Monday, April 15, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ስፖርትበዓለም አገር አቋራጭ ሁለተኛ የወጣው የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ቡድን

በዓለም አገር አቋራጭ ሁለተኛ የወጣው የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ቡድን

ቀን:

በሰርቢያ ቤልግሬድ ከተማ አስተናጋጅነት የተካሄደው 45ኛው የዓለም አገር አቋራጭ አትሌቲክስ ሻምፒዮና፣ ባለፈው ቅዳሜ መጋቢት 21 ቀን 2016 ዓ.ም. ተከናውኗል፡፡ ሁለት ወርቅ፣ አምስት ብርና ሁለት የነሐስ በድምሩ 10 ሜዳሊያዎችን ያስመዘገበው የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ልዑክ፣ ትናንት ረፋድ ላይ አዲስ አበባ ሲገባ አቀባበል ተደርጎለታል፡፡

በዓለም አገር አቋራጭ ሁለተኛ የወጣው የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ቡድን | Ethiopian Reporter | ሪፖርተር

ሁለቱ ወርቆች ዕድሜያቸው ከ20 ዓመት በታች በሆኑ ሴቶች በነጠላና በቡድን በማሸነፋቸው የተገኙ ናቸው፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

ምሥረታውን አንድ ብሎ አራት አሠርታትን ያሳለፈው የዓለም አገር አቋራጭ አትሌቲክስ ሻምፒዮና፣ ዘንድሮ ከ51 አገሮች የተውጣጡ በአጠቃላይ 485 አትሌቶችን አሳትፏል፡፡ በመድረኩ ከውጤታማ አገሮች ተርታ የሚጠቀሰው የኢትዮጵያ አትሌቲክስ፣ በአምስት ምድብ ማለትም ድብልቅ ሪሌ 4 በ2 ጨምሮ በ6 ኪ.ሜ.፣ በ8 ኪ.ሜ. እና በ10 ኪ.ሜ. የሩጫ ውድድር ላይ 14 እንስቶችና 14 ወንዶች በድምሩ 28 አትሌቶች ተሳትፎ ነበራቸው፡፡

ለወትሮ በተተኪ አትሌቶች ክፍተት በተደጋጋሚ ሲተች የሚደመጠው የኢትዮጵያ አትሌቲክስ፣ በቤልግሬዱ፣ የዓለም አገር አቋራጭ ውድድር ላይ በወጣት ሴቶች ስድስት ኪሎ ሜትር ውድድር ላይ ያስመዘገበው ውጤት ጣልቃ ሳያስገቡ ከአንድ እስከ ሦስት በመግባት ማሸነፋቸው አረንጓዴው ጎርፍ አሰኝቷል፡፡

በርቀቱ የተሳተፉት አትሌቶች በተለይም ከአንደኛ እስከ ሦስተኛ ያለውን ደረጃ በመያዝ ያጠናቀቁ ከመሆናቸው ባሻገር፣ ለመሸናነፍ የነበራቸው ፍላጎትና ያሳዩት ትንቅንቅ የዓለም መገናኛ ብዙኃንን ሳይቀር ሲያስደምም ታይቷል፡፡ የውድድሩ አሸናፊ ማርታ ዓለማየሁ ውድድሩን ለማጠናቀቅ የፈጀባት ጊዜ 19፡28 ሲሆን፣ ሁለተኛና ሦስተኛ አይቸውና ሮቤ ዲዳ 19፡32 እና 19፡38 ነበር፡፡

ከሦስቱ ባለድሎች በተጨማሪ በቡድን ወርቅ እንዲገኝ ተፎካክረው 6ኛ፣ 8ኛና 9ኛ ደረጃን የጨበጡት የኔዋ ንብረት፣ ለምለም ንብረትና ሽቶ ጉሚ ናቸው፡፡

በወጣት ወንዶች 8 ኪሎ ሜትር የብር ሜዳሊያ፣ እንዲሁም በድብልቅ ሪሌ (ዱላ ቅብብል) 8 ኪሎ ሜትር የብር ሜዳሊያ ሲገኝ፣ በአዋቂ ሴቶች 10 ኪሎ ሜትር ውድድር ግን ውጤት አልተገኘም፡፡ በአዋቂ ወንዶች በሪሁ አረጋዊ ሁለተኛ ሆኖ የብር ሜዳሊያውን አግኝቷል፡፡

በድብልቅ ሪሌ 8 ኪሜ የሮጡትና ሁለተኛ በመውጣት የብር ሜዳሊያ ያጠለቁት ተሬሳ ቶሎሳ፣ ዳዲ ዱቤ፣ አድኃና ካህሳይ እና ብሪ አበራ ናቸው፡፡ የመጨረሻውን ዙር የሮጠችው ብሪ አበራ መነሻው ላይ ጫማዋ ወልቆባት ተቀደመች እንጂ ቡድኑ የማሸነፍ ቅድመ ግምት አግኝቶ ነበር፡፡

በሌላ በኩል በወጣት ወንዶች 8 ኪሎ ሜትር መዝገበ ስሜ ሁለተኛ በመውጣት የብር ሜዳሊያ ተሸልሟል፡፡

ከተወሰኑ ዓመታት ወዲህ የዓለም አገር አቋራጩን ጨምሮ በተለያዩ ዓለም አቀፍ ውድድሮች ላይ ኢትዮጵያውያን እንስቶች ከወንዶች ይልቅ በውጤታማነታቸው ሲጠቀሱ መቆየታቸው አይዘነጋም፡፡

በዘንድሮው የዓለም አገር አቋራጭ ውድድር ላይ ግን በአዋቂ ሴቶች ውጤት አልተመዘገበም፡፡ ይህ ለምን ሊሆን እንደቻለ ብሔራዊ ፌዴሬሽኑና የሚመለከታቸው አካላት ሙያዊ ግምገማ በማድረግ ምላሽና ማብራሪያ እንደሚሰጡበት ይጠበቃል፡፡

በአጠቃላይ ውጤት ከአንድ እስከ ሦስት ያለውን ደረጃ የምሥራቅ አፍሪካ አገሮች ኬንያ፣ ኢትዮጵያና ዑጋንዳ ተቆጣጥረውታል፡፡ ኬንያ በ6 ወርቅ፣ 2 ብር፣ 3 ነሐስ፣ በድምሩ 11 ሜዳሊያ 1ኛ ስትሆን፣ ኢትዮጵያ በ2 ወርቅ፣ 6 ብር፣ 2 ነሐስ በድምሩ 10 ሜዳሊያ 2ኛ፣ ዑጋንዳ በ1 ወርቅ፣ 1 ብር፣ 3 ነሐስ በድምሩ በ5 ሜዳሊያ 3ኛ ሆነው አጠናቀዋል፡፡ እንግሊዝ በ1 ነሐስ ብቻ አራተኛ ሆናለች፡፡

ትናንት ማክሰኞ መጋቢት 24 ቀን ረፋድ ላይ አዲስ አበባ ቦሌ ዓለም አቀፍ ኤርፖርት ሲደርስ የባህልና ስፖርት ሚኒስትር ደኤታ መስፍን ቸርነት፣ የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ አመራሮችና የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት ረዳት ኮሚሽነር ደራርቱ ቱሉ በተገኙበት አቀባበል ተደርጎለታል፡፡    

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ቪር ጀነራል ትሬዲንግ ኃ/የተ/የግ/ማኀበር የጨረታ ማስታወቂያ

ቪር ጀነራል ትሬዲንግ ኃ/የተ/የግ/ማኀበር በገቢ እና በውጭ ንግድ እንዲሁም...

ያልተቃናው የልጆች የንባብ ክህሎት

አንብቦና አዳምጦ መረዳት፣ የተረዱትን ከሕይወት ጋር አዋህዶ የተቃና ሕይወት...

እንስተካከል!

ሰላም! ሰላም! ውድ ኢትዮጵያውያን ወገኖቼ እንዲሁም የሰው ዘር በሙሉ፣...

የሙዚቃ ምልክቱ ሙሉቀን መለሰ ስንብት

የኢትዮጵያ ዘመናዊ ሙዚቃ በ1950ዎቹ እና በ1960ዎቹ በኪነ ጥበባትም ሆነ...