Wednesday, April 17, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

ንቅለ ተከላ!

ትዕግሥትን በተፈታተነ የረዥም ሰዓት ጥበቃ አንዲት አሮጌ ሚኒባስ ታክሲ መጣች። እነሆ ከፈረንሣይ ሌጋሲዮን በአራዳ ጊዮርጊስ ወደ መርካቶ ልንጓዝ መሆኑ ነው። መሀል አራዳ ፈራርሶ ቁፋሮ በመጀመሩ የመንገዱ አቅጣጫ በወትሮው እንዳልሆነ ግንዛቤ ይያዝ። ‹በእንቅስቃሴ ውስጥ ትግል፣ በትግል ውስጥ ለውጥ› የሚሉት ጽንሰ ሐሳብ የማይታወቅ ይመስል፣ ሁሉም ቦታ ስለመለወጥ እየተወራ ነው። እናም ሕይወታችን በግፊት የውጥር ተይዛ እየተንገዳገደች፣ ይህም ኑሮ ተብሎ መውተርተር አይቀርም፡፡ የሰው ልጅ ከእምነቱ፣ ከፍልስፍናው፣ ከፍላጎቱና ከምኞቱ ለአፍታ ገለል ሳይል የሚፈተነው በእንዲህ ያለ ከባድ ጊዜ ነው። ጊዜ ደግሞ ዋናው የለውጥ መካኒክ ነውና። ‹‹ጎበዝ በትዕግሥት እንደጠበቃችሁን ተረጋግታችሁ ተሳፈሩ…›› እያለ ወያላው ማሳሰቢያ ሲሰጥ፣ ‹‹እንኳን አንተ ላይ ያሉትም ሳይነግሩን ትዕግሥትንና ጥንቃቄን ተላምደነዋል…›› የምትለው መሀል ወንበር ከዳር በኩል እየተቀመጠች ያለች ቀጭን ኮስታራ ሴት ናት፡፡ የእሷ ከሲታ ፊት ላይ የሁላችንም የኑሮ የሸራ ምሥል የተወጠረ ይመስላል፡፡ ‹ተኖረና ተሞተ…› አሉ አለቃ ገብረ ሃና!

ወያላው ተሳፋሪዎችን ተራ በተራ አስገብቶ ሲጨርስ ሾፌሩን ‹‹ሳበው…›› ከማለቱ አሮጌዋ ሚኒባስ መንደርደር ጀመረች፡፡ ወደ መርካቶ የሚደረገው ጉዞ የበርካታ ምስኪኖችን ስብስብ ያቀፈ ለመሆኑ ምስክሩ፣ ብዙዎቹ ኑሮ የከበዳቸውና ሰውነታቸው የገረጣ መሆኑን መደበቅ አለመቻሉ ነው፡፡ ጋቢና ሁለት ሽበት ወጋ ወጋ ያደረጋቸው ጎልማሶች፣ ከሾፌሩ ጀርባ ኑሮ የደቆሳቸው ሁለት እናቶች፣ መሀለኛው ወንበር ላይ ቀጭኗ ኮስታራ ሴትና የቀን ሥራ ያደከመው የሚመስል ወጣት፣ ከእነሱ ጀርባ ሁለት የሚተክዙ ሴት ወጣቶች፣ መጨረሻ ወንበር ላይ በኑሮ ተቀራራቢ የሆኑ ጭቁን መሳይ አዛውንት፣ ወጣትና ጎልማሶች ተሰይመዋል፡፡ ያቺ ትርፍ የምትባለው የወያላ መከዳ ላይ ኑሮና መጠጥ አንድ ላይ ያደቀቁት የሚመስል ጎልማሳ መሳይ ወጣት ተቀምጧል፡፡ ከወያላው መቆሚያ ጀርባ የተሸጎጡ በትርፍነት የተጫኑም አሉ፡፡ እነዚህ የፈረንሣይ ሌጋሲዮንና አካባቢው ነዋሪዎች እንጀራ ሆኖባቸው በጠዋት ወደ መርካቶ ለጉዳዮቻቸው አንድ ላይ ጉዞ ጀምረዋል፡፡ ሾፌርና ወያላም የዚያው አካባቢ ሰዎች ይመስላሉ፡፡ ተመሳሳይ ላባ ያላቸው ወፎች በሏቸው!

ወያላው ሒሳቡን እየተቀበለ፣ ‹‹ዝርዝር ካላችሁ ተባበሩኝ…›› ሲል፣ ‹‹ዘንድሮ እንኳን ሃምሳና መቶ ብር ባለሁለት መቶ ኖቱም ዝርዝር በለው…›› የምትለው ያቺ ኮስታራ ሴት ናት። ሾፌሩ ደግሞ፣ ‹‹ትርፍ ጭነሃል እንዴ?›› ብሎ ድንገት በርግጎ ጠየቀው። ‹‹አዎ ሁለት አሉኝ፣ ምነው?›› ከማለቱ ሾፌሩ በብስጭት፣ ‹‹ስንቴ ትርፍ አትጫን ብዬ ላስጠንቅቅህ አንተ ዕብድ? ያው ሁለት ሆነው ቆመዋል…›› ብሎ ትራፊክ ፖሊሶቹን እየጠቆመ የታክሲዋን ፍጥነት አቀዘቀዘ። ወያላው በበኩሉ፣ ‹‹አንተ ደግሞ ሀቀኝነት ማንን ሲያነሳውና ሲያከብረው አይተህ ነው ትርፍ አልጭንም የምትለው? እየተበላንም ቢሆን መሥራት አለብን ፍሬንድ…›› ብሎ ያደፋፍረው ጀመር። ትራፊክ ፖሊሶቹ አፍ ለአፍ ገጥመው እያወሩ ሳያዩን አለፍናቸው እንጂ፣ ሾፌሩ ቢያዝ ኖሮ የመንገዱ መጨናነቅ ተጨምሮበት ተገትረን መዋላችን ነበር። ‹‹አቤት ሥራና ወሬ፣  በዚህ ዓይነት ስንቱ አገር አጥፊ ይሆን ተዝናንቶ የሚኖረው? ኧረ አቋራጩና ተቆራራጩ በዛ?›› አለች መጨረሻ ወንበር የተቀመጠች ወጣት። ‹‹ምናልባት አዲሱ የልማት መርሐ ግብር እንዲህ ዓይነቱን ልግመኝነት ያስቆም ይሆን?›› ብሎ ፈገግ አለ አንዱ። ፈገግታው ለፎቶ ይመስላል!

‹‹አበስኩ ገበርኩ…›› ይላሉ መጨረሻ ወንበር የተቀመጡ አዛውንት። ግርማ ሞገሳቸው ልዩ ነው። ፀገሩራቸው ሪዛቸውን ጨምሮ ቡፍ ብሎ ቆሟል። ‹‹ምነው አባት? ምን ሆኑ?›› አጠገባቸው የተቀመጠች አጭር ቀይ ኮረዳ ታናግረዋለች። ‹‹ይኼ መልሶ ማልማት የሚሉት ነገር እየጨነቀኝ ነው…›› ሲሉ መለሱላት። ‹‹አይዞዎት ማን የሚሆነውን ያውቃል ብለው ነው?›› ለማወጣጣት ነው ነገሩ። ‹‹ለዚህ እኮ ነው ልጄ ነጋ ጠባ ፈጣሪን አሟሟቴን አሳምረው የምለው። እሱስ ሳይሰለቸው ቀረ ብለሽ ነው?›› ፍስስ ይላሉ ደርሰው በተመስጦ። ‹‹ምነው ካልጠፋ ነገር አሟሟትዎ ያስጨንቀዎታል? ልጆች የሉዎትም? ባለቤትዎስ?›› የምትለቃቸው አትመስልም ወጣቷ። ‹‹ኧረ ሁሉም አሉ፣ የሁሉም አጠገቤ መኖር ነው አንድም የሚያሳስበኝ። በዚያ ላይ አንዳንዱ በአሟሟቱ ይበደልና በአቀባበሩ ይካሳል። ለምሳሌ ይኼው እንደምትሰሚው ከኖርንበት ቀዬ ተፈናቅለን ስንበታተን ቀባሪያችን ዕድራችንም አድራሻው አይታወቅም። የአገር መልማትና መለወጥ ቢያስደስተኝም የእኛ መጨረሻ ግን ያሳስበኛል…›› ብለው ተከዙ፡፡ አንጀት ይበላሉ!

‹‹አባት አይዞዎት፣ በቀደም ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትሩ ደካማ እናቶችና አባቶች እንዳይጎዱ ለሹማምንት ሲያሳስቡ ነበር፡፡ እሳቸው እንዳሉት የኮሪደር ልማቱ ነዋሪዎችን የበለጠ ተጠቃሚ ለማድረግ የታቀደ ስለሆነ፣ እርስዎንና መሰለዎችን፣ እንዲሁም ሌሎች ዜጎችን ይጎዳል የሚለውን የጠላት ወሬ አይስሙ…›› ሲላቸው አንዱ ከፊት በኩል አዛውንቱ ፈገግ አሉ። ፈገግታቸው ውስጥ ያለው ስሜት ባይታወቅም የፊታቸው ፀዳል ግን በጣም ደስ ይላል፡፡ ‹‹ማነህ አንተ ልጅ፣ እኔም የተናገሩትን ሰምቻለሁ፡፡ አዛኝነት የተሞላበት የሚመስለው ንግግራቸው መልካም ነው፡፡ እኔ ግን የሚያሳስበኝ ግሬደሩንና ቡልዶዘሩን የሚያሰማራው የታችኛው ሹም ርኅራኄ አልባነት ነው፡፡ ከላይና ከታች ያለው ሲናበቡ ችግር የለውም፡፡ ለተጠያቂነትም አያስቸግርም፡፡ እኔን የሚያስፈራኝ በአደባባይ የሰማነው መልካም ቃል በጓሮ በኩል እየተጣሰ መከራችንን እንዳያበላን ነው…›› ሲሉ በአንክሮ አዳመጥናቸው፡፡ እኛ የታክሲ ተሳፋሪዎች ያዳመጥነውን ሹማምንቱም ቢያዳምጡት ያስብላል፡፡ ይኸው ነው!

ጉዞ እየቆየ ነውና የሚያስተያየው አንድ እርጉዝ ተሳፋሪ በረዥሙ ስትተነፍስ ሰማናት፡፡ ብዙም ሳትቆይ፣ ‹‹እኔስ ምን አማረኝ መሰላችሁ?›› ብላ ዓይናችን አስፈጠጠችው። በዚህ የኑሮ ውድነት እርጉዝ እናቶች እንዳማራቸው ሳይበሉ እንደሚወልዱ ድንገት ብናስብ ዘመኑን ክፉኛ ረገምነው። ‹‹ምን አማረሽ የእኔ ልጅ?›› አሉዋት አዛውንቱ በትዝታ ወደኋላ እያጠነጠኑ ያሉ መስለው። ‹‹ዱባይ መሄድ…›› ብላ ቀጣዩን ቃል ሳትናገር፣ ‹‹ጉድ እኮ ነው የዘንድሮ እርግዝና ምነው ምግብና መጠጡን አስትቶ ቱሪዝም ላይ ሆነሳ? የእኔዋ ባለፈው አይፎን ፕሮማክስ አማረኝ ብላ ባለ በሌለ አቅሜ አስገዛችኝ…›› ብሎ ወደ ጎልማሳነት ዕድሜ እየተጠጋ ያለ ከሲታ ወጣት ተናገረ። በሞት መሀል ሕይወት የሚዘራ እንዴት ደግ ነው እናንተ!

‹‹ኧረ እኔ አልጨረስኩም፣ እኔ ለማለት አስቤ የነበረው አገሬ ኮምፒዩተር፣ ስልክ፣ መኪና፣ ባቡርና ምንድነው ይኼ ሀብት የሚባለው ማምረቻ እንድትሆን በሚል ምኞት እኮ ነው ዱባይ መሄድ አማረኝ ያልኩት…›› ስትል ሁካታው ጋብ አለ። ‹‹ምናለበት የእኔዋም እንደ አንቺ ወደ ኢንዱስትሪ አገርነት የመሸጋገራችን ዕቅዱ መሳካት ቢያምራት? ችግሩ ሁላችሁም ቢያምራችሁ ከተማው ፈርሶ እንደገና ተገንብቶ ሳያልቅ ምርምር የሚኖር አይመስለኝም…›› አላት። ‹‹ውይ ዘንድሮ ቆንጆ ቆንጆ ሴቶቻችን የብራንድ አምባሳደር እየተባሉ ዘመናዊ ሆቴሎችን፣ ካፌና ሬስቶራንቶችን፣ የቴክኖሎጂ ኩባንያዎችንና ሌሎች ዘመናዊ ነገሮችን እንደሚያስተዋውቁት፣ ለምን ድህነትን በተባበረ ክንድ ለማጥፋት ትልቅ መርሐ ግብር ተዘርግቶ አምባሳደር አይሆኑልንም?›› ብሎ ከኋላችን ካሉት ወጣት ተሳፋሪዎች አንደኛው ሌላውን ቢጠይቀው፣ እንዳልሰማ ሆኖ ሌላ ወግ አስጀመረው። እውነቱን ነው ያልሆነ ቦታ የማይሆን ፈንጂ ረግጦ የነገር አጀንዳ ከሚቀሰቅስ በዘዴ ዞር ማለት ይሻላል፡፡ ‹‹በግራ አሳይቶ በቀኝ መታጠፍ›› ይሉ ነበር የድሮ አራዶች፡፡ የዛሬን አያድርገውና!

‹‹ይኸው በልማት ሰበብ መንገዱ ሁሉ ተዘጋግቶ አሠሪዎቻችን፣ አሰማሪዎቻችን፣ ኢንቨስተሮቻችን በታክሲ ጥበቃ የምናጠፋውን ጊዜ እያሰቡ የአበልና የደመወዝ ጭማሪ ቢያደርጉልን ምናለበት?›› አለ የማይሰማ መስሎት አንድ ወጣት እየተንሾካሾከ። ‹‹ታክሲ የምንሠለፍበትንና የምንጠበቅበት ይታሰብልን ማለትህ ነው?›› ይለዋል ጓደኛው። ‹‹ታዲያስ እንዲህ ተሰባብረን እንዳንሆን ሆነን እየፈጋን የማርፈድ ቅጣት ሰለቸን…›› እያለ ምሬቱን ከቀልድ ወደ ምር ሲያሸጋግረው፣ ‹‹እናንተ ይኼ ነበር የቀረን፣ መቼ ይሆን ሰበብ እየፈለግን ከዚህች ደሃ አገር ጉሮሮ ቀምተን ለመጉረስ ማሰብ የምናቆመው?›› ትላለች ያቺ ኮስታራ ቀጭን ሴት። ‹‹አሄሄ አንቺ ትንሹን ጉርሻ ትያለሽ፣ ምናለበት በልማት ስም የሚዘረፈው መጠኑ የማይታወቅ ሀብት መግቢያው በታወቀ፡፡ በዚህ ላይ ግልምጫውና ሽኩቻውስ ባበቃ አትይም?›› አሉ አዛውንቱ። አሁንም ገላጋይ መጥቶ ሁሉም ጥጉን ይዞ ሕይወቱን ሊያድን ያሸመቀ ድንጉጥ ይመስል ወጉ ኮስተር ሲል ዝምታ ይፈጠራል፡፡ ፍራቻ ይባላል!

አንዳንዱ ከራሱ ብሶት እየተነሳ አስተያየቱን ሲዘነዝር፣ ብዙኃኑ ደግሞ በፍርኃት ሲያዳምጡ ቆይተው ድንገት፣ ‹‹ለመሆኑ አገራችን በየዓመቱ በስንት አኃዝ ነበር እያደገች ነው የተባለው?›› ብሎ ጎልማሳው ሲጠይቅ ‹በፊት በሁለት ነበር አሁን ግን እንጃ› ብሎ ጎን ለጎን ተቀመጡ ወጣቶች አንዱ መለሰለት። ‹‹እሺ እኛና ኑሯችን በስንት አኃዝ ነበር ቁልቁል የምንወርደው?›› ሲል ግን እንኳን የሚመልስ የሚተነፍስ ጠፋ። አዛውንቱ ግን፣ ‹‹አንድ ሰሞን የኩላሊት ንቅለ ተከላ የሚባል ሕክምና በስፋት ይሰማ ነበር፡፡ አሁን ደግሞ በመልሶ ማልማት ስም የማኅበረሰብ ንቅለ ተከላ እንዳይኖር መንግሥትን አደራ ብንለው ምን ይመስላችኋል…›› እያሉን መርካቶ ደርሰን ወያላው ‹‹መጨረሻ…›› ሲለን ዱብ ዱብ እያልን ወረድን፡፡ ግን ነገር ግን ሁላችንም ፍርኃትን ልባችን ውስጥ ደብቀን በሰመመን ስንራመድ አንድ ድምፅ ከሩቅ ይሰማ ነበር፡፡ አዛውንቱ ስለ‹ንቅለ ተከላ› ያነሱት ጉዳይ ግን ልባችን ውስጥ ተሰንቅሮ ተለያየን፡፡ መልካም ጉዞ!

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት