Saturday, April 20, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ኪንና ባህልለአካዴሚያ ውለታ የተሰጠ ክብር

ለአካዴሚያ ውለታ የተሰጠ ክብር

ቀን:

ከወደ አንጀኒ ምን ይሰማል? (1986)፣ የስንኝ ማሰሮ (2008)፣ ከጉሬዛም ማርያም እስከ አዲስ አበባ፣ የሕይወት ጉዞና ትዝታዬ (2008)፣ የህያው ፈለግ (2010)፣ ከየት ወዴት? (2011)፣ ወረርሽኝ (2011) የተሰኙ መጻሕፍትን ጽፈዋል፡፡ በርካታ ቁጥር ያላቸው የምርምር ጽሑፎችንም በዓለም አቀፍ ጆርናል ለማሳተም ችለዋል፡፡ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የተፈጥሮና ሥነ ቀመር ሳይንስ ኮሌጅ ለምርምር የሚውሉና እንደ መማሪያ የሚያገለግሉ ጽሑፎችን በመጻፍ፣ የአካባቢ ተፅዕኖ ጥናትን በተመለከተ መስኩን ፈር የሚያሲይዙ ጽሑፎችን በማበርከትም የላቀ ድርሻ አላቸው፡፡ ‹‹ታዛ›› እና ‹‹ዘመን›› በተባሉ መጽሔቶች ለኅብረተሰቡ የሳይንስ ግንዛቤን የሚሰጡ መጣጥፎችን ሳይታክቱ በመጻፍም ይታወቃሉ፡፡ የሥነ ሕይወት መምህር፣ ተመራማሪ እንዲሁም የአካባቢ ሳይንስ ጥናት ባለሙያ የሆኑት ፕሮፌሰር ኤመረተስ ሽብሩ ተድላ፡፡

የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የተፈጥሮና ሥነ ቀመር ሳይንስ ኮሌጅ (College of Natural and Computational Sciences) መጋቢት 20 ቀን 2016 ዓ.ም. ፕሮፌሰር ኤመረተስ ሽብሩ ተድላ ሕይወት ዘመን አገልግሎት ላበረከቱት አስተዋጽኦ የምሥጋናና የዕውቅና መድረክ አዘጋጅቶ ነበር፡፡

በመድረኩ ላይ የቀድሞ ተማሪያቸው፣ ኋላም የሙያ ባልደረባቸው የሆኑት ማስረሻ ፈጠነ (ፕሮፌሰር) እንደተናገሩት፣ ፕሮፌሰር ሽብሩ ተድላ፣ ከ1962 ዓ.ም. ጀምሮ፣ በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዩኒቨርሲቲ በኋላም አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በመምህርነት፣ በትምህርት ክፍል ኃላፊነት፣ በድኅረ ምረቃ ፕሮግራም ዲንነት፣ በምርምርና ኅትመት ዳይሬክተርነትና በሴኔት አባልነት አገልግለዋል፡፡ በ1987 ዓ.ም. የጡረታ መብታቸውን አስከብረው ከወጡ በኋላም በኤመረተስ ፕሮፌሰር ማዕረግ፣ በዩኒቨርሲቲው የቦርድ አባል በመሆንና በተለያዩ የመማክርት ጉባዔዎች በአባልነት እያገለገሉ የሚገኙ አንጋፋ ምሁር ናቸው፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

‹‹ፕሮፌሰር ሽብሩ ተድላ፣ ፈረንጆች ‘Larger than life’ [ከሕይወትም የላቀ] የሚሉት ዓይነት የጎላ የተፈጥሮ፣ የሰብዕናና የባህሪ መገለጫ ያለው ሙሉ ሰው ነው፡፡ ምን ጊዜም ለመማር ዝግጁ የሆነ ፈጣን አዕምሮ የያዘ፣ ላመነበት ጉዳይ ወደ ኋላ የማይል፣ ፍርኃት የማያውቅና ድፍረት የተላበሰ፣ በጎ ነገር ከማድረግ የማይቆጠብ፣ ዘወትር ከሌሎች ለመማርና ለማወቅ የሚተጋ፣ ጨዋታና ቁምነገሩ የማይጠገብ ነው፤›› ያሉት ማስረሻ (ፕሮፌሰር) በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተቋም ግንባታ ላይ ሰፊ ተሳትፎ የነበራቸው ከመሆኑ ባሻገር ከዩኒቨርሲቲ ውጪ ለኢትዮጵያ የዱር እንስሳትና የተፈጥሮ ጥበቃ ማኅበር ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማበርከታቸው፣ የኢትዮጵያ ተሰነአዊ ቴክኖሎጂን (Ethiopian Society for Appropriate Technology) በመመሥረትና በማሳደግ፣ የኢትዮጵያ ሳይንስ አካዴሚን እንዲደረጅና በእግሩ እንዲቆም በማድረግ በኩልም ጉልህ ሚና መጫወታቸውን የሥነ ጽሑፍ ወዳጅነታቸውና የታሪክ አዋቂነታቸው የዘርፉን ባለሙያዎች የሚያስደምምና የጠለቀ መልዕክት የያዙ ስንኞችን የሚቋጥር ገጣሚ ናቸው ብለዋል፡፡

በተለይ ደግሞ ሳይንስን ለሕዝብ ለማድረስ (ማኸዘብ) በርካታ መጻሕፍትንና መጣጥፎችንም በማበርከት ላይ ይገኛሉ፡፡

የአካዴሚያ ሕይወት

የሥነ ሕይወት ፕሮፌሰሩ ሽብሩ፣ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ በ1955 ዓ.ም. ከተመረቁ በኋላ ለሕክምና ትምህርት ቤት ቴክኒሺያኖችን ለማሠልጠን በመጣ ስኮላርሺፕ ወደ እንግሊዝ አገር፣ ሊቨርፑል ዩኒቨርሲቲ በ1956 ዓ.ም. አቅንተዋል፡፡ በዩኒቨርሲቲው በቴክኒሽያንነት እየሠለጠኑ እያለ በተጨማሪ የዩኒቨርሲቲውን የመግቢያ ፈተና በማለፍ የማስተር ዲግሪያቸውንም፣ የቴክኒሽያንነት የምስክር ወረቀታቸውንም ይዘው በ1958 ዓ.ም. ተመልሰዋል፡፡

በዚሁ ዓመት የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዩኒቨርሲቲ የሕክምና ፋኩሊቲና የሳይንስ ፋኩሊቲ ጣምራ ተቀጣሪ ሆነው ሥራ ሲጀምሩ፣ ለቅድመ ሕክምና ተማሪዎች (የሜዲካል ፓራሲቶሎጂ) መምህርና ከአክሊሉ ለማ (ዶ/ር) ጋር የቢልሃርዝያ ተመራማሪ በመሆን ነው፡፡ በአዋሽ ሸለቆ የቢልሃርዝያን ሥርጭት ለማጥናት የተቋቋመውን ቡድን በመምራትም ከፍ ያለ አስተዋጽኦ አበርክተዋል፡፡

በ1959 ዓ.ም. ወደ ካናዳ፣ ወተርሉ ዩኒቨርሲቲ በመሄድም የዓሳ ጥገኛ ተህዋስያንን በማጥናት የፒኤችዲ ዲግሪ ትምህርታቸውን አጠናቀው በ1962 ዓ.ም. ተመልሰዋል፡፡

ፕሮፌሰር ሽብሩ በ1962 ዓ.ም. በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዩኒቨርሲቲ የሥነ ሕይወት ትምህርት ክፍል አባል ሆነው ሲቀጠሩ፣ ከእሳቸው ከጥቂት ወራት በኋላ ከተቀላቀሉት ተወልደ ብርሃን ገብረ እግዚአብሔር (ዶ/ር) ውጪ በወቅቱ ሌላ ኢትዮጵያዊ መምህር እንዳልነበረ የሚገልጹት ፕሮፌሰር ማስረሻ፣ በመሆኑም የሥነ ሕይወት ትምህርት ክፍልን በሰው ኃይል የመገንባት ኃላፊነት ፕሮፌሰር ሽብሩ ጫንቃ ላይ የወደቀ ኃላፊነት ነበር፡፡ በመሆኑም ይህንን ክፍተት ለመሙላት ፕሮፌሰር መስፍን ታደሰን፣ ፕሮፌሰር ጌታቸው ተፈራን፣ ፕሮፌሰር በየነ ጴጥሮስን፣ ፕሮፌሰር አፈወርቅ በቀለ፣ ፕሮፌሰር ደምሰውን፣ ፕሮፌሰር ዘሪሁን ወልዱን፣ ፕሮፌሰር ሽመልስ በየነንና እኔን (ፕሮፌሰር ማስረሻ ፈጠነ) ለተፈጥሮና ሥነ ቀመር ኮሌጅ መምህራን በመቅጠር ውጤት ያመጡ ናቸው፡፡ በእርሳቸው የተቀጠሩት ምሁራን ዛሬ ሁሉም በየመስካቸው አንጋፋ ፕሮፊሰሮች ለመሆን የበቁ መሆናቸውንም ገልጸዋል፡፡

ፕሮፌሰር ሽብሩ ከመስከረም 1987 ዓ.ም. ጀምሮ የጡረታ መብታቸውን በማስከበር ከዩኒቨርሲቲው ተሰናብተዋል፡፡ ከጡረታ በኋላ በአካባቢ ጥበቃ፣ በአካባቢ ተፅዕኖ ግምገማና ጥናት ላይ ተሰማርተው እንደ አገር የላቀ አበርክቶ ያላቸውን ውጤታማ ሥራዎች በማበርከት ላይ ይገኛሉ፡፡ የአካባቢ ተፅዕኖ ጥናት ፕሮቶኮልና ሥልት በማዘጋጀትም በቀዳሚነት ሊጠቀሱ የሚችሉ ናቸው፡፡

ፕሮፌሰሩ ሽብሩ በብዙ የተቋማት ግንባታ ውስጥ ጉልህ ድርሻ የነበራቸው መሆኑን የሚናገሩት ፕሮፌሰር ማስረሻ፣ በተለይም የኢትዮጵያ ሳይንስ አካዴሚ በመጋቢት 2002 ዓ.ም. ሲቋቋም ፕሮፌሰር ሽብሩን ምክትል ፕሬዚዳንት አድርጎ የመረጠ ሲሆን፣ አካዴሚውን በሕግ በፓርላማ የተደነገገ አካዴሚ በማድረግ፣ ቋሚና ታሪካዊ የሆነ ጽሕፈት ቤት እንዲኖረው በማስቻልና በመንግሥት በጀት የሚንቀሳቀስ ተቋም እንዲሆን በትጋት ሠርተዋል፡፡

የኢትዮጵያ ሳይንስ አካዴሚን ቢሮ ከማቋቋም፣ ከማደራጀትና ፕሮጀክት ከማፈላለግ ባሻገር ዘጠነኛውን የአፍሪካ ሳይንስ አካዴሚዎች ጉባዔ በማዘጋጀት አካዴሚው በአኅጉር ደረጃ እንዲታወቅ በማድረግ በኩልም ጉልህ ድርሻ ነበራቸው፡፡

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በተፈጥሮና ሥነ ቀመር ኮሌጅ የብዝኃ ሕይወት መምህር የሆኑት ፕሮፌሰር ሰብስቤ ደምሰው እንደተናገሩት፣ ፕሮፌሰር ሽብሩ ከሃምሳ ዓመታት በላይ በዩኒቨርሲቲው በመምህርነትና በተመራማሪነት አገልግለዋል፡፡ በዩኒቨርሲቲው ቆይታቸውም በሳይንሱ ዘርፍ ውጤት ያመጡ የምርምር ሥራዎችን ከማበርከት ባሻገር ተማሪዎችን በማብቃትና ተቋም በመገንባት ሒደት ጉልህ ድርሻ አበርክተዋል፡፡

በ1966 ዓ.ም. በነበረው የሥርዓት ለውጥ የውጭ አገር መምህራን አገሪቱን ጥለው በሄዱበት ወቅት ፕሮፌሰር ሽብሩ የኮሌጁ ኃላፊ በመሆናቸው ይህን ክፍተት በመሙላትና እስከ ዛሬም ድረስ አገር የምትኮራባቸውን ምሁራን በማፍራት ለአገር ታላቅ ተግባር የከወኑ ባለውለታ ናቸው፡፡

አገር ጥለው በሄዱ የውጭ መምህራን ምትክ በፕሮፌሰር ሽብሩ ተመልምለው ከተቀጠሩ መምህራን መካከል አንዱ እኔ ነኝ የሚሉት ፕሮፌሰር ደምሰው፣ ፕሮፌሰር ከትምህርቱ (ከሳይንስ) ባሻገር የዘርፈ ብዙ ተሰጥኦ ባለቤት፣ አንደበተ ርቱዕ፣ የአገሪቱን ታሪክ በጥልቀት ለመፈተሽ የሞከሩና ያሰቡትን ነገር ከግብ ሳያደርሱ እንቅልፍ የማይወስዳቸው ሰው መሆናቸውን ይገልጻሉ፡፡

የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የተፈጥሮና ሥነ ቀመር ኮሌጅ ለእኚህ ጎምቱ ምሁር የዕውቅናና የምሥጋና ሽልማት ማዘጋጀቱ የሚያስመሠግነው ነው ያሉት ፕሮፌሰሩ፣ ላበረከቱት ውለታና ከፍ ያለ አስተዋጽኦ በተቋም ብቻ ሳይሆን በአገር አቀፍ ደረጃ ዕውቅና ሊሰጣቸው የሚገባ ነው ብለዋል፡፡

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የተፈጥሮና የሥነ ቀመር ኮሌጅ ለሰጣቸው ዕውቅና ከፍ ያለ ምስጋና ያቀረቡት ፕሮፌሰር ሽብሩ ተድላ እንደተናገሩት፣ ይህ ዓይነቱ የምሥጋናና የዕውቅና ሥነ ሥርዓት የኮሌጁ ባህል ሆኖ መቀጠል ይገባል ሲሉም አሳስበዋል፡፡

‹‹ይህ ኮሌጁ ለእኔ የሰጠውን ዕውቅና ማግኘት እየተገባቸው ሳያገኙ የቀሩና ለዩኒቨርሲቲው ዕድገት ከፍ ያለ አስተዋጽኦ ያበረከቱ በርካታ ግለሰቦች አሉ፡፡ ከእነዚህም መካከል አንዱ የሳይንስ ትምህርት እንዲዳብር፣ በተለይም ለሥነ ሕይወት ትምህርት ክፍል ዕድገት ከፍተኛ አበርክቶ የነበረው ጓደኛዬና ወዳጄ ዶ/ር ተወልደ ብርሃን ገብረ እግዚአብሔር ነው፤›› በማለት አስገንዝበዋል፡፡

‹‹ከመስከረም 1952 ዓ.ም. ጀምሮ በተማሪነት፣ በመምህርነትና ጡረታ ከወጣሁም በኋላ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ጋር በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ መንገድ ያልተቋረጠ ግንኙነት አለኝ፤›› የሚሉት ፕሮፌሰሩ፣ ድኅረ 1966 አብዮቱን ተከትለው የተከሰቱ ውስብስብ ችግሮች በወቅቱ ፈተና ሆነውባቸው ነበር፡፡ ሆኖም እነዚህን ችግሮች ለመፍታት ያደረጉት ጥረት አሁን ላገኙት ዕውቅናና ሽልማት መሠረት የጣሉላቸው ሆነው ማለፋቸውን ያስታውሳሉ፡፡

‹‹የአብዮቱ መከሰት በዩኒቨርሲቲው የሰው ኃይል ፍላጎት ላይ ብዙ ተፅዕኖ አሳድሯል፡፡ በመጀመሪያ የውጭ አገር መምህራን አገር እየለቀቁ ወጡ፣ በሁለተኛ ደረጃ ለትምህርት የተላኩት ወጣት መምህራን ከመመለስ ተቆጠቡ፡፡ ሦስተኛ ወደ ውጭ ልኮ የማስተማሩ ዕድል እየመነመነ ሄደ፣ ዕድል ቢገኝም ወደ ውጭ ሊላኩ የሚችሉ ምሩቆች ትምህርታቸውን ጨርሰው የመመለሳቸው ሁኔታ አጠራጣሪ እየሆነ መጣ፡፡

‹‹ዩኒቨርሲቲው ትምህርት እንዴት ያስተናግድ? መምህራን ከየት ይምጡ? ያሉትን መምህራን እንዴት እናሠልጥን? የሚሉት በወቅቱ ከፍተኛ ችግሮች ሆኑ፡፡ ይህ ውጥረት ባለበት የድኅረ ምረቃ ትምህርት በሥነ ሕይወት ትምህርት ክፍል እንዲጀመር መወሰኑ ሌላ ጣምራ ችግር ሆኖ ተከሰተ፡፡

እንደ ፕሮፌሰር ሽብሩ፣ እነኚህ የተከሰቱ ድርብርብ ችግሮች እሳቸው የትምህርት ተቋሙን እየመሩ በሚገኙበት ወቅት በመሆኑ እነኚህን ችግሮች ለመቅረፍ ከፍተኛ ኃላፊነትንና ጠንካራ ውሳኔን የሚጠይቅ ነበር፡፡

በመሆኑም የሥነ ሕይወት ትምህርት ክፍል የመጀመሪያ ተቀዳሚ ዋና ተግባር ያደረገው፣ ወጣት መምህራን ወደ ውጭ አገር ሄደው የሚማሩበትን መንገድ መፈለግ ነው፡፡ ሌላው እነኚህን ምሁራን ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ጋር የሚያቆራኝ፣ እትብታቸው እንዳይቋረጥ የሚረዳ (መፍትሔ) አብሮ መታሰብ ስለነበረበት፣ ለድኅረ ምረቃ ትምህርት ትኩረት የሰጠ የሳንድዊች ፕሮግራም (Sandwich Programme) የሚባለው ተተለመ፡፡

የሳንድዊች ፕሮግራም ለፒኤችዲ የሚማሩ ወጣት መምህራን ወደ ውጭ ሄደው ለአንድ ዓመት በቀለም ትምህርት እንዲማሩ ማስቻል፣ ቢዚህም ጊዜ የተደራጁ መጻሕፍት ቤቶች ተጠቃሚዎች ሆነው መረጃ እንዲሰበስቡ፣ ይህንንም ተግባር በሚያከናውኑበት ጊዜ በበሳል መምህራን ዕውቀት ተሞክሮ ተጠቃሚ እንዲሆኑ፣ ብሎም የምረቃ ምርምሮቻቸውን ዕቅድ በበቂ መረጃ ላይ ተመሥርተው እንዲነድፉ ማስቻል ነበር፡፡ በተጨማሪም እያንዳንዱ የድኅረ ምረቃ ምርምር በኢትዮጵያ እንስሳት፣ ዕፀዋት ወዘተ ላይ ተመሥርቶ፣ ኢትዮጵያ ውስጥ እንዲካሄድ የሚያደርግ እንደነበር ይገልጻሉ፡፡

እንደ ሥነ ሕይወት ፕሮፌሰሩ ገለጻ፣ የሥነ ሕይወት ክፍል ለሰው ኃይል ግንባታ ያገለገሉ ሁለት ዓበይት የምርምር ፕሮጀክቶች ነበሩት፡፡ አንደኛው ‹‹የፍሎራ ፕሮጀክት›› በተወልደ ብርሃን መሪነትና በስዊድን መንግሥት ዕርዳታ ይሄድ የነበረው ነው፡፡ ሌላው የዓሳ ጥናት ፕሮጀክት በእሳቸው መሪነት በካናዳ መንግሥት ድጋፍ የተካሄዱ ነበሩ፡፡ በእነኚህ ሁለት ፕሮጀክቶችና በተጓዳኝ የትምህርት ዕድል ብዙ የፒኤችዲ ምሩቃንን ለማፍራት ተችሏል፡፡

‹‹እኔ እሠራ በነበረው ፕሮጀክት ጠቅላላ፣ ስድስት ሙሉ ፕሮፌሰሮች፣ እኔንም ከእኔም በኋላ ሥዩም መንግሥቱን፣ ዝናቡ ገብረ ማርያምን (የሐዋሳ ዩኒቨርሲቲ የመጀመሪያ ፕሬዚዳንት የነበረው) እና ሌሎችን ያስተማሩ በሥነ ሕይወት ክፍል ትምህርት እያንዳንዳቸው ቢያንስ ለስድስት ወራት በመምህርነትና ተመራማሪነት ተሳታፊዎች ነበሩ፡፡ በእነዚህና በሌሎችም ምክንያቶች ምሁራንን ለማብቃት በተሠራው ሥራ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በሥነ ሕይወት ትምህርት ክፍል ሙሉ የፕሮፌሰርነት ማዕረግን የተጎናፀፉ መምህራን በላቀ ሁኔታ ሊገኙ ችለዋል፤›› በማለት ይገልጻሉ፡፡

ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ አርባ ምሁራን ያለአግባብ ሲባረሩ፣ እኔም በፈቃዴ ዩኒቨርሲቲውን ለመልቀቅ ወስኜ፣ ለቆ የመውጣት ሒደቱን ሕጋዊ በማድረግ ከ1987 ዓ.ም. ጀምሮ ዩኒቨርሲቲውን እንደለቀቁ የሚናገሩት ፕሮፌሰሩ፣ ሆኖም ግን ለዩኒቨርሲቲው ጋር ያላቸው ግንኙነት አለመቋረጡንና ከጡረታ በኋላም የዩኒቨርሲቲው የቦርድ አባል ሆነው ሲያገለግሉ ቆይተዋል፡፡

የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የተፈጥሮና ሥነ ቀመር ሳይንስ ኮሌጅ የፕሮፌሰር ኤመረተስ ፕሮፌሰር ሽብሩ ተድላን ለመዘከርና ዕውቅና ለመስጠት ባዘጋጀው መድረክ፣ የቀድሞ የኢትዮጵያ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኰንን፣ በየነ ጴጥሮስ (ፕሮፌሰር) እና ሌሎችም የቀድሞ ተማሪዎቻቸው፣ የሥራ ባልደረቦቻቸው፣ ጓደኞቻቸውና ቤተሰቦቻቸው ተካፋዮች ነበሩ፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ሰላማዊ የፖለቲካ ትግልና ፈተናው

የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) የፖለቲካ ኦፊሰር የአቶ በቴ ኡርጌሳን...

አበጀህ ማንዴላ! አበጀሽ ደቡብ አፍሪካ!

በአየለ ት. የፍልስጤም ጉዳይ የዓለም አቀፍ ፖለቲካንም ሆነ የተባበሩት መንግሥታትን...

የውጭ ባለሀብቶች ለኢትዮጵያውያን ብቻ በተፈቀዱ የንግድ ዘርፎች እንዲገቡ የመወሰኑ ፋይዳና ሥጋቶች

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አዓመድ (ዶ/ር) የውጭ ኩባንያዎች በጅምላና ችርቻሮ...