Sunday, May 19, 2024
- Advertisment -
- Advertisment -

የማፍረስ ዘመቻው በብልሹ አሠራሮች ላይም ይቀጥል!

መንግሥት በኮሪደር ልማት አማካይነት የአዲስ አበባ ከተማን ዋና ዋና ሥፍራዎች በማፍረስ፣ አዲስ አበባን ከኬፕታውን ቀጥሎ ተመራጭ የአፍሪካ ከተማ ለማድረግ መጠነ ሰፊ ሥራ ከጀመረ ሰነባብቷል፡፡ በመንግሥት ዕቅድ መሠረት አዲስ አበባን እንደ ስሟ ውብ ለማድረግ የከተማዋ ጭርንቁስ አካባቢዎች ፈርሰው፣ በምትካቸው እጅግ ዘመናዊ ግንባታዎች ለማካሄድ ቀንና ሌሊት እየተሠራ ነው፡፡ በኮሪደር ልማቱ የተጀመረው ግዙፍ የማፍረስ ዘመቻ በብልሹ አሠራሮች ላይም ተጣጡፎ መቀጠል አለበት፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ፈርሰው እንደገና መሠራት ያለባቸው በርካታ ብልሹ አሠራሮች አሉ፡፡ የመጀመሪያው መንግሥታዊ መዋቅር ውስጥ ተንሰራፍቶ የመሸገው ሙስና ሲሆን፣ ሁለተኛው ደግሞ በጥቂቶች ቁጥጥር ሥር ውሎ ሸማቾችን አሳር የሚያበላው ኋላቀር የግብይት ሥርዓት ነው፡፡ ሌሎች ተዛማጅ ብልሹ አሠራሮች እንዳሉ ሆነው እነዚህ ግን ጊዜ ሊሰጣቸው የማይገቡ ናቸው፡፡ መንግሥት በኮሪደር ልማቱ የጀመረው መጠነ ሰፊ የማፍረስ ዘመቻ፣ በሁለቱ ላይ በፍጥነት መጀመር ይኖርበታል፡፡

ልማት የመላው ሕዝብ ተሳትፎ ውጤት በመሆኑ ሕዝቡ ውስጥ የሚባሉ ነገሮችን በቅጡ ማዳመጥ ያስፈልጋል፡፡ በፌዴራልም ሆነ በክልሎች ደረጃ የመንግሥትን በጀት እንዳሻቸው የሚጫወቱበት፣ ተገልጋዮችን ጉቦ ካልተቀበሉ ለማስተናገድ ፈቃደኛ ያልሆኑ፣ በመደበኛ የሥራ ሰዓት በስብሰባ ሰበብ የግል ጉዳያቸውን እያከናወኑ ተገልጋዮችን የሚያስመርሩ፣ ሕዝብ ለማገልገል የተሰጠ ኃላፊነትን ለግል ጥቅም የሚያውሉና በሥልጣን በመባለግ ሕገወጥ ድርጊቶችን የሚፈጽሙ ሹማምንት ተቆጣጣሪ የሌላቸው ይመስል አገር እየበደሉ ነው፡፡ ኃላፊነት ከማይሰማቸው ባለሀብቶች ጋር በመመሳጠር አገር የሚገባትን ጥቅም የሚያሳጡ፣ መንግሥታዊ ተቋማትን እንደ ራሳቸው ኪዮስክ የሚቆጥሩ፣ ቅንና ሀቀኛ ሠራተኞችን የሚያሸማቅቁ፣ ተቋማት ውስጥ የሌብነት ኔትወርክ የሚያደራጁና ለሕግና ለሥርዓት ተገዥ መሆን የማይፈልጉ ሕገወጦች በብዛት አሉ፡፡ መንግሥታዊ ተቋማት ከእንዲህ ዓይነቶቹ ሳይፀዱ ቁሳዊ ነገሮችን ለመለወጥ የሚደረገው ጥረት ሊሳካ አይችልም፡፡

ሕዝብ ከሚመረርባቸው ጉዳዮች መካከል አንዱ የግብይት ሥርዓቱ ነው፡፡ የግብይት ሥርዓቱ እጅግ በጣም ኋላቀር ከመሆኑ የተነሳ የመሠረታዊ ምግቦችም ሆነ የሌሎች ሸቀጦች አቅርቦት መስተጓጎል፣ ሰው ሠራሽ የዋጋ ንረት፣ የምርቶች ድበቃ፣ በአድማ ዋጋ መወሰንና ገበያውን በጥቂቶች ቁጥጥር ሥር ማዋል የመሳሰሉ ሕገወጥ ድርጊቶች በስፋት ይስተዋላሉ፡፡ የግብይት ሥርዓቱ መንግሥትን፣ ነጋዴዎችንና ሸማቾችን እንዲናበቡ እያደረገ በሥርዓት መመራት ሲገባው፣ መንግሥት መዋቅር ውስጥ በተሰገሰጉ ሴረኞች ምክንያት ሕዝብ ያለ ጥፋቱ ይቀጣል፡፡ መንግሥት ገበያው ውስጥ በቀጥታ ጣልቃ ገብቶ ዋጋ መወሰን እንደማይኖርበት የታወቀ ነው፡፡ ነገር ግን ገበያው ጤናማ ሆኖ በሥርዓት እየተከናወነ መሆኑን ቁጥጥር ማድረግ አለበት፡፡ በስመ ነፃ ገበያ ጥቂቶች ገበያውን ተቆጣጥረው ምስቅልቅሉን ሲያወጡት፣ መንግሥት ጉያ ውስጥ የተደበቁ ሌቦች ሽፋን ሰጪ መሆናቸው ይታወቃል፡፡

የግብይት ሥርዓቱ ጤናማና ሁሉን አሳታፊ መሆን ሲገባው መንግሥት ጥጉን እንዲይዝና ሸማቾች ደግሞ አቅም እንዲያጡ ሲደረግ፣ ሥነ ምግባር የጎደላቸው ነጋዴዎችና የጥቅም ሸሪኮቻቸው እንደፈለጉ እንዲሆኑ ተመቻችቶላቸዋል፡፡ በዚህ ምክንያት በፀጥታ ችግር እየደረሰ ካለው የምርቶች አቅርቦት እጥረት ባሻገር፣ ገበያው ውስጥ የገባውን ምርት በሥርዓት ለሸማቾች ለማድረስ አልተቻለም፡፡ በአንድ ቀን ውስጥ ማለትም ጠዋትና ማታ ምክንያት አልባ የዋጋ ጭማሪ ሲደረግ፣ ለምን ብሎ የሚቆጣጠር የሚመለከተው አካል ባለመኖሩ ገበያው በሕገወጦች ተወሯል፡፡ የግብይት ሥርዓቱ ውስጥ ከሚስተዋሉ በርካታ ችግሮች መካከል አንዱ የዋጋ ጉዳይ ነው፡፡ ዋጋ በጥቂቶች በአድማ ስለሚወሰን ሸማቾች የሕገወጦች ታጋች ሆነዋል፡፡ መንግሥት በተደጋጋሚ የትርፍ ህዳግ ተግባራዊ እንዲያደርግ ቢነገረው ሰሚ የለም፡፡ ለዚህ ዋነኛ ችግሩ መንግሥት መዋቅር ውስጥ የተሰገሰጉ ጥቅም አሳዳጆች ናቸው፡፡

ሰሞኑን እንደተነገረው በጅምላና በችርቻሮ ንግድ ውስጥ የውጭ ኩባንያዎች ሲገቡ ችግሩ እንደሚቀረፍ ተስፋ ቢደረግም፣ አሁን በሥራ ላይ ያለው የግብይት ሥርዓት ግን እንደገና ፈርሶ መሠራት አለበት፡፡ ምክንያቱ ደግሞ ጤናማ ውድድር የማይደረግበት፣ በአድማ ዋጋ የሚወሰንበት፣ ከአምራቾች እስከ በላተኛው ድረስ ያለው የአቅርቦት ሰንሰለት በጥቂቶች የታገተበትና በአጠቃላይ ሲታይ ሕገወጦች የበላይነቱን የያዙበት ነው ማለት ይቻላል፡፡ ከላይ ከተጠቀሱት የክፋት ድርጊቶች በተጨማሪ ለጤና ጠንቅ የሆኑ ባዕድ ነገሮች በብዛት ምግቦች ውስጥ መቀላቀል፣ ጊዜ ያለፈባቸው ምግቦችና መድኃኒቶችን መሸጥ፣ ጥራታቸው የተጓደሉ ምርቶችን በገፍ ገበያው ውስጥ ማሠራጨት፣ በሚዛን ማጭበርበርና የመሳሰሉት ይጠቀሳሉ፡፡ እንዲህ ዓይነቱን ብልሹ የግብይት ሥርዓት ታቅፎ መቀጠል ስለማይቻል በፍጥነት የውጭ ተወዳዳሪዎችን ማስገባት የሚደገፍ ተግባር ነው፡፡ ከሥር መሠረቱ መንግሎ በመጣል ሸማቹን ሕዝብ ነፃ ማውጣት ያስፈልጋል፡፡

የብልሹ አሠራሮች መገለጫ ከሆኑት ሌሎች ተጠቃሾች ውስጥ የዜጎች መብት መጣስ ይገኝበታል፡፡ ዜጎች በሕግ የተጎናፀፉትን መብት በሕገወጥ መንገድ በመግፈፍ የሚያሰቃዩ፣ የዜጎችን ክብር የሚዳፈሩ፣ ፍትሕ የሚነፍጉ፣ ራሳቸውን ከሕግ በላይ የሚያደርጉና የተሰጣቸውን ሥልጣን የሚባልጉበት ለብልሹ አሠራሮች መንሰራፋት ዋነኞቹ ምክንያት ናቸው፡፡ የብልሹ አሠራሮች መንሰራፋት ጉዳይ እንደ ቀልድ ሊታይ አይገባም፡፡ አዲስ አበባ ከተማ ፈርሳ እንደምትሠራው ብልሹ አሠራሮች መፍረስ አለባቸው፡፡ በብልሹ አሠራሮች ምክንያት ዜጎች ፍትሕ እንደ ሸቀጥ በገንዘብ እንዲገዙ ተገደዋል፡፡ በብልሹ አሠራሮች ምክንያት ብዙዎቹ መንግሥታዊ ተቋማት መደበኛ ሥራቸውን ማከናወን እያቃታቸው ነው፡፡ ብልሹ አሠራሮች ተቋማትን ከማዳከም አልፈው አገርን እየጎዱ ነው፡፡ በሀቅና በቅንነት አገራቸውን ለማገልገል የሚፈልጉ ዜጎችን ተስፋ እያስቆረጡ ነው፡፡ ብልሹ አሠራሮች በተንሰራፉባቸው ቦታዎች ሌብነትና ብቃት አልባነት ብቻ ናቸው ገነው የሚታዩት፡፡ ስለዚህ የማፍረስ ዘመቻው በብልሹ አሠራሮች ላይም ተጠናክሮ ይቀጥል!    

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች

በሥጋ ላይ አላግባብ እየተጨመረ ያለውን ዋጋ መንግሥት ሊቆጣጠረው ይገባል

በአገራችን የግብይት ሥርዓት ውስጥ ኢኮኖሚያዊ ያልሆኑ ወይም ያልተገቡ የዋጋ...

ኢትዮጵያን የተባበረ ክንድ እንጂ የተናጠል ጥረት አይታደጋትም!

ኢትዮጵያ በአሁኑ ጊዜ ከምትገኝበት ውጥንቅጥ ውስጥ የምትወጣበት ዕድል ማግኘት...

የፖለቲካ ቅኝቱ የሕዝባችንን ታሪካዊ ትስስር ለምን አያከብርም?

በንጉሥ ወዳጅነው የዓብይ አህመድ (ዶ/ር) መራሹ የ2010 ዓ.ም. የለውጥ መንግሥት...

ዛሬም ኧረ በሕግ!

በገነት ዓለሙ በዚህ በያዝነው ሚያዝያ/ግንቦት ወይም ሜይ ወር ውስጥ የተከበረው፣...

በስድስተኛው ዙር ጠቅላላና ድጋሚ ምርጫ የሚሳተፉ ፓርቲዎች በገዥው ፓርቲ ላይ ተቃውሞ እያቀረቡ ነው

በ2013 ዓ.ም. ስድስተኛው ምርጫ ባልተካሄደባቸው ክልሎች በጠቅላላና በድጋሚ ምርጫ...
spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

ኢትዮጵያን የተባበረ ክንድ እንጂ የተናጠል ጥረት አይታደጋትም!

ኢትዮጵያ በአሁኑ ጊዜ ከምትገኝበት ውጥንቅጥ ውስጥ የምትወጣበት ዕድል ማግኘት ብትችል፣ ከበርካታ ታዳጊ አገሮች የተሻለ በዕድገት ጎዳና የመገስገስ እምቅ አቅም እንዳላት የሚያጠራጥር አይደለም፡፡ ይህንን የመሰለ...

የመግባቢያ አማራጮችን ተባብሮ መፈለግ ከጥፋት ይታደጋል!

በአሁኑ ጊዜ ሕዝብና አገርን ጤና የሚነሱ በርካታ ችግሮች በየቦታው እንደ አሸን ፈልተዋል፡፡ ችግሮቹ ከመጠን በላይ እየተለጠጡ ቅራኔዎች ሲበረክቱ ሰከን ብሎ ከመነጋገር ይልቅ፣ የጉልበት አማራጭ...

አገርን ከቀውስ ውስጥ ማውጣት ብሔራዊ አጀንዳ ይሁን!

የአገራቸው መፃኢ ዕድል የሚያሳስባቸው በአገር ውስጥም ሆነ በውጭ የሚኖሩ ወገኖች፣ በየቀኑ የሚሰሟቸው ማቆሚያ ያጡ ልብ ሰባሪ የግጭትና የጦርነት ዜናዎች እንቅልፍ ይነሷቸዋል፡፡ በዚህም ምክንያት ማንኛውም...