Sunday, May 19, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የተጋነነ የጣሪያና ግድግዳ ግብር ተጥሎብናል ያሉ የኢንዱስትሪ ባለቤቶች ለከተማ አስተዳደሩ አቤቱታ አቀረቡ

spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

  • ግብሩን ካልከፈሉ ፋብሪካዎቻቸው ይታሸጋል መባሉ አሳስቧቸዋል

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በቅርቡ ተግባራዊ ያደረገው የጣራና ግድግዳ ግብር ተመን አቅማችንን ያላገናዘበ ነው ያሉ የፋብሪካ ባለቤቶች ለከተማ አስተዳደሩ አቤቱታ አቀረቡ፡፡

በርካታ አምራች ኢንዱስትሪዎች ባሉበት አቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ የሚገኙ በመቶዎች የሚቆጠሩ ባለንብረቶች የጣራና ግድግዳ ግብሩ ምጣኔ ከአቅማቸው በላይ በመሆኑ እስካሁን ግብሩን እንዳልከፈሉ ታውቋል፡፡ 

ቅሬታቸውን የሚገልጽ ፊርማ በማሰባሰብ ለከተማ አስተዳደሩ ባቀረቡበት አቤቱታ፣ የጣሪያና ግድግዳ ግብር ተብሎ እንዲከፍሉ የተጠየቁት የግብር ምጣኔ የሚንቀሳቀሱበትን የኢንዱስትሪ ዘርፍ ባህሪ ፈጽሞ ያላገናዘበ መሆኑን ጠቅሰው ጉዳዩ በልዩ ሁኔታ እንዲታይላቸው ጠይቀዋል፡፡

‹‹በአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ አምራች የሆንን የፋብሪካ ባለቤቶችና ባለንብረቶች ካለፈው ዓመት ጀምሮ የተጣለውን የንብረት ወይም የጣራና ግድግዳ ግብር በጣም የተጋነነ ነው፤›› የሚለው የቅሬታ አቅራቢዎቹ የጽሑፍ አቤቱታ፣ የግብር አጣጣሉ የኢንዱስትሪውን ባህሪ ያላገናዘበ በመሆኑ ፋብሪካዎች ላይ ችግር ማስከተሉን ይገልጻል።

በፋብሪካዎችና በተለያዩ ኢንዱስትሪዎች ላይ የተጣለው የጣራና ግድግዳ ግብር እንደሌለው ንግድ በተመሳሳይ የግብር ምጣኔ ሊሰላ እንደማይገባ በመጠቆም መፍትሔ እንዲሰጣቸው በተደጋጋሚ እየጠየቁ ባሉበት ወቅት ወቅት የጣሪያና የግድግዳ ግብሩን ካልከፈላችሁ ፋብሪካዎቻችሁ ይታሸጋሉ መባላቸው እንዳስደነገጣቸው አመልክተዋል፡፡

ከመሬት ጋር የተያያዙ አንዳንድ ጉዳዮችን ለማስፈጸም ወደ በከተማ አስተዳደሩ ቢሮዎች በሚሄዱበት ወቅትም ‹‹የጣራና የግድግዳ ግብር ስላልከፈላችሁ መስተንግዶ አታገኙም፣›› የሚል ምላሽ የተሰጣቸው ባለ ኢንደስትሪዎች እንዳሉም ያነጋገርናቸው የፋብሪካ ባለቤቶች ጠቅሰዋል፡፡ 

በአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ የተለያዩ ወረዳዎች የሥራ ኃላፊዎች የጣራና ግድግዳ ግብር ያልከፈሉ የአምራች ኢንዱስትሪ ባለቤቶችን ሰብስበው ባነጋገሩበት ወቅትም የተጣለባቸውን የጣራና ግድግዳ ግብር ካልከፈሉ ፋብሪካዎቻቸው እንደሚታሸጉ የተነገራቸው በመሆኑ ጉዳይ በአስተዳደሩ ደረጃ እንዲመለስላቸው ጥያቄ ለማቅረብ  መገደዳቸውን አስታውቀዋል፡፡ 

ወረዳዎቹ ዕርምጃ ከመውሰዳቸው በፊት አስተዳደሩ ጉዳዩን እንዲያይላቸው የከተማ አስተዳደሩን ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች በግንባር አግኝተው ቅሬታቸውን ማሰማታቸውን ገልጸዋል፡፡

ቅሬታ አቅራቢዎቹ ‹‹እኛ የጣራና ግድግዳ ግብር አንከፍልም አላልንም፡፡ የጣራና ግድግዳ ግብሩ ለመኖሪያ ቤትና ለንግድ ቤት ተብሎ ታሪፍ እንደወጣለት ሁሉ ለኢንዱስትሪዎችም ራሱን የቻለ ታሪፍ ወጥቶ እንክፈል ነው ያልነው፤›› ይላሉ፡፡

ኢንዱስትሪዎች በባህሪያቸው ሰፋ ያለ ቦታ የሚይዙ ከመሆኑ አንፃር በተመሳሳይ ታሪፍ ግብሩን መክፈል አዳጋች እንደሆነባቸው አስረድተዋል፡፡ 

ከ300 ሺሕ ብር በላይ የጣራና ግድግዳ ግብር እንዲከፍሉ የፋብሪካ ባለቤቶች ስለመኖራቸው የሚጠቅሱት ቅሬታ አቅራቢዎቹ የትርፍ ግብርን ጨምሮ የተለያዩ የግብር ግዴታቸውን እየተወጡ ሳለ አዲስ በወጣው የጣራና ግድግዳ ግብር ምጣኔ እየተጠየቁ ያሉትን በመቶ ሺዎች የሚቆጠር ክፍያ ለመፈጸም እንደሚቸገሩ ገልጸዋል፡፡

ለአስተዳደሩ ቀርበው ያስረዱትም የተሰማሩበትን የኢንዱስትሪ ዘርፍ ባህሪ ያገናዘበ የጣራና ግድግዳ ተመን እንዲወጣላቸውና በዚሁ መሠረትም የግብር ግዴታቸውን እንደሚወጡ የሚጠይቅ ነው።

ያቀረቡት አቤቱታ ምላሽ ሳያገኝ የተጣለውን የጣራና ግድግዳ ግብር አሁን ባለው ተመን መሠረት እንዲከፍሉ፣ ይህን ካላደረጉ ደግሞ ፋብሪካዎቻቸውን የማሸግ ዕርምጃ ይወሰዳል መባሉ የበለጠ እያሳሰባቸው ተናግረዋል።

ለአስተዳደሩ ያቀረቡትን የቅሬታ ደብዳቤ በግልባጭ ይመለከታቸዋል ላሏቸው አካላት ጭምር እንዲያውቁት በማድረግ ግፊት እንደሚያደርጉም ጠቁመዋል፡፡

የአዲስ አበባ ጣራና ግድግዳ ግብር ሥራ ላይ መዋሉ ከተገለጸበት ጊዜ ጀምሮ ኢንዱስትሪው ለብቻ የራሱ የሆነ የጣራና ግድግዳ ግብር ተመን ሊኖረው እንደሚገባ በተደጋጋሚ ጥያቄ ሲቀርብበት እንደነበር ይታወሳል፡፡ 

በተለይ አምራች ኢንዱስትሪዎችን በአገር አቀፍ ደረጃ የሚወክለው የኢትዮጵያ ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ኢንዱስትሪዎች እንዲከፍሉ የጠየቁት የጣራና ግድግዳ ግብር ታሪፍ መጠን የኢንዱስትሪዎችን አቅምና ባህሪ ያላገናዘበ በመሆኑ ደግሞ ሊታይ የሚገባው ነው ብሏል፡፡

እንደማንኛውም የንግድ ተቋም ተመሳሳይ የግብር መጠን ኢንዱስትሪዎች ላይ መጣል ተገቢ የማይሆንባቸውን ምክንያቶች በማብራራት ጭምር ጉዳዩ መፍትሔ እንዲሰጠው መጠየቁ አይዘነጋም፡፡

በጉዳዩ ዙሪያ ያነጋገርናቸው የኢትዮጵያ ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ፕሬዚዳንት አቶ አበባየሁ ግርማ፣ በኢንዱስትሪዎች ላይ የተጣለውን የጣራና ግድግዳ ግብር ምጣኔ ምክር ቤታቸው ተገቢ ነው ብሎ እንደማያምን ገልጸዋል።

ዋነኛ መከራከሪያቸውም የንግድ ቤቶችና ኢንዱስትሪዎች ባህሪ የተለያዩ ነው የሚሉት አቶ አበባየሁ፣ ኢንደስትሪዎች ለቢሮነት የሚገለገሉበትን፣ ለማምረቻ የሚጠቀሙበትንና አንዳንድ ቦታዎች ላይ ደግሞ ለዕቃ ማከማቻ የከለሉዋቸውን ቦታዎችን ጭምር በመለካት የጣራና ግድግዳ ግብር እንዲከፍሉ መገደዱ ትልቅ ጫና እንደሚፈጥር ይጠቅሳሉ፡፡ 

በጉዳዩ ላይ ከአስተዳደሩ የሥራ ኃላፊዎች ጋር እንደተነጋገሩበት የጠቆሙት አቶ አበባው፣ በጣራና ግድግዳ ግብር ዙሪያ እየታየ ያለው ችግር ዕልባት እንዲያገኝ፣ ለኢንዱስትሪዎች ራሱን የቻለ የጣራና ግድግዳ ግብር ማስከፈያ ምጣኔ እንዲወጣና በዚያ መሠረት ግብሩን እንዲከፈሉ ማድረግ መፍትሔ ይሆናል ብለው ያምናሉ፡፡

የመንግሥት ግብር መከፈል እንዳለበት ምክር ቤታቸው ፅኑ እምነት እንዳለው፣ ነገር ግን የጣራና ግድግዳ ግብር ወጥ በሆነ መንገድ እንዲከፈል የግብር ምጣኔውን ማስተካከል እንደሚገባ አስረድተዋል፡፡ 

በአሁኑ ወቅት የተጣለባቸውን የጣራና ግድግዳ ግብር መክፈል የጀመሩ የተወሰኑ የኢንዱስትሪ ባለንብረቶች ቢኖሩም፣ ቅሬታ የላቸውም ማለት እንዳልሆነ ተናግረዋል።

በአቃቂ ክፍለ ከተማ ሥር በተለያዩ ወረዳዎች ያሉ አምራቾችን ያነጋገሩ የአስተዳደሩ የሥራ ኃላፊዎችም የጣራና ግድግዳ ግብር እየከፈሉ አምራች ኢንዱስትሪዎች ያሉ መሆኑን አሳውቋቸዋል፡፡ ስለዚህ እንደ ሌሎቹ ያልከፈሉ አምራቾች መክፈል አለባቸው የሚለው አቋሙን ማጠናከሩ ታውቋል፡፡

እንደ አቶ አበባው ገለጻ ደግሞ የጣራና ግድግዳ ግብሩን ያልከፈሉ የኢንዱስትሪ ባለቤቶች የግብር ግዴታቸውን ላለመወጣት ሳይሆን የተቀመጠው የግብር ምጣኔ የተጋነና አቅማቸውን የሚፈትን በመሆኑ ነው ይላሉ። ስለሆነም የግብር ምጣኔው እንዲቀንስላቸው አቤቱታ ማቅረባቸውን ይህንንም ያደረጉት የተከማ አስተዳደሩ አዎንታዊ ምላሽ እንደሚሰጣቸው በማመን እንደሆነ ጠቁመዋል።

አክለውም፣ ባለቸው መረጃ በአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ የጣራና ግድግዳ ግብር የከፈሉ ኢንዱስትሪዎች ቁጥር ከአምስት በመቶ ያነሰ መሆኑን ገልጸዋል።

ለአስተዳደሩ የቀረበው አቤቱታ ታይቶ ምላሽ እንደሚሰጥበት እንደተነገራቸውም አቶ አበባው ገልጸዋል። የቀረበውን አቤቱታ ተመልክተው ውሳኔ እንዲሰጡበትም ለሚመለከታቸው የከተማ አስተዳደሩ ቢሮዎች መመራቱን እንደሚያውቁ ተናግረዋል።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የጣራና ግድግዳ ግብርን ካለፈው ዓመት ጀምሮ ተግባራዊ ያደረገ ሲሆን በወጣው  ታሪፍ መሠረት ብዙዎቹ ግብሩን እየከፈሉ ስለመሆኑ መገለጹ ይታወሳል፡፡ የጣራና ግድግዳ ግብር ያለመሆኑንና ከዚህ ቀደም የነበረውን የጣራና ግድግዳ ግብር ምጣኔ በማሻሻል ተግባራዊ የተደረገ መሆኑ መገለጹም ይታወሳል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች