Saturday, April 20, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናየአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ የግዥ ሠራተኞች ከግማሽ ሚሊዮን ብር በላይ ይዘው...

የአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ የግዥ ሠራተኞች ከግማሽ ሚሊዮን ብር በላይ ይዘው መሰወራቸው በፓርላማ ተነገረ

ቀን:

የአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ የግዥ ሠራተኞች 882 ሺሕ ብር ቅድመ ክፍያ ይዘው መጥፋታቸው ተገለጸ፡፡

በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግሥት ወጪ አስተዳደርና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ፣ በዩኒቨርሲቲው የኦዲት ግኝት ሪፖርት ላይ መጋቢት 17 ቀን 2016 ዓ.ም. ባዘጋጀው ውይይት፣ ለግዥ የተሰጠን 882 ሺሕ ብር ቅድመ ክፍያ፣ ሠራተኞቹ ወስደው በመጥፋታቸው ጉዳዩ በሥነ ምግባርና በፀረ ሙስና ኮሚሽን ተይዞ እየተፈለጉ መሆኑን የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ደረጀ እንግዳ (ዶ/ር) ገልጸዋል፡፡

የምክር ቤቱ ቋሚ ኮሚቴና የፌዴራል ዋና ኦዲተር መሥሪያ ቤት አመራሮች ባነሱት ጥያቄ፣ በ2013 በጀት ዓመት በዩኒቨርሲቲው ስፖንሰርነት ትምህርታቸውን ለመማር በገቡት የውል የጊዜ፣ ትምህርታቸውን አጠናቀው ወደ ሥራቸው ያልተመለሱ ሠራተኞች፣ በውል ስምምነቱ መሠረት ለዩኒቨርሲቲው መክፈል የነበረባቸው 7.3 ሚሊዮን ብር ተመላሽ አለመደረጉንም ገልጸዋል፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ደረጀ (ዶ/ር) በ2011 ዓ.ም. እና 2013 ዓ.ም. 18 መምህራን ትምህርታቸውን በተቀመጠላቸው ጊዜ አጠናቀው ባለመመለሳቸው የተለያዩ ዕርምጃዎች መወሰዳቸውን በመግለጽ፣ ከእነዚህ ውስጥ አምስት መምህራን የት እንዳሉ ባለመታወቁ በዋሶቻቸው ላይ ክስ ተመሥርቶ ገንዘቡን እንዲመልሱ በፍርድ ቤት መወሰኑን ተናግረዋል፡፡

በዩኒቨርሲቲው ሕግ መሠረት የዶክትሬት ወይም የሦስተኛ ዲግሪ ትምህርት ለማጠናቀቅ አራት ዓመታት በቂ ቢሆንም፣ በተለያዩ ምክንያቶች ትምህርታቸውን ማጠናቀቅ ላልቻሉ ደግሞ ሁለት ዓመት መጨመር ቢቻልም፣ መምህራኑ በስድስት ዓመታት ውስጥ አጠናቀው ባለመምጣታቸው ከሥራ መሰናበታቸውን ፕሬዚዳንቱ ገልጸዋል፡፡

በተጨማሪም በ2012 በጀት ዓመት በዩኒቨርሲቲው ስፖንሰርነት ትምህርታቸውን የሚማሩ መምህራን ትምህርታቸውን አጠናቀው መመለስ ባለባቸው ጊዜ ውስጥ መመለስ ሲገባቸው፣ የመመለሻ ጊዜ ያሳለፉ መምህራን ትምህርት ላይ እንዳሉ ተደርጎ ደመወዝ፣ የቤት አበልና ትራንስፖርት አበል በአጠቃላይ 266,400 ብር ለምን እንደተከፈለ በቋሚ ኮሚቴው ጥያቄ ቀርቧል፡፡

ለጥያቄው ምላሽ የሰጡት ፕሬዚዳንቱ ትምህርት ላይ ያሉ በማስመሰል ደመወዝ ሲከፈላቸው የቆዩት መምህራን በተቋሙ የሕግ አገልግሎት አማካይነት በዋሶች ላይ ክስ በመመሥረት፣ በየወሩ 2,500 ብር እንዲከፍሉ በፍርድ ቤት ተወስኗል ብለዋል፡፡ በዚህም እስካሁን 60 ሺሕ ብር ተመላሽ መደረጉን አስረድተዋል፡፡

በቋሚ ኮሚቴው ለዩኒቨርሲቲው ከተነሱ ጥያቄዎች መካከል ከተለያዩ ሰባት ድርጅቶች ጋር ሌተር ኦፍ ክሬዲት ተከፍቶ የተፈጸመ ግዥን በተመለከተ ሲሆን፣ ለትምህርት መሣሪያዎች ግዥ 124.4 ሚሊዮን ብር፣ እንዲሁም ዩኒቨርሲቲው እ.ኤ.አ ከ2016 እስከ 2020 ድረስ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ለገዛቸው ጆርናሎች የ1.2 ሚሊዮን ብር ፕሮፎርማ ለምን አልተሰበሰበም የሚለው ይገኝበታል፡፡

በኦዲት ግኝቱ መሠረት 124 ሚሊዮን ብር የግዥ ሰነድ ያልቀረበበትን ምክንያት ማብራሪያ የሰጡት ፕሬዚዳንቱ፣ በወቅቱ ግዥውን የፈጸመው የኢትዮጵያ ንግድ ሥራዎች ኮርፖሬሽን የግዥና ማማከር አገልግሎት ዘርፍ በመሆኑ ነው ብለዋል፡፡

ነገር ግን ከኦዲት ግኝቱ በኋላ ጨረታውን ያካሄደው የመንግሥት ግዥና ማማከር አገልግሎት መሥሪያ ቤት በመሆኑ፣ ለዚህም ማረጋገጫ ከኮርፖሬሸኑ ማምጣት ተችሏል ብለዋል፡፡

ፕሬዚዳንቱ አክለውም 1.2 ሚሊዮን ብር ወጪ የተደረገው የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የጆርናል አገልግሎት ክፍያ በወቅቱ ሳይከፈል ቢቆይም፣ ከቆይታ በኋላ መከፈሉን ተናግረዋል፡

የኦዲት ግኝቶችን መሠረት በማድረገ የተቋሙን የውስጥ የኦዲት አቅም በማጠናከር ቀሪ ሥራዎች ላይ ትኩረት ሰጥቶ በመሥራት፣ የመንግሥትን ሀብትና ንብረት ማስመለስ እንደሚገባ የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ የሺመቤት ደምሴ (ዶ/ር) አሳስበዋል፡፡

የቋሚ ኮሚቴው አባላት ያልተዋራረዱ ሒሳቦች ከተሰብሳቢ ገንዘብ፣ ከንብረት አያያዝና አወጋገድ፣ እንዲሁም ውጭ አገር ለትምህርት ተልከው ከቀሩ መምህራን ጋር በተያያዘ የኦዲት ግኝት በሆኑ የመንግሥትና ሕዝብ ሀብቶች ላይ ትኩረት ሰጥቶ በመሥራት፣ ዩኒቨርሲቲው ሕግ ማስፈጸም ይኖርበታል ብለዋል፡፡

የተሰብሳቢ ገንዘብ መረጃ እስከ የካቲት 15 ቀን 2016 ዓ.ም. ድረስ፣ እንዲሁም ከአጠቃላይ የኦዲት ግኝቶች ማስተካከያ ጋር በተያያዘ በዝርዝር እስከ ግንቦት 30 ቀን 2016 ዓ.ም. ለገንዘብ ሚኒስቴር፣ ለዋና ኦዲተርና ለሚመለከታቸው አካላት ሪፖርት እንዲያቀርብ ቋሚ ኮሚቴው ማሳሰቢያ ሰጥቷል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ሰላማዊ የፖለቲካ ትግልና ፈተናው

የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) የፖለቲካ ኦፊሰር የአቶ በቴ ኡርጌሳን...

አበጀህ ማንዴላ! አበጀሽ ደቡብ አፍሪካ!

በአየለ ት. የፍልስጤም ጉዳይ የዓለም አቀፍ ፖለቲካንም ሆነ የተባበሩት መንግሥታትን...

የውጭ ባለሀብቶች ለኢትዮጵያውያን ብቻ በተፈቀዱ የንግድ ዘርፎች እንዲገቡ የመወሰኑ ፋይዳና ሥጋቶች

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አዓመድ (ዶ/ር) የውጭ ኩባንያዎች በጅምላና ችርቻሮ...