Saturday, April 20, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ከ40 በላይ የታክሲ ማኅበራት ከተሽከርካሪ አስመጪዎች ጋር የገቡት ውል ባለመፈጸሙ ለከፍተኛ ጉዳት መዳረጋቸውን ተናገሩ

ተዛማጅ ፅሁፎች

  • አስመጪው ኩባንያ ሙሉ ክፍያ ለፈጸሙ አስረክቤያለሁ ብሏል

ኦክሎክ ጄኔራል ትሬዲንግ ከተባለ ኩባንያ ጋር ውል ፈጽመናል ያሉ ከ40 በላይ የታክሲ ማኅበራት፣ ተሽከርካሪዎቻቸውም እንዳልቀረቡላቸው በመግለጽ ቅሬታ አቀረቡ፡፡

ከ40 በላይ የቱሪስት ታክሲ ማኅበራት፣ በሥራቸው ከሁለት ሺሕ በላይ አባላት እንዳላቸው ገልጸው፣ በኦክሎክ ጄኔራል ትሬዲንግ ኩባንያ አቅራቢነትና በሄሎው ታክሲ መዝጋቢነት አባሎቻቸው 60 ሺሕ ብር እና ቅድመ ክፍያ በመፈጸም እንደተዋዋሉ የማኅበሩ አባላት ተናግረዋል፡፡

በ2014 ዓ.ም. ደግሞ በውላቸው መሠረት የጠቅላላ ክፍያውን 35 እና 40 በመቶ ቅድመ  ክፍያ የፈጸሙ ቢሆንም፣ ምንም ዓይነት ተሽከርካሪ እንዳልቀረበላቸው የማኅበራቱ አባላት መጋቢት 21 ቀን 2016 ዓ.ም. ባደረጉት ውይይት አስረድተዋል፡፡

ድርጅቱ የገባውን ውል በአግባቡ ባለመፈጸሙ መንግሥት የሰጣቸውን ከቀረጥ ነፃ ዕድል ከዓላማው ውጪ በማዋል፣ ገንዘባቸውን ለዓመታት ያላግባብ እየተጠቀመበት መሆኑን፣ በደልና ክህደት እንደተፈጸመባቸው አባላቱ ለጋዜጠኞች ገልጸዋል፡፡ ሠርተው ለመለወጥ ያላቸውን ንብረት ሸጠው ድርጅቱን በማመን ለዓመታት ቢጠብቁም እንዳልተሳካላቸውና ዛሬም ሰሚ አጥተው በመንከራተት ላይ እንደሚገኙ ገልጸዋል፡፡

በማኅበራቱ አባላት የተነሱ ጥያቄዎች ፈጽሞ ስህተት ናቸው ሲሉ የኦክሎክ ጄኔራል ትሬዲንግ ኩባንያ ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ታመነ ካሳሁን ለሪፖርተር ምላሽ  ሰጥተዋል፡፡

ሙሉ ክፍያን ለማይከፍሉ ማናቸውም የማኅበሩ አባላት ድርጅቱ  ምንም ዓይነት ተሽከርካሪ የመስጠት ግዴታ እንደሌለበት ገልጸዋል፡፡

ሰላሳ አምስት በመቶ ቅድመ ክፍያ የከፈሉ የማኅበሩ አባላት ተሽከርካሪ ተገጣጥሞ  ሲደርሳቸው፣  ቀሪውን 65 በመቶ  ክፍያ በመፈጸም መረከብ እንደሚችሉ  አቶ ታመነ አስረድተዋል፡፡

 ድርጅቱ የትኛውንም  አበዳሪ ተቋም የማቅረብ ኃላፊነት የለበትም ያሉት  ዋና ሥራ አስኪያጁ፣ ማኅበራት በራሳቸው መንገድ ከአበዳሪ ተቋማት ጋር በመዋዋል ገንዘብ  ማቅረብ እንደሚችሉ ተናግረዋል፡፡

በማኅበራት ስም ከቀረጥ ነፃ ገብተው የተገጣጠሙ ታክሲዎችን ከማኅበሩ አባላት ውጪ ለማንም እንዳልሸጡ ተናግረው፣  የተመዘገቡ የማኅበሩ አባላት ሙሉ ክፍያ ፈጽመው ባለመውሰዳቸው ተሽከርካሪዎቹ አገልግሎት ሳይሰጡ ተቀምጠዋል ሲሉ አክለዋል፡፡

ድርጅቱ የመንግሥት አካላት በተገኙበት ለተመረጡ ሰዎች ገንዘብና አቅም ላለቸው መርጦ በሚዲያ ሰጠሁ ብሎ በሚያሳየው የውሸት ዜና መንግሥትን በማሳመን፣ ከልጆቻቸው ጉሮሮ ላይ ወስደው ቤታቸውንና ንብረታቸውን አስይዘው ለቆጠቡት ግን ተስፋ ብቻ እንደሚመግባቸው የተናገሩት የማኅበሩ አባላት ናቸው፡፡

‹‹መረጃ ለማሰባሰብ ገዥ መስለን ስንሄድም ሙሉ ክፍያ ከፍላችሁ መውሰድ ትችላላችሁ በማለት ይነግሩናል፤›› ሲሉ አንድ የማኅበሩ አባል ተናግረዋል፡፡

‹‹ገንዘባችንን ሰጥተን  ዘወትር ወደ ኦክሎክ ጄኔራል ትሬዲንግ በር ተመላላሽ ሆነናል፤›› ያሉት አስተያየት ሰጪው፣ የሚመለከታቸው አካላት መፍትሔ  እንዲያበጁላቸው ጠይቀዋል፡፡

‹‹በአንድ ዓመት ውስጥ ያለ ምንም ጭማሪ  ገጣጥሞ  እንደሚያስረክብ  ሰብስቦ አወያይቶን ነበር፤›› የሚሉት ሌላ አባል ደግሞ፣ የተለያዩ ምክንያቶችን በመደርደር ከዕጥፍ በላይ ትርፍ በመፈለግ ድርጅቱ ሲያጓትት መቆየቱን አክለዋል፡፡

‹‹ከአራት ዓመት በላይ ገንዘባችን የባለሀብት መጠቀሚያ ሁኖ ቆይ~ል፤›› የሚሉት አባሉ፣ በስማቸው የመጣውን ዕድል እንደነፈጋቸው ቅሬታቸውን አቅርበዋል፡፡

በ2014 ዓ.ም. ከጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ተወክለው እንደመጡ የተናገሩት ኃላፊ በተገኙበት  ስብሰባ ከቀረጥ ነፃ እንደተፈቀደላቸውና በአንድ ዓመት ውስጥ እጃቸው እንደሚገባ ቃል ቢገባም፣ ‹‹የደረሰን ነገር የለም፤›› ሲሉ የማኅበሩ አባል የሆኑት ወ/ሮ ትዕግሥት አጥላው ተናግረዋል፡፡

ድርጅቱ የመመዝገቢያውን ጭምሮ 35 በመቶ ለከፈለ ተመዝጋቢ በአጭር ጊዜ ውስጥ እንደሚሰጥ ቃል በገባው መሠረት፣ ገንዘብ በማጣታቸው 25 በመቶውን ከፍለው ቀሪውን ለማሟላት እየሞከሩ ቢሆንም፣ ነገር ግን ስድስት መቶ ሺሕ ብር ከፍለው ያልደረሳቸውን በማየት ተስፋ መቁረጣቸውን ተናግረዋል፡፡

ቅድመ ክፍያውን ለማሟላት ሲሞክሩ በየጊዜው የሚያሻቅበው ከዕጥፍ በላይ የሆነ የዋጋ  ጭማሪ ሌላው ፈተና እንደሆነባቸው ወ/ሮ ትዕግሥት ገልጸዋል፡፡

ማኅበራቱ በሕጋዊ መንገድ የመንግሥት አካላት በተገኙበት ውል ከፈጸሙ ጀምሮ  ከ1.2 ቢሊዮን ብር በላይ ወደ ኦክሎክ ጄኔራል ትሬዲንግ መግባቱን የተናገሩት ደግሞ፣ የማኅበሩ ሰብሳቢ አቶ ጉዑሽ መብራህቶም ናቸው፡፡

ድርጅቱ ተሽከርካሪዎችን በወቅቱ  ካለማቅረቡም ባሻገር ከአባላቱ የሰበሰበውን ገንዘብ  ያለ ምንም ወለድ እየተጠቀመበት እንደሚገኝ አቶ ጉዑሽ አስታውቀዋል፡፡

ኦክሎክ ጄኔራል ትሬዲንግ ሙሉ በሙሉ ሥራ አላቆመም ያሉት ሰብሳቢው፣ ከስምምነቱ ውጪ ከየማኅበራቱ ሙሉ ክፍያ የፈጸሙትን ደውሎ በመጥራት ከአንድ ማኅበር ቢያንስ ለሁለትና ለሦስት አቅም ላላቸው ሰዎች እየሰጠ ነው ሲሉ አብራርተዋል፡፡

በስምምነቱ መሠረት ከ35 እስከ 40 በመቶ የከፈለ ሰው ቀሪውን ከአበዳሪ አካላት ተበድሮ መክፈል የሚቻል ሲሆን፣ ለዚህም አሚጎስ የተባለ ብድርና ቁጠባ ተቋም ለማበደር ፈቃደኛ ቢሆንም፣ ድርጅቱ ሆን ብሎ አልተስማማንም በሚል ምክንያት መቋረጡን  አቶ ጉዑሽ ገልጸዋል፡፡

ከድርጅቱ ጋር ሲዋዋሉ በወቅቱ የነበረው ዝቅተኛው የመኪና ዋጋ 520 ሺሕ እንደነበር ያስታወሱት አቶ ጉዑሽ፣ በአሁኑ ወቅት ከ1.9 ሚሊዮን እስከ ሁለት ሚሊዮን ብር መድረሱን ተናግረዋል፡፡ ኦክሎክ ጄኔራል ትሬዲንግ በየወቅቱ ጭማሪ ሲያደርግ ለአንድም የታክሲ ማኅበራት ሳያሳውቅ በፈለገው መንገድ እንደሆነ አክለዋል፡፡

‹‹ድርጀቱ ያሉበትን ችግሮች ከማኅበራት ጋር ተቀራርቦ ለመነጋገር እንኳን ፈቃደኛ አይደለም፤›› ያሉት ሰብሳቢው፣ ችግሩን እንዲያስረዳ በተደጋጋሚ በደብዳቤና በተለያዩ የመገናኛ ዘዴዎች ጥሪ ቢደረግለትም ለመወያየት ፈቃደኛ እንዳልሆነ አብራርተዋል፡፡

ከዚህ ይልቅ ድርጀቱ የማኅበሩን አባላት ከስምምነቱ ባፈነገጠ መልኩ የፊርማ ሰነድ በማዘጋጀት ግለሰቦችን እየጠራ ለሌላ አራት ዓመት ለማዋዋል እየሞከረ ነው ብለዋል፡፡

ከቻይና በስድስትና በሰባት ሺሕ ዶላር ከቀረጥ ነፃ የገባ ተሽከርካሪ የማኅበሩ አባል ሙሉ ክፍያ መክፈል  ስላልቻለ ለሌላ  ሰው ሁለትና ሦስት ሚሊዮን ብር መሸጥ ወንጀል ነው ሲሉ አቶ ጉዑሽ አክለዋል፡፡

ድርጅቱ ከማኅበራት በተሰጠው ተደጋጋሚ ጥያቄና አቤቱታ መሠረት  ያበላሸውን አስተካክሎ በአጭር ጊዜ ማቅረብ ካልቻለ፣ የሚመለከታቸው የመንግሥት አካላት ጉዳዩን በትኩረት እንዲከታተሉት ሲሉ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

በውለታው መሠረት ተሽከርካሪ ማቅረብ የማይችል ከሆነ  ለሥራ ማስኬጃ የተከፈለውን ጨምሮ  ከአባላቱ የሰበሰበውን ክፍያ ከእነ ከወለዱ ተሠልቶ  ተመላሽ እንዲሆን፣ ተበዳዮች ደግሞ  ሌሎች አማራጮችን እንድፈልጉ ሲሉ ሰብሳቢው  ጠይቀዋል፡፡

በ2013 ዓ.ም.  520  ሺሕ ብር ያወጣ የነበረ የአንድ ተሸከርካሪ ዝቅተኛ ዋጋ በአሁኑ ወቅት  ከሁለት ሚሊዮን ብር ማለፉን የተናገሩት አቶ ጉዑሽ፣ ምንም  እንኳን  ምንዛሪ ሲጨምር  የአባላቱ ክፍያ ይጨምራል የሚል ስምምነቱ ላይ ቢኖርም ነገር ግን ሁሉም  የማኅበሩ አባላት  ተወያይተውና ተስማምተው መሆን ነበረበት ብለዋል፡፡ ነገር ግን ድርጀቱ ያለ ስምምነት ዋጋ  በየወቅቱ  እየጨመረ መቆየቱን  ተናግረዋል፡፡

በውሉ መሠረት አንድ የማኅበሩ አባል ከማኅበሩ መውጣት ቢፈልግ በሦስት ወራት ውስጥ ገንዘቡ ተመላሽ ይሆናል የሚል ቢኖርም፣ ገንዘባቸውን በመመለስ ከማኅበሩ ለመውጣት  የሚጠይቁ ግለሰቦች  በወቅቱ እንደማይመለስላቸውና  ከዚህ ይልቅ  ሦስተኛ ወገን እንዲገባበት እየተደረገ  ነው ሲሉ  ቅሬታቸውን አቅርበዋል፡፡

የድርጅቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ በበኩላቸው የማኅበሩ አባላት በቅድሚያ ማኅበሩን መልቀቃቸውን ማስረጃ ካመጡ፣ ገንዘባቸው ተመላሽ እንደሚደረግላቸው ተናግረዋል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትራንስፖርት ቢሮ በበኩሉ ዜናው እስከ ተጠናቀረበት  ድረስ ከሚድያ አካላት ማብራሪያ ከመጠየቅ ውጪ ከየትኛውም አካል ቅሬታ እንዳልደረሰው ለሪፖርተር አስታውቋል፡፡

የኢትዮጵያ ሕዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋም ጉዳዩ ከታክሲ ማኅበራቱ እንደደረሰውና በጉዳዩ ላይ ለመወያየት ማቀዱን ገልጿል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች