Thursday, April 18, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ቡና ላኪዎች የስም ማጥፋት ዘመቻ እንደተከፈተባቸውና ከውጭ ገዥዎች ክፍያ መሰብሰብ እንዳቃታቸው ተናገሩ

ተዛማጅ ፅሁፎች

  • በሁለት ስያሜ ላኪዎችን ሲያጭበረብር የነበረ የቻይና ድርጅት መያዙ ተጠቁሟል

የተለያዩ የቡና ዓይነቶችን የሚልኩ ድርጅቶች በውጭ ገበያ ከሚገኙ ገዥዎች የስም ማጥፋት ዘመቻ እንደተከፈተባቸው፣ እንዲሁም ሚሊዮን ዶላሮች የሚያወጣ በዱቤ የተላከ ቡና ክፍያ መሰብሰብ እንዳቃታቸው ተናገሩ፡፡

ጉዳዩን በተመለከተ ሪፖርተር ካነጋገራቸውና ስማቸው እንዳይጠቀስ የጠየቁ አንድ ላኪ፣ ‹‹ቡናን በሚመለከት ዓለም አቀፉ ዋጋ ሲዋዥቅ ገዥና ሻጭ ሁሌም ይቸገራሉ፡፡ ዋጋ እየወረደ ከሆነ ገዥ ቶሎ ውል ማፍረስ ነው የሚፈልገው፡፡ ቡና ገዥ ዘንድ ከሚቆይ የሆነ ሰበብ ተፈልጎ የማይመስል ምክንያት በማቅረብ ውል ለማፍረስ ይሞከራል፡፡ በዚህም ሳቢያ ላኪዎች ከፍተኛ ችግር እያጋጠማቸው ነው፤›› ብለዋል። 

ላኪው በምሳሌነት ያቀረቡት፣ ቡና ላኪው ድርጅት አንድ የኤሌክትሮኒክ መልዕክት (ኢሜይል) አልመለስክም በሚል፣ ወይም ቡናው ለገዥ የሚደርስበት ቀን አንድ ቀን እንኳን ቢሆን የሚያልፍ ከመሰላቸው በሁለቱ መካከል በሚደረግ የመልዕክት ምልልስ እንዲዘገይ ይደረጋል፡፡ ገዥዎች መልሰው ውሉን ሻጭ ባለማክበሩ ግብይቱ ይሰረዝ፣ ቡናውም ይመለስ፣ ወይም ዋጋው ይቀንስ ይላሉ ሲሉ ችግሩን አስረድተዋል፡፡

የቡና ዋጋ በዓለም አቀፍ ገበያ ከፍ ሲል ደግሞ የገዥዎች እንቅስቃሴና ዕርምጃቸው በተቃራኒው እንደሚሆን፣ ነገር ግን አጠቃላይ ሒደቱ የተረጋጋ የግብይት ሥርዓት ለመጠበቅ አስቸጋሪ ሁኔታ መፍጠሩ ተገልጿል።

የተለያየ ደረጃ ያላቸውን የኢትዮጵያ ቡናዎች ዓይነቶች ለውጭ ገበያ የሚያቀርቡ ድርጅቶች እየገጠማቸው ካሉ ችግሮች አንዱ፣ በታይዋን የሚገኝ ገዥ ድርጅት የሚፈጽመው የስም ማጥፋት ዘመቻ እንደነበርም ተጠቅሷል። 

ሪፖርተር ያነጋገራቸው ቡና ላኪዎች ስሙን ያልጠቀሱት የታይዋን ድርጅት፣ የድርጅቶቹን ስም በተለያዩ የማኅበራዊ ትስስር ገጾች (እንደ ፌስቡክና ሊንክድን ያሉ)  በመጠቀም፣ በተደራጀ ሁኔታ ስማቸውን እያጠፋ እንደነበረ ተናግረዋል፡፡

የታይዋን ድርጅት እያዛመተ ከነበረው የሐሰት መረጃ፣ ‹ከአንድ የኢትዮጵያ ቡና ላኪ ድርጅት ቡና መግዛቱን፣ ከገዛ በኋላ ያዘዝኩት ቡና ደረጃ አራትና አምስት ቢሆንም የቀረበልኝ ከደረጃዎች ሁሉ በታች የሆነ ቆሻሻ ቡና ነው የተላከልኝ፤›› የሚለው ይገኝበታል ብለዋል፡፡

ይህንን ድርጅት የኢትዮጵያ ቡና ላኪዎች ማኅበር ከቡናና ሻይ ባለሥልጣን ጋር በመሆን ማንነቱን ተከታትሎ ምርመራ በማድረግ እንደደረሰበት ሪፖርተር ማረጋገጥ ችሏል። 

ተመሳሳይ ችግር በሃንጋሪና በጃፓን ከሚገኙ ገዥ ድርጅቶች እንዳጋጠመም ተጠቅሷል። ከሁሉም በተለየ ግን ከቻይና ቡና ተቀባይ ድርጅቶች ከዱቤ የክፍያ ሥርዓት (Cash Against Document-CAD) ጋር በተያያዘ፣ ለቡና ላኪዎች እስካሁን በርካታ ሚሊዮን ዶላሮች እንዳልተከፈሉ ምንጮቹ አስረድተዋል።

በዚህ የክፍያ ሥርዓት አፈጻጸም መሠረት ድርጅቶች ቡናውን ቀድመው የሚልኩ ሲሆን፣ ገዥው ገንዘቡን የሚከፍለው ቡናው ከደረሰ በኋላ ነው። 

በቻይና ድርጅቶች ተይዞ ያለው ገንዘብ ከአንድ ድርጅት ብቻ እንዳልሆነ፣ ይልቁንም ከተለያዩ የቡና ላኪዎች የተጠራቀመ መሆኑም ታውቋል። 

አንድ የሪፖርተር ምንጭ፣ ‹‹ይህ ችግር እስካሁን ሙሉ ለሙሉ አልተፈታም፡፡ መንግሥት ጭምር ጣልቃ ገብቶ መፍትሔ እያፈላለገበት ያለ ችግር ነው። መንግሥታት የሚነጋገሩ ከሆነ በሚል ላኪዎች ጣልቃ ላለመግባት ከዳር ሆነው መፍትሔ እየተጠባበቁ ነው፤›› ብለዋል። 

የቻይና ተቀባይ ድርጅቶች በላኪዎች ላይ እየፈጠሩ ስላለው ችግር ተያይዞ ሲቀርብ ይህ ለመጀመሪያ ጊዜ አይደለም። 

የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለሥልጣን ጥር 23 ቀን 2016 ዓ.ም. ለማኅበሩና ለኢትዩዮጵያ ብሔራዊ ባንክ በጻፈው አስቸኳይ ደብዳቤ፣ ሲያጭበረብር ስላገኘው የቻይና ኩባንያ ማስጠንቀቂያ ሰጥቶ እንደነበር ሪፖርተር ያገኘው ሰነድ ያመለክታል። 

ባለሥልጣኑ በደብዳቤው፣ ‹‹ቻይና የሚገኝ ለቡና ትሬዲንግ ዴኤምሲሲ (LEBUNNA TRADING DMCC) የሚባል ድርጅት ከተለያዩ ላኪዎች በ(CAD) ቡና በመረከብ እንዲከፍል በተደጋጋሚ በአካልም ጭምር ቢጠየቅም ሳይከፍል በመቅረቱ፣ ላኪዎችን ችግር ላይ ከመጣሉም በላይ አገራችን ማግኘት የሚገባትን የውጭ ምንዛሪ እንዳታገኝ አድርጓል፤›› ብሏል፡፡

በባለሥልጣኑ የገበያ ልማትና ቁጥጥር ዘርፍ ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ሻፊ ዑመር የተፈረመው ደብዳቤ፣ ‹‹በተጨማሪም ስሙን ‹SINCHOEM HEBI CORPORATION› በሚል በመቀየር ቡናን ከአገራችን እየገዛ መሆኑን ተደርሶበታል፤›› ይላል።

የተፈጠረውን ችግር ለመፍታት ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴርና በቻይና ከኢትዮጵያ ኤምባሲ ጋር እየሠራ መሆኑን ባለሥልጣኑ በደብዳቤው የገለጸ ሲሆን፣ እስከዛሬ ግን ላኪዎች ስሙን ከቀያየረው ድርጅት ጋር ውል እንዳይፈጽሙ የቡና ላኪዎች ማኅበር እንዲያሳውቅ፣ ብሔራዊ ባንክም ውል እንዳይፈጽሙ እንዲያደርግ መጠየቁ ተጠቅሷል፡፡

በሌላ በኩል ቡና ላኪዎች ከእንግሊዝ ሌላ ፈተና እንደገጠማቸው ታውቋል።  በቅርብ ወራት ውስጥ በእንግሊዝ የሚገኝ አንድ ተቀባይ ድርጅት ከኢትዮጵያ ቡና ላኪ ጋር ተካሶ ነበር ተብሏል። 

ኢትዮጵያዊ ላኪ ድርጅት በእንግሊዝ የቡና ማኅበር ግልግል ዳኝነት አሠራር ሥርዓት (Arbitration Court) ጉዳዩ ታይቶለት አሸናፊ መሆኑን የሪፖርተር ምንጮች ገልጸዋል። 

የሪፖርተር ምንጮች የክሱን ዝርዝር ሁኔታ ከመጥቀስ የተቆጠቡ ሲሆን፣ ዋና ጭብጡ ግን ላኪው ቡናውን በጊዜ ስላልጫነ አክስሮኛል በማለት ውል ለማፍረስ የፈለገ የቡና ተቀባይ ድርጅት፣ ቡናው በተጠቀሰው ጊዜ እንዳይጫን የፈለገው ራሱ ተቀባዩ መሆኑን፣ የቆየውም ድርጅቱ ወቅቱን የጠበቀ ምላሽ ባለመሰጠቱ እንደሆነ ግን ታውቋል። 

ክሱን የመሠረተው የእንግሊዝ ተቀባይ ድርጅት ቢሆንም የግልግል ዳኝነቱ ግን ለኢትዮጵያዊው ላኪ መፍረዱ ተሰምቷል። 

ስማቸው እንዲገለጽ ያልፈለጉ አንድ ላኪ፣ ‹‹እንዲህ ዓይነት አካሄዶችን የሚከተሉ የውጭ ተቀባይ ድርጅቶች የኢትዮጵያ ላኪዎች በየአገራቸው ስላለው የግብይት ሥርዓትና ሕግጋቶቻቸው የግንዛቤ ክፍተት አለባቸው፣ ብንከሳችው አይከራከሩም ከሚል እምነት ተነስተው የሚያደርጉት ነው፤›› ብለዋል። 

የቡና ላኪዎቹን አቤቱታ በተመለከተ ሪፖርተር ያነጋገራቸው የኢትዮጵያ ቡና ላኪዎች ማኅበር ፕሬዚዳንት አቶ ግዛት ወርቁ፣ ‹‹ማኅበሩ ላኪዎችን የሚመክረው ቡና ወደ ውጭ ሲልኩ ውሎችን ተጠንቅቀው እንዲፈጽሙ ነው። ውሉ እያንዳንዱ ቃል ምን እንደሚል፣ የየአገሮቹ ሕግጋት ምን እንደሚፈቅድና እንደሚከለክል ሙሉ ለሙሉ ግንዛቤ እንዲኖራቸው እንነግራቸዋለን፤›› ብለዋል።

አቶ ግዛት አክለውም፣ ‹‹የሕግ አዋቂዎችን አማክሩ፣ የተፈራረማችሁትን ውል ያለ ምንም ማዛነፍ ተከትላችሁ ፈጽሙ፣ ባትፈጽሙ ሕጉ ምን እንደሚል እሱን ዕወቁ የሚል ማሳሰቢያ ነው የምንሰጣቸው፤›› ሲሉ አስረድተዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች