Saturday, April 20, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

የውጭ ምርቶችን በአገር ውስጥ ለመተካት አዋጭው መንገድ ‹‹በተናጠል ከመጓዝ በጋራ መሥራት ነው!››

አገር በቀል ኩባንያዎች ለአንድ አገር ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ወሳኝ ናቸው፡፡ በተለይ የግሉ ዘርፍ የሚኖረው አስተዋጽኦ ከፍተኛ ስለመሆኑ አይታበይም፡፡ ተደጋግሞ የመነገሩን ያህል ግን በተጨባጭ ኢኮኖሚያዊ አስተዋጽኦው በሚጠበቀው ደረጃ የሚገለጽ ነው ወይ? ከተባለ አይደለም ብሎ ለመግለጽ ይቻላል፡፡ አገር የሚያድገው ኢኮኖሚያዊ ዕርምጃው ሊፋጠን የሚችለው የግሉ ዘርፍ በሚያካሂደው ኢንቨስትመንት ነው፡፡ 

ዛሬ አደጉ የሚባሉ አገሮች ለደረሱበት የዕድገት ደረጃ የበቁት የግሉን ዘርፍ የሚያሳትፍና የሚያበረታቱ አሠራሮችን በመዘርጋታቸው ነው፡፡ አገሮች የተለወጡት መንግሥት ባቋቋማቸው ኩባንያዎች ሳይሆን፣ በየዘርፉ ጠንካራ የግል ኩባንያዎች እንዲፈጠሩ በማድረጋቸው ነው፡፡ ለኩባንያዎቻቸው የሚሰጡት ክብር፣ እንዲሁም የአገር በቀል ኩባንያዎቻቸውን ምርት ዜጎቻቸው እንዲጠቀሙ በማድረግ ጭምር ነው፡፡   

በየትኛውም የዓለም ክፍል ተገኘ ለሚባለው ኢኮኖሚያዊ ዕድገት መሠረቱ የግል ዘርፍ መሆኑ የመታመኑን ያህል፣ ይህንን ወሳኝ ጉዳይ ከኢትዮጵያ አንፃር ስናየው ገና ብዙ የሚቀረው ነው፡፡ የግል ዘርፉ ጠንካራ አይደለም፡፡ ጠንካራ አደረጃጀት የለውም፡፡ በሥነ ምግባር የታነፀ አሠራር አለው ወይ? ከተባለም በአብዛኛው ችግር የሚታይበት ነው፡፡ በአብዛኛው በቶሎ ትርፍ የሚገኝበት ዘርፍ ላይ የተከማቸ በመሆኑ አገራዊ ጠቀሜታ ያላቸው ኢንቨስትመንቶች ላይ የሚሳተፉቱ እጅግ ጥቂቶች ናቸው፡፡ በአስመጪነት ንግድ ላይ ብቻ ተንጠልጥሎ የቆየው የኢትዮጵያ የቢዝነስ ሥራ ዕሳቤ ከግል ጥቅም በስተቀር ወደ አገር ኢኮኖሚ የሚሻገር ትርፍ የማያመጣ አይደለም።

ዘርፉ እንዲህ ያሉ በርከት ያሉ ችግሮች ያሉበት ቢሆንም፣ አሁንም አገር ለመለወጥ የግል ዘርፉን ከማበረታታትና ከማጠናከር ውጪ አማራጭ የለም፡፡ ካሉባቸው ችግሮች አላቅቆ ወደሚፈለገው አቅጣጫ እንዲራመድ የውዴታ ግዴታ መሆን አለበት፡፡ ኢኮኖሚን ለማሳደግ፣ የዋጋ ንረትን ለማቃለል፣ የውጭ ምንዛሪ ገቢን ለማሳደግና አጠቃላይ ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ለማምጣት የግል ዘርፉና የመንግሥት ትብብር ደግሞ ትልቅ ቦታ ሊሰጠው ይገባል፡፡ 

የግል ዘርፉ በትክክል አገር የሚለውጥ አቅሙን ማውጣት የሚችለው መንግሥት ምቹ የሆኑ አሠራሮችን ሲያመቻችለት ጭምር ነው፡፡ የግል ዘርፍ ፍላጎትና ጥረት ድጋፍ ካላገኘ ጠቃሚ ኢንቨስትመንቶችን ማካሄድ አይቻልም፡፡ ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታቸው የጎሉ ቢዝነሶች ላይ ኢትዮጵያውያን ተሳትፎ በተጨባጭ እንዲጎላ ከተፈለገም እስከዛሬ በተሄደበት መንገድ መጓዝ ውጤት እንደማያመጣ መታወቅ አለበት፡፡ 

እንደ አገር ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ ገበያ ላይ የምትታወቅባቸውን ምርቶች የሚያቀርቡ ኩባንያዎች እንዲኖሩን ግድ ከሆነ ደግሞ የግል ዘርፉ በተናጠል ከሚያካሂደው ቢዝነስ ጎን ለጎን በጋራ የመሥራትን ልምድ ማዳበር አለበት፡፡ ያልተመጠነ ትርፍ ከሚጋበስበት የቢዝነስ ዘርፍ በመውጣት አገራዊ ጠቀሜታ የሚሰጡ ትልልቅ ኢንዱስትሪዎችን ለማደራጀት ከአገር ባለሀብት በላይ ሊመጣ የሚችል የለምና ከሕንፃ ግንባታና ዕቃ አስመጥቶ ከማከፋፈል ያለፈ ሥራ ይጠበቅባቸዋል፡፡  

ከሰሞኑ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከታማኝ የግብር ከፋዮች ጋር ባደረጉት ውይይት፣ ‹‹ለአገሪቱ በከፍተኛ ወጪ የምታስመጣቸውን እንደ ብረትና የግንባታ ማጠናቀቂያ ምርቶችን በአገር ውስጥ ለማምረት ባለሀብት ሰብሰብ ብለው ከመጡ እናግዛለን፤›› ማለታቸው አንድ መነሻ ሊሆን ይችላል፡፡ 

እነዚህ ምርቶች በየዓመቱ ከፍተኛ የሆነ የውጭ ምንዛሪ የሚወጣባቸው ናቸው፡፡ የውጭ ምንዛሪ እጥረት በገጠመ ቁጥር የሚፈጠረው የምርት እጥረት ደግሞ ብዙ የግንባታ ሠራዎችን እንዲጓተቱ አድርጓል፡፡ እነዚህን ለኮንስትራክሽን ምርቶች በአገር ውስጥ ለማምረት የሚጠይቀው ወጪ ቀላል ባይሆንም እንደተባለው ትልልቅ የሚባሉ የአገራችን ባለሀብቶች የሚጣመሩ ከሆነ እነዚህን ኩባንያዎች ለማቋቋም የሚቸገሩ አይሆንም፡፡ ሰብሰብ ብለው ከመጡ መንግሥት የሚደግፋቸው ስለመሆኑ ቃል ከተገባ ደግሞ ቀጣዩ ዕርምጃ የባለሀብቶቹ ይሁንታና ቆራጥ ውሳኔ ይሆናል፡፡ 

እንዲህ ያለውን አጋጣሚ በአግባቡ መጠቀም ያስፈልጋል፡፡ በተለያየ መንገድ ባለሀብቶች ትልቅ ኩባንያ መፍጠር የሚችሉ ስለመሆኑ ብረትና የማጠናቀቂያ ዕቃዎችን ለማምረት የተሰጣቸውን ዕድል መጠቀም ከቻሉ ሌሎች ሥራዎችን በተመሳሳይ መንገድ ለመሥራት ያስችላቸዋል፡፡ በተለይ በገበያ ውስጥ እጥረት ያለባቸው ምርቶችንና እዚሁ በቀላሉ መሠራት እየቻሉ ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን በተመሳሳይ መንገድ ለማምረት በተናጠል ከመጓዝ በጋራ ሆኖ መሥራት ራሳቸውንም አገራቸውንም ለመጥቀም ያስችላል፡፡  

ስለዚህ የአገራችን ትልልቅ ኩባንያዎች በየግል ከሚሠሩት ቢዝነሳቸው ባሻገር በጋራ ተጣምረው ፋይዳ ያላቸው ማምረቻቸውን ቢፈጥሩ በኢትዮጵያ ውስጥ ብዙ የገበያ ችግር ያለባቸውን ምርቶች በቀላሉ የሚያመርቱ ኢንዱስትሪዎችን ለመገንባት የማይችሉበት ምንም ምክንያት የለም፡፡ 

በየጊዜው እያደገ የሚሄደውን የገበያ ፍላጎት ለመሙላት እስከዛሬ እንደምናደርገው ሁሉንም ነገር ከውጭ በማስገባት እየሸፈኑ መሄድ ከዚህ በኋላ የሚያዋጣ አይሆንም፡፡ የአገር ውስጥ አምራች የሚያመርቱትና ምርት የመጠቀም ባህሉ እንዲኖር ማስቻሉም አብሮ ጎን ለጎን መጎልበት ያለበት ተግባር ነው፡፡ በኢትዮጵያ ሊመረቱ የሚችሉ ምርቶች ከውጭ እንዳይገቡ የሚያግዝ ሕግ አውጥቶ በአግባቡ መተግበር ይገባል። ይህም ትልልቅ አገር በቀል ኩባንያዎች እንዲስፋፉ ያግዛል፡፡ በጥቅሉ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ቃል በገቡት መሠረት የብረት ማምረቻና ሌሎች የኮንስትራክሽን ግብዓቶችን ለማምረት ባለሀብቶች ሰብሰብ ብለው ከመጡ እናግዛለን ማለታቸውን የአገራችን ባለሀብቶች እንደ ዋዛ ሊመለከቱት የማይገባ ጉዳይ መሆኑን መገንዘብ አለባቸው፡፡ ስለዚህ ባለሀብቶች ሰብሰብ ብለው ‹‹ይሄው መጥተናል›› ብለው አጋጣሚውን ሊጠቀሙበት ይገባል፡፡

ይህ ከተሳካ ደግሞ ወሳኝ የሚባሉ ምርቶችን በተናጠል ሳይሆን በጋራ መገንባት የሚቻል መሆኑን ማሳያም ሊሆን ይችላልና የግል ዘርፉ አገራዊ ጠቀሜታ ያላቸው ኩባንያዎችን በመፍጠር ታሪክ መቀየር ይኖርበታል፡፡ በዚህ ሰሞናዊ አጋጣሚ ለአገር ዕድገት ወሳኝ የሆነውን የብረት ማምረቻ ለሚተክሉ መንግሥት የገባውን ቃልና ባለሀብቶቹ የሚወስዱትን ዕርምጃ አብረን እናያለን፡፡ 

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት