Saturday, April 20, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ተሟገትየየካቲት 66 አብዮት - ማጠቃለያ

የየካቲት 66 አብዮት – ማጠቃለያ

ቀን:

በበቀለ ሹሜ

1) በዛሬው ዓለምና በምሥራቅ አፍሪካ አካባቢ ያለውን አመል ያወጣ አየር ንብረት ከእነዓውሎ ንፋሱና ወጨፎው ኢትዮጵያ በደንብ እየገመተችና እየተጠነቀቀች መራመድ ይጠበቅባታል፡፡ በዓለማችንና በአፍሪካ ቀንድ ዙሪያ ያለውን ግልጽና ሥውር ፖለቲካ መፈልፈልና መረዳት ያሻታል፡፡ በየትኛውም ልዕለ ኃያልነት ላይ ዛሬ ቅዠት ሊኖረን አይገባም፡፡ ልዕለ ኃያልነት በፍትሐዊነት እንደማይለካና ሁሉም ልዕለ ኃያል ዘንድ ድፍጠጣ እንዳለ፣ ሁሉን መኮነንና መራቅም ሆነ አንዱን ትቶ ለሌላው ማዘጥዝጥ ጉዳት እንደሆነ፣ ታሪክ ካስገነዘበች ውላ አድራለች፡፡ እናም የእነሱን ተተናኳይነት የሚቋቋምና ድጋፋቸውን ሊያኮስስ የሚያስችል ፍትሐዊ አየር በሌለበት ሁኔታ፣ ስለጠላትነትነታቸውና ስለሴራቸው ማነብነብም ሆነ ከእነሱ ጋር መዘራጠጥ ለጥቃት ራስን ማጋለጥ ነው፡፡ የዛሬ ብልህ ዲፕሎማሲ፣ ያለማወላወል ለጠላትም ለወዳጅም መነገርና የይፋ አቋም ተደርጎ መያዝ ያለበትን፣ በሆድ መደበቅ ያለበትን፣ ላለመጠቃት ከእኔ ይቅር መባል ያለበትን፣ እንዲሁም ተከፍቶ መሳቅንና የጠብ ውርጭትን በውይይት ማለሳለስን ያውቃል፡፡

ቀጣናዊ ትስስር የአፍሪካ ቀንድ የህልውናና የግስጋሴ ትርታ ባልሆነበት ሁኔታ ስለባህር በርና ስለጂኦ ፖለቲካዊ ጥቅም ቢያወሩ ወሬው የብቻ ትንፋሽ ይሆናል፡፡ አለኝታ ለመሰኘት የሚያበቃ የሰላምና የልማት ተቀዳሚ ሚና በቀንዱ ውስጥ ከመያዝና ምሳሌ ከመሆን ባሻገር፣ የጎረቤቶችን ልማት የሚኮረኩር አስተዋጽኦ ማድረግ አስፈላጊ ነው፡፡ የዚህ ዓይነት ሚና ከዘመድ መቆጠርን ያመጣል፡፡ የባህር በርን ጉዳይ የቤተ ዘመድ መጠቃቀም ጉዳይ ያደርገዋል፡፡ ይህ ዝምድና በተናጠል ቢጀመርም ትስስርና ልማትን ወደብ ማግኛ ዘዴ (መንገድ) አድርጎ የመጠበብ ጉዳይ አይደለም፡፡ በዛሬው የዓለማችን ሁኔታ ቢያንስ በአካባቢያዊ ቀጣና መተሳሰርና ወደ ማኅበረሰብ ማደግ የህልውናና የግስጋሴ ነባራዊ ዓውድ መሆኑ በሁሉም ጎረቤታም አገሮች ዘንድ ልብ መባሉና የእንቅስቃሴ ትርታ መሆኑ ወሳኝ ነው፡፡ የዚያ ዓይነት ዕይታንና ትልምን በሚጋራ ቀጣና ውስጥ ወደብ የለሽ አገርን ወደብ እንዲያገኝ ማድረግ አተካሮ የሚያስነሳ አይሆንም፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

ትስስር ከልብ የጋራ ትልም የሆነበት ቀጣናዊ ዓውድ ላይ መድረስ ግን ቀላል አይደለም፡፡ በየፈርጁ ለመያያዝ ጥረት እየተደረገም ዛሬ ድረስ የአፍሪካ ቀንድ አገሮች በተናጠል የጥቅም ዕይታና በስስት እንዲታጠሩ የሚለፉ፣ የሚከፋፍሉና ወደ ሽኩቻ ለማስገባት የሚሹ ቀበኞች አሉ፡፡ ቀበኞቹን የማይናቁ በጥባጮች የመሆን ዕድል የሚሰጣቸው ደግሞ በቀጣናችን ውስጥ ቀበኞችን የሚስቡ ድክመቶች በመንግሥት ደረጃም ሆነ በልሂቃን ደረጃ መኖራቸው ነው፡፡ የዱሮ ቅኝ ገዥዎች የመጠጣ ሥልት ዛሬም በቀጣናችን ውስጥ አለ፡፡ በየብስ የታጠሩ አገሮችን አፍኖ የማለብን አሮጌ ዘዴ ጥቅሜ ብለው ከአሮጌ ጊዜ ጋር የሚዋቡ መንግሥታት ዛሬም አሉ፡፡ ‹‹የአፍሪካ ነፃነት! የአፍሪካ ውህደት!›› የሚባል ነገር፣ በቀጣና ደረጃ እንኳ አብሮ የመመዘዝ ራዕይ መፍጠር ያልቻለ ገና ባዶ መፈክር ነው፡፡ በቅኝ ገዥዎች አስተሳሰብና ከፋፋይነት ውስጥ መዳከር እስኪ ታፈርበት ድረስ ትግሉ ማንገላታቱም አይቀሬ ነው፡፡

ትግል ሲባልም በአንደበት መተካተክ አይደለም፡፡ የኢትዮጵያ ህዳሴ በአፈና የማይከሽፍ መሆኑን የሚመሰክር መስፈንጠር ማሳየትና በዚህ ስኬት አማካይነትም በቀጣናው ውስጥ ያሉ ገትጋታ መንግሥታትንና ልሂቃንን አባንኖ፣ በማኅበረሰባዊ ማዕቀፍ ውስጥ አገራዊ ጥቅምን ወደ ማሰብ እንዲመጡና የወርቃማው ዕድል ተቋዳሾች እንዲሆኑ መማረክ፣ ዋናው የትግል መስክ ነው፡፡ በመማረኪያው ስኬት ውስጥም ብዙ ሰበዞች አሉ፡፡ የአገር ውስጥ ሰላምን የጫካ ተኳሾች የማይረብሹት ማድረግ፣ የአገራዊ ምክክርን አሳክቶ የተከታይ ማሻሻያዎችን ሒደት መጀመር/ማፍጠን፣ የምክር ቤት አወካከልን ከምርጫ ውጤቶች ምጣኔ ጋር አገናኝቶ ፓርላማን ሕይወታማ ማድረግና በመንግሥት አመራር ውስጥ ተሳታፊነትን የአንድ አሸናፊ ፓርቲ በጎ ፈቃድ ከመሆን ማስፋት፣ ከዚሁም ጋር የአገር ፍቅር ውላችን ሆኖ በአጠቃላይ ዕውቀት ደረጃ ኅብረተሰባችን መያዝ ያለበትን የጋራ ታሪክ ቢጋር መፈልቀቅ፣ የደርግ ሰዎችና ፖለቲከኞች የፈጠሩትን ውዥንብር ሁሉ የገፈፈ ይህንን መሳይ ስንቅ ይዞ እንደ ዓርማታ የጠነከረ ኢትዮጵያዊ ማንነትን በወጣቱ በኩል ለማነፅ የሚያስችለውን ብሔራዊ የውትድርና አገልግሎት ማስጀመር፣ በልማትና በወታደራዊ አቅም ከመጠንከር ጋር ለቀጣናችን ማኅበረሰባዊ ዕርምጃ ታማኝ ተዋናይ መሆንን ማስመስከር፣ እነዚህ ሁሉ አብረው የሚፈኩ ናቸው፡፡

ለቀጣናዊ ትስስር የታመነ ተዋናይነት ምን ማለት እንደሆነ በቅጡ ሊጤን ይገባል፡፡ ‹እሾህን በሾህ›/ ማነቆን በማነቆ የመመለስ ታክቲክና ‹‹የጠቀመ ነገር እሾሃምም ቢሆን ልክ ነው›› የሚል አስተሳሰብ (‹‹ዋይልድ ፕራግማቲዝም››) እዚህ ላይ አያዋጣም፡፡ አርዓያነት ያለው መልካም ተግባር አከናውኖ በውስጠ ታዋቂ ‹‹ብታውቅ እወቅበት›› የሚል መልዕክት ከማስተላለፍ ያለፈ ንቁ ሚናንም ይፈልጋል፡፡ የመታረምን ውጤት በሚያስከትል ብልኃት፣ የጥፋት መንገዶችንና ጉዞዎችን የመታገልን ኃላፊነት ይጠይቃል፡፡ አንድ የጎረቤት አገር በተናጠል አገርነት አሮጌ ዕይታ ውስጥ ተጣቦ ከትስስር ነክ ውጥን ጋር ቢጋጭና የውጭ ጣልቃ ገብነት መጫወቻ ሆኖ የቀጣናውን ሰላም ቢያውክ፣ ከእናካቴው እንደ አገር ያለውን ህልውና የሚያሳጣ ሥርዓት አልባነትን ቢታከክ ጉዳቱ የመላ ቀጣናው ነው፡፡ በዳር ተመልካችነት ያ እንዲሆን መፍቀድም ትልቅ ጥፋት ነው፡፡ ለምሳሌ የሆነ ጎረቤት አገር አቅም ኖረውም አልኖረው በጥቅሜ መጣሽ ብሎ በኢትዮጵያ ላይ ጥቃት/ጦርነት ቢከፍት፣ ኢትዮጵያ ከጥፋት ንፁህ ነኝ የምትልበት ወፍራም ዶሴ ቢኖራትም ዋጋ የለውም፡፡ ጥቃት/ጦርነት ሊከፈትባት መቻሉ በራሱ ትልቅ የፖለቲካና የዲፕሎማሲ ኪሳራ ይሆንባታል፡፡ 

2) በጣም ረዥም የጋራ ታሪክ ያላቸው ሕዝቦች ዛሬ ሁለት ቦታ ኢትዮጵያና ኤርትራ ሆነው ይገኛሉ፡፡ የሕዝብ ዝምድናና የታሪክ መስተጋብር ቀጣናውን በጥቅሉ የሚመለከት ቢሆንም፣ የሁለቱ ከሌሎቹ የተለየ ቁርኝት አለው፡፡ የሁለቱም አገሮች ታሪክ በየብቻ ካርታቸው ውስጥ ሳይወሰን ሁለቱም ዘንድ የሚገኝ ነው፡፡ የሚያጎላው ጠፍቶ እንጂ የሚጋሩት አኩሪ ገድል ትንሽ አይደለም፡፡ የሥጋና የባዕድ ዘመድ አዝማዶች ሁለቱም አገሮች ውስጥ ተበትነው ዛሬም ድረስ አሉ፡፡ ቁርሾን መጣል ኤርትራዊ ማንነት መቀነስ የሚመስላቸው ውስን አላዋቂዎች ፈረንጅ አገር ተቀምጠው ከኢትዮጵያውያን ጋር ላለመደራረስ ሲሞክሩ ይታዩ እንጂ፣ ዛሬም ድረስ የኢትዮ-ኤርትራ ሰዎች በጋብቻ መዛመዳቸው አልተበጠሰም፡፡ የመበጠስ ዕድልም የለውም፤ ዕጣ ፈንታቸው እጅግ የተያያዘ ነውና፡፡ እናም ስለኢትዮጵያ ጥቅምና ኃላፊነት ማጠቃለያ ሊሰጡ ተነስቶ፣ ኤርትራን ቢረሱ የገዛ አገርን የመርሳት ያህል ይሆናል፡፡

በ1960ዎች የተራማጅ ትግል ውስጥ የኤርትራ ተወላጆች ለውጥ ለሁሉም ይተርፋል ብለው በኢትዮጵያዊነት ጥላ ተዋድቀዋል፡፡ የኤርትራ የሃርነት ትግልም ለኢትዮጵያ ይተርፋል ብለው የመሃል አገር ተራማጆች ኤርትራ በረሃ ገብተዋል፡፡ ይህንን ሰፊ ልብና እምነት ይዘው መታገላቸውም ስህተት አልነበረም፡፡ ስህተት የሆነው የትግል መንገዳቸውና ትልማቸው የተሳሰረ ዕጣቸውን ያላንፀባረቀና ያላገለገለ መሆኑ ነበር፡፡ የጋራ ዕጣችንን በአግባቡ ሳይረዳ ከመተሳሰር ያነከሰውና በደም የቀለመው ትግላችን የሁለት አገርነት ውጤት ላይ ካደረሰን በኋላም፣ የጋራ ዕጣችንን ያልተቀበለና የጎዳ ጥፋት ሠርተናል፡፡ ዝምድናችንን የቂም መወጫ ከማድረግም ተሻግረን ማካሄድ ያልነበረብንን ጦርነት አካሂደናል፣ የጋራ ጥቅማችንን አኩርፈን ሃያ ዓመታት ያህል ቆይተናል፡፡ የሚደንቀው ይህንን ሁሉ አልፈን ዛሬ ላይ ከደረስን ወዲያም ይኼው ኩርፊያና ቅያሜ ፈጥኖ የናፈቀን ሆነናል፡፡ ይህ ሁሉ ተደምሮ፣ በወጣት ተራማጅነት ጊዜ ካጠፋነውም ጥፋት ይበልጥ፣ በጉልምስና ጊዜያችን፣ ሁለት ቦታ ሥልጣን የያዙ መንግሥታት ሆነን ያጠፋነው ይበልጣል፡፡

ጥፋት የቀጠለው ከጥፋት ለመማር አለመፍቀድ ለረዥም ጊዜ ስለቀጠለ ነው፡፡ ይህም የሆነው ጥፋት ከዓይንና ከልብ ተሠውሮ አይደለም፡፡ የወደብ የለሽነትን ጉዳት የኢትዮጵያ ግዑዝ መሬት ጭምር ያውቃል፡፡ የኤርትራም ከኢትዮጵያ መቆራረጥ ምን ያህል የኤርትራ ልማትን እንደ ገነዘ፣ የኤርትራ ግዑዙ የብስና ባህር አፍ አውጥቶ ይለፈልፋል፡፡ ተሬው ሕዝብና ወጣት ካጤነውም ውሎ አድሯል፡፡ ኢትዮጵያና ኤርትራ ከመታረቃቸው በፊት በስደት የነበሩ የኤርትራና የኢትዮጵያ ወጣቶች አብረው የስደት ኑሮን ገፍተዋል፡፡ ከዕርቅ በኋላም የኤርትራና የኢትዮጵያ ዘመዳሞች በዓለም መድረክ ላይ ተጋግዘው ሲጮሁ ታይተዋል፡፡ በዕርቁ ጊዜ ሩቅ ለሩቅ እንደተላቀሰው ሕዝብ ባይሆኑም መሪዎቹም በጣም ደስተኞች ነበሩ፡፡ ግን የእውነታን እውነት አዳምጦ ጥፋትን ለማረም አልበቁም፡፡

ለኤርትራ ወገኖቻችን ኢትዮጵያ የስደት መሸጋገሪያ ብቻ አደለችም፡፡ ድንበር አልፎ የመግባት ዕድል ወለል ተደርጎ ቢከፈት፣ ኢትዮጵያ ውስጥ ሕይወቱን ለማቋቋም ግልብጥ ብሎ ከኤርትራ የሚፈልሰው የትየለሌ እንደሚሆን ጥርጥር የለውም፡፡ የወደብ እንቅስቃሴ ይዞት የሚመጣውን ጥቅምና ከኢትዮጵያ ሸቀጥና አገልግሎት ወደ ኤርትራ በማንቀሳቀስ የሚገኘውን የንግድ ጥቅም አስተውሎ ከኢትዮጵያ ወደ ኤርትራ የሚጎርፈውም ነጋዴ የኤርትራን ከተሞች ባጨናነቀ ነበር፡፡ ከዕርቅ በኋላ ገርበብ ተደርጎ የነበረው በር ተመልሶ የተዘጋው በደኅንነት ሥጋት ብቻ ይምሰል እንጂ፣ ሁለቱም መንግሥታት የሁለቱን አገሮች የኢኮኖሚ ተራክቦና የሕዝብ ዝውውር ሥርዓት ለማስያዝ የሚያስችል ዝግጁነቱና ድፍረቱ ስላልነበራቸውም ነበር፡፡ ዝም ብለው ሕዝቡን ቢለቁት ትርምሳቸውን እንዳያወጣው ስለፈሩም ሳይሆን አልቀረም፡፡

የኢትዮጵያና የኤርትራ የጋራ ዕጣና ጥቅም በሁለት አገርነት የማይበጠስ መሆኑ ታውቆ፣ አገራዊ ሉዓላዊነትን ‹‹የማጣት›› ሥጋት በማይፈጥር አኳኋን የዝምድናቸው መስተጋብር፣ እንደ ምንና በምን ደረጃ ጀምሮ ወደ ምን ዓይነት ትስስር ያምራ? በሕወሓታውያንና በኤርትራ ሃርነት በኩል ያለ የከረመ ቁርሾ እንደምን ይቃለል? በኢሳያስ መንግሥት ደጋፊዎችና ተቃዋሚዎች ዘንድ ያለውና በባህር ማዶ አገር እስከ መደባደብ የባረቀው ቅራኔ እንደምን ይፈታ? በኤርትራ አገረ መንግሥት ውስጥ ያሉ ልሂቃንና ከኤርትራ ውጪ ያሉ ልሂቃን እንደምን ለአገራቸው በሚበጅ ትልም ላይ አብረው መሥራት ይችላሉ? የኤርትራና የኢትዮጵያ ልሂቃን የሁለቱን አገሮች እንደምን በመተሳሰብ መጥቀም ይችላሉ? እነዚህን በመሳሰሉ ጉዳዮች ላይ የኢትዮጵያና የኤርትራ ምሁራን አብሮ በደንብ የተጠና ሥራ እየሠሩ ይፋ የማድረጋቸው ተግባር ለነገ የማይባል ነው፡፡

3) ለመበጥበጥ የሚሻ ኃይል ለመበጥበጥ የሚደፍረው ሰሚ እስካገኘ መሆኑ እውነት ነው፡፡ ግን አሁን ባለንበት ሁኔታ የአፍሪካ ቀንድ ቀጣና ለበጥባጭ ጆሮ የማይሰጥበት ሁኔታና ደረጃ ውስጥ አይደለም፡፡ ከዚህ አኳያ የግብፅ አማሳይነት በዝምታና በንቀት ብቻ መታለፍ የለበትም፡፡ ዛሬ ኢትዮጵያን የአፍሪካ ቀንድ አለመረጋጋት ምንጭ አድርጋ ‹‹ወንጃዩዋ›› ግብፅ፣ በኢትዮጵያ ላይ የላከከችው የራሷን ነውር ነው፡፡ ይህ ኢትዮጵያን የማጥቃት ተግባር ከጥንት ጀምሮ የለማባት ባህርይ ነው፡፡ የኢትዮጵያ መረጋጋትንና መልማትን የውኃ ደኅንነቴ (የስስቴ) ሥጋት ነው ብላ እስካመነች ድረስ ወደፊትም ይቀጥላል፡፡ ግን እሷ ስለማታርፍ እኛም ከእሷ ጋር ስንላፋ እንኑር አይደለም ጉዳዩ፡፡ የአፍሪካን መረጋጋትና ፀጥታ ለማናጋት በላይና በታች የምትል፣ አሳፋሪ ያጣች ሙሬ መሆኗ፣ ዝም መባል የሌለበት የዛሬ አንድ ሁነኛ ችግር ነው፡፡ የብጥበጣ ሙሬነቷ በደንብ ቀልሎ ውርደቷ ወደ የሚሆንበት ደረጃ እንዲደርስ ከወዲሁ በደንብ የታቀደ ሥራ መሠራት መጀመር አለበት፡፡ የኢትዮጵያን ልማት ለማሰናከልና ኢትዮጵያን ከጎረቤቶቿ ጋር ለማቀያየም/ለማጋጨት የሚሆን የቅራኔ ንቃቃት በመብራት የምትፈልግ፣ ንቃቃት አስፍታ የጣልቃ ገብነት መግቢያ ለማድረግ የምትሠራ፣ ከዚያም አልፎ ከኢትዮጵያ የተሸካከረ/የተጋጨን ጎረቤትን ዕርካቧ ለማድረግና ኢትዮጵያን ከቅርብ ሆኖ ለማጥቃት የምታደራ አገር ነች፡፡ በእነዚህ ሁሉ አቅጣጫዎች በምታደርገው መቅበዝበዝ የቀጣናውን አለመረጋጋት ለማባባስ ሁነኛ ጠንቅ ሆኖ ትገኛለች፡፡

ይህንን ባህርይዋን በደንብ መርምሮና በማስረጃዎች አደራጅቶ ለኢጋድም ለአፍሪካ ኅብረትም ማሳወቅና ከክፍለ አኅጉራዊና ከአኅጉራዊ ሰላም አኳያ ድርጊቷ እንዲመዘን ማመልከት ተገቢ ነው፡፡ ኢትዮጵያን ለማናከስና ለማጥቃት በላይ በታች እያለች ምንም እንዳልተደረገ ያህል በታላቁ ግድብ ላይ ‹‹መደራደርም›› ለወጉ ያህል የሚካሄድ ቧልት ይሆናል፡፡ የድርድሩ ፍሬያማነት የማዕዘን ድንጋይ የዓባይን ውኃ በአጋርነት ትስስብ ለመጠቀም ዝግጁ ሆኖ መገኘት ነው፡፡ ከዚህ ባሻገር የአፍሪካ ኅብረት አባል አገሮቹ ከአፍሪካ ኅብረት መርሆች ጋር የሚጋጭ ወይም የአፍሪካ አኅጉር ሰላምን ሊያማስል የሚችል ማኅበር አባልነት ያላቸው መሆን አለመሆናቸውን የማረጋገጥም ጥንካሬ ሊያዳብር አይገባው ይሆን?  የሌላ ማኅበር ውሳኔና ቃል ኪዳን የአፍሪካ ኅብረት ሰላም ውስጥ ገብቶ ሊያቦካ ሲሞክርም እንዳልታየ ታይቶ መታለፍም ያለበት አይመስለኝም፡፡ የመጨረሻዎቹን ነጥቦች የሰነዘርኳቸው ለአፍሪካ ሰላም ከመቆርቆር ጎን ቆሜ፣ የዓለም አቀፍ ግንኙነትና ሰላም አዋቂዎቻችን መላ ቢሉ በማለት ነው፡፡

4) እስካሁን በተከታታይ በቀረቡ ጽሑፎቼ ልመረምር የሞከርኩት ሁለት ነገሮችን ነው፡፡ አንደኛው ጉዳይ በ50 ዓመታት የደፋ ቀና ጉዞው መጎልመስ የቸገረውን የፖለቲካችንን ድክመት የተመለከተ ነው፡፡ የፖለቲካችን የጥንካሬና የድክመት ታሪክ በግማሽ ምዕት ዓመቱ ውስጥ መጥተን የሄድነውና ያለነው ፖለቲካ ቀመሶች ታሪክ ነው፡፡ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ታሪኩ የማይመለከተው የለም፡፡ ስህተት/ጥፋት ተሠራ እያልን ስናወራ ስለራሳችን ገመና ማውራታችን ነው፡፡ ስንወቅስም የወቀሳው ማረፊያ እኛው ነን፡፡ ከዚህ የድክመትና የአላዋቂነት ጥግ ቆሜም በጥፋት ባለድርሻነት የኢትዮጵያን ኅብረተሰብ ይቅርታ እጠይቃለሁ፡፡

ይቅርታዬ ትሁት የመሆን ጉዳይ አይደለም፡፡ እኛ ወጣት በነበርንበት የለውጥ ጊዜ ለስህተቶችና ለጥፋቶች የሚያጋልጡ ብዙ ነገሮች ነበሩ፡፡ በእኛም ውስጥ በእኛም አቅራቢያ የልምድ መማሪያ እጅግም አልነበረም፡፡ ስለሌሎችና ስለስኬቶቻቸው የምናውቀው ብዙው ነገር ከሩቅ ዝናና ከመጻሕፍት/ከፕሮፓጋንዳዊ ኅትመቶቻቸው የተገኘ ነበር፡፡ ዛሬ ግን መማሪያ የሚሆኑት የደፋ ቀና ልምዶች በአገራችንም በዙሪያችንም በሽበሽ ናቸው፡፡ ዓይናችንን ሊወጉ ከደረሱ ከእነዚህ ልምዶች መማር አለብን፡፡ ‹‹እንማር!›› ብለን በምንጮኸውም ሆነ ዝም ብለን በምንታዘበው ልሂቃን ዘንድ ከደሙ ንፁህ መሆን ብሎ ነገር የለም፡፡ ‹‹ሸኔ›› የሚባሉትንም ሆነ ፋኖዎችን ከእነ አስተሳሰባቸውና ከእነ ግብራቸው ያፈራናቸው እኛው ነን፡፡ እነሱም ሌሎቹም የቀውስ ተዋንያን፣ የእኛው ገመና ልጆች ናቸው፡፡ እናም የእኛን የአዛውንቱንና የጎልማሶቹን ልሂቃን የጥፋት ድርሻ ማውሳት የምር እንጂ የመመፃደቅ ነገር አይደለም፡፡ 

ጽሑፎቼ ያተኮሩበት ሌላው ጉዳይ ደግሞ፣ የአካባቢያችንና የአገራችን ወቅታዊ ሁኔታዎች ናቸው፡፡ የፊተኛው ላይ ከጊዜ መራቅ ጋር አብሮ የሚመጣ የትውስታ መመናመን ፈተና ቢሆንም፣ ጊዜውን የሚያወሱ ጽሑፎችን በማገናዘብ የተዘነጋን ማስታወስ ይቻላል፡፡ ሁለተኛው፣ ያለንበትን የአሁን ጊዜ የሚያስተውል በመሆኑ የሚቀል ይምሰል እንጂ ከባድ ነው፡፡ ከባድ የሚያደርገው አንደኛው ነገር የምናወራው/ የምናብላላው እየተላወሱ ያሉ ድርጊቶችን መሆኑ ነው፡፡ ሌላው ሥራ አክባጁ ነገር ደግሞ አስተማማኝ መረጃን ከፍሬ ከርስኪው የመለየቱ ነገር ነው፡፡

በዓለማችን ስመኛ መገናኛ ብዙኃን የሚለቀቁ መረጃዎች አመራረጣቸውና አተናተናቸው ከተለያየ የጥቅም ጥግ ይቃኛል፡፡ አንዱ ያጋነናቸውን ሌላው መልምሎ ድድ በድድ ያደርጋቸዋል፡፡ ከዚህ ባሻገር በኢንተርኔት ጥበብ አማካይነት የመጣው ዲጂታል ሚዲያ የመረጃ ምንጮችንና ይዘቶችን በቁጥጥር ማጣራት እንዳይቻል አድርጎታል፡፡ ሐሰተኛ መረጃ እየተፈበረከና ከእውነት ጋር እየተለወሰ ለውጊያ ይውላል፣ በገንዘብ መቃረሚያነት ይሸቀጣል፡፡ ከዚህ ዓይነቱ ጫካ ውስጥ ትክክለኛ የሆነውን መረጃ መለየት መቻል ከባድ ሥራ ነው፡፡ ከመረጃ ተቋማት እስከ መንግሥታት ድረስ መረጃ የማይደባብቅ፣ የማይበርዝና የማያብል የለም ማለት ይቀላል፡፡

ስለሶማሊያ፣ ስለግብፅ፣ ስለኤርትራና ስለኢትዮጵያ የፖለቲካ ጥልፍልፍ ብዙ እንደሚወራ ሁሉ ብዙ የማናውቀው ነገር አለ፡፡ እንዲያውም የምናቀው በጣም ትንሽ ነው፡፡ የኢትዮጵያና የኤርትራ የቅርብ ቅሬታ ከምን እንደመጣ ከግምት በቀር አፍ ሞልቶ እርግጡ ይህ ነው ተብሎ የሚታወቅ ነገር የለም፡፡ ስንትና ስንት ወሬ ይሰለቅ እንጂ፣ በሕወሓትና በፌዴራል መንግሥቱ መሃል የተጀመረውን የፕሪቶሪያን ስምምነት የማከናወን ነገር ለምን እንደ ተንሻፈፈና ለምን እንደ ተንቀረፈፈ በእርግጠኝነትና በይፋ የሚታወቅ ነገር የለም፡፡ እንደዚህ ያሉ ችግሮች፣ በቅርጥፍጣፊ መረጃዎችና የዝርዝር ደሃ በሆኑ ጥቅል መረጃዎች ላይ ትንታኔዎች እንዲመሠረቱ ያደርጋሉ፡፡ የእኔም ትንታኔዎች አንባቢ ላለማሳሳት ቢጥሩም፣ ከተጠቀሰው የመረጃ ውስንነት ውጪ አይደሉም፡፡ ተጠነቀቅሁ እያልኩም ተሳስቶ ከማሳሳት አላመለጥኩም፡፡ 

ከጥቂት ወራት በፊት የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር መሪ ጌታቸው ረዳ በፕሪቶሪያው ስምምነት መሠረት ትጥቅ የማስፈታቱ ሒደት እንደሚወራለት እንዳልሆነና ወደ ሁለት መቶ ሺሕ ያህል ትጥቅ ያልፈታ ሠራዊት እንዳላቸው ተናግሮ ነበር፡፡ ይህንን መረጃ ማመን አቅቶኝና ‹ለምን?› ከሚል ጥያቄ ጋር አጣብቄ በሆዴ ይዤው ነበር፡፡ ከተወሰነ ጊዜ በኋላ ከፌዴራል መንግሥት ሰዎች በኩል በፕሪቶሪያው ስምምነት መሠረት ትጥቅ የማስፈታቱ ሥራ በጥሩ አኳኋን እየተካሄደ ስለመሆኑ ድፍን ያለ መረጃ ተሰጠ፡፡ እኔ ‹‹ጠንቃቃው›› የመንግሥት የመታመን ኃላፊነትን አብዝቼ ከሐወሓቶች የቅጥፈት ልማድ ጋር አነፃፀርኩና፣ ሁለት መቶ ሺሕ ጦር ስለመኖሩ የተወራው ከፋኖ ጋር ያለውን ጣጣ ለማጫጫስ እንጂ፣ ስለተደበቀ ሠራዊት በይፋ መናገር ትጥቅ አስፈቱኝ ብሎ መለፈፍ ይሆናል የሚል ትርጉም ሰጠሁት፡፡ አሁን ግን ትጥቅ ያልፈታ ሠራዊት መኖሩን መንግሥትም ፈረንጆቹም የሚያውቁት ነገር እንደሆነ ተረዳን፡፡ በዚህም ረገድ ባልተሟላ መረጃ ስለቀባጠርኩት ነገር ይቅርታ እጠይቃለሁ፡፡

በስህተቴ ባፍርም፣ ልክን ለማወቅ ጥሩ ደወል ሆኖኛል፡፡ የእኔ ሁነኛ ትኩረት የአገራችን የውስጥ ሰላም መረጋገጡ ነው፡፡ ይህ የውስጥ ሰላም ከዚህ በኋላ የሚፈልገውም፣ የሚወራ ነገር ሳይሆን ድርጊትን ነው፡፡ የውስጥ ሰላም እጃችን ከገባ፣ አጠቃላይ ምክክሩ ዕርቁና የልማት ግስጋሴው የሚሻው እንደ እኔ ያለውን ከሥራ የራቀ ጡረተኛ ሳይሆን፣ ለየሥራ ዘርፎቹ ቅርብ የሆኑ ሊቃውንትንና ባለሙያዎችን ነው፡፡ እናም የይቅርታ ጥያቄዬ የመሰናበቻም ነው፡፡ አሁንም ደግሜ ይህ ዓመት ስለሰላም ዕጦት ከማውራት የምንገላገልበት ዓመት እንዲሆን በፅኑ እመኛለሁ፡፡

ሰላም ሲሰፍን የመንግሥት ከጦርነት ጋር የተያያዘ ወጪ ይቀንሳል፡፡ ገበያውን የሚሻማው ወታደራዊ ግዥ ይቀላል፡፡ በሰላም ማጣት ከምርት ተግባር የተፈናቀሉ፣ የተጓጎሉ/በሙሉ አቅማቸው ከመሥራት የታወኩ ሁሉ፣ ሰላም ሲመጣ፣ በመልሶ መቋቋም ሒደት ወደ ሙሉ አቅም አምራችነት ይተላለፋሉ፡፡ በሰላም ማጣት ይታወክ የነበረ ሥርጭትና ክፍፍል ለመሳለጥ ዕድል ያገኛል፡፡ በዚህ ላይ የራሳቸውን ፍጆታ ለመሸፈን ተጓዳኝ ግብርና ውስጥ የገቡ ተቋማትና የከተሞች የግብርና እንቅስቃሴ ሲጨመር፣ በውስጥ ገበያ አቅርቦት ረገድ የሚፈጠረው ማሻቀብ፣ የኑሮ ውድነትን የማርገብ ፈጣን ተፅዕኖ ይኖረዋል፡፡ ይህ አንዱ የሰላም በረከት ነው፡፡

ሰላም መጥቶ ትኩረት ወደ መልሶ ግንባታና ግስጋሴ ሲዞር፣ ሆን ተብሎ ታቅዶ መፍትሔ ከሚፈለግላቸው ጉልህ ችግሮች ባሻገር፣ ብዙ ጭፍጫፊ ችግሮችም በእግረ መንገዳዊ ሒደት ይቃለላሉ፡፡ ሰላም ሲታጣ ብዙ ጣጣዎች የሚጎትቱ ችግሮች አበዛዝና አቅማቸው፣ ሰው በሽታ የመከላከል አቅሙ ሲደክም እንደሚደርሱበት ጥቃቶች ያለ ነው፡፡ የመዳቀቅ አጋጣሚን የሚጠብቁ ውዳቂ ችግሮች ሁሉ ይሠፍሩበታል፣ ያጎሳቁሉታል፡፡ የሰላም ዕጦት ተሞክሯችን ይህንንም አሳይቶናልና ለሰላም የሚኖረን ስስት ከዚህ በኋላ የሚልቅ ይመስለኛል፡፡ በሰላም ዕጦት ተሞክሯችን ጊዜ የተገላለጡት ችግሮች ቢጎዱንም፣ ምን ዓይነት ችግሮች ላይ መጠንቀቅ እንዳለብንም እንድንለይ ጠቅመውናል፡፡ ከዚህ አኳያ ትምህርት ሰጪ ልምዶችን ከሰላም ዕጦታችን ለመጭመቅ እንሞክር፡፡

  • ሥራ አጥነት የማኅበራዊ ጥፋቶች መፈልፈያ ሊሆን መቻሉ ተራ ዕውቀት ነው፡፡ ያለፈ ልምዳችን ግን ከዚህ አልፎ ሥራ አጥነት የፖለቲካ ቀውስን ሊመግብ እንደሚችል፣ ከዚያም ናጠጥ ብሎ ሥራ አጥነት ራሱ እንደ ፖለቲካ እንቅስቃሴ ሊሠራራው እንደሚችል (ለዝርፊያ ፖለቲካዊ ምክንያት ሲሰጠው/ለተራ ዘረፋ ‹‹ሒሳብ የማወራረድ›› ፖለቲካዊ ዓላማ ሲያስታጥቀው) ዓይተናል፡፡ የሥራ አጥነትን መዘዝ በየፈርጁ በደንብ ስለቀመስነው ሥራ አጥነትን ከእንግዲህ ቸል እንደማንለው ይገመታል፡፡
  • ሥራ አጥነትና ማኅበራዊ አጥፊነት ከተወሰነ ማኅበረሰብ ጋር ተያይዞ፣ ሰላምና ፀጥታ በተዳከመበት ሰዓት፣ ጭፍን የደቦ ቅጣት ከአንድም ሁለት ጊዜያት በተወሰኑ ሥፍራዎች አጋጥሟል፡፡ ዛሬም ማኅበራዊ ጥፋትን ከተወሰነ ማኅበረሰብ ጋር ላዛመደ ልብታ የተመቸ ማኅበራዊ ችግር አዲስ አበባ ድረስ ይታያል፡፡ ይህ ዓይነቱ ችግር የሕዝብ ቁጥር ዕድገትን (የወሊድ ዕድገትን) ችግሮች እንደ አካባቢያዊ አደማመቃቸው የሚገባቸውን ማቃኛ ያለ መስጠት ውጤቶች ናቸው፡፡ እንዲህ ያሉ ችግሮች ተከታታይ መፍትሔና ጥንቃቄ እንደሚያሻቸው የሰላም ቀውሳችን አስታውሶናል፡፡
  • አካባቢያዊ/ብሔረሰባዊ የሥነ ልቦና ቁርኝት ያለ ነው፡፡ ሥነ ልቦናዊ ቁርኝቱ እስከ መደጋገፍ ሊሄድ ይችላል፡፡ የመደጋገፍ ደረጃው ከማኅበረሰብ ማኅበረሰብ ሊበላለጥም ይችል ይሆናል፡፡ የበቀሉበትን አካባቢ/ማኅበረሰብ በልማት ነክ ሥራዎች መደገፍ አግባብ ነው፡፡ ጉዳት/ዕጦት ያለበት የወንዝ ልጅ ሲያጋጥም ለማንም ሰው ከሚያደርጉት በላይ የድጋፍ እጅ ዘለግ ሊል ይችላል፡፡ የሰውየውን ጥረት ለማገዝ መሞከርም ማለፊያ ነው፡፡ የዚህ ዓይነት ትግግዞች አውቀውትም ሆነ ሳያውቁት በፌዴራላዊ አስተዳደሮች ውስጥ ባሉ የግልም ሆነ መንግሥት የሥራ/የሙያ መስክ ውስጥ ለሐሜት የሚመች ክምችት መፍጠራቸው ግን መዘዘኛ ሊሆን ይችላል፡፡ መገለጫቸው የተለያየ ነው፡፡ ‹‹ጥቅም ያለበትን ሥፍራ የተቆጣጠሩት/ዋና ዋና ሥልጣኗን በቅጥልጥል የያዟት የ‹ሀ› አካባቢ ሰዎች ናቸው… የ‹ሀ› ንግድ ዘርፉን የተቆጣጠሩት የእከሌ አካባቢ ሰዎች ናቸው …›› የሚሉ ሐሜቶች ከስብጥር ጉድለት ጋር ተያይዘው ሊመጡ ይችላሉ፡፡ እንዲህ ያሉ ችግሮች ሙስናንና አሻጥርን ከማኅበረሰባዊ ማንነት ጋር እስከ ማገናኘት ሊወስዱ ይችላሉ፡፡ የመንግሥትና የሕዝብ ትምምን ላይም ጉዳት ሊያደርሱ ይችላሉ፤ ሲያደርሱም ታይቷል፡፡
  • ሐሜት ከስብጥር ጉድለት ሊበቅል እንደሚችል ሁሉ፣ የስብጥር ማነስን ለማስተካከል በመሞከር ጊዜም ሊመጣ እንደሚችል ልምዳችን አሳይቶናል፡፡ አድልኦዊ ድልድልንና አያያዝን በፍትሐዊነት መንፈስ ለማስተካከል መሞከር ጤናማ ነው፡፡ አድልኦው የደንብ/የመብት ያህል ሆኖ የኖረ ከሆነ፣ ጥልቀት የለሽ ማስተካከያ ለማድረግ ሲጣር እንኳ፣ ጥረቱ የተለመደ ‹መብትን› እንደ መንካት መስሎ ሊቆረቁር ይችላል፡፡ በለውጡ ጥቂት ዓመታት ውስጥ ከዚህ ቀደም እጅግም ፍትሐዊ የመንግሥት መስተንግዶ ያልነበራቸውን ቤተ እምነቶች ውስን ጥያቄዎች ለመመለስ ተሞክሯል፡፡ በመንግሥት መሥሪያ ቤቶችም ውስጥ ያለውን ማኅበረሰባዊ ሥርጭት በፆታም ሆነ በሌሎች ገጽታዎች ለማዥጎርጎር ተሞክሯል፡፡ ሙከራውን በፍትሐዊነት አስተሳሰብ ጎሽ ያሉት እንደነበሩ ሁሉ፣ ‹‹ዛሬማ ጊዜው የሌላ/የሌሎች ነው›› ያሉትም ነበሩ፡፡ ከዚህ በፊት ያልነበረ ነገር ሆኖ በማየታቸው ብቻ፣ ከእነሱ መብት ላይ ተቆርሶ ለሌላ የታደለ ወይም እነሱ የተዘነጉ/የተገፉ ሆኖ የምር የተሰማቸው ክፍሎች ነበሩ፡፡ ባይበደሉም የተበደሉ ያህል የተፈጠረባቸው የመንፈስ መደፍረስ፣ ብሶተኛ መጉረምረምንም አስከትሎ ነበር፡፡ ይህንን ስሜት ለቀም አድርገው ለጨለምተኛ ፖለቲካ ንግድ የተጠቀሙበትም ፖለቲከኞች ነበሩ፡፡ ይህ ተሞክሮ፣ የደደረ አድልኦ ኖሮ ኖሮ ሲነካካ፣ ታሪካዊ መብት የተደፈረ ያህል መንዘርዘር ሊፈጥር እንደሚችልና የአያያዝ ጥንቃቄ እንደሚሻ፣ ወደፊትም አድልኦዎችን መብት እስኪመስሉ ሳያስረጁ ለፍትሐዊነት መሥራት እንደሚገባ አስተምሯል፡፡
  • በውጭ ጸሐፊያን የተደረሱ ኢትዮጵያ ነክ የታሪክ ሥራዎች የጠቀሙትን ያህል አሳሳችና አናቋሪ ግምገማችን ዕሳቤዎችንና ሥነ መንግሥታዊ ሥዕሎችን ሰንቅረዋል፡፡ የገዥዎች ፍላጎት የተጫናቸው ነባር የአገር ውስጥ የታሪክ ሥራዎችም የሰዎችን ግንዛቤ አሳስተዋል፣ ከፋፍለዋል፡፡ እንደ ‹‹አማራ›› ያሉ ስያሜዎች በነባር ጊዜያት የነበራቸው ትርጓሜ ዛሬ ከሚሸከሙት ዕሳቤ በጣም የተለየ ሆኖ ሳለ፣ ሰዎች ግን ዛሬ ባለው ትርጉሙ እየተረዱ የተሳሳተ ግንዛቤ ሲፈጥሩ ቆይተዋል፡፡ በሰዎች ላይ የሚደርሱ የአስተሳሰብ/የአመለካከት ለውጦች የታሪክ አረዳድ ላይ የራሳቸውን ተፅዕኖ አሳርፈዋል፣ ግንዛቤን የማሳሳትና የመከፋፈል ሚና ተጫውተዋል፡፡ እነዚህን ከመሳሰሉ አቅጣጫዎች የሚመጡ አሳሳችነቶችን፣ ሙያዊው የታሪክ ጥናት መክቶ/አቃንቶ፣ ልሂቃንና ኅብረተሰብ ያልተዛባ (የሁሉን ፈርጀ ብዙ ተራክቦ ያዘማመደ) የታሪክ ዕውቀት ለማስያዝ አልበቃም፡፡ እናም፣ የኢትዮጵያ ታሪክ በሚባል ይዘት ላይ ተቃዋሚና አወዳሽ ተፈጠረ፡፡ የፊተኞቹ የታሪክ ጸሐፊዎች የዘለሏቸውን እየመዘዙና የደበዘዙትን እያጋነኑ ነባር ትርጓሜዎችን እንደሚሹት እየቀየሩ የጸፉ የተቃውሞ ታሪኮች ተፈጠሩ፡፡ የተቃውሞ ፖለቲካና የተቃውሞ ‹‹ታሪክ›› አንድ ላይ ተሸራረቡ፡፡ ወግ አጥባቂ ፖለቲካና አወዳሽ ‹‹ታሪክ›› አንድ ላይ ገጠሙ፡፡ የሁለቱ ንቁሪያ የአገር ወዳድነትን ልቦና ሁለት ቦታ በጥቆ አምታታ፣ ጭራሽ አገር ወዳድነትን አስጠቃ፡፡ አስጠቂነቱም ጦር እስከ ማማዘዝና ደም እስከ መፋሰስ የበረታ ሆነ፡፡ ይህ ተመልሶ እንዳይመጣ ምን መደረግ አለበት? የታሪክ ሥራዎች ከመንግሥታዊ ፖለቲካና ከተቃውሞ ፖለቲካ የሚላቀቁት በምን ዓይነት ሥርዓት ቢመሩ ነው? ታሪክን የምናጠናውና የምንጽፈው ለምንድን ነው? ለእነዚህ ጥያቄዎች ሥርዓታዊ ምላሽ ከመስጠት ባሻገር፣ በእነዚህ ጉዳዮች ላይ ልሂቃንና ሕዝብ የተግባባ ንቃተ ህሊና እንዲኖራቸው መሥራት አስፈላጊ ነው፡፡ ይህንን በማሳካት ረገድ፣ ከዴሞክራሲ ግንባታ ጋር የመደበኛና የጎልማሳ ትምህርት ሥርዓታችን ፍሬያማ መሆን ወሳኝ ነው፡፡
  • የኅብረተሰባችንን የዕርምጃ ትርታ በአግባቡ ተረድቶ መራመድ ከብዶን የተደናበርነውንና ያጠፋነውን ያህል መጋጋጥና መቆሳሰል ደርሶብናል፡፡ ‹‹ትግራይ ጥንታዊ ኢትዮጵያ የተወጠነችበት ሥፍራ›› ሲባል እንዳልሰማን በ21ኛው ክፍለ ዘመን የትግራይ ፅንፈኛ ብሔርተኛነት ኢትዮጵያን ሊያፈርስ ሲሠራ ዓይተናል፡፡ ‹‹ኢትዮጵያዊ ነኝ እንጂ ብሔር የለኝም/ አማራ የሚባል ጠባብ ቀፎ ውስጥ ራሴን ማስገባት አልፈልግም›› ሲባል እንዳልሰማን፣ የአማራ ብሔርተኝነት ተፈጥሮና የኢትዮጵያን ባንዲራ የአንገት ልብሱ አድርጎ በጨለምተኛ መደናበርና ጥይት ኢትዮጵያን ሊያፈርሳት ሲተናነቃት አስተዋልን፡፡ ‹‹ጠባቦች/ጠባብ ብሔርተኞች›› ሲባሉ የነበሩና በገዥዎች ሲገፉ የነበሩ ዥንጉርጉሮቹ የኢትዮጵያ ማኅበረሰቦች የገዥዎችን አልፎ ሂያጅነት ከአገር ህልውናዊ ዋጋ ጋር ሳያሳክሩ ኢትዮጵያን ለማዳን ሲዋደቁም አየን፡፡ ተሞክሯችን ብዙ ደምና ውድመት ቢያስገብረንም፣ ጠባብ አተያይ ፊት ካሳዩት ማንንም ሠፈር ለሠፈር እያርመጠመጠ ከአገራዊ ዕይታና ተግባር ጋር ሊያጋጭ እንደሚችል አረጋግጦልናል፡፡ ማረጋገጫውም በደም የተጻፈ የታሪክ ሰነድና ዓምድ ሆኖ በውስጣችን ስለተተከለ፣ ከእንግዲህ ‹‹ጠባብ ብሔርተኛ›› እያለ በሌላው ላይ ጣት ጠቋሚና ተቺ ልሁን ባይ በመሀላችን እንዳይኖር፣ ‹‹ለኢትዮጵያ ብዙ ዋጋ ከፍያለሁ›› የሚል ትምክህትም አቀርቅሮ እንዲሰናበት አድርጓል፡፡ ይህ አሉታዊ ተሞክሯችን የተገኘ በረከት ነው፡፡
  • ከፖለቲካ ስህተቶች/ጥፋቶች የሚበቅሉ ቅሬታዎች ቀላል መስለው አሸልበውና ተጠራቅመው ምቹ አጋጣሚ ሲያገኙ፣ በዋዛ የማይሸነገሉ የፖለቲካ ጣጣዎች ሊፈጥሩ እንደሚችሉ በኢትዮጵያ የቅርብ ልምድ ዓይተናል፡፡ ከእነዚህ ልምዶች በቅጡ ተማርን ማለት የምንችለው፣ ዕርምጃዎችና ውሳኔዎች ማለፍ የሚገባቸውን ሕጋዊ ሒደት ሁሉ አሟልተው እንዲመጡ ስናደርግ፣ ስህተቶችንና ጥፋቶችን ጊዜ ሳያልፍባቸው ማረም ስንችል፣ ቀላል የሚመስሉ ብሶቶችን ሳንንቅ እንዲደመጡ ማድረግ ስንችል ነው፡፡ ከዚህ ጋር፣ የመንግሥትንና የሕዝብን የትምምን ደረጃ (ሕዝቦች ምን ያህል አገረ መንግሥታቸውን የመብቶቻቸውና የፍትሐዊነት አለኝታቸው አድርገው እንደሚመለከቱት) ከጊዜ ጊዜ መመዘን አስፈላጊ ነው፡፡ ምዘናው ትርጉም የሚኖረውም፣ ፍትሐዊ የልማትና የኑሮ ለውጥ ግስጋሴ እስካልደነቆረ ነው፡፡
  • ካለፉ ስህተቶች/ጥፋቶች ጋር የተያያዙ ጣጣዎቻችን ግን ገና አልተገባደዱም፡፡ ሰላም ማጣታችን፣ ፖለቲከኞች ፖለቲካቸውን ከእምነት ጋር እንዲለውሱ ዕድል ሰጥቷል፡፡ ፖለቲካ አመጣሽ ጥቃት የደረሰባቸውም ቤተ እምነቶች/የእምነት መሪዎች፣ ጥቃትን በመቃወም ምክንያት ወደ ፖለቲካ ተስበዋል፡፡ ከዚህም ላለፈ ቡትለካ ግርግር መንገድ ሰጥቷል፡፡ አሮጌው የመነጠል ፖለቲካ፣ ካባ ለብሶ አደረጃጀቴን ከፈለኩት የእምነት ተቋም ጋር፣ ከአገር ውጭም ተሻግሬ መቀላቀል ሃይማኖታዊ መብቴ ነው፣ መንግሥትና ሃይማኖት ተለያይቷልና በመብቴ ማንም አይገባም ባይ ሆኗል፡፡ የአንዳንድ ጮካ ነን ባዮች ፅንፈኛ ፖለቲካም ሥምሪቱን ቀይሮ በፓርቲ ሰነዶቻቸው/በውሳኔዎቻቸው ላይና በመሪዎቹ ዲስኩር ላይ የማይታይ ሆኗል፡፡ የሰላም መገኘት እንዲህ ያለውን የተቧካና ሥውር ሥራ በየአጥቢያ በየአጥቢያው ለማበጃጀት ፋታ ይሰጠናል፡፡ ሰላምን ዘላቂ የምናደርገው የሕዝብንም የህሊና ነፃነት/አማርጦ ወሳኝነት ሕይወት እንዲያገኝ ማድረግ የምንችለው፣ የትኛውም ዓይነት ፖለቲካ ቤተ እምነትን ሥውር ቤቱ የማያደርግበትን ሁኔታ ስንፈጥር ነው፡፡ ይህ ተግባር፣ ለውጡ ከሚፈተንባቸው የሰላም ጊዜ ጉዳዮች አንዱ ነው፡፡
  • ተዛማች ተባዮችንና በሽታዎችን የመቆጣጠርና የማጥፋት መርሐ ግብሮች የፈለገ መንግሥታዊ ወልጋዳነት ቢኖር ሊኮረፍባቸው የማይችሉ፣ ቀጣናዊና ከዚያም ዕልፍ ያለ ትግግዝን የሚያስገድዱ ጉዳዮች ናቸው፡፡ እነዚህን ነገሮች በትብብር በማሳካት ረገድ ኢትዮጵያ ንቁ ሚና ማሳየቷና በአረንጓዴ ኢኮኖሚና በሕዝብ ኑሮ መሻሻል ትርጉም ያለው ለውጥ ማምጣቷ፣ የሚያመነጨው ወጋገን ከቀጣናችን አልፎ የሚያበራ ነው፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝቦች በአራቱም ማዕዘን የሚያሳዩት (የከፋ ድህነትንና ከድርቅ ጋር የሚመላለስ የረሃብ አደጋን ያሸነፈ) የኑሮ ለውጥ፣ ጎረቤት ዘንድ ሊኖር ከሚችል ማኅበራዊ ጉስቁልና ጋር ተስማምቶ ሊኖር አይችልም፡፡ የጎረቤት ጎስቋሎች ወደ ኢትዮጵያ ቢሰደዱም፣ ኢትዮጵያ ከልማት ረድዔቷ ብታቋድስም፣ ኅብረተሰቧ ላይ የታየው የኑሮ ለውጥ ጎረቤት ዘንድ ባለ ፍዘት ላይ ንዝረት መፍጠሩ አይቀርም፡፡ ማለትም የኢትዮጵያ ፈጣን ልማት በአዎንታዊ ትቅቅፍ መንገድም ሆነ ለደነዝ መንግሥታት ድማሚት በመሆን መንገድ፣ ለጎረቤቶቻችን ሕዝቦች መድኅን መሆኑ አይቀርም፡፡ ይህንን መሰሉን በጎ የልማት ተፅዕኖ በአካባቢዋ ላይ ኢትዮጵያ መፍጠር ቻለች ማለት ደግሞ፣ በልማቷ ተጋቦት ውስጥ የጎረቤት የባህር በሮችም የኢትዮጵያን ልማት ለመቀላቀል የሚጓጉበት ውስጠ ወይራ አብሮ ተፈጠረ ማለት ነው፡፡ የዚህ ዓይነት መሳሳብ ተፈጠረ ማለት ደግሞ፣ ከአገራዊ ሉዓላዊ መብቶች የተወሰኑትን ቀንሶና የቀጣናዊ ማኅበረሰብ የጋራ መብቶች አድርጎ መያያዝ ሰባኪ የማይፈልግ የሁሉ ፍላጎት ሆኖ አጠገባችን ይገሸራል ማለት ነው፡፡

ሰላምና አረንጓዴ ልማት ለአገራችን፣ ለቀጣናችን፣ ለአኅጉራችንና ለዓለማችን!!!

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ሰላማዊ የፖለቲካ ትግልና ፈተናው

የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) የፖለቲካ ኦፊሰር የአቶ በቴ ኡርጌሳን...

አበጀህ ማንዴላ! አበጀሽ ደቡብ አፍሪካ!

በአየለ ት. የፍልስጤም ጉዳይ የዓለም አቀፍ ፖለቲካንም ሆነ የተባበሩት መንግሥታትን...

የውጭ ባለሀብቶች ለኢትዮጵያውያን ብቻ በተፈቀዱ የንግድ ዘርፎች እንዲገቡ የመወሰኑ ፋይዳና ሥጋቶች

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አዓመድ (ዶ/ር) የውጭ ኩባንያዎች በጅምላና ችርቻሮ...