Monday, April 15, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊእያንሰራራ የሚገኘው የቲቢ ሥርጭት

እያንሰራራ የሚገኘው የቲቢ ሥርጭት

ቀን:

ኢትዮጵያ ውስጥ እ.ኤ.አ. በ2035 ቲቢ የማኅበረሰብ የጤና ሥጋት ወደ ማይሆንበት ደረጃ ለማድረስ የሚያስችል ዕቅድ ተይዟል፡፡ ለዕቅዱም ስኬታማነት አንድ ቢሊዮን ዶላር በጀት ማስፈለጉን ጤና ሚኒስቴር አስታውቋል፡፡

የሚኒስቴሩ የቲቢ፣ የሥጋ ደዌና የሌሎች ሳምባ በሽታዎች መከላከያና መቆጣጠሪያ ዴስክ ኃላፊ አቶ ታዬ ለታ እንደገለጹት፣ ለእንቅስቃሴው ስኬታማነት ከሚያስፈልገው በጀት ውስጥ 30 ከመቶ ያህሉ ተገኝቷል፡፡

እያንሰራራ የሚገኘው የቲቢ ሥርጭት | Ethiopian Reporter | ሪፖርተር
የጤና ሚኒስትር መቅደስ ዳባ (ዶ/ር)

ገንዘቡም የተገኘው ከመንግሥትና ከአጋር ድርጅቶች መሆኑን ገልጸው፣ የቀረውን 70 ከመቶ በጀት ለመሸፈንም ፕሮጀክት ሐሳብ ተዘጋጅቶ ለአጋር ድርጅቶች እንደሚቀርብና በዚህም ላይ ክልሎች የየራሳቸውን አስተዋጽኦ እንዲያበረክቱ የሚጠየቁ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

‹‹በእርግጥ ቲቢን መግታት እንችላለን›› በሚል መሪ ቃል የዓለም የቲቢ ቀንና 18ኛው ዓመታዊ የቲቢ ምርምር ጉባዔ በተከናወነበት ሥነ ሥርዓት ላይ አቶ ታዬ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ዕቅዱ በሁሉም የአገሪቱ ክፍሎች የሚተገበረው ለሰባት ዓመታት ያህል ነው፡፡

ተግባራዊ በሚደረግባቸው ሰባት ዓመታት ውስጥ ከ100,000 ሰዎች መካከል በቲቢ የሚያዙ ሰዎች ምጣኔ ከአሥር በታች ከሆነ ቲቢ የማኅበረሰቡ የጤና እክል ወደማይሆንበት ደረጃ ላይ ለመድረሱ ማረጋገጫ እንደሚሆን አክለዋል፡፡

የቲቢ በሽታ በዓይን የማይታይ ከባክቴሪያ ቤተሰብ የሚመደብ፣ ማይክሮ ባክቴሪያም ቲዩበርከሎስስ ተብሎ በሚጠራ ተህዋስ የሚመጣ ተላላፊ በሽታ መሆኑን ገልጸው፣ በዓለም አቀፍ ደረጃም ገዳይ ከተባሉ በሽታዎች መካከል ዋነኛውና ግንባር ቀደም መሆኑን አስረድተዋል፡፡

የቲቢ በሽታዎች ብዙ ዓይነቶች ሲሆኑ፣ ዋና ዋናዎቹ ደግሞ የሳምባና የአጥንት መሆናቸውን የተናገሩት አቶ ታዬ፣ የአጥንት ቲቢ ፓስቸራይዝድ ያልሆነ ወይም ጥሬ ወተት በመጠጣት፣ የሳምባ ቲቢ ደግሞ ከአፍና ከአፍንጫ በሚወጣው በባክቴሪያው በተበከለ ትንፋሽ ወይም በማስነጠስና በማሳል እንደሚመጣ ገልጸዋል፡፡

እያንሰራራ የሚገኘው የቲቢ ሥርጭት | Ethiopian Reporter | ሪፖርተር
የዩኤስኤአይዲ ሚሽን ዳይሬክተር ስኮት ሆክላንደር

የሳምባ ታማሚ ሆኖ ወደ ጤና ተቋም ያልሄደ፣ ሕክምና ጀምሮ ያቋረጠ፣ ነፋሻ አየርና የፀሐይ ብርሃን የሚያስገባ መስኮት የሌለው፣ አለበለዚያም መስኮቱ ዘወትር ዝግ ሆኖ የሚውል ቤት፣ ብዙ ተሳፋሪዎችን ይዞ ግራና ቀኝ ያሉትን መስኮቶች ዘግቶ አገልግሎት የሚሰጥ ተሽከርካሪ፣ ማረሚያ ቤቶችና ሌሎችም የንፅህና ጉድለቶች የሳምባ በሽታ አስተላላፊ መሆናቸውንም አክለዋል፡፡

ቲቢ ሁሉንም የኅብረተሰብ ክፍሎች የሚያጠቃ ቢሆንም፣ በአብዛኛው እያጠቃ ያለው አምራች ኃይሉን መሆኑን ጠቁመው፣ በበሽታው የመያዝ ምልክቶች ውስጥም ከአንድ እስከ ሁለት ሳምንታት የሚዘልቅ ሳል፣ ሌሊት ላይ በላብ መዘፈቅ፣ የምግብ ፍላጎት እየቀነሰ መምጣትና የሰውነት ድካም ተጠቃሾች መሆናቸውን አስረድተዋል፡፡

ምልክቶች እንደታዩ የመንግሥትና የግል ጤና ተቋማት በመሄድ፣ የሕክምና አገልግሎት ማግኘት እንደሚቻል፣ አገልግሎቱም የሚሰጠው በነፃ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

በዓለም በዓመት ወደ 1.3 ሚሊዮን የሚጠጉ ሰዎች በቲቢ ባክቴሪያ ምክንያት ለህልፈተ ሕይወት እንደሚዳረጉ፣ 10.6 ሚሊዮን የሚሆኑ ሰዎች ደግሞ በባክቴሪያው እንደሚያዙ፣ ከእነዚህም መካከል 7.4 ሚሊዮን የሚሆኑ ሰዎች ተለይተው ሕክምናቸውን በመከታተል ላይ እንደሆኑ ጠቁመዋል፡፡

እንደ ኃላፊው ኢትዮጵያ ውስጥ በዓመት 156,000 ሰዎች በቲቢ ይያዛሉ፣ ከእዚህም መካከል 135,000 ያህሉ ተለይተው በመታከም ላይ ናቸው፡፡ 16 ሺሕ ሰዎች ደግሞ ይሞታሉ፣ ሌሎች 20,000 ታማሚዎች ወደ ጤና ተቋም ሳይሄዱ በቤታቸው ውስጥ ይገኛሉ፡፡

የቲቢ ሥርጭት በተለይም በአዲስ አበባ ከተማ ከፍ እያለና አድማሱን እያሰፋ መምጣቱን ጠቁመው፣ በከተማዋ ከ7,000 በላይ የሚሆኑ የቲቢ ሕሙማን መገኘታቸውን፣ የሥርጭቱም መጠን ከፍ ሊል የቻለው በሥራና በሌላም ምክንያት ወደ አዲስ አበባ በየጊዜው የሚገባው የሰው ቁጥር እየጨመረ በመምጣቱ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

እንደ አቶ ታዬ፣ ኢትዮጵያ በዓለም ቲቢና ፀረ ተህዋስያን መድኃኒቶችን የተለማመዱ የቲቢ በሽተኞች ካሉባቸው 30 አገሮች ተርታ ተሠልፋ የነበረ ቢሆንም፣ ከዚህ ወጥታለች፡፡

በ2020 የሰዎች በቲቢ የመያዝ ምጣኔ 20 በመቶ፣ የመሞት ምጣኔ ደግሞ 35 በመቶ እንዲሆን በዓለም አቀፍ ደረጃ የወጣውን ግብ ኢትዮጵያ ሙሉ ለሙሉ በማሳካቷም፣ ፀረ ተህዋስን መድኃኒት ከተለማማዱ የቲቢ በሽታዎች ነፃ እንድትሆን፣ በዓለም አቀፍ ደረጃ የተቀመጠውንም ግብ ለማሳካት እንደቻለች፣ መንግሥት፣ አጋር ድርጅቶችና ባለድርሻ አካላት ተቀናጅተው መንቀሳቀሳቸው ለስኬቱ ምክንያት መሆኑን አክለዋል፡፡

ይህም ሆኖ ግን ባለፉት አራትና ሦስት ዓመታት የኮቪድ-19 ወረርሽኝ መንሠራፋት፣ ግጭቶች፣ ድርቅ፣ መፈናቅሎችና የሰሜኑ ጦርነት መከሰት የቲቢ ሥርጭት እንዲያንሠራራ ማድረጉን ጠቁመዋል፡፡

ባለፈው መስከረም በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በተካሄደው ዓለም አቀፍ ጉባዔ ላይ ቲቢ የማኅበረሰብ የጤና ተግዳሮት እንዳይሆን ለማድረግ ጉዳዩ በይበልጥ የሚመለከታቸው አገሮች ቃል ገብተዋል፡፡

ኢትዮጵያም ይህንን ቃል ተግባራዊ ለማድረግ የሚያስችላትን ሰፊ ሥራ በማከናወን ላይ ነች ያሉት ደግሞ የአርማወር ሀንሰን ምርምር ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተርና የቲዩበርክሎስስ ምርምር አማካሪ ምክር ቤት ሰብሳቢ አፈወርቅ ካሱ (ፕሮፌሰር) ናቸው፡፡

እንደ ፕሮፌሰሩ፣ ምርምርና ጥናት ተደርጎ የሚገኘው ምክረ ሐሳብ በሚመለታቸው አካላት መተግበር አለበት፡፡ ለዚህም ዕውን መሆን የከፍተኛ ትምህርትና የምርምር ተቋማት እንዲሁም በቲቢ ዙሪያ የሚሠሩ አካላት ሊቀናጁና ሊተባበሩ ይገባል፡፡

ምክር ቤቱ በ2001 መቋቋሙን፣ በዘንድሮው ጉባዔ ከተለያዩ የአፍሪካ አገሮች የመጡ የቲቢ ተመራማሪዎች መሳተፋቸውን፣ በመረጃ ላይ የተመሠረተ የቲቢ ጥናትና ምርምር ባህልን ለማሳደግ የበኩሉን አስተዋጽኦ በማድረግ ላይ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡

የጤና ሚኒስትር መቅደስ ዳባ (ዶ/ር)፣ በኢትዮጵያ የቲቢ በሽታን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የተሠሩ ተግባራት ውጤታማ መሆናቸውን ገልጸው፣ ሆኖም በቲቢ የተያዙ ሰዎች አሁንም መገለል እንደሚደርስባቸው አስረድተዋል፡፡

በቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ሚሌኒየም ሕክምና ኮሌጅ፣ በኢትዮጵያ የኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩትና በአዲስ አበባ ጤና ቢሮ አስተባባሪነት መጋቢት 13 ቀን 2016 ዓ.ም. በተከናወነው መድረክ፣ ዩኤስኤአይዲ ያዘጋጀውና በአርሶ አደሩ አካባቢዎች የሚተገበር የቲቢ መከላከልና ሕክምና ፕሮጀክት ይፋ ሆኗል፡፡

ባለፉት 25 ዓመታት በኢትዮጵያ ቲቢን ለመከላከልና ለመቆጣጠር ሥራዎች 350 ሚሊዮን ዶላር ያህል ድጋፍ ማድረጉን የገለጸው ዩኤስኤአይዲ፣ ኢትዮጵያ ቲቢን በ2030 ለማጥፋት ለጀመረችው ሥራ፣ ‹‹ከግሎባል አክስለሬተር ፕላስ ኢንሽየቲቭ›› በ2024 የስድስት ሚሊዮን ዶላር ድጋፍ እንደሚያደርግ ገልጿል፡፡ የኢትዮጵያ መንግሥት ስድስት ሚሊዮን ዶላር ማች ፈንድ እንደሚያወጣም ታውቋል፡፡

የዩኤስኤአይዲ ሚሽን ዳይሬክተር ስኮት ሆክላንደር እንዳስታወቁት፣ የዩኤስኤአይዲ ቲቢ ሎካል ኦርጋናይዜሽንስ ኔትዎርክ (ቲቢ ኤልኦኤን) በአፋር፣ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ፣ በጋምቤላና በሶማሌ ቲቢን ለመከላከል ለሚሠራው ሥራ የሚደግፍ ይሆናል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ የቲቢ ምርመራን ለማስፋፋት የአንድ ሚሊዮን ዶላር ሲድ ፈንድ ይለግሳል፡፡    

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ቪር ጀነራል ትሬዲንግ ኃ/የተ/የግ/ማኀበር የጨረታ ማስታወቂያ

ቪር ጀነራል ትሬዲንግ ኃ/የተ/የግ/ማኀበር በገቢ እና በውጭ ንግድ እንዲሁም...

ያልተቃናው የልጆች የንባብ ክህሎት

አንብቦና አዳምጦ መረዳት፣ የተረዱትን ከሕይወት ጋር አዋህዶ የተቃና ሕይወት...

እንስተካከል!

ሰላም! ሰላም! ውድ ኢትዮጵያውያን ወገኖቼ እንዲሁም የሰው ዘር በሙሉ፣...

የሙዚቃ ምልክቱ ሙሉቀን መለሰ ስንብት

የኢትዮጵያ ዘመናዊ ሙዚቃ በ1950ዎቹ እና በ1960ዎቹ በኪነ ጥበባትም ሆነ...