Saturday, April 20, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናሕወሓት ዕውቅናው እንዲመለስለት ያቀረበውን ጥያቄ ቦርዱና ፍትሕ ሚኒስቴር የሕግ መሠረት የለውም አሉ

ሕወሓት ዕውቅናው እንዲመለስለት ያቀረበውን ጥያቄ ቦርዱና ፍትሕ ሚኒስቴር የሕግ መሠረት የለውም አሉ

ቀን:

  • ጠቅላይ ሚኒስትሩ ግን ዕውቅናውና ፈቃዱ እንደሚመለስ ተናግረዋል

በሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት ምክንያት በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በሽብርተኝነት ተፈርጆ የዕውቅና ፈቃዱን የተነጠቀው ሕወሓት፣ በፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት እንደተገለጸው በሕገ መንግሥቱ መሠረት እንዲመለስለት ያቀረበው ጥያቄ የሕግ መሠረት የለውም ሲሉ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድና ፍትሕ ሚኒስቴር ምላሽ ሰጡ፡፡

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድና የፍትሕ ሚኒስቴር በአመፅ ድርጊት በመሳተፉ ምክንያት ፈቃዱ እንዲሰረዝ የተደረገው ሕወሓት መልሶ ዕውቅና የማግኘት ሕጋዊ መሠረት የለውም ቢሉም፣ ሕወሓት ግን ዕውቅናው በፕሪቶሪያ ስምምነት እንደተገለው በሕገ መንግሥቱ መሠረት መፈቀድ አለበት ብሏል፡፡

ሕወሓት በሰሜን ኢትዮጵያ ለሁለት ዓመታት በተካሄደው ጦርነት ተሳታፊ በመሆኑ፣ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በሽብርተኝነት መፈረጁ የሚታወስ ሲሆን፣ የፓርቲነት ፈቃዱም ሆነ ስያሜው በምርጫ ቦርድ መሰረዙ አይዘነጋም፡፡ በፌዴራል መንግሥትና በሕወሓት መካከል በደቡብ አፍሪካ ፕሪቶሪያ በተደረሰ የሰላም ስምምነት፣ ጦርነቱ ከቆመ በኋላ ሕወሓት ከሽብርተኝነት እንዲሰረዝ ሲደረግ፣ የፓርቲነት ፈቃዱ ግን አለመመለሱ ይታወቃል፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ከትግራይ ክልል ከተውጣጡ የኅብረተሰብ ክፍሎች ጋር ባለፉት ሳምንታት ውስጥ ባደረጉት ውይይት፣ የሕወሓት ዕውቅናና ፈቃድ መመለስ እንዳለበትና ይህንንም ለምርጫ ቦርድ በማሳወቅ በቅርቡ ችግሩ እንደሚፈታ መናገራቸው ይታወሳል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህንን ቢሉም፣ በቅርቡ የተሾሙት የምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ወ/ሮ ሜላተወርቅ ኃይሉ ሰሞኑን ከመገናኛ ብዙኃን ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ፣ በአመፅ ድርጊት በመሳተፉ ምክንያት ፈቃዱ የተሰረዘ ፓርቲ መልሶ እንደገና ፈቃድ እንዲያገኝ የሚያስችል የሕግ ድንጋጌ እንደሌለ ገልጸዋል፡፡ ሰብሳቢዋ አክለውም ፈቃዱን መስጠት ባይቻልም በአዋጁ መሠረት እንደ አዲስ መመዝገብ ይችላል ብለዋል፡፡

የሕጋዊነትና የፈቃድ ጉዳይ በፕሪቶሪያው ስምምነት እንደተመለከተው በሕገ መንግሥቱ መሠረት ምላሽ የሚሰጠው መሆኑን ለሪፖርተር የገለጹት የሕወሓት ጽሕፈት ቤት የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ እያሱ ተስፋዬ፣ እንደ አዲስ መመዝገብ የሚለው ጉዳይ ግን ፍፁም ተቀባይነት የለውም ብለዋል፡፡ ‹‹ከፌደራል መንግሥት ጋር ባለን ግንኙነት የፓርቲውን ፈቃድ የመመለሱ ሒደት ላይ መስማማት ተደርሶ አቅጣጫ የተሰጠበት ሲሆን፣ በአጭር ጊዜ እንዲጠናቀቅ ነው እየጠየቅን ያለነው፤›› ሲሉ አስረድተዋል፡፡

ሪፖርተር ያነጋገራቸው በፍትሕ ሚኒስቴር የንቃተ ሕግ ዳይሬክቶሬት ረዳት ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ አቶ መዓዛ ሃይማኖት እንደገለጹት በአገሪቱ ሕግ መሠረት በፓርቲነት የተመዘገበና ዕውቅና ያገኘ ፓርቲ በኃይል ድርጊት ተሰማርቶ ከተገኘ ሕጋዊ ሰውነቱን ያጣል፡፡ ሕወሓትም በዚህ ድርጊት ተሰማርቶ በመገኘቱ ምርጫ ቦርድ የወሰደው ፈቃድ የመንጠቅ ዕርምጃ ሕጋዊ መሠረት የተከተለ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ‹‹በአገሪቱ ባለው ሕግ መሠረት ሕወሓት የቀድሞውን ፈቃድ ማግኘት አይችልም›› ያሉት አቶ መዓዛ፣ እንደ አዲስ መመዝገብን ግን አይከለከልም ሲሉ የምርጫ ቦርድን ውሳኔ አጠናክረዋል፡፡ 

ምንም እንኳን የፍትሕ ሚኒስቴር ለሕወሓት ሕጋዊ ፈቃድ ለመስጠት የሚያስችል የሕግ ማሻሻያ እያደረገ ባይሆንም፣ ማሻሻያው ቢደረግ እንኳን ከዚህ በፊት የተሰጠውን ውሳኔ የሚሽር አለመሆኑን ጠቁመዋል፡፡   

ለፍትሕ ሚኒስቴር አስተያየት ምላሻቸውን የሰጡት አቶ እያሱ፣ ‹‹የሰላም ስምምነቱን ተግባራዊ ለማድረግ እየተንቀሳቀስን ባለንት ወቅት፣ የፓርቲውን ዕውቅና ማግኘት ከሰላም ስምምነቱ ውጪ አድርጎ መመልክት አግባብ አይደለም፤›› ብለዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ሰላማዊ የፖለቲካ ትግልና ፈተናው

የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) የፖለቲካ ኦፊሰር የአቶ በቴ ኡርጌሳን...

አበጀህ ማንዴላ! አበጀሽ ደቡብ አፍሪካ!

በአየለ ት. የፍልስጤም ጉዳይ የዓለም አቀፍ ፖለቲካንም ሆነ የተባበሩት መንግሥታትን...

የውጭ ባለሀብቶች ለኢትዮጵያውያን ብቻ በተፈቀዱ የንግድ ዘርፎች እንዲገቡ የመወሰኑ ፋይዳና ሥጋቶች

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አዓመድ (ዶ/ር) የውጭ ኩባንያዎች በጅምላና ችርቻሮ...