Saturday, April 20, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊደጅ የሚጠኑ ታካሚና አስታማሚዎች

ደጅ የሚጠኑ ታካሚና አስታማሚዎች

ቀን:

ሕክምናን በጥቂት ወረፋ ማግኘት ብርቅ ወደሆነባት አዲስ አበባ የታመሙ ቤተሰቦቻቸውን ለማሳከም ከየክልሉ የሚመጡ በርካቶች ናቸው፡፡ አዲስ አበባም ሲመጡ በጥቂት ቀናት ምናልባትም በአንድ ቀን ሕክምና ጨርሰው የሚመለሱ የሚመስላቸው ቀላል አይደሉም፡፡

የሕክምና ሒደት ለዚያውም በኢትዮጵያ ደረጃ የሚወስደው ጊዜ እንዳለ ሆኖ፣ ታማሚና አስታማሚዎች በዚሁ ልክ ሳይዘጋጁና ግንዛቤው ሳይኖራቸው ሲስተጓጎሉ መታየት ለአዲስ አበባ የሪፈራል ሆስፒታሎች ብርቅ አይደለም፡፡

ለተለያዩ ሕክምና መጥተው ለቀናትና አሊያም ለወራት እንደሚጉላሉ በሆስፒታሎችም ሆነ በመንግሥት ቢታወቅም፣ ለበርካታ ዓመታት ያለመፍትሔ የተዘነጋ አጀንዳ ነው፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

የሆስፒታሎች፣ የሕክምና ግብዓቶች፣ የሕክምና ዓይነቶችና የሕክምና ባለሙያዎች ላይ ክፍተት እንዳለ ቢታወቅም፣ የእናቶችና ሕፃናት ሕክምና ላይ ይሻል እንደሆነ እንጂ፣ ለአብዛኞቹ በተለይም ተላላፊ ላልሆኑት በሽታዎች ሕክምና ከቀዬአቸው ብዙ ኪሎ ሜትሮችን ተጉዘው ሕክምናን መሻት፣ ለጤናው ዘርፍ ጫና፣ ለታካሚና አስታማሚም እንግልት ሆኗል፡፡

ለዚህ ደግሞ በአዲስ አበባ ያሉትን ሆስፒታሎች መጎብኘት በቂ ነው፡፡ በካንሰር ሕክምና በሺዎች የሚቆጠሩ የሪፈራል ታካሚዎችን የሚያስተናግደው የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የጥቁር አንበሳ ሪፈራል ሆስፒታል ሕሙማን ከእነአስታማሚዎቻቸው ከሚጉላሉበት አንዱ ነው፡፡

ከአቅሙ በላይ የተሸከመው ሆስፒታሉ፣ በሕክምናው ዘርፍ የራሱን ለመወጣት ጥረት ቢያደርግም፣ የመጡለትን ታካሚዎች በጥቂት ቀናት አስተናግዶ ለመሸኘት ከሕክምና አሰጣጥ ውስብስብነትና የሚፈለጉ ሕክምናዎችን በሚፈለገው ልክ ካለማግኘት የተነሳ፣ ሕሙማንን በጊዜ መሸኘት አይቻለውም፡፡ በዚህም ምክንያት ታማሚና አስታማሚ ሲጉላሉ ማየት የተለመደ ነው፡፡

በሆስፒታሉ ለ20 ቀናት ያህል ልጃቸውን በተኝቶ መታከም ሲያስታምሙ የከረሙ አባትም ትዝብታቸውን አጋርተውናል፡፡ በሆስፒታሉ በርካታ ከየክልሉ የመጡ ሕሙማንና አስታማሚዎችም ገንዘብ ከፍለው መመገብ ካለመቻላቸው የተነሳ መከራቸው የሚጀምረው ከረሃባቸው ነው፡፡ ሕክምና አግኝቶ ማደሪያ መሻትም ቀጣዩ ፈተና ነው፡፡

ታማሚ የመጀመርያ ምርመራ ካደረገበት ቀን አንስቶ የሚሰጠው የጊዜ ቀጠሮ፣ እንደ ዓይነታቸው የላቦራቶሪ ምርመራዎች የሚወስዱት ቀናትና የሁሉም አገልግሎት አለመገኘት፣ ሕክምና በራሱ የሚወስደው ቀናት ተጨማምሮ የሚሄዱበት ያጡ፣ እዚያው በየኮሪደሩ ለማደር ተገደዋል፡፡

ለሚቀምሱት ደግሞ ተኝተው የሚታከሙ አስታማሚዎች፣ በተለይ የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ከሆስፒታሉ የሚሰጣቸውን አሊያም ከቤተሰብ የመጣላቸውን እያቋደሷቸው ቀጠሯቸውን ለመጠበቅ ተገደዋል፡፡

ይህ ችግር ዛሬ የመጣ ሳይሆን በርካታ ዓመታትን ያስቆጠረ ነው፡፡ በተለይ የካንሰር ታማሚዎችና አስታማሚዎች የሆስፒታሉን አጥር ተጠግተው የሚያድሩበት ጊዜም የቅርብ ጊዜ ትዝብታችን ነው፡፡

የጨረር ሕክምና የወሰዱ ሕሙማን በርካቶች በአንድ ላይ ከሚያድሩባቸው ቤቶች ዝቅተኛ ዋጋ ከፍለው ማደር፣ ካልቻሉም ከጎዳና ማሳለፍ ደግሞ፣ ዘመድም አቅምም የሌላቸው የተፈተኑበት ክስተት ነው፡፡

ይህ አጋጣሚ የጥቁር አንበሳ ብቻ ሳይሆን በሌሎችም ሆስፒታሎች ቀናት የሚወስዱ የተመላላሽ ሕክምና ታማሚዎችና አስታማሚዎች ላይ የሚከሰት ነው፡፡

ይህንን ችግር የተገነዘቡ በጎ አድራጊዎችና ድርጅቶች የሕሙማንን ስቃይ ለመጋራት የሕክምና ወጪ ከመሸፈን አንስቶ ቤት ተከራይቶ እስከ ማስቀመጥ የተጓዙትም መንግሥት ሊወጣ የሚገባውን ባለመወጣቱ፣ የጤና ዘርፍም ይህንን ሊሸከም ባለመቻሉ ነው፡፡

ወ/ሮ አይከል በሲር በቅንጭላት ካንሰር ታሞ የሚሰቃየውን ሕፃን ልጃቸውን ለማሳከም ከደቡብ ወሎ ዞን ከላላ ወረዳ ተነስተው አዲስ አበባ ከመጡ ከአምስት ወራት በላይ አስቆጥረዋል።

አዲስ  አበባ እንኳንስ ታማሚ ልጅ ተይዞ ለጤነኛም ያስቸግራል የሚሉት ወ/ሮ አይከል፣ በተለይ አዲስ አበባ እንደገቡ ሰሞን ችግሩ በእጅጉ በርትቶባቸው እንደነበር ያስታውሳሉ።

ወ/ሮ አይከል፣ የሚጠጉበት ዘመድም ሆነ የሚያውቁት ሰው ባለመኖሩ፣ ከሁሉም በላይ በሽተኛ ልጅ ይዞ መጠጊያውና ማደሪያው በጣም ፈተና እንደነበር፣ ምግብም ቢሆን በቀላሉ የሚገኝ አልነበረም ይላሉ።

ችግሩ የሁሉንም ታማሚዎችና አስታማሚዎች በር የሚያንኳኳ ስለመሆኑ ብዙዎች ይናገራሉ። የወ/ሮ አይከል ዓይነት ዕጣ ፈንታ የሚገጥማቸው ታማሚዎችም ቀላል አይደሉም፡፡

ከተለያዩ የኢትዮጵያ አካባቢዎች የተሻለ ሕክምና ለማግኘት እንዲሁም ሕመማቸው ከአካባቢያቸው ሆስፒታል አቅም በላይ በመሆኑ በሪፈር የሚመጡ ታማሚዎች አዲስ አበባ ያልጠበቁትንና ያላሰቡትን ችግር ይዛ ትጠብቃቸዋለች።

ወደ መጡበት ሆስፒታል ገብተው አልጋ በመያዝ ሕክምና እስከሚጀምሩ ድረስ ለማደሪያና ለምግብ የሚወጣ ወጪ ለሕክምና ከሚወጣው ወጪ እንደማይተናነስ ይናገራሉ።

 ይህን የሚያደርጉት በጣም ጥቂቶች እንዲሆኑ ውሎ አዳራቸውን በየሆስፒታሉ አጥር አድርገው የሆስፒታል ቀጠሯቸው ደርሶ ወደ ውስጥ እስኪገቡ በተስፋ የሚጠብቁ ታማሚዎች ምስክር ናቸው።

በተለይ ደግሞ እንደ ካንሰር ያሉ ረዘም ላለ ጊዜ ክትትል የሚያስፈልጋቸው  የሕመም ዓይነቶች ስቃዩን ያበዙታል።

ወ/ሮ አይከል የልጃቸውን ሕክምና ቶሎ ጨርሰው የመሄድ ትልቅ ተስፋ እንደነበራቸው አውስተው፣ ነገር ግን ልጃቸው በቀላሉ አገግሞ ወደ ቀዬአቸው መመለስ እንዳልቻሉ ያስረዳሉ።

ምንም እንኳን በአሁኑ ወቅት ዕድል ገጥሟቸው ተስፋ አዲስ ፓረንትስ በተባለ ግብረ ሰናይ ድርጅት ተጠልለው ልጃቸውን በጥሩ ሁኔታ እያስታመሙ እንደሆነ ተናግረዋል።

ነገር ግን ወደ እዚህ ድርጅት ከመግባታቸው በፊት የነበረው ፈተና በጣም ከባድ ነበር የሚሉት ወ/ሮ አይከል፣ በወቅቱም ከፍተኛ ገንዘብ ያወጡ እንደነበር ያስታውሳሉ።

‹‹ፈጣሪ ረድቶኝ ወደ ተስፋ አዲስ በጎ አድራጎት ማኅበር ባልገባ ኑሮ የልጅ ሕይወት ቀርቶ የእኔ ጤነኛነትም አሳሳቢ ነበር፤›› ያሉት ወ/ሮ አይከል፣ መሰል ዕድል ሳያገኙ በሽተኛ ልጆችን ይዘው በየበረንዳው ያሉ እናቶችና አባቶችን የሚረዳቸው አካል ቢገኝ የተሻለ ነው ይላሉ።

ብዙ ጊዜ ከክልል አዲስ አበባ ወደሚገኙ ሆስፒታሎች የሚገቡ ታማሚዎች  ምናልባት ከጥቂቶች በስተቀር ብዙዎቹ በሆስፒታል አልጋ ይዘው መታከም አማራጭ የሌለው ምርጫቸው ይሆናል።

 እነዚህ ሰዎች የሁለትና ሦስት ሳምንታት ቀጠሮ ሲሰጣቸው ኑሮ ፈተና ይሆንባቸዋል።

ብዙ ኪሎ ሜትሮችን አቋርጠው ወደ አዲስ አበባ ሆስፒታሎች የሚገቡ ታካሚዎች ቀጠሮ ደርሷቸው ወደ ሆስፒታል እስኪገቡ፣ ዘመድ ያለው ወደ ዘመዱ ሲጠጋ ዘመድ የሌለው ደግሞ አጋር በመያዝ ለከፍተኛ ወጪ ሲጋለጡ፣ ገንዘብም ሆነ መጠጊያ የሌላቸው ደግሞ ሕመምተኛ ልጆችን በመያዝ በየሆስፒታሉ አጥር ተጠግተው ጊዜያቸውን ይጠባበቃሉ።

‹‹ወደ ቤተሰብ መጠጋት ለጊዜው ማረፊያ ሊሆን ይችላል ከዚህ ባለፈ ግን ሰው ማስቸገር ከቤተሰብ ጋርም መቀያየም ነው፤›› ያሉት ደግሞ ከሞያሌ የመጡት አቶ ዶፋ ናቸው።

አቶ ዶፋ ልጃቸው በካንሰር ሕመም ተይዞባቸው ለሕክምና ወደ አዲስ አበባ ከመጡ ከዓመት በላይ ሆኗቸዋል።

በአንድ ዓመት ውስጥ ልጃቸውን ለማሳከም ብዙ መስዋዕትነትን እንደከፈሉ የሚናገሩት አቶ ዶፋ፣ በተለይ የመጀመሪያዎቹን ሦስት ወራት አዲስ አበባ ከሚገኙ ዘመዶቻቸው ተጠግተው ያሳለፉ ቢሆንም፣ በጣም ይሳቀቁ እንደነበር ያስታውሳሉ።

አቶ ዶፋና የወ/ሮ አይከል ተስፋ አዲስ ፓረንትስ ማኅበር በሰጣቸው በማዕከሉ ተጠልለው የማሳከም ዕድል ልጆቻቸውን እያሳከሙ ይገኛሉ።

ተስፋ አዲስ ፓረንትስ በጎ አድራጎት ማኅበር በካንሰር ሕመም የሚሰቃዩ ሕፃናትን  ከወላጆቻቸው ጋር በማንሳት ሕክምናቸውን እስኪጨርሱ በመንከባበብ የሚረዳ ማኅበር ነው።

የወ/ሮ አይከልና የአቶ ዶፋ ዕጣ ፈንታ ሳይገጥማቸው የቀሩ በርካታ ሕመምተኞችም ሆኑ ከሕመምተኞች ያልተናነሰ መከራ የሚደርስባቸው አስታማሚዎች  ከችግር ላይ ችግር ደርበው የተሟላ ሕክምና ሳያገኙ የሚመለሱ በርካታ ናቸው።

ሌሎች ደግሞ በሕክምና ጥሪታቸውን በመጨረሳቸው ተመልሰው የሚገቡበትን በማሰብ ከመሄድ መቅረትን መርጠው ጎዳና ላይ ወጥተው ለልመና እጃቸውን ይዘረጋሉ። ከዛሬ ነገ በማለት ከበሽታው ቢያገግሙ እንኳን ወደ ቤተሰብ መመለስን ይተውና ኑሮውን ጎዳና ላይ የሚያደርጉ ብዙዎች ናቸው።

እንደ ተስፋ አዲስ ፓረንትስ በጎ አድራጎት ማኅበርና ማቲዎስ ወንዱ የኢትዮጵያ ካንሰር ሶሳይቲ መሰል በጎ አድራጎት ማኅበራት ቢበዙ በየሆስፒታሉ አጥር የተኙ ወገኖችን በማንሳት የተሻለ እንክብካቤ በማድረግ ችግሩን ማቃለል በተቻለ ነበር።

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ሰላማዊ የፖለቲካ ትግልና ፈተናው

የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) የፖለቲካ ኦፊሰር የአቶ በቴ ኡርጌሳን...

አበጀህ ማንዴላ! አበጀሽ ደቡብ አፍሪካ!

በአየለ ት. የፍልስጤም ጉዳይ የዓለም አቀፍ ፖለቲካንም ሆነ የተባበሩት መንግሥታትን...

የውጭ ባለሀብቶች ለኢትዮጵያውያን ብቻ በተፈቀዱ የንግድ ዘርፎች እንዲገቡ የመወሰኑ ፋይዳና ሥጋቶች

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አዓመድ (ዶ/ር) የውጭ ኩባንያዎች በጅምላና ችርቻሮ...