Monday, April 15, 2024
- Advertisment -
- Advertisment -

መንግሥት የሚቀርቡለትን ጥያቄዎች ማዳመጥ አለበት!

በአገር ሁለንተናዊ ጉዳዮች ላይ ሁሌም መስማማት ሁሌም መጣላት አይቻልም፡፡ በሚያስማሙ ጉዳዮች ላይ የጋራ ግንዛቤ እንደሚኖረው ሁሉ፣ በማያስማሙት ላይም ልዩነትን በማክበር በጨዋነት መነጋገር ተገቢ ነው፡፡ ሥልጣን ላይ ያለው መንግሥት በሚወስዳቸው የተለያዩ ዕርምጃዎች ምክንያት ደጋፊዎች ሲኖሩት፣ የዚያኑ ያህል ተቃውሞ የሚያሰሙበት መኖራቸው የሚጠበቅ ነው፡፡ የአገር ጉዳይ ሲነሳ ከብሔራዊ ደኅንነትና ጥቅም ቀጥሎ ዘርፈ ብዙ የልማት ሥራዎች የጋራ ስምምነት ይጠይቃሉ፡፡ በዕቅድና በአፈጻጸም ላይ ግን የተለዩ ምልከታዎች መኖራቸውም አይቀሬ ነው፡፡ ሥልጣን የያዘው ገዥው ብልፅግና ፓርቲ በሕዝብ ድምፅ ለአምስት ዓመታት በተሰጠው ኮንትራት መሠረት አገር ሲያስተዳድር፣ በሚወስዳቸው የተለያዩ ዕርምጃዎች ምክንያት የተለያዩ ጥያቄዎች ከመራጩ ሕዝብ ሲነሱለት ምላሽ የመስጠት ግዴታ አለበት፡፡ አሠራሩም በሕጉ መሠረት የግልጽነት፣ የተጠያቂነትና የኃላፊነት መርህ መከተል ይኖርበታል፡፡

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በአዲስ አበባ ከተማ የተጀመረው ‹‹የኮሪደር ልማት›› ከተለያዩ አቅጣጫዎች ጥያቄዎች እያስነሳ ነው፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) እና የከተማዋ ከንቲባ ወ/ሮ አዳነች አቤቤ ለሚነሱት ጥያቄዎች በአለፍ ገደም ምላሽ እየሰጡ ነው፡፡ ይህ መጠነ ሰፊ ፕሮጀክት በርካታ የከተማዋን ነዋሪዎች ሕይወት የሚነካ በመሆኑ፣ በተለያዩ ርዕሰ ጉዳዮች ጥያቄዎች መነሳታቸው የሚጠበቅ ነው፡፡ በልማት ስም ከመኖሪያቸውና ከመሥሪያ ቦታቸው የሚነሱ ዜጎች ጉዳይ አንደኛው ሲሆን፣ ከከተማዋ ነባር ቅርሶችና ትውስታዎች መጥፋት ጋር የተያያዘው ሌላው ጉዳይ ነው፡፡ መንግሥት ነዋሪዎችን ከአካባቢያቸው ሲያስነሳቸው የማኅበራዊ ትስስር ድራቸው መበጣጠሱም ሌላው ጥያቄ ነው፡፡ አዲስ አበባ ከተማ ተለውጣ እንደ ስሟ ውብ ትሆናለች እየተባለ ሲነገር፣ ለልማቱ አካባቢዎቻቸውን ለቀው ወደ ሌላ ሥፍራ የሚዛወሩ ዜጎች ተጠቃሚነት ጉዳይስ እንዴት ነው ተብሎ ጥያቄ ይቀርባል፡፡

ነባር አካባቢዎች ከነዋሪዎች ነፃ ተደርገው ከተዘጋጁ በኋላ የከተማ አስተዳደሩ በሚፈልገው መሠረት አልሚዎች በጨረታ ሲጋበዙ፣ አካባቢው በዚህ ጊዜ ተፈላጊ እንዲሆን አስተዋፅኦ ያበረከቱ ዜጎች ከሚገኘው ጥቅም የሚያገኙት ትሩፋት ምንድነው የሚሉ ጥያቄዎች ይነሳሉ፡፡ በሌላ በኩል የፌዴራል መንግሥትም ሆነ የከተማ አስተዳደሩ ለአምስት ዓመት በተሰጣቸው የኮንትራት ኃላፊነት፣ የከተማውን ሰፊ ክፍል በከፍተኛ መጠን አፍርሰው ሲለውጡ ታሪክና ቅርሶች እንዳይጠፉ ለምን ጥንቃቄ አያደርጉም የሚል ጥያቄም ይከተላል፡፡ የከተማ ነባር ክፍሎችን እንዳለ ከማፍረስ ይልቅ ታሪካቸውን ጠብቆ ማሳመር ለምን አልተፈለገም የሚል ጥያቄም አለ፡፡ በሕዝብ ድምፅ ሥልጣን የያዘ መንግሥት አሠራሩ በምክር ቤቶች ቁጥጥር የሚደረግበት ስለሆነ፣ ግልጽነትና ተጠያቂነት በተግባር መኖሩን ማረጋገጥ የግድ ይላል፡፡ ከዚሁ ጎን ለጎን ልማቱ ከሕዝብ ጋር ተመክሮበት ነው የተጀመረው ሲባል፣ ጥያቄ የሚያነሱ ወገኖችን በተጨባጭ ማሳመን አለበት፡፡

አዲስ አበባን የመለወጥ ፕሮጀክት ላይ የሚነሱ ጥያቄዎች ጠጠር የሚሉት ያለ ምክንያት አይደለም፡፡ አዲስ አበባ ከተማ ተለውጣ አንደኛዋ የአፍሪካ ውብ ከተማ መሆን እንዳለባት ብዙዎችን ያስማማል፡፡ አዲስ አበባ በፍፁም የቆሻሻ መጣያ መስላ መታየትም የለባትም፡፡ አዲስ አበባ ንፁህ፣ ውብና ለነዋሪዎቿ ምቹ መሆን ይኖርባታል፡፡ አዲስ አበባ የሁሉም ኢትዮጵያውያን ዋና ከተማቸው ስትሆን፣ የአፍሪካ ኅብረት መቀመጫ በመሆኗም የአፍሪካውያን ሁለተኛ ቤታቸው ናት፡፡ አዲስ አበባን በብሔር ወይም በጥቅም ትስስር የተወሰኑ ወገኖች ለማድረግ እንደማይሞከረው ሁሉ፣ ሌላው ቀርቶ በተለያዩ ጉዳዮች የሚመጡ የውጭ ዜጎች ሳይቀሩ እንደ ራሳቸው ከተማ እንዲያይዋት የማድረግ ኃላፊነት መኖር አለበት፡፡ በእነዚህና በሌሎች ምክንያቶች አዲስ አበባ በአፍሪካ ብቻ ሳይሆን፣ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተመራጭ ከተማ እንድትሆን ማሳመር ተገቢ ነው፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ መልማትና መለወጥ ግን ታሳቢ ማድረግ ያለበት ነጥቦች አሉ፡፡ እነሱም በነዋሪዎቿ ፈቃደኝነት ላይ የተመሠረተ የልማት ዕቅድ፣ ከጭቅጭቅና ከአድሎአዊነት የራቀ የጋራ ዓላማና ግብ፣ ከብልሹ አሠራሮች የፀዳ መንግሥታዊ መዋቅር፣ ሌብነትንና ዝርፊያን በተግባር የሚጋፈጡ ባለሙያዎችና ሠራተኞች፣ ለመጪው ትውልድ ብቻ ሳይሆን አሁን ላለው ጭምር ተጨንቀው የሚሠሩ አመራሮች ናቸው፡፡ መንግሥት ከየትኛውም አቅጣጫ ለተነሳ ጥያቄ ሁሉ ምላሽ የመስጠት ግዴታ ባይኖርበትም፣ በተለይ የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎችንና የአገር ጉዳይ ያሳስበናል የሚሉ ዜጎችን ማዳመጥ አለበት፡፡ እየተከናወነ ያለው ሥራ በእርግጥም ከተማን ለማልማትና ለመለወጥ እንደሆነ የጋራ ግንዛቤ የሚፈጠረው፣ ይመለከተናል የሚሉ ወገኖች የሚያነሷቸው መሠረታዊ ጥያቄዎች በአግባቡ ምላሽ ሲያገኙ ነው፡፡ ከዚያ በተረፈ የተለመደው የብሽሽቅ ፖለቲካ ውስጥ ዘው ተብሎ ሲገባ ፋይዳ ቢስ ይሆናል፡፡

ኢትዮጵያ ሰላም ሆና በልማትና በዕድገት ጎዳና መገስገስ የምትችለው በሁለንተናዊ ጉዳዮች ላይ መግባባት ሲኖር ነው፡፡ ልዩነት ሲፈጠርም ወደ ጉልበት መፈታተሽ ከመግባት በፊት በንግግርና በድርድር ችግሮችን መፍታት ሲለመድ ነው፡፡ ይህንን መልካም ባህል ለመገንባት ጊዜ ቢወስድም፣ አሁንም ቢሆን ቀስ በቀስ መለማመድ ይቻላል፡፡ የፖለቲካ ልዩነትን የሁሉም ነገሮች መነሻና መድረሻ በማድረግ ቅራኔ መፈልፈል ያተረፈው፣ ወቅት እየጠበቁ መተላለቅና ውድመት ብቻ ነው፡፡ አዲስ አበባ ስታምር ሌሎች ከተሞች የበለጠ ውብ እንዲሆኑ መትጋት፣ አዳዲስ ከተሞች እንዲፈጠሩ መማሰንና በየደረጃው ያሉ ገጠር ቀመስ ከተሞች እንዲዘምኑ ማገዝ የአሁኑ ትውልድ ኃላፊነት ነው፡፡ መንግሥትም ቢሆን ከሕዝብ በተሰጠው አደራ ኃላፊነቱን ለመወጣት ጥንቁቅ መሆን ይጠበቅበታል፡፡ ሥራውም ግልጽ ሆኖ ተጠያቂነት እንዳለበት ማወቅ አለበት፡፡ መንግሥት የሚቀርቡለትን ጥያቄዎች ማዳመጥ ይኖርበታል!

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች

ቪር ጀነራል ትሬዲንግ ኃ/የተ/የግ/ማኀበር የጨረታ ማስታወቂያ

ቪር ጀነራል ትሬዲንግ ኃ/የተ/የግ/ማኀበር በገቢ እና በውጭ ንግድ እንዲሁም...

ያልተቃናው የልጆች የንባብ ክህሎት

አንብቦና አዳምጦ መረዳት፣ የተረዱትን ከሕይወት ጋር አዋህዶ የተቃና ሕይወት...

እንስተካከል!

ሰላም! ሰላም! ውድ ኢትዮጵያውያን ወገኖቼ እንዲሁም የሰው ዘር በሙሉ፣...

የሙዚቃ ምልክቱ ሙሉቀን መለሰ ስንብት

የኢትዮጵያ ዘመናዊ ሙዚቃ በ1950ዎቹ እና በ1960ዎቹ በኪነ ጥበባትም ሆነ...

ስለዘር ፖለቲካ

በሀብታሙ ኃይለ ጊዮርጊስ  ‹‹በቅሎዎች ዝርያችን ከአህያ ነው እያሉ ይመፃደቃሉ›› የጀርመኖች...
spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

የማፍረስ ዘመቻው በብልሹ አሠራሮች ላይም ይቀጥል!

መንግሥት በኮሪደር ልማት አማካይነት የአዲስ አበባ ከተማን ዋና ዋና ሥፍራዎች በማፍረስ፣ አዲስ አበባን ከኬፕታውን ቀጥሎ ተመራጭ የአፍሪካ ከተማ ለማድረግ መጠነ ሰፊ ሥራ ከጀመረ ሰነባብቷል፡፡...

ለድጋፍ ብቻ ሳይሆን ለተቃውሞም ማስተንፈሻ ይሰጥ!

በሕዝብ ድምፅ ተመርጦ ሥልጣን የያዘ መንግሥት ዋነኛ ሥራው በሕግ መሠረት የተሰጡትን ኃላፊነቶች በብቃት መወጣት ነው፡፡ የሕዝብን ሰላምና ደኅንነት ማስጠበቅ፣ የአገርን የግዛት አንድነትና ሉዓላዊነት ማስከበር፣...

የፖለቲካ ምኅዳሩ እንዳይዳፈን ጥንቃቄ ይደረግ!

የኢትዮጵያ የፖለቲካ ምኅዳር አሁንም ጤና አልባ ሆኖ የተለመደው ተስፋ አስቆራጭ ሁኔታ ውስጥ ነው የሚገኘው፡፡ ካለፉት ሃምሳ ዓመታት ወዲህ ሊሻሻል ያልቻለው የፖለቲካ ምኅዳር ሰሞኑን አዲስ...