Thursday, April 18, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

መጀመሪያ ራስን መግራት!

ሰላም! ሰላም! የተከበራችሁ ወገኖቼ ሳምንት አልፎ ሳምንት ሲተካ በደጉም በክፉም የሚያነጋግሩን በርካታ ጉዳዮች አሉን፡፡ ከሁሉም ነገር በፊት በአስቸጋሪ ሁኔታዎች ውስጥ ሆነንም ቢሆን ሰላም ለመባባል በመብቃታችን ፈጣሪን ተመስገን ማለት አለብን እላለሁ፡፡ ሙስሊም ክርስቲያኑ በረመዳንና በሁዳዴ ፆማቸው ከፈጣሪያቸው ጋር በፀሎት እየተነጋገሩ ባሉበት በዚህ ጊዜ፣ ከምንም ነገር በላይ ለአገራቸው ሰላምና ደኅንነት አጥብቀው እንደሚጨነቁ ማንም አይስተውም፡፡ አዛውንቱ ባሻዬ ሁለመናቸውን ፀሎት ላይ አድርገው፣ ‹‹ፈጣሪዬ የአገራችንና የሕዝባችንን ነገር አደራ…›› እያሉ ሲለምኑ ባለሱቁ ጋሼ አደም፣ ‹‹አላህ አደራህን የኢትዮጵያንና የሕዝባችንን ውሎና አዳር…›› በማለት በፀሎት ሲተጉ በአለፍ ገደም መስማቴ አልቀረም፡፡ እኔም ኃጢያተኛው ደላላው አንበርብር ምንተስኖት፣ ‹‹ፈጣሪዬ የእኛን ያልተገባ ሥራ ሳይሆን የእነዚህን አዛውንቶች ፀሎት ሰምተህ በምሕረትህ ጎብኘን…›› እያልኩ አንገቴን ሰበር አደርጋለሁ፡፡ ተባብረን ብንፀልይ እኮ ፈጣሪ ከእኛ እንደማይርቅ ብዙ ማስረጃዎች እንዳሉ የሩቁን ትተን የቅርቡን ማስታወስ ነው፡፡ ለዚህ ደግሞ መለስ ብለን ያለፍንባቸውን ውጣ ውረዶች መቃኘት በቂ ነው፡፡ ከበቂም በላይ እንጂ!

ምሁሩ የባሻዬ ልጅ፣ ‹‹አንበርብር ሕዝባችን ከፈጣሪ ቀጥሎ ለመንግሥት መታዘዝ ልማዱ ስለሆነ ለሕግ መከበር ትልቅ ሥፍራ ይሰጣል፡፡ በዚህም ምክንያት አብዛኛው ሕዝባችን በእስልምናና በክርስትና እምነቶች ውስጥ ሆኖ ለፆምና ለፀሎት መትጋቱ፣ ለሕግ የበላይነትና በሥርዓት ለመኖር የሚሰጠው ክብር የሚደንቅ ነው፡፡ እስቲ አፍሪካም ሆነ ሌላ ቦታ ዞር ዞር ብለህ አስስ፡፡ ዳቦ ላይ አሥር ሳንቲም ለምን ተጨመረ ተብሎ መንግሥት ሊገለበጥ ይችላል፡፡ በሱዳን በቅርቡ የአል በሽር መንግሥት የተገለበጠው በዚህ ሳቢያ ነበር፡፡ እኛ ዘንድ ግን ከፈጣሪ ቀጥሎ መንግሥት የሚከበረውና የዋጋ ጭማሪው ከመቶ በላይ ፐርሰንት ቢሆንም ነውጥ የሌለው፣ ለሕግ መከበር በመትጋትና ሁሉንም ነገር ለፈጣሪ በመተው ነው…›› ሲለኝ በውስጤ ብዙ ነገሮች እየተመላለሱ ነበር፡፡ ይህንን የመሰለ ሕዝብ ኃላፊነት የማይሰማቸው የመንግሥት ሹማምንትና ስግብግብ ነጋዴዎች ተባብረው ሲደቁሱት፣ ፈጣሪ ለምን ዝም አለ ብዬ ስብሰለሰል ምሁሩ የባሻዬ ልጅ የውስጤ ነገር ገብቶት ነው መሰል ሳቀብኝ፡፡ ከሳቅ በላይ ንዴት ነበር ውስጤን የሚንጠው!

በቀደም ዕለት ከቦሌ ወደ አራት ኪሎ ሚኒ ባስ ተሳፍሬ ስጓዝ ሾፌሩ የከፈተው ሙዚቃ በቅርቡ ዳዊት ጽጌ የለቀቀው የአሰፋ አባተ ዘፈን ነበር፡፡ ‹‹…ፊርማና ወረቀት ጠፊ ነው ተቀዳጅ፣ መተማመን ብቻ ይበቃል ለወዳጅ…›› የሚለው ማለቴ ነው፡፡ ‹‹…ማመን መተማመን ሆነ ትርጉም አልባ፣ ከዳር ከዳር ብቻ ሽርትት እንደ ተልባ…›› እያለ ዘፈኑ ሲቀጥል አጠገቤ የተቀመጡ ሸበቶ አዛውንት፣ ‹‹ጉድ እኮ ነው ከበፊት ጀምሮ እርስ በርስ መተማመን አጥተን ነው አገራችንን የግጭት፣ የድህነትና የልመና ማሳ ያደረግናት…›› እያሉ ሲቆጩ፣ ‹‹አባት ያሉት እውነት ነው፡፡ የበፊቱ ጦስ ነው እንዲህ ያለ ውጥንቅጡ የወጣ ጊዜ ላይ የጣለን…›› ብሎ አንዱ ከኋላችን ሲናገር እኔ በሐሳብ ጭልጥ አልኩ፡፡ ምሁሩ የባሻዬ ልጅ በአንድ ወቅት የነገረኝ ትዝ አለኝ፡፡ ‹‹ወንድሜ አንበርብር ይህችን የመሰለች ወርቅ የመሰለች አገር አልምተን በሥልጣኔ ወደፊት ከገፉት አገሮች እኩል መሆን ሲገባን፣ ይኸው ጥልቅ ድህነት ውስጥ ሆነን ያረጀ ከተማ ለማደስ እየተተራመስን ሥቃያችንን እናያለን…›› ነበር ያለኝ፡፡ የባጡን የቆጡን ጭንቅላቴ ውስጥ ሳወጣ ሳወርድ የሾፌሩ የሙዚቃ ማጫወቻ፣ ‹‹አፈረሱት አሉ መሀል አራዳን፣ ያለ እናት ያለ አባት ያሳደገንን…›› የሚለውን የከተማ መኮንን ዕድሜ ጠገብ ዘፈን ሲለቅብን እየፈረሰች ያለችው አራት ኪሎ ደረስን፡፡ አይ አራት ኪሎ!

በቀደም ዕለት ማታ ቤቴ ተቀምጬ በቴሌቪዥን ‹‹ታማኝ›› የተባሉ ከፍተኛ ግብር ከፋይ ባለሀብቶች ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር ሲወያዩ እያዳመጥኩ ነበር፡፡ ውዴ ማንጠግቦሽ ጆሮዋን በኢርፎን ደፍና ቲክቶክ ላይ አፍጥጣለች፡፡ ‹‹የአገር ጉዳይ የሚነገርበት የፖሊሲ ውይይት እያለ ለምን ዝባዝንኬ ነገር ላይ ትጣጃለሽ…›› እያልኩ ከምሁራን የተኮረጀ ማሳሰቢያ ቢጤ ጣል ሳደርግባት፣ ‹‹ምናልባት ለአንተ ድለላ የሚጠቅም ነገር ካለ ራስህ ተከታተል፡፡ እኔ ግን ጥያቄውም ሆነ ምላሹ ምን እንደሆነ ስለማላውቅ ጊዜዬን አላባክንም…›› ስትለኝ ደነገጥኩ፡፡ ጎበዝ እንዴት ነው ነገሩ ከማጀት እስከ አደባባይ መደማመጥም ሆነ መተማመን እየጠፋብን መድረሻችን አስፈራኝ እኮ፡፡ ለማንኛውም እኔ ውይይቱን መከታተል ጀመርኩ፡፡ መቼም የሰው ልጅ ውስጥ ምን ዓይነት ሐሳብ እንዳለ አዋቂው ፈጣሪ ቢሆንም፣ ውይይቱ በከፍተኛ ጥንቃቄና ዲፕሎማሲ የተከናወነ መሰለኝ፡፡ ባለሀብቶቹ እንደተባለው ቀላል ሚዛን አይደሉም፡፡ ፍላጎታቸውም ገደብ ያለው አይመስልም፡፡ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ የቀረቡት ጥያቄዎችም ሆኑ ምላሾች ጥንቃቄ የተሞላባቸው እንደነበሩ የደላላ ጭንቅላቴ ነግሮኛል፡፡ ይኼ ይጥፋኝ እንዴ!

ለውይይቱ ያልተጋበዘ ነገር ግን ከባድ ሚዛኖቹ ውስጥ የሚገኝ ጎልማሳ ደንበኛዬ ባለሀብት ስለውይይቱ ስጠይቀው፣ ‹‹አንበርብር እኔ ፖለቲካ መስማትም ሆነ ማውራት አልፈልግም…›› ሲለኝ፣ ‹‹እኔ እኮ ስለንግድና ኢንቨስትመንት የተደረገ ሁላችንንም የሚነካን ጉዳይ እንጂ፣ ከፖለቲካ ጋር የሚያገናኝ ነገር አይደለም እንነጋገርበት ያልኩህ…›› ማለት፡፡ አጅሬው በትዝብት መልክ እያየኝ ሳቅ ብሎ፣ ‹‹የእኔ ወንድም እዚህ አገር ሁሉም ነገር የሚገናኘው ከፖለቲካ ጋር ስለሆነ ጎመን በጤና ብሎ ማደር ነው የሚያዋጣው…›› ካለኝ በኋላ፣ ‹‹ሰዎቹ እጅግ ጥንቃቄ በተሞላበት መንገድ መነጋገራቸውን መቼም አንተም አትክድም፡፡ እነሱ በዚያ ሁኔታ ያለፉበትን ውይይት የምተነትነው እኔ ማን ሆኜ ነው…›› ብሎኝ ወደ ተቀጣጠርንበት ጉዳይ ነገሩን ሲያዞረው ከዝምታ በቀር የምናገረው አልነበረም፡፡ ይህንን ጉዳይ የሚያፍታታልኝ ያው ምሁሩ የባሻዬ ልጅ ስለነበር እሱን እስከማገኝ ወደ ድለላ ሥራዬ ተሰማራሁ፡፡ ለማንኛውም መንግሥት እንደ ሲኖትራክ ፍሬን እፍን አድርጎ የያዘው የብድር ገደብ እስኪለቀቅ፣ ጠባይ ያስፈልጋል ተብሎ ዝም ማለት የተፈለገ ለምን እንደመሰለኝ ለራሴም አልገባኝም፡፡ ወይ ነገር መሸሽ እንበለው!

የድለላ ሥራዬ የማያደርሰኝ ቦታ የለም፡፡ መቼ ዕለት ነው ካዛንቺስ ብቅ ብዬ ነበር፡፡ የድሮዋ የደራችው ካዛንቺስ ጭር አለችብኝ፡፡ ደግነቱ ወደ ውስጥ ገባ ሲባል እነዚያ የድሮ መንደሮች ታሪክ ነጋሪ መስለው በሩቅ ይታያሉ፡፡ የእነሱም ተራ ደርሶ እስኪፈራርሱ ድረስ ካዛንቺስ ምልክት እንዳታጣ ያገዙ ይመስላሉ፡፡ በኢንተርኮንቲነንታል ሆቴል ጀርባ ቁልቁል ተወርዶ ኢሊሌ ሆቴልን አልፎ ያሉ አፓርታማዎች ስደርስ፣ ኢትዮጵያ ውስጥ ሳይሆን ውጭ አገር የሄድኩ እስኪመስለኝ አካባቢው ግራ አጋባኝ፡፡ ከበስተጀርባው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅትን ምድረ ግቢ ተገን ያደረገው አካባቢው በአጭር ጊዜ ውስጥ ተለውጦ ካዛንቺስን ታሪክ ያደረጋት ይመስላል፡፡ ካላቸው አራት አፓርትመንት ቤቶች አንደኛውን እንዳሻሽጥላቸው የጠሩኝ ዳያስፖራ መሳይ አዛውንት፣ ‹‹አቶ አንበርብር በጥሩ ሁኔታ የያዝኩት ቤት ስለሆነ ደህና ገዥ ፈልግልኝ፡፡ ጨዋና ኩሩ የሆነ እንጂ ከሜዳ በአጋጣሚ የታፈሰ ሲሳይ ያገኘ ወመኔ እንዳታመጣብኝ…›› ሲሉኝ፣ ‹‹እርስዎ ሸጠው መገላገል እንጂ ደባል እኮ አይደለም የሚያስፈልግዎ…›› ከማለቴ፣ ‹‹አቶ አንበርብር ንብረቴን ብሸጥም ለአካባቢያችን የማይበጅ ዱርዬ እንዲመጣብኝ አልፈልግም…›› ብለው አቌረጡኝ፡፡ ጎበዝ ለአገር ጭምር እንዲህ መልካም የሚመኝ ሰው ሲያጋጥመኝ በጣም ነው ደስ የሚለኝ፡፡ እናንተስ!

አዲስ አበባን አካልዬ አዛውንቱ እንደሚፈልጉት መልካም የሚባል ገዥ አግኝቼ ከተስማሙልኝ በኋላ ኮሚሽኔን ተቀብዬ ስንሰነባበት፣‹‹አቶ አንበርብር ለስሜቴ ተጨንቀህ እንደምፈልገው ጨዋ ሰው ስላገኘህልኝ አመሠግንሃለሁ…›› ብለው ከኮሚሽኔ በተጨማሪ ጉርሻ እንደሰጡኝ መናገር አለብኝ፡፡ መልካም ሥራ ሲያሸልም ደስ ይላል፡፡ ለአገራቸው መልካም ሥራ የሚያከናውኑ ሰዎች ሲሸለሙ ደስ ይለኛል፡፡ ምን ያደርጋል የዘንድሮ ሹመትና ሽልማት በቲፎዞ እየሆነ ብዙዎች እየተረሱ ነው መሰል ፈጣሪ የሚርቀን፡፡ ‹‹ከአዋቂ በላይ ታዋቂ በሚከበርባት አገር ውስጥ ጥራዝ ነጠቅነት በዝቶ ነው መከራችንን የምናየው…›› ይሉኝ የነበሩት ፆምና ፀሎት ላይ እየበረቱ ያሉት አዛውንቱ ባሻዬ ነበሩ፡፡ እሳቸው አሁን አርምሞ ውስጥ ሆነው ምንም ባይናገሩም፣ ‹‹ልጅ አንበርብር በመምህርነት፣ በውትድርና፣ በሐኪምነት፣ በመንግሥት ሠራተኝነትና በተለያዩ ሙያዎች አገራቸውን ያገለገሉ ምን የመሳሰሉ ሰዎች እያሉን መድረኩን የተቆጣጠሩት ጥራዝ ነጠቆች ሆነው እኮ ነው መስማማት የራቀን…›› ይሉኝ የነበረው አይረሳኝም፡፡ ልጃቸውም በዚህ ጉዳይ ይሉኝታ የሚባል ነገር አያቅተውም፡፡ ‹‹ኢትዮጵያ እኮ እዚህ የደረሰችው አገራቸውን ከልባቸው በሚያፈቅሩ ቅኖች፣ ሀቀኞች፣ ጀግኖችና አርቆ አሳቢዎች እንደሆነ እየተረሳ አገር አጥፊዎች ሲፈነጩ ማየት ያበሳጫል…›› ይለኝ ነበር፡፡ እውነት ነው!

ስልኬ ከአንድ ፈላጊዬ እስክታገናኘኝ እየተጠባበቅኩ እግሬን ለማፍታት ቀስ እያልኩ ስራመድ፣ ‹‹አንበርብር ምንተስኖት…›› የሚል ድምፅ ሰማሁ፡፡ ድምፁ ወደ መጣበት አቅጣጫ አንገቴን መለስ ሳደርግ፣ ‹‹አንበርብር እኔ ነኝ…›› እያለ አንድ የማላውቀው ሰው በፈገግታ ተሞልቶ ወደ እኔ ተንደረደረ፡፡ አጠገቤ ደርሶ እጁን ለሰላምታ እየዘረጋ፣ ‹‹አንተ አታውቀኝም እኔ ግን በዝና አውቅሃለሁ…›› ሲለኝ፣ ‹‹እንዴት ነው ነገሩ እኔ ዘፋኝ፣ የቴአትር ወይም የፊልም ተዋናይ አይደለሁ፡፡ አሊያም ደግሞ በአገር የታወቅኩ ከፍተኛ ግብር ከፋይ ሀብታም እንዳልሆንኩ የታወቀ ነገር ነው…›› እያልኩ ስስቅ፣ ‹‹ምን ነካህ አንበርብር አንተ እኮ በአዲስ አበባ ከተማ የታወቅህ ዋናው የደላሎች ቁንጮ ነህ…›› እያለ መለሰልኝ፡፡ ለማንኛውም ሰውዬው ጸሐፊ እንደሆነ ነግሮኝ ፈቃደኛ ከሆንኩ የሕይወት ታሪኬን ከእነ ገጠመኞቼ በመጽሐፍ ለማሳተም ፈቃደኝነቴን ጠየቀኝ፡፡ እኔ ግን ስንትና ስንት ያልተዘመረላቸው ኢትዮጵያውያን ባሉበት አገር ውስጥ ፈፅሞ አልሞክረውም ብዬ አመሥግኜ ሸኘሁት፡፡ የአንድ ደላላ ታሪክ ቢጻፍ በርካታ ተያያዥ ጉዳዮች እንዳሉ ቢያስረዳኝምና የሰውዬው ሐሳብም ትክክል ቢሆንም፣ እኔ ግን ቅድሚያ የሚሰጣቸው በርካታ የታሪክ ባለቤቶችን አስሶ ቢያገኝ እንደሚመረጥ ነው ሞግቼ አሳምኜ የሸኘሁት፡፡ ጎበዝ እየተሳሰብን እንጂ!

በሉ እስቲ እንሰነባበት፡፡ የዕለት ውሎዬ ተገባዶ ወደ ቤቴ ከመሄዴ በፊት ምሁሩን የባሻዬ ልጅ ግሮሰሪ ቀጥሬው ወደ እዚያ አዘገምኩ፡፡ ቀኑ ተገባዶ መሸት ሊል ሲል ግሮሰሪ ቁጭ ብለን ያላበውን ቢራ እየቀማመስን ወጋችንን ስንሰልቅ፣ ልክ እንደ የሒሳብ መመዝገቢያ ማሽን ‹‹ዜድ ሪፖርት›› ማለት ነው፡፡ ግሮሰሪ ስደርስ ምሁሩ ወዳጄ ቀድሞኝ ደርሶ ከስልኩ ማስታወሻ ቢጤ እያነበበ ነበር፡፡ ሰላምታ ተለዋውጠን ቢራችንን መጎንጨት ስንጀምር፣ ‹‹በአገር ልማትም ሆነ ዕድገት የባለቤትነት ስሜት ሊኖር የሚችለው ሁላችንም አንድ ገጽ ላይ ስንሆን ነው…›› የሚል ጠጠር ያለ መልዕክት ያዘለ ድምፅ ከባንኮኒ በኩል ሰማን፡፡ ተናጋሪው ከዕድሜም ከዕውቀትም ገፋ ያደረገ ጎልማሳነትን እያለፈ ያለ ሲሆን፣ አዳማጩ ደግሞ ሰላሳዎቹን ያጋመሰ የተማረ መሳይ ነው፡፡ ምሁሩን የባሻዬ ልጅ ጠቀስ ሳደርገው፣ ‹‹መልዕክቱ በግራም ሆነ በቀኝ ጎራ ፈጥረው ለሚነታረኩ ወገኖች መልካም ምሳሌ ይመስለኛል…›› አለኝ፡፡ የጋራ በሆኑ ጉዳዮች ላይ ለመስማማትም ሆነ በልዩነት ሐሳብን ለማጥራት መደማመጥ ሲያስፈልግ፣ ሁሌም ንትርክና ለግጭት ጥርጊያ የሚከፍቱ ዘለፋዎች ላይ ብቻ ማተኮር እየጎዳን ያለ መሰለኝ፡፡ መሰለኝ ያልኩት አጉል ድምዳሜ ላይ ላለመድረስ ብቻ ሳይሆን፣ እናንተም የተለየ ሐሳብ ካላችሁ ብዬ ነው፡፡ የአገር ጉዳይ አንዱ ባለቤት ሌላው ባዕድ ወይም ታዛቢ እንዲሆን የሚደረግበት አጉል ነገራችን ስለሚታክት፣ እስቲ በግራም ሆነ በቀኝ የተሠለፋችሁ ወገኖች ራሳችሁን መርምሩ፡፡ ‹‹ራስን ለመመርመር ግን መጀመሪያ ራስን መግራት ያስፈልጋል…›› የሚለው ምሁሩ ወዳጄ ነው፡፡ መልካም ሰንበት!

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት