Sunday, May 19, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ለወለድ ነፃ ባንክ አገልግሎት የፖሊሲና የአሠራር ማሻሻያዎች እንዲደረጉ ተጠየቀ

spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎትን በተፈለገው ደረጃ ለማስፋፋት አሳሪ የሚባሉ ሁኔታዎች እየተፈተሹ መፍትሔ እንዲሰጣቸው እየተደረገ ቢሆንም የበለጠ ውጤታማ የሚሆነው ግን ዘርፉ ራሱን የቻለ አደረጃጀት በብሔራዊ ባንክ ሥር ሲኖረው እንደሆነ ተጠቆመ፡፡

በኢትዮጵያ የመጀመርያው ሙሉ በሙሉ ከወለድ ነፃ ባንክ በመሆን የሚጠቀሰው የዘምዘም ባንክ ፕሬዚዳንት ወ/ሮ መሊካ በድሪ እንደገለጹት፣ ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎቶች ወደፊት እንዳይራመዱ የሚያደርጉ አንዳንድ አሠራሮች በኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ እየተፈተሹ ማሻሻያ እየተደረገባቸው ነው፡፡ ነገር ግን ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት እየሰፋ ከመምጣቱ አንፃር በአሁኑ ወቅት ራሱን የቻለ አደረጃጀት እንዲኖረው ግድ እያለ በመሆኑ፣ በብሔራዊ ባንክ ውስጥ የራሱ የሆነ ሱፐር ቪዥን ዘርፍ ሊደራጅ እንደሚገባ አመልክተዋል፡፡

በኢትዮጵያ በአጭር ጊዜ ውስጥ ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት ካገኘው ተቀባይነት አንፃር፣ የዚህ አደረጃጀት አስፈላጊነት በርካታ ጠቀሜታ እንዳለው ያስታወሱት ፕሬዚዳንቷ፣ በአሁኑ ወቅት ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት የተሰባሰበው ተቀማጭ ገንዘብ ከሁለት መቶ ቢሊዮን ብር በላይ መድረሱን እንደ ምሳሌ ጠቅሰዋል፡፡ ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት የሚጠቀሙ የኅብረተሰብ ክፍሎችም ቁጥራቸው እየጨመረ፣ እንዲሁም የፋይናንስ (ብድር) መጠኑም እያደገ ነውና፣ የፖሊሲ ክፍተትም ኖሮ ዘርፉ በዚህ ደረጃ እያደገ በመምጣቱ ልዩ ትኩረት እንደሚያስፈልገው ተናግረዋል፡፡

እንደ መደበኛው ባንክ ነፃ የፋይናንስ ዘርፍም የራሱ የሆነ ተቆጣጣሪ (ሱፐር ቪዥን) ኖሮት እንዲሠራበት ማድረግ እስካሁን ያልተተገበሩ በርካታ አዳዲስ አሠራሮችን ለማስጀመርና የፋይናንስ አካታችነትን የበለጠ ለማስፋት የሚያግዝ ስለመሆኑም ጠቅሰዋል፡፡

ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት የሃይማኖትም ሆነ ሌላ ምንም ነገር የሌለበት መሆኑንም አስታውሰዋል፡፡ የቢዝነስ ሞዴሉ በሚመርጠው መንገድ ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት የሚፈልግ ማንኛውም ማኅበረሰብ የሚገለገልበት ከመሆኑ አንፃርም፣ ዘርፉን ለማሳደግ በብሔራዊ ማክሮ ኢኮኖሚ ኮሚቴ ጭምር ውክልና ያስፈልገዋል ብለው እንደሚያምኑ ከፕሬዚዳንቷ ማብራሪያ ለመገንዘብ ተችሏል፡፡

ከዚህ ባሻገር ከወለድ ነፃ ባንኮች በፍጥነት ሊተገበር ይገባል ብለው ጥያቄ እያቀረቡበት ያለው ጉዳይ፣ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ መደበኛ ባንኮች የገንዘብ እጥረት ሲያጋጥማቸው የሚሰጣቸውን ዓይነት የብድር አገልግሎት ለወለድ ነፃ ባንኮችም እንዲያቀርብ የሚል ነው፡፡

‹‹በመደበኛው የባንክ አገልግሎት የገንዘብ ችግር በሚኖርበት ጊዜ የመጨረሻው አበዳሪ ብሔራዊ ባንክ ነው›› ያሉት ወ/ሮ መሊካ፣ ሙሉ ለሙሉ ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት የሚሰጡ ባንኮች ግን እንደ መደበኛው ባንክ ብድር ከብሔራዊ ባንክ የማግኘት ዕድል የላቸውም፡፡

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ከወለድ ነፃ ባንኮች የገንዘብ እጥረት ሲያጋጥማቸው ሸሪዓን መሠረት ያደረገ ብድር ለመስጠት የሚያስችለው አሠራሮች ገና ተግባራዊ ያለመደረጉ እንደ አንድ ክፍተት የሚታይም ነው ተብሏል፡፡ ይህ አሠራር እስኪዘጋ ድረስ ግን ከወለድ ነፃ የተሰበሰበ ተቀማጭ ገንዘብን ባንኮች እርስ በርሳቸው እንዲበዳደሩ በጥናት ላይ የተሠረተ አሠራር ቢተገበር በአንዳንድ ባንኮች ፋይናንስ ሳይደረግ የተቀመጠን ገንዘብ ወደ ኢኮኖሚ ውስጥ ለማሠራጨት የሚጠቅም ስለመሆኑ አስረድተዋል፡፡ ለዚህም ብሔራዊ ባንክ የራሱ ሚና ያለው ሲሆን፣ ይህ ግን እንደ ጊዜያዊ መፍትሔ የሚታይ ነው፡፡ ዘላቂ መፍትሔ ግን ብሔራዊ ባንክ ሙሉ ለሙሉ ከወለድ ነፃ ለሆኑ ባንኮች ብድር ለመስጠት የሚያስችለው የሸሪዓውን አሠራር መዘርጋት መሆኑን አመልክተዋል፡፡

እንደ ዘምዘም ባንክ ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት ማነቆ የሆኑትን ጉዳዮች በመንቀስ መሆን የሚገባቸውን አሠራሮች የመፍትሔ ሐሳቦችን የዓለም አቀፍ ልምዶችን አካቶ ለብሔራዊ ባንክ ማቅረቡንም ገልጸዋል፡፡ ዘምዘም ባንክ ለብሔራዊ ባንክ ካቀረባቸው ጥያቄዎች መካከል ለአንዳንዶቹ ምላሽ እየሰጠ ቢሆንም፣ በሒደትም ለቀሪዎቹ ጥያቄዎች ምላሽ ይሰጣል ብለው እምነት ያላቸው ወ/ሮ መሊካ ከወለድ ነፃ የባንክ አገለግሎት ዛሬ ለደረሰበት ደረጃ በሒደት ማሻሻያዎች እየተደረጉ መሆኑነም አስታውሰዋል፡፡

በዘርፉ አሁን የሚታዩ ክፍተቶች ከወለድ ነፃ ባንክ ወደ ገበያ በሚገባበት ወቅት ከነበረው አሠራር ጋር የተያያዙ ስለመሆናቸው የጠቀሱት ፕሬዚዳንቱ፣ ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት ወደ ገበያ በገባንበት ወቅት ሙሉ በሙሉ እንደምንፈልገው ዓይነት የሕግ ማዕቀፎች ተቀርጸው ካለመሆኑ ጋር የሚያያዝ መሆኑን ያምናሉ፡፡ ሌሎች የሕግ ማዕቀፎች ተቀርፆላቸው አገልግሎቱ አለመጀመሩ እንዲሁም የራሱ አደረጃጀት (ሱፐርቪዥን) ሳይኖረው የተጀመረ በመሆኑም ነገሩን ከፈረሱ ጋሪውን ያስቀደመ ሆኖ አንዳንድ አሠራሮች ላይ ችግር ሊፈጥር መቻሉን ጠቅሰዋል፡፡  

አሁን ላይ ግን ብሔራዊ ባንክ ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት ጋር በተያያዙ እየሠራባቸው ያሉ ሥራዎች የነበሩ ችግሮችን እያጠበቡ ስለመሆኑ የጠቀሱት ወ/ሮ መሊካ ሳይገልጹ፣ በቅርቡ የወጣውን አንድ መመርያ በምሳሌነት ጠቅሰዋል፡፡

ሙሉ በሙሉ ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት ሽርክናን መሠረት ያደረገ በመሆኑ ከዚህ አሠራር ጋር የተናበበ መመርያ መውጣቱ ትልቅ ነገር ነው ይላሉ፡፡

ዘርፉ ትርፍና ኪሳራን የመጋራት አገልግሎት በመሆኑ ብዙ ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎቶች ኢትዮጵያ ውስጥ ተግባራዊ ለማድረግ ማነቆ የሆኑ ነገሮችን የሚቀርፍ የተለያዩ ኢንቨስትመንቶችን ለመሥራት የሚያስችል መመርያም ነው ብለው ሌሎች ማሻሻያዎችም ደረጃ በደረጃ ይደረጋሉ የሚል ተስፋ አላቸው፡፡

ከማዋቀር አንፃር የቀረበውን ጥያቄ በአወንታዊነት የተቀበለው መሆኑ ተገልጿል፡፡ ከእነዚህ መካከል ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት በብሔራዊ ባንክ ውስጥ የራሱ አደረጃጀት እንዲኖረው ማድረግ አንዱ ሲሆን ሌላው ደግሞ በብሔራዊ ደረጃ የማማከር አገልግሎት የሚሰጥ የሸሪዓ ኮሚቴ እንዲዋቀር ማድረግ ነው፡፡

አሁን የሸሪዓ የምክር አገልግሎት የሚሰጠው በየተናጠል በመሆኑ ወጥ የሆነ የሸሪአ የማማከር የሚያስችል አሠራር ቢዘረጋ አገልግሎቱን የበለጠ ማድረግ የሚቻል መሆኑንም ጠቅሰዋል፡፡ ብሔራዊ ባንክም የሸሪዓ አማካሪ ኮሚቴን ከማዋቀር አንፃር የቀረበውን ጥያቄ በአወንታዊነት የተቀበለው መሆኑም ተገልጿል፡፡

በኢትዮጵያ ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት አሰጣጥ ጋር በተያያዘ የዘርፉ ባለሙያዎች አገልግሎቱ በሚፈለገው ደረጃ እየተሰጠ ያለመሆኑን ያምናሉ፡፡

ከወለድ ነፃ አገልግሎት የሚሰጥባቸው እጅግ በርካታ የፋይናንስ አቅርቦቶች በሌሎች አገሮች በሰፊው የሚሰጡ ሲሆን በኢትዮጵያ ግን ለዚህ የሚሆን ሕግ ባለመኖሩ እንቅፋት ስለመሆኑ ይናራሉ፡፡

ዘርፉ እየሰፋ ከመምጣቱ አንፃር ተጨማሪ የፖሊሲና የአሠራር ማሻሻያዎችን መጠየቁ ተፈጥሯዊ ነው የሚሉት እነዚሁ ባለሙያዎች አሁንም ተጨማሪ ፍላጎቶች እያሳዩ ነው፡፡

ከነዚህ መካከል ራሱን የቻ ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት ይኑር የሚለው አንዱ ነው፡፡ በቅርቡ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የሲቢኢ ኑር ከወለድ ነፃ የባንክ አገለግሎት አሥረኛ ዓመት ክብረ በዓል ላይ በሸሪዓ አማካሪ ኮሚቴዎችና በሃይማኖት አባቶች በኩል ሲቢኢ ኑር ከንግድ ባንክ ወጥቶ ራሱን መንግሥታዊ ባንክ ይሁን የሚል ጥያቄ ለመንግሥት ቀርቧል፡፡

ከወለድ ነፃ ባንክ አገለግሎት መጀመርያ በመስኮት ደረጃ ከለውጡ በኋላ ደግሞ ሙሉ በሙሉ ከወለድ ነፃ የባንክ አገለግሎት መስጠት እንዲቻል መፈቀዱ ይታወሳል፡፡

በዚህ መሠረት በአሁኑ ወቅት ሙሉ ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት የሚሰጡ አራት ባንኮችና አገልግሎቱን በመሠረቱት ደረጃ የሚሰጡ ባንኮች ቁጥር ሃያ ደርሷል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች