Wednesday, April 17, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ዓለምአዲሱ የሴኔጋል ፕሬዚዳንት ባሲሩ ዲዮማዬ  ፋዬ

አዲሱ የሴኔጋል ፕሬዚዳንት ባሲሩ ዲዮማዬ  ፋዬ

ቀን:

ሴኔጋላውያን በአገሪቱ ታሪክ በዕድሜ ትንሹ የተባሉትን የ44 ዓመት ጎልማሳ ፕሬዚዳንታቸው አድርግው የመረጡት ባለፈው ሳምንት ነበር፡፡

ተመራጩ ፕሬዚዳንት ባሲሩ ዲዮማዬ ፋዬ ከተቃዋሚ ጎራ የመጡ ሲሆን፣ 54 በመቶ ድምፅ በማግኘት የሴኔጋል ፕሬዚዳንትነቱን ሥልጣን ከማኪ ሳል የተረከቡት ከእስር በተለቀቁ በአሥረኛ ቀናቸውና ልደታቸውን በሚያከብሩበት ዕለት ነው፡፡

አዲሱ የሴኔጋል ፕሬዚዳንት ባሲሩ ዲዮማዬ  ፋዬ | Ethiopian Reporter | ሪፖርተር
የሴኔጋል ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ መራዘም አገሪቱን ተቃውሞ ውስጥ ከቷት ነበር
(ሮይተርስ)

በተሰናባቹ ፕሬዚዳንት ፍላጎት ከወር በፊት ሊካሄድ የነበረው ምርጫ መራዘም፣ በምዕራብ አፍሪካዊቷ ሴኔጋል ተቃውሞ በመቀስቀሱ፣ የአገሪቱ ሕገ መንግሥታዊ ምክር ቤት ምርጫው በወር ውስጥ እንዲካሄድና የቀድሞ ፕሬዚዳንት ሥልጣንም እ.ኤ.አ. ከሚያዝያ 2024 እንዳያልፍ ውሳኔ ማስተላለፉ ይታወሳል፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

ይህንን ተከትሎ ሰባት ሚሊዮን የአገሬው ሰዎች በተሳተፉበት ምርጫ፣ የፕሬዚዳንትነት መንበሩን ለመቆናጠጥ የሚያስችል ድምፅ ያገኙት ፋዬ፣ በአገሪቱ ሙስናን ጨምሮ እየተስተዋሉ ያሉ ችግሮችን ይቀርፋሉ ተብሎ ተስፋ ተጥሎባቸዋል፡፡

ማክሰኞ መጋቢት 24 ቀን 2016 ዓ.ም. ቃለ መሐላ የፈጸሙት ፕሬዚዳንት ፋዬ፣ በአገሪቱ ለውጥ እንደሚያመጡ ቃል ገብተዋል፡፡

ከአስር ቀናት በፊት ከእስር በምሕረት ከተለቀቁት ተቃዋሚ ፖለቲከኞች አንዱ የሆኑት የአሁኑ ፕሬዚዳንት፣ የምርጫ ቅስቀሳቸው የተጀመረው እሳቸው እስር ቤት እያሉ ነበር፡፡

የታክስ ተቆጣጣሪ ሆነው በሚያገለግሉበት ወቅት በአገሪቱ የተንሰራፋውን ሙስና ለማየት የቻሉት የሕግ ባለሙያው ዲዮማዬ፣ አሁንም በእስር ላይ ከሚገኙትና ከምርጫ ውድድር ከታገዱት ዝነኛው ፖለቲከኛ ኦስማን ሶንኮ ልምድና ዕውቀት የቀሰሙ ናቸው፡፡

ፕሬዚዳንት ፋዬ ምርጫውን ማሸነፋቸውን ተከትሎ ባደረጉት ንግግርም፣ በሥልጣን ዘመናቸው ለአገራዊ ዕርቅ፣ የኑሮ ዋጋን ለማቅለልናን ለሙስና መዋጋት ቅድሚያ እንደሚሰጡ ጠቁመዋል፡፡

የነዳጅ ዘይት፣ ጋዝና የዓሳ ምርት ዘርፉን በማዘመንና በማሳደግም የሴኔጋልን ሉዓላዊነት መልሰው እንደሚገነቡ ተናግረዋል፡፡

ፋዬ የምዕራብ አፍሪካ የኢኮኖሚና የሞኒታሪ ዩኒየን አባላት የሆኑት ሴኔጋልን ጨምሮ ስምንት የምዕራብ አፍሪካ አገሮች ከሚጠቀሙበት ሴንትራል አፍሪካ ፍራንስ (ሲኤፍኤ ፍራንክ) አገራቸውን የማስወጣት ፍለጎት አላቸው፡፡

በሲኤፍኤ መገበያየት የፈረንሣይ የቅኝ ግዛት ውርስን (ሌጋሲ) የሚያስቀጥል ነው የሚሉት ፕሬዚዳንቱ፣ በግብርና ላይ ኢንቨስት በማድረግ አገራቸው በምግብ ራሷን እንድትችል ማድረግ ግባቸው መሆኑም ፍራንስ 24 ዘግቧል፡፡

‹‹ሴኔጋል ከሁሉም አገሮች ጋር ተስማምታና በተዓማኒነት ትሠራለች፡፡ ከሴኔጋል ጋር በተለያዩ ዘርፎች ተከባብሮና ሁሉንም ተጠቃሚ በሚያደርግ መልኩ ለመሳተፍ ከሚፈልግ ጋር እንሠራለን፤›› ብለዋል፡፡

ላለፉት 30 ዓመታት መጣ ሄደት በሚል ካለፈው አንድ ወር ወዲህ ደግሞ ጠንከር ባለ ተቃውሞ ስትሸበር ለኖረችው ሴኔጋል፣ ዴሞክራሲያዊ ምርጫ ተካሂዶ የፕሬዚዳንትነት ሥልጣኑ በተቃዋሚ እጅ መውደቁ፣ ከአሜሪካ እስከ ፈረንሣይ፣ ከአፍሪካ ኅብረት እስከ የአውሮፓ ኅብረትን ይሁንታ አግኝቷል፡፡

የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከንም፣ ከፋዬ ጋር በነበራቸው የስልክ ቆይታ፣ አሜሪካ ከሴኔጋል ጋር ጠንካራ ትብብር የመፍጠር ፍላጎት እንዳላት ገልጸዋል፡፡

ለሴኔጋል ሁለንተናዊ ዕድገት ተስፋ የተጣለባቸው ፋዬ፣ በወታደራዊ መፈንቅለ መንግሥት ወታደራዊ አገዛዝ ሥር በመውደቃቸው፣ ከምዕራብ አፍሪካ የኢኮኖሚ ማኅበረሰብ (ኢኮዋስ) የታገዱት ቡርኪና ፋሶ፣ ማሊ፣ ጊኒና ኒጀር ወደ ማኅበረሰቡ እንዲመለሱ እንደሚፈልጉም አስታውቀዋል፡፡

የአዲስ ትውልድ ፖለቲካ በሴኔጋል

በሴኔጋል የፖለቲካ ታሪክ እ.ኤ.አ. በ2014 የአሁኑ ፕሬዚዳንት ፋዬ እና ዕውቁ ፖለቲከኛ ኦስማን ሶንኮ የመሠረቱት ፓስተፍ ፓርቲ፣ በዚያኑ ዓመት በመንግሥት እንዲፈርስ መደረጉ፣ ወጣቶች በፖለቲካ እንዲሳተፉ ዕድል የፈጠረ ነበር፡፡ የወጣቱን አዲስ ትውልድ ፖለቲካ ይወክላሉ የተባሉት ፋዬ፣ ከብዙ ውጣ ውረድ በኋላ ዛሬ ሥልጣኑን ለማግኘታቸውም የወጣቱ ድጋፍ አስተዋጽኦ አድርጓል፡፡

ለቀድሞ የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማና ለደቡብ አፍሪካ ፀረ አፓርታይድ ታጋይ ኔልሰን ማንዴላ አድናቆትን በመቸር የሚታወቁት ፋዬ፣ በወጣቱ ዘንድ ይበልጥ ተቀባይነትን ቢያገኙም፣ ወሳኝ ፈተናዎች ይጠብቃቸዋል፡፡

በሴኔጋል ብሔራዊ ምክር ቤት አብላጫ ወንበር አለማግኘታቸው አዳዲስ ሕጎችን ለማሳለፍ አንዱ ተግዳሮት በመሆኑም፣ ከሌሎች ጋር ጥምረት መፍጠር ግድ ይላቸዋል፡፡

18 ሚሊዮን ሕዝብ ባላት ሴኔጋል፣ 75 በመቶ ያህሉ ሕዝብ ከ35 ዓመት በታች መሆኑና የሥራ አጥ ቁጥር 20 በመቶ መድረሱ፣ ሌላው የተመራጩ ፕሬዚዳንት ፈተና ነው፡፡

በርካታ ወጣቶች የተሻለ ሕይወት ፍለጋ ወደ አውሮፓ የሚያደርጉት አደጋ የተሞላበት ስደትም፣ ሌላው ፕሬዚዳንቱ መፍታት የሚገባቸው ችግር ከመሆኑ አጃንስ ፍራንስ ፕሬስ ዘግቧል፡፡ 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ሰላማዊ የፖለቲካ ትግልና ፈተናው

የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) የፖለቲካ ኦፊሰር የአቶ በቴ ኡርጌሳን...

አበጀህ ማንዴላ! አበጀሽ ደቡብ አፍሪካ!

በአየለ ት. የፍልስጤም ጉዳይ የዓለም አቀፍ ፖለቲካንም ሆነ የተባበሩት መንግሥታትን...

የውጭ ባለሀብቶች ለኢትዮጵያውያን ብቻ በተፈቀዱ የንግድ ዘርፎች እንዲገቡ የመወሰኑ ፋይዳና ሥጋቶች

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አዓመድ (ዶ/ር) የውጭ ኩባንያዎች በጅምላና ችርቻሮ...