Sunday, May 19, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

‹‹በሌሎች ክልሎች ያለው የሰብዓዊ ዕርዳታ ፍላጎት ከትግራይ አንፃር አነስተኛ ነው ብዬ ለመግለጽ አልችልም›› ራሚዝ አላክባሮቭ (ዶ/ር)፣ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የኢትዮጵያ ተወካይና የሰብዓዊ ዕርዳታ አስተባባሪ 

በኢትዮጵያ የሰብዓዊ ዕርዳታ የሚያቀርቡ ዓለም አቀፍ የረድዔት ድርጅቶችና ሠራተኞች በአገሪቱ በሚከሰቱ የበሽታ ወረርሽኞች፣ ድርቅ፣ ጎርፍና ጦርነት ምክንያትለፉት ጥቂት ዓመታት በእጅጉ ተፈትነው ነበር። በኮቪድ-19 ወረርሽኝ፣ በዩክሬንና በጋዛ ግጭቶችና እየተካረረ በመጣው የዓለም ጂኦ ፖለቲካዊ ፉክክር፣ እንዲሁም በአሁኑ ወቅት እየተስተዋለ በሚገኘው ዓለም አቀፍ የኢኮኖሚ ቀውስ ምክንያት እንደ ኢትዮጵያ ያሉ አገሮች ሊያገኙ የሚችሉት ሰብዓዊ ድጋፍ እየቀነሰና ፈተና ውስጥ እየገባ ነው። ለምሳሌ ... 2023 ሰብዓዊ ዕርዳታ ለሚያስፈልጋቸው ወደ 20 ሚሊዮን ለሚጠጉ ኢትዮጵያውያን ምላሽ ለመስጠት ከሚያስፈልገው 3.9 ቢሊዮን ዶላር ውስጥ የተገኘው አንድ ሦስተኛው ብቻ ነበር። የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የኢትዮጵያ ተወካይና የሰብዓዊ ዕርዳታ አስተባባሪ ራሚዝ አላክባሮቭ (/) በኢትዮጵያ ያለውን የሰብዓዊ ዕርዳታ አቅርቦት አጠቃላይ ሁኔታ፣ በሰሜኑ ጦርነት ወቅት የነበሩ ፈታኝ እክሎችና የወደፊት ተግዳሮቶችን በተመለከተ የሚሉት አላቸው። በፖሊሲ አወጣጥና በሰብዓዊ ምላሽ የሥራ መስክ የሦስት አሠርት ዓመታት ልምድ ያካባቱት አላክባሮቭ (/) ወደ እዚህ መስክ ከመቀላቀላቸው በፊት በአገራቸው አዘርባጃን ሐኪም ነበሩ። በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የተለያዩ ኤጀንሲዎች በተለያዩ ኃላፊነቶች ያገለገሉ ሲሆን፣ ለአብነትም በሱዳንና በሶማሊያ ዩኤንኤፍፒኤ ፕሮግራም ኦፊሰር፣ በአፍጋኒስታንና ፍልስጤም የሰብዓዊ ዕርዳታ ኦፊሰር በመሆን አገልግለዋል። ባለፈው ነሐሴ ወር ደግሞ በተመድ የኢትዮጵያ ሕፈት ቤት ዋና ተወካይ ሆነው ተሹመዋል። በኢትዮጵያ ስላሉ የሰብዓዊ ምላሽ ጥረቶች፣ ስለሰብዓዊ ዕርዳታ ፕሮግራሞችና የገንዘብ ድጋፎች፣ እንዲሁም የወደፊት የሰብዓዊ ዕርዳታ ዕጣ ፈንታን በተመለከተ ሳሙኤል ቦጋለ ከእሳቸው ጋር ያደረገው ቆይታ እንደሚከተለው ተሰናድቷል።

ሪፖርተርኢትዮጵያ ውስጥ ብዙ ችግሮች አሉ። እነዚህን ችግሮች ለመቅረፍ ለሰብዓዊ ዕርዳታ ኤጀንሲዎች ከባድ ይመስለኛል። የእርስዎ ምልከታ ምንድነው?

አላክባሮቭ፡- እዚህ አገር በጣም የተደባለቁ ሁኔታዎች መኖራቸውን ተረድቻለሁ። በግጭት፣ በተራዘመ ድርቅ፣ ጎርፍና በአየር ንብረት አደጋዎች የተጎዱ አካባቢዎች አሉ። የእነዚህ አስቸጋሪ ሁኔታዎች ጥምረትና የኮቪድ-19 ወረርሽኝን ተከትሎ የተፈጠረው ዓለም አቀፍ የኢኮኖሚ መቀዛቀዝ ሲታከልበት ደግሞ ከፍተኛ የሆነ የሰብዓዊ ዕርዳታ ሸክም ይፈጥራል ብዬ አስባለሁ። በዚህ ላይ ደግሞ በመላ አገሪቱ ከፍተኛ የልማት ሥራዎች ይካሄዳሉ። ምክንያቱም ይህ ትልቅ አገር ነው። እኔ ከነበርኩባቸው ቦታዎች ጋር ሲነፃፀር ኢትዮጵያ ውስጥ መሥራት የበለጠ ከባድ አይመስለኝም። የሰብዓዊ ድጋፍ ሥራችን ውስብስብ አይደለም። እርግጥ ነው አስቸጋሪ ሁኔታዎች አሉ። በተለይ አሁን እያጋጠመን ያለው ዋነኛ ችግር የሰብዓዊ ድጋፍ ለማድረግ የሚያስችል በቂ ሀብት ካለመገኘቱ ጋር የተያያዘ ነው። እ.ኤ.አ. በ2023 በኢትዮጵያ ለምናደርገው አጠቃላይ የሰብዓዊ ድጋፍ ያስፈልገናል ብለን ከጠየቅነው ገንዘብ ውስጥ ማግኘት የቻልነው 35 በመቶውን ነው። በግልጽ ለማየት እንደሚቻለው ዓለም አቀፋዊ የኢኮኖሚ መቀዛቀዝ አለ፣ የጋዛ ሁኔታ አለ፣ የዩክሬን ጦርነት አለ።

በእነዚህ ምክንያቶች የተነሳ በአጠቃላይ ለሰብዓዊ ዕርዳታ የሚውል የሀብት አቅርቦት ችግር ወይም ውስንነት ተፈጥሯል። እኛም ለከፍተኛ የሀብት እጥረት ተዳርገናል። በዚህ ዓመት በኢትዮጵያ ለምናደርገው የሰብዓዊ ዕርዳታ ድጋፍ ወደ ሦስት ቢሊዮን ዶላር የሚጠጋ ሀብት (ገንዘብ) ያስፈልገናል። ነገር ግን አሁን ከአየር ንብረት ለውጥ ጋር ተያይዞ በተለየ ሁኔታ በትግራይ፣ በአማራና በአፋር ክልሎች የተከሰተው ድርቅ ያስከተለውን ከፍተኛ የሰብዓዊ ዕርዳታ ፍላጎት ለመመለስ አንድ ቢሊዮን ዶላር ቅድሚያ ተሰጥቶት እንዲለቀቅልን እየጠየቅን ነው። የጠቅስኳቸው ችግሮች በከፋ ሁኔታ በትግራይ፣ በአማራና በአፋር አካባቢዎች የተከሰቱ ቢሆንም በእውነቱ ችግሩ በእነዚህ አካባቢዎች ብቻ ሳይሆን በመላ አገሪቱ ነው። ለዚህ ተግባር የሚያስፈልገንን ሀብት የምንጠይቅበት አንድ ዝግጅት በመጪዎቹ ሳምንታት ውስጥ በጄኔቫ ይኖረናል። በአሁኑ ጊዜ ለእኛ ቁልፍ ጉዳይ ለሰብዓዊ ዕርዳታ የሚውል ሀብት እጥረት ነው።

ሪፖርተር፡- የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በኢትዮጵያ ለሚያደርጋቸው እንቅስቃሴዎች ቅድሚያ የሚሰጠው እንዴት ነው? 

አላክባሮቭ፡- ወደፊት ለመራመድ የችግሮቹን መንስዔዎች መፍታት እንደሚያስፈልገን ግልጽ ነው። የችግሮቹ መንስዔ ደግሞ በሁሉም አካባቢዎች ሁሉን አቀፍና ቀጣይነት ያለው ልማት አለመኖሩ ነው። ቅድሚያ የምንሰጠው የሰብዓዊ ዕርዳታ ፍላጎቶቹ ዋና መንስዔዎች ላይ በማተኮርና ዘላቂ መፍትሔዎችን በመፍጠር እነዚያን የሰብዓዊ ዕርዳታ ፍላጎቶች ማስቀረት ነው። ይህም ማለት የግብርና ምግብ ሥርዓትን በማዳበር ላይ በማተኮር ነው። ለዚህ ደግሞ ጥራት ያላቸው የግብርና ግብዓቶችን ማለትም የዘር፣ የአፈር ማዳበሪያ፣ የእርሻ መሣሪያዎችንና ማሽነሪዎችን አርሶ አደሩ አግኝቶ ሥራውን እንዲሠራ ማድረግ ያስፈልጋል። እናም እነዚህ አርሶ አደሮች በበቂ ሁኔታ እንዲያመርቱና የእሴት ሰንሰለት በመፍጠር ከገበያ ጋር እንዲተሳሰሩ ማድረግ አለብን። አሁን፣ አንዳንድ ንጥረ ምግቦችንና እንደ የሕፃናት ፎርሙላና ወተት የመሳሰሉትን ከሌሎች አገሮች ነው የምናስመጣው። እነዚህን ምርቶች ኢትዮጵያ ውስጥ እንዲመረቱ መፍትሔ መፈለግ አለብን።

ሥራዎችን እንዴት መሥራት እንዳለብን በጣም ቀላል መፍትሔዎችን መጥቀስ እችላለሁ። በመኪና ውኃ በምናቀርብባቸው አካባቢዎች የውኃ ጉድጓዶችን ማዘጋጀት አለብን። ከዚያም እነዚህ የውኃ ጉድጓዶች የፀሐይ ኃይልን እየተጠቀሙ መሆናቸውንና ለኅብረተሰቡም ሆነ ለሆስፒታሎች ዘላቂ የውኃ አቅርቦት መፍጠራቸውን እናረጋግጣለን። ከዚያም እነዚህ የውኃ ጉድጓዶች ጥቅም ላይ ውለው ለኅብረተሰቡም ሆነ ለሆስፒታሎች ዘላቂ የውኃ አቅርቦት እንዳላቸው እናረጋግጣለን። የምግብ ድጋፍ በምናደርግባቸው አካባቢዎች ደግሞ ራሳችንን በተሻለ ሁኔታ በማደራጀት የአገር ውስጥ የምግብ ምርቶችን እዚሁ ማምረት መጀመር አለብን። ይህም ማለት የጓሮ አትክልቶችን ማምረት፣ የዶሮ ዕርባታና የአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖዎችን የተላመዱ ቴክኖሎጂዎችን ማዳበር ማለት ነው። ለወደፊቱም የአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖዎችን የማላመድ ሒደት ዘላቂው የመፍትሔ መንገድ ነው። እርግጥ ነው እነዚህ ተግባራት በአንድ ሌሊት ሊመጡ አይችሉም።

ሪፖርተርበኢትዮጵያ ያለው ችግር በአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖዎችና በተፈጥሮ አደጋዎች ላይ ብቻ የተገደበ አይደለም። የኢትዮጵያ ሰላም ሁኔታ እያሽቆለቆለ ሲሆን ብዙ ሰው ሠራሽ ቀውሶችም አሉ። ለእነዚህ ችግሮች ምን መፍትሔዎች ትጠቁማላችሁ? 

አላክባሮቭበመጀመሪያ ደረጃ በአገሪቱ ሰላም ግንባታ ላይ ለሚደረገው ጥረት ሁሉ ዕውቅናና አድናቆት መስጠት እፈልጋለሁ። የመንግሥታቱ ድርጅት በሰላም ሒደት ውስጥ ያለው ሚና ለሰላም አስተዋጽኦ ማበርከት ነው። እነዚህ በተባበሩት መንግሥታት የልማት ፕሮግራም (ዩኤንዲፒ) እና በአንዳንድ አጋሮች ድጋፍ ከሚተገበሩ ፕሮጀክቶች ጋር በቀጥታ የተያያዙ ናቸው። ለምሳሌ የቀድሞ ተዋጊዎችን ትጥቅ ማስፈታት፣ ማሰባሰብና ከማኅበረሰቡ ጋር ዳግም የማዋሀድ (DDR) ያሉ ፕሮግራሞችን እንደግፋለን። ከዚህ በተጨማሪም የሰሜን ኢትዮጵያ ክልሎችን ማለትም ትግራይን፣ አማራንና አፋርን የሚሸፍን የሰላም ድጋፍ ፕሮግራም አለን። ይህም የክልሎቹ ነዋሪዎችን የኑሮ ሁኔታ ለማሻሻል፣ ሥራና ሌሎች አማራጭ ዕድሎችን ለመፍጠር ያለመ ነው። ሰዎች የጦር መሣሪያ የሚያነሱትና ብዙ ጊዜ ይህንን የሚያደርጉት የኢኮኖሚ ዕድል ማግኘት ሳይችሉና የልማት ዕድሎችን ሲነፈጉ ነው። ስለዚህ እኛ በዚህ ጉዳይ ላይ እየሠራን ነው። አሁን በሰሜን ኢትዮጵያ እየተተገበረ ያለው ይህ ጅምር እኛ እያደረግን ያለውን አንዱ ማሳያ ነው። ሌላው በቅርቡ በትግራይ ያደረግነው ድጋፍ ነው። በትግራይ ለዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ፣ ለመልካም አስተዳደር ማሻሻያ፣ በተለይም የአካባቢ አስተዳደር መዋቅሮችን የበለጠ ሙያዊ ለማድረግና ለሕዝቡ የተሻለ አገልግሎት ለመስጠት የተጀመረውን ሒደት እያገዝን ነው። ይህም እንደ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የኢትዮጵያ ጽሕፈት ቤት በኢትዮጵያና በአፍሪካ ኅብረት የሚመሩ ሒደቶችን ለመደገፍ ልናደርጋቸው የምንችላቸው አስተዋፅኦዎች ናቸው።

ሪፖርተርየተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ብዙ ጊዜ ችግሮችን በመፍታት ረገድ ይዘገያል ተብሎ ይተቻል። የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የኢትዮጵያ ተፋላሚ ኃይሎችን ወደ ድርድር ጠረጴዛ እንዲመጡ ጫና በማድረግ ረገድ በቂ ሥራ ሠርቷል ብለው ያምናሉ?

አላክባሮቭ፡- ሰላምን በሚመለከት እኛ የት እንደቆምን በግልጽ አሳይተናል ብዬ አምናለሁ። ሰላም የግድ አስፈላጊ ነው። ሰላም እንዲመጣ ደግሞ በሒደቱ ድርሻ ያላቸው ሁሉም አካላት ኃላፊነት ነው። ወደ ኢትዮጵያ የሰላም ሒደት ስንመጣ ጉዳዩ የሚመራው በአፍሪካ ኅብረት ነው። በኢትዮጵያ መንግሥት ባለቤትነትና በአገር አቀፍ ደረጃ የሚመራ ሒደት ነው። የእኛ ሚና ከሰላም የሚገኙ ትሩፋቶች እንዲቀርቡ ማገዝ ነው። በዚህ ረገድ ሚናችንን ለመወጣት ደግሞ ራሳችንን በተቻለ መጠን አዘጋጅተናል። ለምሳሌ የቀድሞ ታጋዮችን በፍጥነት ትጥቅ የማስፈታትና ወደ ማኅበረሰቡ እንዲቀላቀሉ የማድረግ ጉዳይ በቀጥታ ባለን የሀብት አቅርቦት ላይ የተመሠረተ ነው። እኛ በራሳችን ማድረግ አንችልም፣ ነገር ግን አሁን ካሉት ፕሮግራሞችና እየተካሄዱ ካሉ ፕሮጀክቶች ጋር በማገናኘትና በማዋሀድ ለመተግበር የሚያስችሉንን መፍትሔዎች ለመፈለግ እየሞከርን ነው። የገንዘብ አቅርቦቱ ካለፉት ዓመታት በእጅጉ ያነሰ በመሆኑ እነዚህ ተግዳሮቶች ይበልጥ ውስብስብ እየሆኑ መጥተዋል። አማራጭ የፈጠራ ሐሳቦችን በመጠቀም መፍትሔ ማምጣት ይፈልጋል። ለምሳሌ የግሉን ዘርፍ ተሳትፎ ይጠይቃል። በተለምዶ ከእኛ ጋር ከሚተባበሩ ዘርፎች ውጪ ካሉ ሌሎች ዘርፎችን የሀብትና የግብዓት አቅርቦት ማግኘትን ይጠይቃል። በዚህ አካባቢ በፍጥነት ተንቀሳቅሶ ውጤት ማግኘት ፈታኝ ሊሆን ይችላል፣ ነገር ግን የምንችለውን ሁሉ እያደረግን ነው። አሁንም ሰላምን ለማምጣት እየተረደጉ ለሚገኙ ጥረቶች በሙሉ እውቅና መስጠትና ከሰላም ውጪ ሌላ አማራጭ እንደሌለ አፅንኦት መስጠት እፈልጋለሁ። ሁሉም ችግሮች በሰላማዊ መንገድ መፈታት አለባቸው፣ መሆንም አለበት። ምክንያቱም ኢትዮጵያ ሰላም ትፈልጋለች። ኢትዮጵያ ለወጣቶቿ ምቹ ሁኔታዎችን መፍጠር አለባት፣ የኢኮኖሚ ልማት ዕድሎች መፍጠር ያስፈልጋታል። እነዚህ ደግሞ ለሁሉም ዕድገቶች የማዕዘን ድንጋዮች ናቸው።

ሪፖርተርከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ የመጣው ግጭትና የታጣቂዎች ትጥቅ አለመፍታት የፕሪቶሪያውን የሰላም ስምምነት እውነተኝነት አጠራጣሪ እያደረጉትና ሥጋት ውስጥ እየከተቱት ነው። በዚህ ምክንያት እስካሁን የተደረገው የሰብዓዊ ድጋፍና ጥረት ከንቱ ይሆናል ብለው ይፈራሉ?

አላክባሮቭአልፈራም፣ ተስፋ ቆራጭ አይደለሁም። ስለሒደቱ ፍርኃትን፣ ብሩህ ተስፋን ወይም ተስፋ መቁረጥን መግለጽ የእኔ ሥራ አይደለም። ነገር ግን ስለሒደቱ ያለኝ ስሜት በጎ ነው። የሰላም ሒደቱን ዕውን ማድረግ አለብን። ዕውን ማድረግም ይገባናል። ነገሩን የማየው እንደዚያ ነው። ነገር ግን በጥያቄህ ውስጥ ያሉት አማራጮች እኛ ትኩረት የምናደርግባቸው ጉዳዮች አይደሉም። እኛ መፍትሔዎች ላይ ማተኮርና እነዚህን መፍትሔዎች በተቻለ መጠን ወደ ጠረጴዛው እንዲመጡ ማድረግ ነው። የተለመዱት ለጋሾች የገንዘብ ድጋፍ ማቅረብ ካልቻሉ ከግሉ ዘርፍ ጋር የተያያዙ ኢኮኖሚያዊ መፍትሔዎችን ወይም አዳዲስ መፍትሔዎችን መፈለግ አለብን። እናም በዚህ መንገድ ዕርዳታ ለሚያስፈልጋቸው ሰዎች አማራጭ የኑሮ ዘዴ ማቅረብ ይገባናል። አንድ ነገር ልብ በል። በየትኛውም አገር የሚፈጠሩ ግጭቶች ዋነኛ መንስዔ ኢኮኖሚያዊ አቅም ማጣት ነው። ለእንዲህ ዓይነት ግጭቶች ወይም ችግሮች ሁሉ መንስዔ ኢኮኖሚያዊ ነው። ድሆች የመሥራት ዕድል ካላገኙ፣ ወጣቶች የመማር ዕድል ካላገኙና የወደፊት ዕጣ ፈንታቸው ጨለማ ከሆነ በእጃቸው ያለውን የጦር መሣሪያ ማንሳታቸው አይቀሬ ነው። ሰዎች የጦር መሣሪያ የሚያነሱት ተስፋ ሲያጡና የወደፊት ዕድላቸው እንደተዘጋ ሲሰማቸው ነው። ስለዚህ እኛም ይህንን በማስወገድ ወጣቶች ተስፋ እንዲሰማቸውና የወደፊት ዕጣ ፋንታቸው ብሩህ እንደሆነ እንዲሰማቸው ዕድሎችን መፍጠር አለብን። የበለፀገ ሕይወት የመምራት፣ የማዳበርና የመማር ዕድል እንዳላቸው እንዲሰማቸውና ከዚያ ውጪ ያሉ አማራጮች አያስፈልጉኝም እንዲሉ ማደረግ ዋናው የትኩረት ነጥብ መሆን አለበት። ስለዚህ ለወጣቶች ተጨማሪ ዕድሎችን መፍጠር አለብን።

ሪፖርተርበጦርነቱ ወቅት የወንጀል ድርጊት የፈጸሙትን ተጠያቂ የማድረግ ጉዳይስ? 

አላክባሮቭ፡- ያ በጣም አስፈላጊ ነው። ይህ ጉዳይ እንዳይፈጸም ዋነኛ መንስዔ የሆነው አጥፊዎች ሳይከሰሱ የመታለፋቸው ልማድ ነው። ይህ ግን ሊፈቀድ አይችልም። ወንጀሎችን የፈጸሙ ሁሉ፣ በሰብዓዊነት ላይ የተፈጸሙ ወንጀሎች፣ በሴቶች ላይ በደል የፈጸሙ፣ በሲቪል ሕዝብ ላይ በደል የፈጸሙ ሁሉ ለፍርድ መቅረብ አለባቸው። በዚህ ላይ ምንም ጥያቄ ሊኖር አይገባም። እኛ እንደ ተመድ በዚህ ጉዳይ ላይ በጣም ግልጽ ነን። ወንጀለኞች ሳይቀጡ መቅረት የለባቸውም። እናም እነዚህ ነገሮች እንዲከሰቱ በፍጹም መቀበል አንችልም።

ሪፖርተርእስካሁን ወንጀለኞችን ለፍርድ በማቅረብ ረገድ በቂ የተሠራ ይመስልዎታል? 

አላክባሮቭ፡- በዚያ መስክ ብዙ ጥረቶችን ዓይተናል፣ ግን ከዚህ የበለጠ ማድረግ ይቻላል። ሁሉም አጥፊዎች ተጠያቂ እስካልሆኑ ድረስ እኛም ጥረታችንን አናቆምም። ለዚህም ከአገር አቀፍ ፍርድ ቤቶች፣ ከፍትሕ ሚኒስቴር፣ መንግሥታዊ ካልሆኑ ድርጅቶች፣ ከሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች፣ ከኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽንና ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በጋራ እንሠራለን። ከእነዚህ የሕግ ጥሰቶች መካከል አንዳቸውም መተው የለባቸውም፡፡ እናም ሳይመረመሩና ምላሽ ሳይሰጥባቸው መተው የለባቸውም።

ሪፖርተርየሰብዓዊ ዕርዳታ ድርጅቶች በአገሪቱ ውስጥ ካሉ ችግሮች ይልቅ በሰሜን ኢትዮጵያ፣ በተለይም በትግራይ ለተከሰቱት ቀውሶች ትኩረት ይሰጣሉ የሚሉ ወቀሳዎች አሉ። የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ሰብዓዊ ዕርዳታ በሚሰጥበት ጊዜ ምን ቅድመ ሁኔታዎችን ያስቀምጣል? 

አላክባሮቭ፡- እኔ ኢትዮጵያ ከመጣሁበት ቀን ጀምሮ በትግራይ ብቻ ሳይሆን፣ በሁሉም ክልሎች የሰብዓዊ ዕርዳታ ሁኔታዎችን ለመመለስ ማድረግ የሚገባኝን ጠብቄአለሁ። ሰብዓዊ ችግሮች ባሉባቸው ክልሎች ሁሉ በእኩል መገኘት አለብን፣ እኛ እያደረግን ያለነውም ይህንኑ ነው። ቅድመ ሁኔታዎችን በተመለከተ ያነሳኸውን ጥያቄ እንመልከት። በምናደርጋቸው ሰብዓዊ ድጋፎች በሙሉ በጤና፣ በማኅበራዊ ልማት፣ በግብርና ማብቃት፣ በግብርና ሥርዓት ልማት፣ ለአርሶ አደሮች ዕድል በመፍጠር፣ ለሴቶችና ወጣቶች የሚደረጉ ማናቸውም ዕገዛዎች ከማንኛውም ቅድመ ሁኔታ የፀዱ ናቸው። መሆን ያለበትም እንደዚያ ነው። ስለዚህ መሠረታዊ ከሆኑት የግልጽነትና የተጠያቂነት መሥፈርቶች በስተቀር የምናደርጋቸው ድጋፎች ከማንኛውም ቅድመ ሁኔታ ነፃ ናቸው። ይህንንም ሁል ጊዜ በይፋ እናገራለሁ። በአጠቃላይ የሰብዓዊ ዕርዳታ ወይም የዕርዳታ ዘርፍን ፖለቲካ ማድረግ ሊፈቀድ፣ ወይም ሲሆንም ሊታለፍ አይገባም። የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በሰብዓዊነት መርሆዎች ላይ የሚሠራ ገለልተኛ ድርጅት ነው። ያ በመሠረታዊነት የእኛ ነጥብ ነውና በገንዘብ ለሚረዱ ሁሉ የምናገረው ይህንን ነው። ለእነዚህ ዘርፎች ከመሠረታዊ የተጠያቂነት መሥፈርቶች ባለፈ ማንኛውንም ቅድመ ሁኔታ አንቀበልም፣ አንደግፍምም።

ሪፖርተርትግራይ በሰሜን ኢትዮጵያ የነበረው ጦርነት ማዕከል ነበረች። የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ከፍተኛ ባለሥልጣናት ኢትዮጵያን በጎበኙ ቁጥር ወደ ትግራይ በተደጋጋሚ የሚጓዙት በዚህ ግንዛቤ ነው?

አላክባሮቭቆይ ይህንን ጉዳይ ላብራራ። በኢትዮጵያ የተመድ ጽሕፈት ቤት ኃላፊና የሰብዓዊ ዕርዳታ አስተባባሪ እንደ መሆኔ ሁሉንም ክልሎች ጎብኝቻለሁ። በእርግጥ ትግራይ የጦርነቱ ማዕከል ነበረች። ነገር ግን በሌሎች ክልሎች ያለው የሰብዓዊ ዕርዳታ ፍላጎት ከትግራይ አንፃር አነስተኛ ነው ብዬ መግለጽ አልችልም። እንዲያውም በአንዳንድ ቦታዎች ከትግራይም የበለጠ ሰብዓዊ ቀውስ ሊኖር እንደሚችል አስባለሁ። የተወሰኑ የአፋር አካባቢዎችን፣ የአማራና የጋምቤላ አካባቢዎችን ጎበኝቻለሁ፡፡ በእነዚህ አካባቢዎችም ብዙ ችግሮችን አይቻለሁ። አንዳንዶቹም በከፋ ሁኔታ ሊገለጹ የሚችሉ ናቸው። ስለዚህ አንዱን አካባቢ ከሌላው ማወዳደር አልፈልግም። የተመድና ሌሎች የረድኤት ድርጅቶች ባለሥልጣናት ለምን ትግራይ ክልል ደጋግመው ለመጎብኘት መረጡ ለሚለው፣ በጦርነቱ ምክንያት የተለየ ትኩረት ወደ ትግራይ አመዝኗል። በተጨማሪም በጣም ንቁ የሆኑ በውጭ የሚኖሩ የትግራይ ተወላጆች የፈጠሩት ተፅዕኖ አለ። ነገር ግን እኔ ኢትዮጵያን ለመጎብኘት ለሚመጡ የተመድ ኃላፊዎች በሙሉ የማስተላልፈው መልዕክቴ፣ ለሁሉም ክልሎች እኩል ትኩረት ሰጥተው ሁሉንም ባሳተፈና በተደራጀ መንገድ እንዲሠሩ ነው። ገንዘባችንን ወዴት አካባቢ እንደምንልክ፣ የሰብዓዊ ድጋፍ ኢንቨስትመንታችንንና ራሳችንን እንዴት እንደምናደራጅ ብትመለከት ለየትኛውም ክልል የተለየ ቅድሚያ የተሰጠበት ሁኔታ አለመኖሩን መገንዘብ ትችላለህ።

ሪፖርተርዳያስፖራው እንዴት ነው በእንዲህ ዓይነት ሁኔታ ላይ ተፅዕኖ የሚፈጥረው?

አላክባሮቭ፡- እኔ እንደማስበው የውጭ ጎብኚዎች ከዓለም አቀፍ ሚዲያ፣ ከራሳቸው አገር ፓርላማ ወይም ከኢትዮጵያ ዳያስፖራ ቡድን አባላት የሚያገኙትን መረጃ ይዘው ነው ወደ ኢትዮጵያ የሚመጡት። ብዙዎቹ በጣም ንቁ ናቸው፡፡ በተለይም በሰሜን ኢትዮጵያ በተለይም በትግራይ ውስጥ ስላሉ ችግሮች ትኩረት ሰጥተው ነው የሚመጡት። ስለሁሉም ችግሮች ላይናገሩ ይችላሉ። እኔ ኢትዮጵያን ለመጎብኘት የሚመጡ የውጭ ልዑካንን በምቀበልበት ጊዜ አብዛኞቹ የሚያነሱልኝ የመጀመሪያ ጥያቄ ትግራይን የተመለከተ ነው። እኔም ስለትግራይ መጠየቃችሁና መናገራችሁ ተገቢ ነው፣ ነገር ግን እባካችሁ በመላ ኢትዮጵያ ስላለው ችግርም መወያየት አለብን እላቸዋለሁ። በሁሉም የኢትዮጵያ አካባቢዎች ስላለው የሰብዓዊ ድጋፍ ፍላጎት እንወያይ፣ ነገሮችንም ከሰብዓዊ ቀውስ አንፃር ብቻ አንመልከት እላቸዋለሁ። ይህንን የምለው በሰሜን ኢትዮጵያ ያለውን ችግር ለማሳነስ ሳይሆን፣ በሁሉም የአገሪቱ ክፍሎች በጣም ፍትሐዊ በሆነ መንገድ መሰማራታችንን መቀጠል አለብን ለማለት ነው። በየክልሉ እኛን የሚፈልጉ ሰዎች አሉ። ትኩረታችን በሰብዓዊ ፍላጎቶች ላይ ብቻ መሆን የለበትም። በልማት ላይ የበለጠ ትኩረት ሰጥተን መሥራት ስለሚገባን ነው።

ሪፖርተር– ዳያስፖራው የሚያደርገው ጫና በሰብዓዊ ዕርዳታ ተግባራችሁ ላይ ተፅዕኖ አሳድሯል ማለት ነው? 

አላክባሮቭ፡- የኢትዮጵያ ዳያስፖራ የሚያደርገውን እንቅስቃሴ አደንቃለሁ፡፡ ምክንያቱም ግንዛቤን እየፈጠሩ ስለሆነና የተወሰኑ ችግሮች ትኩረት እንዲያገኙ ስለሚያደርጉ። እርግጥ ነው የኢትዮጵያ ዳያስፖራ አባላት ከተለያዩ የኢትዮጵያ አካባቢዎች እንደ መውጣታቸው መጠን፣ በአንዳንዶቹ ችግሮች ላይ የበለጠ ትኩረት ሊሰጡ ይችላሉ። ዞሮ ዞሮ መጨረሻ ላይ ትኩረት የምታገኘው ግን ኢትዮጵያ ነች። የሆነው ሆኖ ይህን የሚያደረጉት ማኅበረሰባቸውን ለማገዝ በመሆኑ በዚህ በጣም ደስ ይለናል። እናም በዚሁ እንዲቀጥሉ አበረታታቸዋለሁ። ነገር ግን አንዳንድ ነገሮችን ማረምና በመሬት ላይ ያለውን የሰብዓዊ ሁኔታ ሙሉ ሥዕል ማስቀመጥ ይገባናል። የሰብዓዊ ቀውስ ሁኔታዎችን ከአንድ ሰው አንፃር ሳይሆን በአጠቃላይና በተሟላ መንገድ መግለጽ ይኖርብናል። ሁሉም ሰው ሰብዓዊ ድጋፍ ለማሰባሰብ መንቀሳቀሱ ጥሩ ነው። ሁሉም ይንቀሳቀስ፣ ነገር ግን በአዎንታዊ መንገድና እውነታውን በመናገር መሆን አለበት። እንደ እውነቱ ከሆነ ሁሉም ሰው ሰብዓዊ ቀውሶችን በአዎንታዊ መንገድ ለመፍታት እየሞከረ ነው። ስለሆነም በአዎንታዊ መንገድ መንቀሳቀስ እንጂ ግጭትና ተቃርኖ ውስጥ መግባት አያስፈልገንም። አንድ አካባቢ የበለጠ ድጋፍ አገኘ ማለት ከሌላው አካባቢ ኮታ ላይ ወስዶ ነው ማለት አይደለም። ወይም ከሌላው አካባቢ የሚያገኘው ተጨማሪ ኮታ ኖሮት ነው ማለት አይደለም። ማንም ሰው በብሔር፣ በሃይማኖት ወይም በሌላ ምክንያት ምግብ ወይም ሌላ የሰብዓዊ ድጋፍ እየተነፈገ አይደለም። አንዳንድ ጊዜ በማኅበራዊ ትስስር ገጾች ላይ እነዚህን ዓይነት ነገሮች ሲሠራጩ እናያለን። ላረጋግጥላችሁ የምፈልገው የሰብዓዊ ዕርዳታ ሥርጭቱ በጣም ፍትሐዊ ነው። በመንግሥት በኩል ከአደጋ ሥጋት አመራር ኮሚሽን ጋር በጣም ተቀራርበን እንሠራለን። ይህ ፕሮጀክትም በተጨባጭ የፍላጎት ምዘና ላይ ተመሥርቶ የሚተገበር ነው።

ሪፖርተርበኢትዮጵያም ሆነ በሌሎች አገሮች በአጠቃላይ ግጭት በሚካሄድባቸው አካባቢዎች ሰብዓዊ ድጋፍ ማድረግ ምን ያህል ከባድ ነው? 

አላክባሮቭ፡- ወታደራዊ ግጭት ያለበት ቦታ ወይም የጦር መሣሪያን የሚያካትት እንቅስቃሴ ባለበት ቦታ ለሚገኙ ማኅበረሰቦች ሰብዓዊ ዕርዳታ ማድረስ አንችልም። እንዲህ ዓይነት ሁኔታ ሲፈጠር ተግባራዊ የምናደርገው የግጭት ወቅት እንቅስቃሴ ዘዴና መርህ አለን። ይህም ግጭቱ የሚካሄድባቸው አካባቢዎች አለመሄድ ነው። እንዲህ ዓይነት ሁኔታ ሲከሰት ለሁሉም አካላት የረድዔት ተቋም መሆናችንንና የሕክምና ዕርዳታ ወይም ምግብ ለማቅረብ ብቻ እየተንቀሳቀስን እንጂ፣ ከየትኛውም ዓይነት ግጭት ጋር ግንኙነት ወይም ተሳትፎ እንደሌለን እናሳውቃለን። ወደ ኢትዮጵያ ከመምጣቴ በፊት በብዙ አገሮችና በተለያዩ ቦታዎች ሠርቻለሁ። እስካሁን ድረስ ኢትዮጵያ ውስጥ ሆን ተብሎ በሰብዓዊ ዕርዳታ ሰጪ ሠራተኞች ላይ የተደረገ ጥቃት እንዳላየሁ ማረጋገጥ እፈልጋለሁ።

ሪፖርተርበሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት ወቅት በሰብዓዊ ዕርዳታ ሰጪዎች ላይ የሚደርሰው ጥቃት ዋነኛ መነጋገሪያ ጉዳይ አልነበረም እንዴ?

አላክባሮቭእኔ እ.ኤ.አ. በ2021 እና በ2022 ኢትዮጵያ ውስጥ አልነበርኩም፣ ስለዚህ በዚያ ጉዳይ ላይ አስተያየት መስጠት አልችልም። ነገር ግን ግጭት በሚካሄድባቸው የኢትዮጵያ አካባቢዎች ያለውን ሁኔታ እኔ ከሠራሁባቸው ቦታዎች (የውጭ አገሮች) ጋር ለማነፃፀር ብሞክር፣ ምንም ነገር እንደማላገኝ ወይም አንድም ነገር ለንፅፅር የሚሆን ምንም ነገር እንደማይኖር በእርግጠኝነት መናገር እችላለሁ። እኔ እንደማስበው ኢትዮጵያ ውስጥ ሁሉም ሰው የሰብዓዊ ድጋፍ ሥራ የጥቃት ዒላማ መሆን እንደሌለበት የሚገነዘብ ይመስለኛል። የዕርዳታ ሠራተኞች የተኩስ ልውውጥ በሚካሄድበት አካባቢ ውስጥ ሳያውቁ ገብተው የተገኙባቸው አጋጣሚዎች ነበሩ እንጂ፣ ሆን ተብሎ በእነሱ ላይ የተደረገ ጥቃት አልነበረም። ስለዚህ ቀደም ብዬ እንደገለጽኩት በግጭት ወቅት ተግባራዊ የምናደርገው የእንቅስቃሴ ዘዴዎች ስላሉን እነሱን በመጠቀም አሁንም የሰብዓዊ ዕርዳታችንን በየክልሉ እያቀረብን ነው። ምናልባት በአንድ አካባቢ ያልጠበቅነው ነገር ተከስቶ ወይም በሆነ ምክንያት የሰብዓዊ ዕርዳታችንን ባሰብነው ቀን ወይም ሳምንት ላናደርስ እንችላለን። ነገር ግን ከየትኛውም ክልል ሰብዓዊ ዕርዳታችንን አቋርጠን አልወጣንም። ይህንን ተግባራችንም በሁሉም የኢትዮጵያ ቦታዎች ማድረስ እንቀጥላለን።

ሪፖርተርበምግብ ዕርዳታ ስርቆት ተፈጽሟል በሚል ምክንያት ዕርዳታ ለበርካታ ወራት ተቋርጦ ነበር፣ ባለፈው ኅዳር ወር እንደገና የተጀመረ ቢሆንም። የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የተቋረጠውን የሰብዓዊ ዕርዳታ ፕሮግራም ዳግም ከመጀመሩ በፊት ምን ዓይነት የሥርጭት ዘዴዎችን ነው ለመከተል የወሰነው? 

አላክባሮቭ፡- የዓለም ምግብ ፕሮግራም (WFP) በተጋላጭነት ላይ የተመሠረተ የሰብዓዊ ዕርዳታ አሰጣጥ ሒደትን በዝርዝር ያቀርባል። ከአጋሮቹ ጋር በጋራ በተጋላጭነት ላይ የተመሠረተ የማነጣጠር ሒደት አዘጋጅተናል። በዚህ ሒደት ማኅበረሰቡ ራሱ በጣም ተጋላጭ የሆኑትን ይለያል። በግምገማው ላይ የተመሠረተውን ለመለየት ከኃላፊዎች፣ ከካህናት፣ ከተመረጡ የማኅበረሰቡ አባላት፣ ከሁሉም የአገር ሽማግሌዎችና ወጣቶች የተውጣጣ ኮሚቴ አለ። ከዚሁ ጋር የተያያዘ የቅሬታ ኮሚቴም አለ። ለጠቃሚዎች ዲጂታል መታወቂያ እየተሰጠ ነው። ባር ኮድ ማድረግና ሁሉንም አቅርቦቶች መከታተልን ጨምሮ የተጀመሩ ብዙ አዳዲስ ዘዴዎች አሉ። ምናልባት ይህ በዓለማችን ካየሁት እጅግ የላቀ የዕርዳታ ሥርጭት ሥርዓት ነው። እንደ እውነቱ ከሆነ ሌላ ቦታ እንዲህ ያለ ነገር አላየሁም። ነገር ግን አሁን ያለው መሠረታዊ ችግር ለምግብ ዕርዳታ የገንዘብ አቅርቦት አለመኖር ነው። እመነኝ ከዚህ ቀደም ስንቀበል የነበረውን የሰብዓዊ ዕርዳታ መጠን ከዚህ በኋላ ማግኘት አንችልም። በዓለም ላይ በየትኛውም ቦታ ሰፊ የምግብ ዕርዳታ የሚቀርብበት ሁኔታ አብቅቷል ወይም ጊዜው አልፏል። ዓለም ተለውጧል። የሰብዓዊ ዕርዳታ በጣም እየቀነሰ ነው። ስለሆነም የበለጠ በራስ አቅም ላይ መተማመንና ራስን ችሎ ለማምረት መሥራት ያስፈልጋል። ለዚህም ነው እኛ ምርጥ ዘርና ሌሎች የግብርና ግብዓቶችን በማቅረብ አገሮች በራስ ላይ የተመሠረተ የግብርና ምርት ማምረት እንዲጀምሩ መደገፍ ላይ ትኩረት አድርገን መሥራት የጀመርነው።

ሪፖርተርየኢትዮጵያ መንግሥት የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ የሚያደርገውን ጥረት እንዴት ይገመግሙታል? 

አላክባሮቭ፡- በኢትዮጵያ ለችግር ተጋላጭ ለሆኑ የኅብረተሰብ ክፍሎች 250 ሚሊዮን ዶላር የሚጠጋውን የስንዴና የምግብ መግዣ ወጪ የሚሸፍነው መንግሥት ነው። የእኛ የሰብዓዊ ሀብት ዕቅድ (HRP) ከመንግሥት ጋር የተጣመረበት ምክንያትም ይህ ነው። የተመድ የረድኤት ኤጀንሲዎች ከመንግሥት ጋር ተቀናጅተው የሚሠሩባት አገር ኢትዮጵያ ብቻ ናት። ለዚህም ነው ብሔራዊ የሰብዓዊ ሥርዓቶች በኢትዮጵያ ጥቅም ላይ የዋለው፡፡ ብሔራዊ የሰብዓዊ ዕርዳታ አቅርቦት ሥርዓት እ.ኤ.አ. በ2016 በቱርክ ኢስታንቡል በተካሄደው የዓለም የሰብዓዊ ጉዳዮች ጉባዔ ላይ ነው ከፍተኛ አድናቆት ያገኘው። 

ተዛማጅ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች ለማግኘት

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች


ተዛማጅ ፅሁፎች

‹‹ግጭቶች በሰብዓዊ ዕርዳታ ሥራዎቻችን ላይ የሚያሳድሩትን አሉታዊ ተፅዕኖና እየተከሰተ ያለውን ሥቃይ እያየን ነው›› ሆላንደር ሆላንደር፣ የአሜሪካ ዓለም አቀፍ ተራድኦ ድርጅት የኢትዮጵያና የጂቡቲ ዋና...

ከበርካታ የአፍሪካ አገሮች መካከል ኢትዮጵያ ለአሜሪካ የቅርብ ወዳጅ እንደሆነች ይነገርላታል፡፡ ክፍለ ዘመንን የተሻገረው የሁለቱ አገሮች ግንኙነት ሰሞኑን ዲፕሎማቲክ ግንኙነት የጀመሩበትን 120ኛ ዓመት ክብረ በዓላቸውን...

‹‹በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚኖሩንን እንቅስቃሴዎች ሊያግዙ የሚችሉ ተቋማት ያስፈልጉናል›› ገመቹ ዋቅቶላ (ዶ/ር)፣ የአይ ካፒታል አፍሪካ ኢንስቲትዩት ዋና ሥራ አስፈጻሚ

የኢትዮጵያንና የምሥራቅ አፍሪካን የፋይናንስ ተቋማት መሠረት በማድረግ በየዓመቱ የሚካሄደው የምሥራቅ አፍሪካ የፋይናንስ ጉባዔ፣ በበርካታ አጀንዳዎች አማካይነት በተለይ ለፖሊሲ አውጪዎች ግብዓቶችን ሲያቀርብ ቆይቷል፡፡ ከዚህ ጎን...

‹‹ኢትዮጵያ ብዙ ፈተና እየገጠማት ቢሆንም ከፈተናው ውስጥ ቀስ እያልን እንወጣለን ብዬ አስባለሁ›› ዳንኤል በቀለ (ዶ/ር)፣ የኢሰመኮ ዋና ኮሚሽነር

ከጥቂት ዓመታት በፊት በኢትዮጵያ የመንግሥት ለውጥ መካሄዱን ተከትሎ  በቀደሙት ጊዜያት ከተቋማዊ ስሙ ባለፈ በሚያከናውናቸው ተግባራት፣ ተቋሙን ይመሩት በነበሩ ኮሚሽነሮች፣ እንዲሁም በአጠቃላይ ተቋማዊ ባህሪው ከአስፈጻሚው...