Sunday, May 19, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ግብርና ሚኒስቴር የምግብ ደኅንነትና ጥራት ስትራቴጂ ይፋ አደረገ

spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

ግብርና ሚኒስቴር ከ248 ሚሊዮን ዶላር በላይ በጀት የሚጠይቅ አዲስ አገር አቀፍ የምግብ ደኅንነትና ጥራት ስትራቴጂ ይፋ አደረገ፡፡

ስትራቴጂው አምስት ዋና ዋና ግቦችን የያዘ ሲሆን፣ ከ248 ሚሊዮን ዶላር በላይ በጀት እንደሚያስፈልገው፣ ከግብርና ሚኒስቴር የተገኘው ሰነድ ያሳያል፡፡

የትግበራ ጊዜው ሰባት ዓመታት እንደሆነና የግብርና ሚኒስቴር፣ የኢትዮጵያ ግብርና ባለሥልጣንና የኢትዮጵያ የግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት በዋናነት የሚያስፈጽሙ ተቋማት መሆናቸውን ቅዳሜ ሚያዝያ 5 ቀን 2016 ዓ.ም. በስካይላይት ሆቴል ስትራቴጂው ይፋ ሲደረግ ተገልጿል፡፡

ከአጠቃላይ በጀቱ አንድ በመቶ የሚሆነውን የምግብ ደኅንነት የተመለከቱ የሕግና ተቋማዊ ማዕቀፎች ለመቅረፅ፣ ለማጠናከርና ለማስፈጸም የሚውል ነው ተብሏል፡፡ በተመሳሳይ ሌላው አንድ በመቶ ወጪ የተቀዳሚ የግብርና ምርቶችን (Primary Agricultural Produces) ደኅንነትና ጥራትን ለማስጠበቅ፣ የባለድርሻ አካላትን ትብብርና ቅንጅት ለማጠናከር፣ እንዲሁም አስፈላጊውን ሀብት በዘርፉ ለማዋል እንደሚውል ሰነዱ ይጠቁማል፡፡

የተቀዳሚ የግብርና ምርቶችን ደኅንነትና ጥራት ማስጠበቅ አስፈላጊነትን ለማስተዋወቅና በማኅበረሰቡ ዘንድ ለማስረፅ፣ ዘርፉን የተመለከቱ ጥናቶችን እንዲሁም የቴክኖሎጂ የምርምር ግኝቶችን ተግባር ላይ ለማዋልና የዕውቀት ሽግግር ለማካሄድ በጀት መመደቡ ታውቋል፡፡

ትልቁ የበጀት ክፍል 89 በመቶ ያህል የሚሆነው የምግብ ደኅንነትና ጥራት፣ አስተዳዳርና ቁጥጥር አሠራሮችን በተቀዳሚ የግብርና ምርቶች ላይ ለማጠናከርና የሕዝቡን ጤና ለማስጠበቅ የሚረዳ መሆኑ ተገልጾ፣ ከዚህ በተጨማሪም ተወዳዳሪ የንግድ ሥርዓትና የገበያ ትስስርን ለመፍጠር የሚያስችሉ አሠራሮችን ተግባራዊ ለማድረግ የሚውል ነው ተብሏል፡፡

ስትራቴጂውን ያቀረቡት በግብርና ሚኒስቴር የምግብ ጥራትና ደኅንነት አማካሪ አቶ ቴዎድሮስ ግርማ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ወደ ውጭ የሚላኩ ምርቶች ጥራትና ደኅንነታቸው ባለመጠበቁ ምክንያት ተመላሽ እየተደረጉ ነው፡፡

በተለይ ደግሞ ከምግብ ደኅንነት ጋር ተያይዞ ሰፊ ክፍተቶች እንዳሉ የገለጹት አማካሪው ከዚህ ቀደም የእንስሳት ተዋጽኦ ምርቶች፣ የተለያዩ ቅመማ ቅመሞችና ጥራጥሬዎች ሲላክላቸው የነበሩ አገሮች አሁንም ተመላሽ እያደረጉ በመሆናቸው ገበያ እየታጣ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

የስትራቴጂውን አስፈላጊነት በተመለከተ በሰነዱ ላይ የቀረበው ትንታኔ ኢትዮጵያ በተመረጡ ሰባት የግብርና የወጪ ንግድ ምርቶች ደኅንነትና ጥራት ለማረጋገጥ 30 ሚሊዮን ዶላር ኢንቨስት ብታደርግ፣ በዓመት ተጨማሪ 1.9 ቢሊዮን ዶላር ከወጪ ንግድ ማግኘት እንደምትችል ተጠቅሷል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች