Wednesday, June 19, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የፋይናንስ አገልግሎቶች በተወሰኑ አካባቢዎችና ዘርፎች መከማቸታቸው እንዳስደነገጠው ብሔራዊ ባንክ አስታወቀ

spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

የኢትዮጵያ የፋይናንስ ዘርፍ አገልግሎቶች ውስን በሆኑ የከተማ አካባቢዎችና በተወሰኑ ዘርፎች ላይ ብቻ መከማቸታቸውን በጥናት ያገኙት ውጤት እንዳስደነገጣቸው፣ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ኃላፊዎች አስታወቁ፡፡

የብሔራዊ ባንክ ገዥ አቶ ማሞ ምሕረቱ፣ የኢትዮጵያ የፋይናንስ አገልግሎት ሰጪዎችን ትኩረት በተመለከተ መጋቢት 27 እና 28 ቀን 2016 ዓ.ም. በስካይላይት ሆቴል በተዘጋጀ መድረክ እንዳስረዱት፣ የፋይናንስ ዘርፉ በውስጥ የቢዝነስ ዓይነትና በተወሰኑ አካባቢዎች ላይ በልዩ ትኩረት ተከማችቶ ይገኛል ብለዋል፡፡

ብሔራዊ ባንክ ባዘጋጀው የሁለት ቀናት ‹‹የኢትዮጵያ የዲጂታል ክፍያ ኮንፈረንስ›› ላይ የተገኙት ገዥው፣ በሁለተኛው ቀን ከእሳቸው ጋር በተካሄደው ጥያቄና መልስ መርሐ ግብር ላይ ለግብርና ስለሚደረግ የፋይናንስ አቅርቦት ጥያቄ ተነስቶላቸው ነበር፡፡

አቶ ማሞ ለጥያቄው በሰጡት ምላሽ፣ ግብርና ለኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ጠቃሚ ዘርፉ መሆኑን፣ መንግሥትም የግብርናን ምርታማነት ማሳደግና አጀንዳው ማድረጉንና ብሔራዊ ባንክም ልዩ ትኩረት እንደሚሰጠው አስረድተዋል፡፡

በኢትዮጵያ በአነስተኛ ይዞታዎች ላይ የሚያርሱ አርሶ አደሮች በሰፋፊ የግል እርሻዎች ከሚሠሩት በበለጠ፣ የግብርና ምርት ወደ ገበያ እንደሚያቀርቡ ቢታወቅም፣ አቶ ማሞም በሰጡት ምላሽ ላይ እንደገለጹት ግን፣ የአነስተኛ ይዞታ አርሶ አደሮች በቂ የሆነ የፋይናንስ አገልግሎት አያገኙም፡፡

የንግድ ባንኮችና አጠቃላይ የፋይናንስ አገልግሎት ሰጪዎች ስለሚሰጡት የቢዝነስ የትኩረት አቅጣጫ የገለጹት ገዥው፣ በኢትዮጵያ መታወቅ ያለበት ነገር ቢኖር የአገሪቱ ፋይናንስ በተወሰነ ዘርፍ ላይ ተከማችቶ ይገኛል ብለዋል፡፡ ‹‹የፋይናንስ ዘርፉ በተወሰነ አካባቢ መከማቸቱ በእጅጉ የሚያስገርም ነው፤›› ብለዋል፡፡

በከተሞች፣ በተወሰኑ የሥራ መስኮች፣ እንዲሁም በጥቂት ተበዳሪዎች ላይ የፋይናንስ ዘርፉ ትኩረት እንደሚያደርግ ከገለጹ በኋላ ብሔራዊ ባንክ በቅርቡ ጥናት አካሂዶ ዘርፉ፣ ‹‹ለምን በተወሰኑ አካባቢዎች ላይ ትኩረት እንዳደረገ ስናይ አስደንግጦናል፤›› ብለዋል፡፡

የፋይናንስ ተቋማቱ በበቂ ሁኔታ ትኩረት ያላገኙ ዘርፎች ላይ እንዲያተኩሩ መወትወት የብሔራዊ ባንክ ፍላጎት እንደሆነ፣ ነገር ግን ባንኮቹ አብዛኛውን ጊዜ ማስያዣ እንደሚፈልጉ አስረድተዋል፡፡ የፋይናንስ ቴክኖሎጂ አቅራቢዎች ግን በዚህ ላይ ትኩረት ሰጥተው የግብርናን ዘርፍ ማሳደግ እንደሚችሉ፣ በዕለቱ ውይይቱ ላይ ለተገኙ የፋይናንስ ቴክኖሎጂ ድርጅቶች ተወካዮች መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡

በብሔራዊ ባንክ በኩል ባንኮችና የማይክሮ ፋይናንስ ተቋማት ለግብርናው ዘርፍ ለማበደር እንዲበረታቱ የሚችሉትን ሁሉ እንዲያደርጉ፣ ባንኮችም የተወሰነ የብድር መጠናቸውን ለግብርና እንዲያቀርቡ የሕግ ማዕቀፍ ተዘጋጅቶ እንደነበረ፣ ነገር ግን በበቂ ሁኔታ የፋይናንስ አቅርቦት አለመደረጉን አቶ ማሞ አብራርተዋል፡፡

‹‹ለግብርና ዘርፍ ስለሚቀርብ ብድር ስንናገር ሰዎች አሁንም የፋይናንስ ዘርፉ ለግብርናው በቂ መጠን ያለው ብድር እንደሚያቀርብ ይረሳሉ፤›› ሲሉ የተደመጡት አቶ ማሞ፣ ‹‹የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከፍተኛውን የግል ብድር አቅርቦት ለግብርና ዘርፉ፣ በተለይም ለማዳበሪያ አቅርቧል፤›› ብለዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች