Saturday, April 20, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ሦስት የፋይናንስ ተቋማት በድምሩ 130.6 ሚሊዮን ብር የሚያወጡ አክሲዮኖችን ከመዋዕለ ንዋይ ገበያ ገዙ

ተዛማጅ ፅሁፎች

የኢትዮጵያ የመዋዕለ ንዋይ ገበያ አክሲዮን ማኅበር በመጨረሻው የአክሲዮን መሸጫ ሳምንት 130.6 ሚሊዮን ብር ዋጋ ያላቸው አክሲዮኖችን ለተለያዩ ሦስት የፋይናንስ ተቋማት በመሸጥ የአክሲዮን ሽያጩን አጠናቀቀ፡፡

የመዋዕለ ንዋይ ገበያው ለአንድ ዓመት ተኩል ሲያካሂድ የቆየውን የአክሲዮን ሽያጭ ባጠናቀቀበት ያለፈው ሳምንት የመጨረሻ ቀናት የአክሲዮን ግዥ የፈጸሙት የፋይናንስ ተቋማት አንበሳ ባንክ፣ አማራ ባንክና ኒያላ ኢንሹራንስ ናቸው። ሦስቱ የፋይናንስ ተቋማት በድምሩ 130.6 ሚሊዮን ብር ዋጋ ያላቸው አክሲዮኖችን ግዥ ፈጽመዋል።

ሦስት የፋይናንስ ተቋማት በድምሩ 130.6 ሚሊዮን ብር የሚያወጡ አክሲዮኖችን ከመዋዕለ ንዋይ ገበያ ገዙ | Ethiopian Reporter | ሪፖርተር
ኒያላ ኢንሹራንስ ኩባንያ ከኢትዮጵያ መዋዕለ ንዋይ ገበያ አክሲዮን ማኅበር የ20 ሚሊዮን ብር
አክሲዮኖችን ለመግዛት በተፈራረመበት ወቅት ጥላሁን ኢስማኤል (ዶ/ር) የኢትዮጵያ መዋዕለ ንዋይ
ገበያ ዋና ሥራ አስፈጻሚና አቶ ያሬድ ሞላ የኒያላ ኢንሹራንስ ዋና ሥራ አስፈጻሚ

ከሦስቱ የፋይናንስ ተቋማትም ሆነ በአጠቃላይ በመዋለ ንዋይ ገበያው አክሲዮን ከገዙ የፋይናንስ ተቋማት መካከል አማራ ባንክ ከፍተኛውን የአክሲዮን ግዥ በሳምንቱ መጨረሻ ዓርብ መጋቢት 20 ቀን ፈጽሟል። አማራ ባንክ 90.6 ሚሊዮን ብር ዋጋ ያላቸው አክሲዮኖችን ከመዋዕለ ንዋይ ገበያው በመግዛት፣ ከፋይናንስ ተቋማት መካከል ከፍተኛውን ድርሻ ለመያዝ ችሏል።

እስካሁን የአክሲዮን ግዥ ከፈጸሙ ባንኮችና ኢንሹራንስ ኩባንያዎች መካከል አዋሽ ባንክ 70 ሚሊዮን ብር ዋጋ ያላቸውን አክሲዮኖች በመግዛት ቀዳሚውን ድርሻ ይዞ እንደነበር አይዘነጋም፡፡ 

አማራ ባንክ ከመዋዕለ ንዋይ ገበያው የገዛው የአክሲዮን መጠን በገበያው ውስጥ የአሥር በመቶ ባለድርሻ እንደሚያደርገው የባንኩ ተጠባባቂ ዋና ሥራ እስፈጻሚ አቶ ጫንያለው ደምሴ የግዥ ስምምነቱ በተፈረመበት ወቅት ተናግረዋል።

‹‹በአገራችን የመዋዕለ ንዋይ ገበያ መጀመሩ ሀብት በማሰባሰብ የገንዘብ ሥርዓቱን በአዳዲስ ፈጠራዎች መደገፍ፣ የኢንቨስትመንት ሥጋቶችን የመጋራት አሠራርን ለማስፋትና የአገርን ኢኮኖሚ ለመደገፍ ከፍተኛ አስተዋጽኦ አለው፤›› ያሉት አቶ ጫንያለው፣ በዚህ ኩባንያ ውስጥ ከፍተኛ መጠን ያለው የአክሲዮን ግዥ የፈጸመው ኩባንያው የሚኖረውን አስተዋጽኦ ከግምት በማስገባት ነው፡፡ 

መንግሥት ከፍተኛ ትኩረት ሰጥቶት የአክሲዮን ገበያ በተደራጀ መልኩ እንዲቋቋም የአክሲዮን ኩባንያ ሊመሠረት የባንኩ ዳይሬክተሮች ቦርድ በመዋዕለ ንዋይ ገበያው የአሥር በመቶ ድርሻ እንዲኖረው ውሳኔ ሊያሳልፍ መቻሉንም ጠቅሰዋል፡፡ 

የኢትዮጵያ መዋዕለ ንዋይ ገበያ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ጥላሁን እስማኤል (ዶ/ር) እንደገለጹት፣ የመዋዕለ ንዋይ ገበያን ለመመሥረት የመጀመሪያውን የሥራ አስፈጻሚ ስብሰባ ያደረጉት በዕለቱ የአክሲዮን ግዥ ስምምነት በተደረገበት የአማራ ባንክ አዳራሽ ውስጥ እንደነበርና በአክሲዮን መሸጫ የመዝጊያ ዕለትም አማራ ባንክ ጋር ስምምነት መደረጉን ገልጸዋል፡፡ 

የመጀመሪያውንም መፈጸሚያውን እዚሁ በማድረጋቸው ደስተኛ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡ በዚህ ሳምንት አክሲዮን ከገዙ የፋይናንስ ኩባንያዎች መካከል አንዱ የሆነው ኒያላ ኢንሹራንስ የ20 ሚሊዮን ብር አክሲዮን መግዛቱ ታውቋል፡፡ በተመሳሳይ አንበሳ ኢንተርናሽናል ባንክ የ20 ሚሊዮን ብር አክሲዮን በመግዛት የኢትዮጵያ መዋዕለ ንዋይ ገበያ አክሲዮን ኩባንያ መሥራች ከሚሆኑ ባንኮች መካከል አንዱ ሊሆን ችሏል፡፡  

የኩባንያው ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ያሬድ ሞላ በኢትዮጵያ የሰነድ መዋዕለ ንዋዮች ገበያ መቋቋም የግልም ሆነ ተቋማዊ ኢንቨስትመንት እንዲስፋፋና እንዲጠናከር ያደርጋል፡፡ በተለይ ኢንቨስት የማድረግ አቅምና ፍላጎት ኖሯቸው በውስን የኢንቨስትመንት አማራጮች የተነሳ ብዙ ዕድል ላልነበራቸው ኢትዮጵያውያን ሰፊ የኢንቨስትመንት በር የሚከፍት ነው ብለዋል፡፡

ከዚህ በተጨማሪም የፋይናንስ ገበያ መረጋጋት በአገር ውስጥ በመፍጠር፣ እንዲሁም የአገሪቱን ኢኮኖሚ በማሳደግና ተጨማሪ የሥራ ዕድል በመፍጠር ረገድ ዓይነተኛ አስተዋጽኦ አለው ያሉት ዋና ሥራ አስፈጻሚው፣ በመሆኑም በአገራችን ገበያው እንዲጀመር በጣም ስንመኘውና ስንናፍቀው ቆይተን የነበረ በመሆኑ አሁን ሥራው  በመጀመሩ ትልቅ ዕድል መሆኑን አመላክተዋል፡፡ 

‹‹የሰነድ መዋዕለ ንዋዮች ገበያ መቋቋም ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ሁሉ  ለኢንሹራንስ ኢንዱስትሪው የተለየና ሁሉን አቀፍ ዕድል የያዘ ነው፤›› ያሉት አቶ ያሬድ፣ የመጀመሪያው ኢንሹራንስ ኩባንያችን እንደ ኢንስቲዩሽናል ኢንቨስተር በራሱ በኤክስቼንጁ ላይ የባለቤትነት ድርሻ በመያዝ ኢንቨስት የሚያደርግ ነው ብለዋል፡፡ ሁለተኛው  በገበያው የተመዘገበ (ኢንሊስትድ) ካፒታል ኩባንያ በመሆን ለማደግም ሆነ ለመስፋፋት የሚያስፈልገውን ካፒታል በቀላሉ ለማግኘት የሚያስችለውን ዕድል ከመፍጠሩም በላይ በካፒታል አቅራቢውና ገዥው መካከል የኢንተር ሚዲያሪነት ሥራ መሥራት የሚያስችል ዕድሎች  እንደሚኖሩት በመጥቀስ የሰነድ መዋዕለ ንዋይ ገበያ መፍጠር ለኢንሹራንስ ኩባንያዎች የገበያው መቋቋም ዘርፈ ብዙ ጥቅም ያለው መሆኑንም አስረድተዋል፡፡

ለአንድ ዓመት ተኩል ለሚሆን ጊዜ ሲያካሂዱ የነበሩትን የአክሲዮን ሽያጭ በዕለቱ ያጠናቀቁ መሆኑን የገለጹት ጥላሁን (ዶ/ር)፣ የኢትዮጵያ መዋዕለ ገበያ አክሲዮን ማኅበር በሚጠበቅበት ደረጃ አገልግሎቱን ለመስጠት ዝግጁ ነው፡፡ ከዚህ ሥራ ጋር ተያያዥ የሆኑ መመርያዎችን የኢትዮጵያ ብሔራዊ እያሻሻለ አንደሚገኝም ጠቅሰዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች