Sunday, May 19, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

እንስተካከል!

ሰላም! ሰላም! ውድ ኢትዮጵያውያን ወገኖቼ እንዲሁም የሰው ዘር በሙሉ፣ ከሰብዓዊ ፍጡራንም አልፎ እንስሳትና አዕዋፋት፣ በተጨማረም ዕፅዋትና ሌሎች ፍጡሮች በሙሉ ባላችሁበት ሰላም ሁኑ፡፡ እኛ የአምላክ ፍጡራን በተሰጠን ዕድሜ ሰላማዊ ሆነን የሕይወት መንገድን ስናቀና፣ ተፈጥሮም ሚዛናዊ ሆና እንደምትቀጥል የሚነግረኝ ምሁሩ የባሻዬ ልጅ ነው፡፡ በተለይ የሰው ልጅ በሁሉም ፍጡራን ላይ የበላይ ሆኖ እንዲገኝ በአምላክ አምሳል በመፈጠሩ፣ ከማንም በላይ ለሰላምና ለመልካም የሕይወት ዕርምጃ አርዓያ ሆኖ መገኘት እንዳለበት ይኸው ምሁሩ ወዳጄ ደጋግሞ ስለሚነግረኝ እኔም ሰላም እመኝላችኋለሁ፡፡ በቀደም ዕለት ምን ሆነ መሰላችሁ? እስቲ ፈርሳ እንደ አዲስ ልትሠራ ነው የተባለችውን የጥንቷን አራዳ የአሁኗን ፒያሳ ልቃኛት ብዬ መሄድ፡፡ መለስ ቀለስ እያለ የሚያስፈራራውን ዝናብ እየታገልጉ ፒያሳ ስደርስ፣ አንዱን የጥንት ደላላ ወዳጄን አገኘሁት፡፡ ‹‹ወንድሜ እንዴት ነህ ከፒያሳ መፍረስ በኋላ…›› ስለው፣ ‹‹አንበርብር መጀመሪያ ፈርቼ ነበረ፣ ነገር ግን አዲሱን መኖሪያዬን መልመድ ስጀምር ያለፈው መራራ ሕይወቴ ሰላም እንዳልነበረው መገንዘብ ጀመርኩ…›› ሲለኝ በእጅጉ ደነቀኝ፡፡ ያልጠበቅኩት ነበራ!

ይኼ ደላላ ወዳጄ ሠራተኛ ሠፈር ተወልዶ፣ እዚያው አድጎና ተድሮ፣ እዚያው ቤተሰብ መሥርቶ ልጆቹን እያሳደገ የነበረ መሆኑን ስለማውቅ፣ ‹‹እስቲ በደንብ አብራራልኝ…›› ብዬው ዝርዝሩን ለማወቅ ተመቻቸሁ፡፡ ‹‹ወንድሜ አንበርብር እኔ እዚህ የፈረሰ ሠፈር ውስጥ የተጣበበች ጎጆ ውስጥ ነው የተወለድኩት፡፡ አባቴና እናቴ በየተራ ከዚህ ዓለም ከተለዩ በኋላ የሠፈሬን የእኔ ቢጤ ኮረዳ አግብቼ ሦስት ልጆች ወልጄ ነበር ስኖር የነበረው፡፡ አሁን ግን ምን የመሰለ ባለሁለት ክፍል ኮንዶሚኒየም ከመታጠቢያ ቤትና ከኩሽና ጋር ተሟልቶልን ሲሰጠን ያለፈ ሕይወቴ የባከነ እንደነበር አሁን ገባኝ፡፡ ሞራሉ የደቀቀ ሠፈር ውስጥ አጉል አራዳ ሆነን ያገኘነውን እየበላንና እየጠጣን መኖር ኑሮ አለመሆኑን የተገነዘብኩት አሁን ነው፡፡ ሥራ ቢቀዘቅዝም ዕድሜ ለድሮ ወዳጆቼ አንዳንድ ሥራ እየለቀቁልኝ እንደ ሰው መኖር ጀምሬያለሁ፡፡ የከተማው አስተዳደርም በመሬት ጉዳይ ላይ ጥሎት የነበረውን ዕግድ በማንሳቱ ደግሞ መነቃቃት ይጀመራል ብዬ ተስፋ አድርጌ ይኸው የደንበኞችን ጥሪ እየተጠባበቅኩ ነው…›› ሲለኝ የእሱ ደስታ እኔም ዘንድ ተጋብቶ ፊቴ ፈካ፡፡ ደስ ሲል!

በነገራችን ላይ ለምን እንደሆነ ባላውቅም ሰዎች ደስ ሲላቸው እኔም ደስ ይለኛል፡፡ ምሁሩ የባሻዬ ልጅ፣ ‹‹አንበርብር በሰዎች ደስታ እኛም ተደሳች ስንሆን ሰላም ይከበናል፡፡ ለምሳሌ አንድ ጎረቤትህ አልፎለት ቤቱን ሲያሳምር ሄደህ ምን ላግዝህ በለው፡፡ እውነቴን ነው የምልህ እሱ ውስጥ የምታየው ደስታ አንተም ውስጥ ይጋባል፡፡ የቆርቆሮ አጥሩን ወደ ግንብ ለመቀየር ሲያስብ አንተ መልቀቅ ስላለበት ሃምሳ ሳንቲ ሜትር መሬት ከምታስብ ይልቅ፣ አንተ አቅም ባይኖርህ በጉልበት ለማገዝ ፈቃደኝነትህን ብታሳየው የእሱ ግንብ ለአንተ ሰርቪስ ቤቶች ግድግዳ እንደሚሆን ብትረዳ ጥቅሙ የጋራ ነው…›› የሚለኝ ምን ያህል ውስጣዊ ሰላም እንደሚፈጥር ለመረዳት ኮሌጅ መበጠስ አይገባኝም ነበር፡፡ ‹‹እኛ እኮ ከመሬት ጋር ያለን ቁርኝት እርስ በርስ ሰላም እንደሚነሳን ለማየት ሩቅ መሄድ የለብንም፡፡ አጥር ሲታጠር የመሬት መስፋትና መጥበብ የሚፈጥርብን ክፋት እያስተናነቀን፣ አንድ አገር ውስጥ እየኖርን የእንትን አካባቢ እንትና ዘንድ እንጂ እንቶኔ ጋ መጠቃለል የለበትም እያልን ስንተላለቅ የጠላት መሳቂያና መሳለቂያ መሆናችን ያሳዝናል…›› ሲለኝ ውስጤ ይቃጠላል፡፡ እህህህ…!

ከፒያሳው ደላላ ወዳጄ ብሶትና ቁጣ ስጠብቅ አዲስ ሕይወትና ተስፋ በመስማቴ እየተገረምኩ ተሰነባብተን ስንለያይ፣ ወዲያው የስልኬ የማንቂያ ደወል መጮህ ሲጀምር ከኪሴ አውጥቼ በሰላምታ የታጀበ ምላሽ ሰጠሁ፡፡ የደወሉልኝ በጣም የማከብራቸው ደንበኛዬ ናቸው፡፡ በጥብቅ እንደሚፈልጉኝ ነግረውኝ ወደ ቢሮአቸው ከነፍኩ፡፡ ቦሌ ዋናው መንገድ ላይ ከሚገኘው እጅግ በጣም ዘመናዊ፣ ውብና ፅዱ ሕንፃቸው ደርሼ ዝንጥ ባለ አስተናጋጅ መሪነት ከቢሮአቸው ሳልዘገይ ተገኘሁ፡፡ ሞቅ ያለ ሰላምታ ሰጥተውኝ፣ ‹‹አቶ አንበርብር በል ቀልጠፍ ብለህ እዚሁ ቦሌ ዙረያ እስከ አንድ ሺሕ ካሬ ሜትር ይዞታ ፈልግልኝ፡፡ ያው እንደሰማኸው በቀደም ዕለት የከተማው አስተዳደር የጣለውን የመሬትና መሬት ነክ ይዞታ ዕግድ አንስቷል፡፡ አንድ ልጄ ለተለያዩ አገልግሎቶች የሚውል ዘመናዊ ሕንፃ ስለሚገነባ በአዲሱ መመርያ መሠረት ከመንገድ ገባ ያለ እንዲሆን አደራ…›› ሲሉኝ፣ ሀብታምና መንግሥት ምን ያህል እየተናበቡ ሥራቸውን እንደሚያከናውኑ ከድሮ ልምዴ ያገኘሁት ትውስታ በአዕምሮዬ ተመላለሰ፡፡ እኔ ምለው ሀብታምና መንግሥት እንዲህ ሲናበቡ እኛ ምን ነክቶን ነው ደማችን የሚንተከተው እያልኩ ነበር፡፡ ያሰኛል!

ምሁሩ የባሻዬ ልጅ መቼም ለዚህ መልስ አያጣምና ጉዳዩን ሳነሳለት፣ ‹‹በአንድ በኩል ለእዚህ ችግር ተጠያቂው መንግሥት ነው፡፡ ያሰበውን ነገር ለመፈጸም ሲል ደሃ እንዴት ይሆናል ብሎ ከመጨነቅ ይልቅ፣ እኔ ያዘዝኩትን የመፈጸም ግዴታ ስላለበት የመጣው ይምጣ ብሎ ያሻውን ያደርጋል፡፡ ይህን ጊዜ ፖለቲከኞችና አክቲቪስቶች የምትላቸው የእኛን ስሜት የሚያጋግል አጀንዳ ይዘው ብቅ ይሉና ደማችን እንዲፈላ ያደርጋሉ፡፡ በዚህ ጊዜ ከመንግሥት ጋር እንላተምና የምታየው ዓይነት ችግር ይፈጠራል፡፡ ሀብታም ግን ሞልቶ ከሚተርፈው በረከት ለመቌደስ ሲል ከመንግሥት ጋር መጣላት አይፈልግም፡፡ ይልቁንም ከበረከቱ ድርሻውን ለማንሳት ሲል ተፎካካሪዎቹን መጣል ስላለበት በተለይ ለአክቲቪስቶች ዳረጎት እየሰጠ ትርምስ ይፈጥራል፡፡ ፊት ለፊት ወጥቶ በሰላ አንደበት ለአገር ልማት እየዘመረ ከጀርባ ግን ጦርነት ሳይቀር ፋይናንስ ያደርጋል፡፡ መንግሥት ሲጠራው ደግሞ ሚሊዮን ብሮችን የታቀፈ ቼክ ይዞ ይገኛል፡፡ እንደ እኔና አንተ ዓይነቱ የዋሃን ግን በፖለቲከኞችና በአክቲቪስቶች እየተነዳንና እየተላተምን ከሕይወት ዕጦት እስከ ኑሮ መናጋት ድረስ መከራ እንበላለን…›› እያለ ሲያብራራልኝ ውስጤ በፍርኃት ራደ፡፡ ወቸ ጉድ!

መቼ ዕለት ነው በጊዜ ቤቴ ገብቼ እራት በላልቼ ቴሌቪዥኑ ላይ ሳፈጥ ድንገት አንድ ንግግር ጆሮዬን ሳበው፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በገንዘብ ሚኒስትር ደኤታው ጥያቄ እየቀረበላቸው ስለዲጂታል ኢኮኖሚ ማብራሪያ እየሰጡ ነበር፡፡ እኔ መቼም ከሁለተኛ ደረጃ የዘለለ ትምህርት ስለሌለኝ እንዲህ ረቀቅ ያለ ትንተና ሲሰጥ ለማወቅ ስለምፈልግ በአንክሮ አዳምጣለሁ፡፡ ለዚህ ዋናው ተፅዕኖ ፈጣሪው ምሁሩ የባሻዬ ልጅ ነው፡፡ እሱ አዕምሮዬን እየወቀረልኝ ሌላው ቢቀር የሚባለውን ለማዳመጥ የሚያስችል ማስተዋል አዳብሮልኛል፡፡ እናም ጠቅላይ ሚኒስትሩ የፒያሳን ጉዳይ ድንገት በምሳሌነት አነሱ፡፡ በፒያሳ ጉዳይ በርካታ ወቀሳዎች እንዳሉ ተናግረው ደፈር ብሎ ዕርምጃ ካልተወሰደ አሮጌ ነገር ታቅፎ መዝለቅ እንደማይቻል አስረዱ፡፡ ፒያሳ ውስጥ ይኖሩ የነበሩ ሰዎች እጅግ በጣም በሚያሳዝን ሁኔታ ይኖሩ እንደነበር፣ አሁን ግን ከበፊቱ የተሻለ መኖሪያና መሥሪያ እያገኙ መሆናቸውን አከሉ፡፡ ስለፒያሳ መፍረስ ወቀሳ የሚያቀርቡ ግን እዚያ እንደማይኖሩ ይልቁንም እንደ ሲሲዲ የመሳሰሉ ውብ መኖሪያቸው፣ ውስጥ ሆነው፣ እነሱ የማይኖሩትን ሌሎች እየማቀቁበት እንዲቀጥሉ ማሰባቸው እንደሚያስገርም ነበር የተናገሩት፡፡ ቃል በቃል ባይሆንም ሐሳቡ ይህ ነበር፡፡ የዚያ ወዳጄ ስሜት እዚህ የገጠመ መሰለኝ!

አንዱ በቀደም ዕለት ቀጥሮኝ የሚከራይ ቢሮ ላሳየው ወደ ሩዋንዳ አካባቢ እንሄዳለን፡፡ እሱ የሚኖረው ሰሚት ዘመናዊ መንደር ውስጥ ሲሆን፣ አንደኛው ቢሮው ቦሌ መድኃኔዓለም ነው፡፡ ይኸኛው የሚከራየው ቢሮ ግን ተጨማሪ ነው፡፡ ‹‹አንበርብር እነዚህ ሰዎች ፒያሳን አፍርሰው ሲያጠፉ እንዴት ዝም ይባላል…›› እያለ የዘመናዊ ቱሶን መኪናውን መሪ በቡጢ ሲደልቅ፣ ‹‹ወዳጄ እባክህ የማትኖሩበትን አካባቢ ለምን ፈረሰ እያላችሁ አታላዝኑ ተብሏል እኮ…›› አልኩት፡፡ ‹‹ማን ነው ያለው እባክህ…›› ብሎ ሲያፈጥብኝ፣ ‹‹ተረጋጋ እባክህ ጠቅላይ ሚኒስትሩ  ናቸው ያሉት…›› ከማለቴ፣ ‹‹ወይ እኔ መቼ ነው እባክህ እንዲህ ያሉት…›› ዓይን ዓይኔን ሲያየኝ፣ ‹‹በወዲያኛው ሳምንት በዲጂታል ኢኮኖሚ ውይይት ላይ ነው…›› እያልኩ ሳስረዳው፣ ‹‹አንተ እኔ እኮ አልሰማሁም ተቆጡ እንዴ…›› እያለ ተርበተበተ፡፡ ወይ የሀብታም ነገር እንዲህ ጭብጥ ለማከል ነው እንዴ ያ ሁሉ ድንፋታ እያልኩ በሆዴ፣ ‹‹እሳቸውስ አልተቆጡም፣ ከአነጋገራቸው የተረዳሁት ግን አዛኝ ቅቤ አንጓች አትሁኑ ያሉ መሰለኝ…›› ብዬው ዝም አሰኘሁት፡፡ ነገርኳችሁ እኮ ሀብት ያደረጁ በአጭሩ እኛ ደግሞ በረጅሙ እያበራን እኮ ነው የምንሸዋወደው፡፡ እየተናበብን!

የኩዳዴ ፆምን በከፍተኛ ተመስጦ እየፆሙ የሚገኙት አዛውንቱ ባሻዬ በአንድ ወቅት የነገሩኝ ነገር አይረሳኝም፡፡ በአንድ መንደር ውስጥ የሚኖሩ ሰዎች በአካባቢው ገዥ እየተጨቆኑ ይኖሩ ነበር፡፡ ገዥው በነዋሪዎቹ ላይ የሚያደርሱት እንግልት አልበቃ ብሏቸው አንድ ቀን ከደኑ ውስጥ ጎረምሳ ዝሆን እያስነዱ ያስመጣሉ፡፡ ለነዋሪዎቹም ዝሆኑን እንዲመግቡና እንዲንከባከቡ ቀጭን ትዕዛዝ ይሰጣሉ፡፡ ጎረምሳው ዝሆን መንደሩ ውስጥ እንደ ልቡ እየተዘዋወረ የነዋሪዎቹን እርሻ፣ መኖሪያቸውን፣ ጎተራቸውን፣ አጥራቸውንና መገልገያዎቻቸውን እያተረማመሰ ከባድ ጉዳት አደረሰ፡፡ በዚህ ድርጊት የተማረሩ ነዋሪዎች ተሰባስበው ይመካከሩና ዝሆኑ ወደ ደኑ እንዲመለስ እንዲደረግ ለገዥው በሰላማዊ ሠልፍ ለማሳወቅ ይስማማሉ፡፡ መፈክሮች አዘጋጅተው ‹ዝሆኑ ወደ ደኑ ይመለስ..› እያሉ ወደ ገዥው ቤት ይሄዳሉ፡፡ ገዥው ከሩቅ በመፈክር ታጅቦ ወደ እሳቸው የሚመጣውን ሠልፈኛ ከሩቅ ሲመለከቱ፣ አጃቢዎቻቸውን መሣሪያ አስይዘው መጠባበቅ ይጀምራሉ፡፡ መፈክር የሚያሰማው ‹ዝሆኑ› ሲል ተቀባዮች ‹ወደ ደኑ ይመለስ› እያሉ ሲቃረቡ ድምፃቸው መቀነስ ይጀምራል፡፡ የተቀባበሉ መሣሪያዎች አነጣጥረዋላ፡፡ ሰውየው ‹ዝሆኑ› ሲል ጭራሽ ዝምታ ሰፈነ…›› ብለው ባሻዬ በሳቅ ንግግራቸውን አቌረጡ፡፡ ያስፈራላ!

‹‹…መፈክር የሚያሰማው እየደጋገመ ‹ዝሆኑ…› ቢልም ሠልፈኞቹ በዝምታ እንደተሸበቡ ገዥው ዘንድ ይደርሳሉ፡፡ ይህን ጊዜ ገዥው በንዴት ውስጥ ሆኖ ‹ዝሆኑ ምን…› እያለ ሲያፈጥና ጋሻ ጃግሬዎቹ ጠመንጃዎቻቸውን ሲያነጣጥሩ አንድ አዛውንት ከሠልፈኞቹ መሀል ወደፊት ወጣ ብለው ‹ጌታዬ ዝሆኑ…› ማለት ሲጀምሩ፣ ገዥው ከቅድሙ በባሰ ንዴት ውስጥ ሆኖ ‹ዝሆኑ ምን…› ብሎ ሲያፈጥባቸው የደነገጡት አዛውንት ‹ጌታዬ ዝሆኑ ብቸኝነት ስላጠቃው ሚስት እንዲያስመጡለት ነው…› ብለው ሲናገሩ፣ ‹እንዲያ ከሆነ ጥያቄያችሁ በቅርቡ ሚስት እናጋባዋለን፣ እናንተም ሁለቱን በትጋት ተንከባከቡ…› ብለው ሠልፉ ተበተነ…›› ብለው ባሻዬ እንደገና ሳቁ፡፡ ባሻዬ ያኔ እንደነገሩኝ ነዋሪዎቹና ገዥው በዚህ ደረጃ የተፈራሩት ጉልበት የመተዳደሪያ ሕግ በመሆኑ ነው፡፡ ምሁሩ ልጃቸውም፣ ‹‹አንበርብር ገዥና ሕዝብ በመሀላቸው መተማመን ከሌለ አባዬ እንዳለው የብሶት ጥያቄ ይዘህ ቀርበህ የሚጠብቅህ መልስ አራንባና ቆቦ ይሆናል፡፡ ድጋፍህ የውሸት ተቃውሞህ የክፋት ተደርጎ ሥቃይህን ስትበላ ትኖራለህ…›› ብሎኝ ነበር፡፡ መንግሥት ለሕዝብ፣ ሕዝብ ደግሞ ለመንግሥት አሳቢ ሆነው በሰላም የሚኖርበት ጊዜ ቢኖረን እላለሁ፡፡ ምኞት አይከለከል!

እስኪ እንሰነባበት፡፡ እዚህም እዚያም እየረገጥኩና ከተማውን እያካለልኩ እንጀራዬን ሳሳድድ ያን ያህል ጠብ የሚል ነገር አልነበረም፡፡ እኚያ ደንበኛዬ ከሰጡኝ የቅድመ ኮሚሽን ክፍያ ላይ ለውዴ ማንጠግቦሽ የሚገባትን ሰጥቼ ከላዩ ላይ ለቢራ ቀንሼ፣ ከምሁሩ የባሻዬ ልጅ ጋር ቀጠሮ ተሰጣጥተን ስለነበር ግሮሰሪ ተሰይመናል፡፡ ግሮሰሪያችን ከወር እስከ ወር በደንበኞች ስለምትጨናነቅ የደንበኞች የኑሮ ሁኔታን ለመረዳት አያዳግትም፡፡ ዳኞች፣ ጠበቆች፣ ዓቃቢያነ ሕግ፣ ነጋዴዎች፣ መምህራን፣ የመንግሥትና የግል ድርጅት ተቀጣሪዎች፣ ካድሬዎች፣ ወዘተ በየዓይነቱ ስለሚታደሙ ግሮሰሪያችን ሁሌም ሙሉ ናት፡፡ የወር ደመወዝ ጠባቂዎች ብቻ ሳይሆኑ የዕለት ገቢ ባለቤቶች ብዙ ስለሆኑ ግሮሰሪያችን ድምቅ እንዳለች ነው፡፡ ምሁሩ የባሻዬ ልጅ፣ ‹‹የፍቅር እስከ መቃብር መጽሐፍ ዋና ገጸ ባህሪ ፊታውራሪ መሸሻ ‹ባላገር የሚበላው ቢያጣ የሚከፍለው አያጣም…› ያሉት የያኔዎቹን ብቻ ሳይሆን የእዚህ ዘመን ሰዎችንም ይመለከታል…›› እያለኝ ቢራችንን ስናወራርድ በውስጤ ይመላለስ የነበረው፣ ከበፊት ጀምሮ እስካሁን ድረስ እያለፍንበት ያለው የሕይወት ሰበዝ ነው፡፡ ለዚህም ነው መሰል ከላይ እስከ ታች እንስተካከል የምለው፡፡ መልካም ሰንበት!

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት