Sunday, May 19, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

- Advertisement -

ፌርማታ ፅሁፎች

እኔኑ በላሁት

ትኩስ ፅሁፎች

አቦ ርቦኛል፡፡

ቤት ውስጥ የሚላስ የሚቀመስ የለም፡፡ ቅድም ትልቅ ፒዛ አስመጥቼ ቁራሽ ሳላስተርፍ አነከትኩት፡፡ ረሃቡ ግን አልተወኝም፡፡ የሆነ የሚበላ ነገር ፍለጋ ገባሁ፡፡ ምንም ላገኝ አልቻልሁም፡፡ የዳቦ ቁራጭ፣ የብስኩት ሽራፊ፣ የምንም ፍርፋሪ እንኳን የለም፡፡ የምግብ መደርደሪያውን ፈተሽሁ፣  ማቀዝቀዣውን በረበርሁ፣ ማድቤቱንም አተራመስሁ ወለሉ ላይ፣ ከምድጃው ጀርባ፣ … የወዳደቀ እንኳን የእህል ዘር የለም፡፡ ሌላ ቦታ መፈለግ አለብኝ፡፡

ይሄኔ ክብሬን አገኘሁት፣ ጎረስሁት፡፡ ለመግመጥም ሆነ ለማኘክ አስቸገረኝ፡፡ ስለዚህ እንዳለ ዋጥሁት፡፡ ይሄ የተረገመ ነገር ጉሮሮዬ ላይ ተወትፎ ሊገድለኝ ነበር፤ እንደምንም ገፍቼ ከጉሮሮዬ አወረድሁት፡፡ ግን ይሄም ረሃቤን ጋብ አላደረገልኝም፤ ተጨማሪ አሰኘኝ፣ ሌላ አስፈለገኝ፡፡

ከዚያ ኩራቴን ቀቀልሁት፡፡ በጎረስሁት ቁጥር ምሬቱ ይጨምራል፡፡ ሆዴ ግን ገና አምጣ እያለ ያጉረመርማል፡፡ ርህራሄዬን በጥብጬ ጨለጥሁት፡፡ አይ ጥፍጥናው! ይሄኛውስ በቀላሉ ወረደ፡፡

ፍቅር፡፡

የምን ፍቅር? እንዲህ ያለው ነገር በዚህ አገር ከታየ ስንት ዘመኑ፡፡ እሱን መፈለግ አቆምሁ፡፡ በምትኩ እንባዬን ተጎንጭቼ ይቅርታዬን አገሳሁ፡፡

ከዚያ ትንሽዬ ተስፋ አገኘሁ፡፡ የሰነበተ እና የሻገተ ስለሆነ አንዴ ገመጥ አደረግሁት፡፡ ልክ አልሠራሁም፣ መዋጥ አቃተኝ፡፡ ለተጨማሪ ምግብ ግን አሁንም ቦታ አለኝ፡፡

እምነት ትንሽ፣ ግን ደግሞ ጣፋጭ ነገር ነው፡፡ እንደ ጮማም፣ እንደ ፍራፍሬም፡፡

ይኸው ነው፡፡ ምንም አልተረፈኝም፡፡ ሁሉንም ጠራርጌ ስለበላሁ ከአልጋ መውረድ እንኳን ተሳነኝ፤ ክብደቴ እጥፍ በእጥፍ ጨምሯላ! ይሁን የትም መሔድ አያስፈልገኝም፡፡ ለጊዜው አልተራብሁም፡፡ 

… ነገ ግን ሁሉም ነገር እንዳዲስ ይጀመራል፡፡

– በኦገስት ሬሚየር፣   ተርጓሚ – ቴዎድሮስ አጥላው

- Advertisement -
- Advertisement -

ተጨማሪ ለማንበብ

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች