዚያ ማምራታቸውን ተናግረዋል፡፡

የኢትዮጵያ የልብ ማዕከል፣ ሲሄዱ በርካታ ወረፋ እንዳለ እንደተነገራቸው፣ ማዕከሉ ለኢትዮ ኢስታምቡል በሰጠው መረጃ መሠረትም ወረፋ ከያዙ ከአራት ወራት በኋላ ስልክ ተደውሎላቸው ልጃቸውን በነፃ ማሳከም እንደሚችሉ እንደተነገራቸው ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

ከዚህ በፊት ልጃቸውን ለማሳከም ብዙ ውጣ ውረዶችን ማየታቸውን ጠቅሰው፣ ኢትዮ-ኢስታንቡል ጠቅላላ ሆስፒታል በፈጠረላቸው መልካም ዕድል አሁን ልጃቸው በሙሉ ጤንነት ላይ እንደምትገኝ አስረድተዋል፡፡ በአሁኑ ወቅት ልጃቸው አምስተኛ ዓመቷን መያዟን ያስታወሱት እኚህ እናት፣ ባለሀብቶች እንዲህ ዓይነት ችግሮችን በማየት የተለያዩ ድጋፎችን እንዲያደርጉ ተማፅነዋል፡፡

ከልጅነቷ ጀምሮ የልብ ክፍተት ተጠቂ የሆነችው ሌላዋ ሕፃን ፈርሃን ነስሩ ነች፡፡ ሕፃን ፈርሃን አምስት ዓመት እስኪሞላት ድረስ በበሽታው መያዟን እንደማያውቁ የተናገሩት ወላጅ እናቷ፣ በልጅነቷ የድካም ስሜትና ራስ ምታት ይታይባት እንደነበረ ገልጸዋል፡፡

በወቅቱ የተለያየ ቦታዎች በመሄድ ሕክምና ይከታተሉ እንደነበር ያስታወሱት ወላጅ እናቷ፣ በሽታው ከታወቀ በኋላ ከጅማ ሪፈር ተጽፎላት ወደ ጥቁር አንበሳ ሆስፒታል መላኳን ገልጸው፣ በሆስፒታሉም ለጥቂት ጊዜያት ሕክምናዎችን ከተከታተለች በኋላ በኢትዮጵያ የልብ ማዕከል ወረፋ እንድትይዝ መደረጉን ይናገራሉ፡፡

በሽታው ከታወቀ ጀምሮ ለምርመራ ብዙ ወጪ ማውጣታቸውን በማስታወስ፣ ኢትዮ ኢስታንቡል ሆስፒታል ባመቻቸላቸው ነፃ የሕክምና ዕድል በመጠቀም ልጃቸው የቀዶ ሕክምና ማድረግ መቻሏን ገልጸዋል፡፡ በልብ በሽታ በርካታ ሕፃናት እየተሰቃዩ ስለመሆናቸው መታዘባቸውን የተናገሩት እኚህ እናት፣ መንግሥት ችግሩን በመረዳት አፋጣኝ መፍትሔ መፍጠር ይኖርበታል ብለዋል፡፡

የኢትዮ ኢስታንቡል ጠቅላላ ሆስፒታል የአዋቂና የሕፃናት የልብና የደረት ቀዶ ሕክምና ለኅብረተሰቡ ከመስጠት ባሻገር፣ ማኅበራዊ ኃላፊነቱን ለመወጣት በዓመት ለ300 በልብ ሕመም ለሚሰቃዩ ሕፃናት ነፃ የቀዶ ሕክምና የሚሰጥ መሆኑን የሆስፒታሉ ባለቤትና ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ብርሃን ተድላ ተናግረዋል፡፡

በየዓመቱም 300 የልብ ችግር ያለባቸውን ሕፃናት በነፃ ለማከም አቅዶ እየሠራ መሆኑን ጠቅሰው፣ ባለፈው አንድ ወር ውስጥ ስድስት ሕፃናት ታክመው መዳናቸውን አስረድተዋል፡፡

በሕክምና ዘርፍ ውስጥ የተሰማሩ ባለሀብቶችም አቅማቸው በፈቀደ መጠን በተመሳሳይ በጎ ሥራ በመሳተፍ መንግሥትን ማገዝና የአገርን ችግር መፍታት እንደሚገባቸው አክለው ገልጸዋል፡፡

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ፣ የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ፕሬዚዳንት ሼህ ሐጂ ኢብራሂም ቱፋ፣ የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ ካርዲናል ብርሃነ ኢየሱስ ሱራፌል፣ የኢትዮጵያ የወንጌል አማኞች አብያተ ክርስቲያናት ጽሕፈት ቤት  ኃላፊ መጋቤ ጌትነት ለማና ሌሎች ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ሚያዝያ 5 ቀን 2016 ዓ.ም. የኢትዮ ኢስታንቡል ጠቅላላ ሆስፒታልን ጎብኝተዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

በሥጋ ላይ አላግባብ እየተጨመረ ያለውን ዋጋ መንግሥት ሊቆጣጠረው ይገባል

በአገራችን የግብይት ሥርዓት ውስጥ ኢኮኖሚያዊ ያልሆኑ ወይም ያልተገቡ የዋጋ...

ኢትዮጵያን የተባበረ ክንድ እንጂ የተናጠል ጥረት አይታደጋትም!

ኢትዮጵያ በአሁኑ ጊዜ ከምትገኝበት ውጥንቅጥ ውስጥ የምትወጣበት ዕድል ማግኘት...

የፖለቲካ ቅኝቱ የሕዝባችንን ታሪካዊ ትስስር ለምን አያከብርም?

በንጉሥ ወዳጅነው የዓብይ አህመድ (ዶ/ር) መራሹ የ2010 ዓ.ም. የለውጥ መንግሥት...

ዛሬም ኧረ በሕግ!

በገነት ዓለሙ በዚህ በያዝነው ሚያዝያ/ግንቦት ወይም ሜይ ወር ውስጥ የተከበረው፣...