Monday, April 15, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

በሆቴሎች ብቻ ተወስኖ የቆየው የኮኮብ ደረጃ ምዘና ተያያዥ የሆኑ ተቋማትን ሊያካትት ነው

ተዛማጅ ፅሁፎች

በሆቴሎች ብቻ ተወስኖ የቆየው የኮኮብ የደረጃ ምዘና በቱሪዝም እሴት ሰንሰለት ውስጥ አገልግሎት የሚሰጡ ሌሎች ተቋማትን ሊያካትት መሆኑን፣ የቱሪዝም ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡

በቀጣይ የባለኮኮብ ደረጃ ይሰጣቸዋል ከተባሉት ተቋማት ውስጥ ሎጆች፣ ሬስቶራንቶች፣ አስጎብኚ ድርጅቶችና መሰል አገልግሎት ሰጪ ተቋማት እንደሚገኙበት የቱሪዝም ሚኒስትር ናሲሴ ጫሊ ገልጸዋል፡፡

ሚኒስትሯ ይህንን የተናገሩት መጋቢት 19 ቀን 2016 ዓ.ም. የዓለም ቱሪዝም ድርጅት ያስቀመጣቸውን አስገዳጅ መሥፈርት ላሟሉ ሆቴሎች፣ የኮኮብ ደረጃ ምደባ ውጤታቸውን ይፋ ባደረጉበት ወቅት ነው፡፡

ከሆቴሎች በተጨማሪ በሌሎች የቱሪዝም ዘርፍ የተሰማሩ አካላት በቀጣይ በሚካሄደው የደረጃ ምደባ ሥርዓት ውስጥ የሚካተቱ መሆኑን የተናገሩት ሚኒስትሯ፣ በዘርፉ የተሰማሩ አካላት ከወዲሁ ዝግጅት እንዳደርጉ አሳስበዋል፡፡  

በ2014 እና 2015 ዓ.ም. ምዘና ከተደረገላቸው 64 ሆቴሎች መካከል አስገዳጅ የደረጃ መሥፈርቱን አሟልተው የተገኙት 31 ሆቴሎች ብቻ መሆናቸው ይፋ ተደርጓል፡፡

አስገዳጅ የደረጃ መሥፈርቱን አሟልተው ከተገኙት መካከል ሰባቱ ባለአራት ኮኮብነት ደረጃ የተሰጣቸው ሲሆን፣ ዘጠኝ ሆቴሎች ደግሞ የሦስት ኮከብ ደረጃን አግኝተዋል፡፡ አምስት ሆቴሎች የሁለት ኮከብና ስምንት ሆቴሎች ባለአንድ ኮኮብነት ደረጃን ሲያገኙ፣ ሁለት ሆቴሎች ደግሞ ከደረጃ በታች መሆናቸውም ተነግሯል፡፡

በአጠቃላይ በዕለቱ የኮኮብነት ደረጃ የተሰጣቸውን ሆቴሎች ጨምሮ፣ ከአንድ እስከ አምስት ደረጃ ያላቸው ሆቴሎች 369 መድረሳቸውን ሚኒስትሯ ጠቁመዋል፡፡

ምዘና የተደረገባቸው ሆቴሎች በአዲስ አበባ፣ በቢሾፍቱና በአዳማ ከተሞች የሚገኙ መሆናቸው ነው የተገለጸው፡፡

የኮኮብነት ደረጃውን ለመስጠት ከ12 በላይ መሥፈርቶች እንደነበሩ የተናገሩት ሚኒስትሯ፣ የንፅህና አጠባበቅ ጉድለት ከባለአምስት ኮኮብ ደረጃ ከያዙ ሆቴሎች ጀምሮ በስፋት የታዩ ችግሮች መሆናቸውን አብራርተዋል፡፡

የእሳት አደጋ መከላከያ አለመኖርና ሌላኛው የብዙ ሆቴሎች ችግር እንደሆነም አክለዋል፡፡

የኮኮብነት ደረጃን የመስጠት ሥልጣን የቱሪዝም ሚኒስቴር ብቻ ሆኖ ሳለ፣ አንዳንድ ክልሎች በራሳቸው የኮኮብነት ደረጃ ለመስጠት መሞከራቸውን የተናገሩት ሚኒስትሯ አካሄዱ አግባብነት የሌለው ነው ብለዋል፡፡

በአዲስ አበባ ከአምስት እስከ ሦስት የኮኮብ ደረጃ የነበራቸው ሆቴሎች እንደገና በተደረገ ምልከታ አስገዳጅ ሁኔታዎችን ሳያሟሉ፣ ወይም ከደረጃ በታች ሆነው መገኘታቸውን ተናግረዋል፡፡

በመጪው ሳምንት ለ340 ሆቴሎች እንደገና የደረጃ ምደባ እንደሚደረግ ሚኒስትሯ አስታውቀዋል፡፡

የሆቴል ባለቤቶች በበኩላቸው ቀደም ሲል የተሠሩ ሕንፃዎች ዘመኑ ከሚጠይቀው መሥፈርት ጋር አለመጣጣም፣ የቦታ ጥበትና አስፈላጊ የሆኑ ዕቃዎች በወቅቱ አለመቅረብ የተጠየቀውን ደረጃ ለማማላት እንቅፋት እንደሆኑባቸው ተናግረዋል፡፡ 

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች