Monday, April 15, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊ‹‹የፋዘር ቤት›› ትሩፋት

‹‹የፋዘር ቤት›› ትሩፋት

ቀን:

በኢትዮጵያ ሙዚቃ ውስጥ ስማቸው በክብር ከሚወሳ ከያኒያን መካከል ጸሐፊ ትውኔት፣ የዜማና የግጥም ደራሲ ተስፋዬ አበበ ይገኙበታል፡፡ ለበርካታ ታዋቂና አንጋፋ ሙዚቀኞች የዜማና የግጥም ድርሰት በማዘጋጀትም ይታወቃሉ፡፡ በተለይ ደግሞ ታዳጊዎችና ወጣቶችን በኪነ ጥበባት ዘርፍ በማሠልጠን አያሌዎችን ማፍራት የቻሉ መሆናቸውም ይነገራል፡፡

‹‹የፋዘር ቤት›› ትሩፋት | Ethiopian Reporter | ሪፖርተር
ተዋናይዋ ኮከብ ተስፋዬ

ከብላቴና ዕድሜያቸው ጀምሮ ከአርቲስት ተስፋዬ (በተማሪዎቻቸው አጠራር ፋዘር) እግር ሥር ቁጭ ብለው በኪነ ጥበብ ሙያ ተኮትኩተው ካደጉ ተሰጥዖቸውን አሳድገው ለፍሬ ከበቁ ልጆች መካከል የሥጋ ልጃቸው የሆነችው ኮከብ ተስፋዬ አንዷ ናት፡፡

ተዋናይዋ ኮከብ ተስፋዬ በተለያዩ ፊልሞችና ቴአትሮች ላይ በተዋናይነት፣ በደራሲነትና በአዘጋጅነት መሳተፏን ትገልጻለች፡፡ በአዲስ አበባ ማዘጋጃ ቤት ይቀርብ የነበረው፣ ተከታታይ በሆነውና 18 ክፍል በዘለቀው ‹‹የቃል ኪዳን ሕይወት›› የተሰኘ ተውኔት በ1994 ዓ.ም. በልጅነት ዕድሜዋ በመሪ ተዋናይነት የሠራችበት ነው፡፡  

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

‹‹አምታታው በከተማ›› በተሰኘ በአባቷ በተስፋዬ አበበ የተዘጋጀ ተውኔት ላይ ከአንጋፋ ከያኒያን ከእነ ዓለሙ ገብረ አብ፣ ሲራክ ታደሰ፣ ዘነበች ታደሰ (ጭራ ቀረሽ)፣ ቴዎድሮስ ተስፋዬና ከሌሎችም አንጋፋ አርቲስቶች ጋር የሠራች ሲሆን፣ በወቅቱም ዕድሉን አግኝታ ከእነሱ ጋር በመሥራቷ ደስተኛ መሆኗን ትናገራለች፡፡

ወደ መንፈሳዊነት የሚያደላ ዘውግ ባለውና ‹‹የይቅርታ ዘመን›› በተባለ ተውኔትም መሪ ተዋናይት በመሆን ተጫውታለች፡፡

በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን በ1990ዎቹ እሑድ ከሰዓት በሚተላለፍ ‹‹120›› በተሰኘ ፕሮግራም ላይ ‹‹አጋጣሚ›› በሚል ርዕስ በተዘጋጀ ተከታታይ የቴሌቪዥን ድራማ ላይ እኩይ ገጸ ባህሪ በመወከል ተሳትፋለች፡፡  

በተስፋዬ አበበ በተዘጋጀውና ‹‹አብዲሳ አጋ›› በሚል፣ የአርበኛውን ሕይወት በሚዘክር ተውኔትም የአብዲሳ አጋን ባለቤት ‹‹መነን››ን በመወከል መሳተፏን የምትናገረው አርቲስት ኮከብ፣ ይህንም ተውኔት የቀድሞው ፕሬዚዳንት ግርማ ወልደ ጊዮርጊስ በተገኙበት ብሔራዊ ቤተ መንግሥት ኢዮቤልዩ ተጋብዛ ለማቅረብ በመቻሏ በኪነ ጥበብ ሕይወቷ እንደ ስኬት የምትቆጥረው ነው፡፡

በ2008 ዓ.ም. ‹‹የአውሬው ርግቦች›› በተሰኘ ተውኔትም ከዳንኤል ተገኝ ጋር መሪ ተዋናይ ሆና መተወኗን፣ ‹‹ያልነደደ እሳት›› ተውኔት ላይም የዋና ገጸ ባህሪ ሚና ኖሯት መሥራቷን ትናገራለች፡፡  

ከኢትዮ ታለንት ሾው ጋር በመተባበር በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ‹‹ዓመት በዓል›› የተሰኘ በራሷ የተጻፈና የተዘጋጀ ተውኔት ላይ በመሪ ተዋናይነት መሥራቷንና ሌሎችም በርካታ በስምና በቁጥር የዘነጋቻቸውን ተውኔቶች ሠርታለች፡፡

በአሁኑ ወቅትም ‹‹ባለን እናመስግን›› የሚል ተውኔት ጽፋ በማዘጋጀት ከኅብር ግኝት የኪነ ጥበብ ማኅበር ጋር በመሆን፣ በተለያዩ የኢትዮጵያ ክፍሎች በመዘዋወር ለማቅረብ ማቀዷን የምትናገረው አርቲስቷ፣ የተውኔቱ ጭብጥም ሰላምን፣ አብሮነትን፣ አንድነትንና ፍቅርን የሚሰብክ ነው፡፡ 

‹‹አባቴ በኪነ ጥበብ ዘርፉ በተለይም በሙዚቃና በተውኔት ሙያ ኮትኩቶ ካሠለጠናቸውና ወደ ኪነቱ መንገድ ከመራቸው ታዳጊዎቹ መካከል አንዷ እኔ ነኝ፡፡ በዚህም ለአባቴ ከፍ ያለ ምስጋና አለኝ፤›› ትላለች፡፡

በአሁኑ ወቅት በአርቲስት ተስፋዬ አበበ የኪነ ጥበብ ማዕከል ፕሮዳክሽን ማናጀር ሆና እያገለገለች እንደምትገኝ የምትናገረው አርቲስት ኮከብ፣ ማዕከሉ ለሃምሳ አምስት ዓመታት ያህል ‹‹የፋዘር ቤት›› እየተባለ ያለ ምንም ክፍያ በተለያዩ የኪነ ጥበብ ዘርፎች ወጣቶችን ሲያሠለጥን ቆይቷል፡፡

ካለፉት ሦስት ዓመታት ወዲህ ግን የማዕከሉን ደረጃ ከፍ በማድረግ ከቴአትርና ከሙዚቃ ባሻገር የሜክአፕ (ሥነ ገጽ) እና የሞዴሊንግ ሥልጠናዎችን በማካተት በክፍያ ወጣቶችን እየተቀበለ በሠርተፊኬት እያስመረቀ እንደሚገኝ ትናገራለች፡፡   

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ቪር ጀነራል ትሬዲንግ ኃ/የተ/የግ/ማኀበር የጨረታ ማስታወቂያ

ቪር ጀነራል ትሬዲንግ ኃ/የተ/የግ/ማኀበር በገቢ እና በውጭ ንግድ እንዲሁም...

ያልተቃናው የልጆች የንባብ ክህሎት

አንብቦና አዳምጦ መረዳት፣ የተረዱትን ከሕይወት ጋር አዋህዶ የተቃና ሕይወት...

እንስተካከል!

ሰላም! ሰላም! ውድ ኢትዮጵያውያን ወገኖቼ እንዲሁም የሰው ዘር በሙሉ፣...

የሙዚቃ ምልክቱ ሙሉቀን መለሰ ስንብት

የኢትዮጵያ ዘመናዊ ሙዚቃ በ1950ዎቹ እና በ1960ዎቹ በኪነ ጥበባትም ሆነ...