Monday, April 15, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የድሬዳዋ አስተዳደርና የድሬዳዋ ንግድ ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ውዝግባቸውን ለመፍታት ተስማሙ

ተዛማጅ ፅሁፎች

የድሬዳዋ አስተዳደርና የድሬዳዋ ንግድ ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤትን ለዓመታት ሲያወዛግብ ለቆየው የንግድ ምክር ቤቱ ሕንፃ ዕልባት ይሰጣል የተባለ የመፍትሔ ሐሳብ ላይ ስምምነት ላይ መደረሱ ተጠቆመ፡፡ 

የድሬዳዋ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤትና የጫት እርሻ ዕርባታና ኢንዱስትሪ ውጤቶች ላኪና አስመጪዎች ንብረት የሆነው ባለአራት ወለል ሕንፃ በድሬዳዋ አስተዳደር ያለአግባብ ተወርሶ በመቆየቱ የፌዴራል መንግሥት ለባለቤቶቹ እንዲወስን ቢወስንም ሕንፃውን የወረሰው የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር ሕንፃውን ሊመልስ ባለመቻሉ ከ12 ዓመታት በላይ ሲያወዛግብ መቆየቱ ይታወሳል፡፡ 

በድሬዳዋ የንግድ ኅብረተሰብ የተገነባውን ሕንፃ የከተማ አስተዳደሩ ለራሱ አገልግሎት እየተገለገለበት የሚገኝ በመሆኑ ሕንፃውን አልመልስም በማለት ጉዳዩ በፍርድ ቤት ተይዞ ክርክር ሲደረግበት ቢቆይም ሰሞኑን በአስተዳደሩ፣ በኢትዮጵያና በድርዳዋ ንግድ ምክር ቤቶች መካከል በጉዳዩ ላይ ባደረጉት ውይይት ወደ መፍትሔ ይወስዳል ባሉት ሐሳብ ላይ ስምምነት ሊደርሱ ስለመቻላቸው ጉዳዩን በቅርበት እየተከታተለው የሚገኘው የኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡ 

የኢትዮጵያ ንግድ ምክር ቤት ሕንፃ ለምክር ቤቱ እንዲመለስ ከተወሰነ በኋላ የድሬዳዋና ንግድ ምክር ቤትም የተወረሰበት ሕንፃ እንዲመለስ ውሳኔ ቢተላለፍም ይህ ውሳኔ ተግባራዊ ሳይሆን መቅረቱን ያስታወሱት የኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ዋና ፀሐፊ አቶ ውቤ መንግሥቱ አሁን ግን ሲያወዛግብ የቆየውን ይህንን ጉዳይ በንግድ ለመፍታት ከድሬዳዋ አስተዳደር ጋር መግባባት ላይ መደረሱን ገልጸዋል፡፡ 

አስተዳደሩ ያለአግባብ ወስዶ እየተጠቀመበት የሚገኘውን ሕንፃ በተመለከተ ሁለቱ ወገኖች በቅርቡ ተገናኝተው በመወያየት ችግሩን ለመፍታት ያስችላል የተባሉ አማራጭ የመፍትሔ ሐሳቦች ላይ መነጋገራቸውን አቶ ውቤ ገልጸዋል፡፡ 

የኢትዮጵያ ንግድ ምክር ቤት በተገኘበት የሁለቱ ወገኖች ውይይት ላይ የድሬዳዋ አስተዳደር ሕንፃው ላይ የድሬዳዋ ሬዲዮና ቴሌቪዥን ዋና ማሠራጫነት እየተጠቀመበት በመሆኑና የተከላቸውን መሣሪያዎች ለማንሳት ከባድ እንደሚሆንበት አስታውቋል፡፡ 

ሌሎች የአስተዳደሩ ሥራዎችም በሕንፃው ውስጥ የሚሰጥ በመሆኑ እነዚህን ሁሉ አገልግሎቶች የሚያስተጓጉል በመሆኑ ንግድ ምክር ቤቱ ንብረቱን በሌላ አማራጭ እንዲያገኝ ተመጣጣኝ የሆነ ቦታና የመገንቢያ ገንዘብ ለመክፈል ዝግጁ መሆኑን አስታውቋል፡፡ 

አስተዳደሩ ያቀረበውን ሐሳብ ተንተርሶ የሕንፃው ባለቤት የሆኑት የድሬዳዋ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤትና አስመጪና ላኪዎቹ በጉዳዩ ላይ መክረው የቀረበው የመፍትሔ ሐሳብ ተፈጻሚ ለማድረግ የኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት የድሬዳዋ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት፣ የድሬዳዋ አስተዳደር ከጫት ላኪዎች ማኅበር የተወከሉ አባላት እንዲቋቋም ከስምምነት ላይ ተደርሶ ኮሚቴው ተቋቁሟል፡፡ 

ከድሬዳዋ ንግድ ምክር ቤት ያገኘነው መረጃ እንደሚያመለክተውም በአስተዳደሩ ሕንፃውን ቢመልስላቸው የሚመርጡ ቢሆንም አሁን የቀረበውን የመፍትሔ ሐሳብ አማራጭ በማጣት ለመቀበል መገደዳቸውን የሚያመላክት ነው፡፡ የፌዴራል መንግሥት ውሳኔ በሕግ አግባብ መፈጸም ሲገባው ባለመፈጸሙ ቅሬታ እንዳላቸው ያመላከቱት እኚሁ የድሬዳዋ ንግድ ምክር ቤት ከፍተኛ ኃላፊ አሁንም ጉዳዩ እንዳይጓተትና የተባለው ተፈጻሚ እንዲሆን የሚሹ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡ 

አሁን በተደረገው ስምምነት መሠረት ለሕንፃው ባለቤቶች ሕንፃው ባለመመለሱ ያጡትን ጥቅም ጨምሮ ሕንፃው እንዲመለስ  ውሳኔ ከተሰጠ በኋላ ተበድረው ለሕንፃው ያወጡት የዕድሳት ወጪና ሌሎች አማራጮችን ታሳቢ ያደረገ ካሳ ያስፈልጋል የሚል አቋም አላቸው፡፡ 

ኮሚቴውም ይህን ሁሉ ጉዳይ ከግምት በማስገባት ዕልባት የማይገኝ ከሆነ ግን አማራጭ ስለሌለ አዲሱን የመፍትሔ ሐሳብ የሚቀበሉ መሆኑንም ሳይጠቅሱ አላለፉም፡፡ ኮሚቴው ግን እስካሁን ወደ ሥራ አለመግባቱ ጉዳዩን እንዳጓትተው ግን ሥጋታቸውን ገልጸዋል፡፡ 

በጉዳዩ ላይ ተጨማሪ ማብራሪያ የሰጡን አቶ ውቤ በበኩላቸው አስተዳደሩ ወደዚህ ውሳኔ የገባው ሕንፃውን መመለስ ለአስተዳደሩ ከፍተኛ ወጪን የሚያስከትል በመሆኑ ነው የሚል ማብራሪያ በጉዳዩ ላይ ለመምከር ወደ ድሬዳዋ ተጉዞ ለነበረው የኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ቦርድ እንደተሰጠ ጠቁመዋል፡፡ 

ስለዚህ የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር ካቢኔ ከዚህ በኋላ ሕንፃውን መመለስ ስለማያዋጣ የድሬዳዋ ንግድ ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ለሕንፃው ተመጣጣኝ የሆነ የመገንቢያ ቦታ፣ የሕንፃ መገንቢያ ወጪውና ከዚሁ ጋር ተያይዞ ንግድ ምክር ቤቱ ያወጣውን ወጪ ለመሸፈን ስለወሰነ በዚሁ መሠረት ተፈጻሚ እንዲሆን መግባባት ላይ መደረስ መቻሉን አቶ ውቤ አብራርተዋል፡፡ ከዚህ ውሳኔ ተፈጻሚነት የቴክኒክ ድጋፍ ጭምር ላይ ማድረግ አስተዳደሩ ቃል በመግባት ኮሚቴው መቋቋሙንና የኮሚቴውም መቋቋም ከንቲባው ለሚመለከታቸው ሁሉ በደብዳቤ አሳውቀዋል፡፡ ኮሚቴው ሰባት አባላት ያሉት ሲሆን የኮሚቴው ሰብሳቢ የከተማ አስተዳደሩ ከንቲባ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ሊሆኑ ኮሚቴው ስለመቋቋሙና ሥራውን በተመለከተ ለሚመለከተው ሁሉ የከተማ አስተዳደሩ ከንቲባ በደብዳቤ አሳውቀዋል፡፡ 

ኮሚቴው በሁለት ወሮች ውስጥ ሥራውን አጠናቆ ለከንቲባው እንደሚያቀርብ የገለጹት አቶ ውቤ ይህ ኮሚቴ ዋነኛ ተግባሩ አስፈላጊውን መረጃዎች በማደራጀት በሕንፃው ምትክ ሊሰጥ የሚባውን ክፍያና ሌሎች ሊደረጉ የሚገባቸውን ዕገዛዎች  የሚያቀርብ ይሆናል፡፡ 

እስካሁን የነበረውንም ውዝግብ ለመቋጨት የኢትዮጵያ ንግድ ምክር ቤት የድሬዳዋ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤትና የጫት ላኪዎች ማኅበር በሐሳቡ ላይ የተስማሙ በመሆኑ በተጠቀሰው ጊዜ ውስጥ ኮሚቴው ሥራውን እንደሚጨርስ አቶ ውቤ ያላቸውን ተስፋ ገልጸዋል፡፡ 

ኮሚቴው የሕግ ባለሙያዎችን ጭምር ይዞ የሚሠራ በመሆኑ ትክክለኛ መረጃ በማቅረብ በአጭር ጊዜ ከአስተዳደሩ ቃል በተገባው መሠረት ንግድ ምክር ቤቱና የአስመጪና ላኪ ማኅበሩ የራሳቸውን ሕንፃ እንዲገነቡም የኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ጥራቱን እንደሚቀጥልም ከአቶ ውቤ ማብራሪያ ለመገንዘብ ተችሏል፡፡ 

የኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት የድሬዳዋ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት የሕንፃ በፌዴራል መንግሥት እንዲመለስ ውሳኔ ከተሰጠበት ጊዜ ጀምሮ ጉዳዩን በቅርብ ሲከታተል መቆየቱን ያስታወሱት አቶ ውቤ አሁን የተደረሰበት ስምምነት ላይ ሊደርስ የቻለውም የንግድ ምክር ቤቱ ቦርድ ከድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ጋር ባደረገው ምክክር ነው፡፡ 

አዲስ አበባ ላይ ከሚገኘው የኢትዮጵያ ንግድ ምክር ቤት ሕንፃ ሌላ ሊጠቀስ የሚችል የሕንፃ ባለቤት የሆነው የድሬዳዋ ንግድ ምክር ቤት ጉዳዩ መፍትሔ እስኪያገኝ ድረስ እያጣራ ነውም ተብሏል፡፡ 

በመፍትሔ የተቋቋመው ኮሚቴው በቶሎ ሥራውን እንዲሠራ የማስተባበሩ ኃላፊነት በኢትዮጵያ ንግድ ምክር ቤት ላይ የወደቀ በመሆኑ ኮሚቴው ሥራ ከመጀመሩ በፊት አስፈላጊ ናቸው የተባለ መረጃዎችን እያደራጀ ስለመሆኑም አቶ ውቤ አብራርተዋል፡፡ 

በድሬዳዋ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤትና በኢትዮጵያ የጫት የእርሻ ዕርባትና ኢንዱስትሪ ውጤቶች ላኪና አስመጪ ማኅበር በጋራ የተገነባው ባለአራት ወለል ሕንፃ በፌዴራል መንግሥት ውሳኔ ይመለስ ተብሎ የነበረው በ2003  ዓ.ም. ነው፡፡ 

የድሬዳዋ አስተዳደር ግን ይህንን ትዕዛዝ  ላለመፈጸም በማንገራገሩ ንግድ ምክር ቤቱ በፍርድ ቤት ክስ መሥርቶ ሲከራከር በቀድሞ ጉዳዩ ዕልባት ሳያገኝ ለዓመታት ቆይቷል፡፡ 

ከአዋጅ ውጪ የተወረሰ ንብረት በመሆኑ  ይመለስ የተባለው ሕንፃ ሊመለስልን አልቻለም የሚለው ለጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ጭምር አቤት ቢባልም አዎንታዊ ምላሽ ሳያገኝ መቅረቱም ይታወሳል፡፡ 

የመንግሥት የልማት ድርጅቶች ይዞታና አስተዳደር የሕንፃውን ጉዳይ በተመለከተ ክርክር ሊደረግበት ለነበረው የድሬዳዋ ምድብ ፍትሐ ብሔር ችሎት በጻፈው ደብዳቤ የሕንፃው ባለቤቶች ሕንፃው የተመለሰላቸው  በመሆኑ በዚህ መሠረት ተፈጻሚ እንዲሆንላቸው ጠይቆ እንደነበር አይዘነጋም፡፡ 

አሁን ስምምነት ላይ በተደረሰበት መንገድ ጉዳዩ ዕልባት የሚያገኝ ከሆነ በፍርድ ቤት ከዚህ ቀደም ከሊዝ ነፃ ቦታና የመገንቢያ ቦታ ይሰጣቸው የሚል የተወሰነውን ውሳኔ ያጠናክራል ተብሏል፡፡ 

ንግድ ምክር ቤት ግን እስካሁን ሲከራከር የቆየው ይህም የፍርድ ቤት ውሳኔ ተፈጻሚ ሊሆንልኝ አልቻለም በሚል እንደነበር መገለጹ አይዘነጋም፡፡ 

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች