Saturday, April 20, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ብሔራዊ ባንክ በንብ ባንክ ላይ የጣለው የገንዘብ ቅጣትና ባንኩን ከችግር የማውጣት ዕርምጃዎች

ተዛማጅ ፅሁፎች

  • ባለአክሲዮኖች የባንኩን ካፒታል ወደ 20 ቢሊዮን ብር ለማሳደግ ወስነዋል

አዲሱ የንብ ኢንተርናሽናል ባንክ የዳይሬክተሮች ቦርድ ባንኩን ከገባበት ችግር ለማውጣት የተለያዩ ዕርምጃዎችን እየወሰደ ሲሆን፣ መሠረታዊ ችግሮችን ለይቶ ለመፍታትና ባንኩን ወደ ቀደመ ሥፍራው ለመመለስም የ90 ቀናት ዕቅድ በመንደፍ ወደ ትግበራ መግባቱ ታውቋል።

በዚሁ ዕቅድ መሠረትም፣ ባለፈው ቅዳሜ መጋቢት 14 ቀን 2016 ዓ.ም. የባንኩን ባለአክሲዮኖች ለአስቸኳይ ጠቅላላ ጉባዔ በመጥራት የባንኩን ካፒታል የማሳደግና በ2015 ሒሳብ ዓመት የተገኘው ትርፍ ለባለአክሲዮኖች ሳይከፋፈል ለካፒታል ማሳደጊያ እንዲውል የውሳኔ ሐሳብ አቅርቦ በጠቅላላ ጉባዔው አፀድቋል።

ከሁለት ዓመታት በፊት የባንኩን ካፒታል እስከ ሰኔ ወር 2018 ዓ.ም. ባለው ጊዜ ውስጥ ወደ አሥር ቢሊዮን ብር ለማሳደግ ተላልፎ በነበረው ውሳኔ ላይ የተቀመጠውን የጊዜ ገደብ ተሻሽሎ የጊዜ ገደቡ ወደ ሰኔ 2016 ዓ.ም. እንዲያጥር በአዲሱ ቦርድ የቀረበው የውሳኔ ሐሳብም ባለፈው ቅዳሜ በተካሄደው አስቸኳይ የባለአክስዮኖች ጠቅላላ ጉባዔ ላይ በአብላጫ ድምፅ ፀድቋል።

ከዚህም ባለፈ ሰሞኑን በተካሄደው የባንኩ አስቸኳይ ጠቅላላ ጉባዔ ላይ የባንኩን ካፒታል በተጨማሪ አሥር ቢሊዮን ብር ለማሳደግ የውሳኔ ሐሳብ የቀረበ ሲሆን፣ በጉዳዩ ላይም ባለአክሲዮኖች ሰፊ ውይይትና ክርክር ካደረጉ በኋላ የቀረበውን የውሳኔ ሐሳብ በመቀበል የባንኩን ካፒታል ወደ 20 ቢሊዮን ብር ለማሳደግ ወስነዋል። 

የባንኩን ካፒታል በተጨማሪ አሥር ቢሊዮን ብር በማሳደግ ወደ 20 ቢሊዮን ብር ከፍ ለማድረግ የቀረበው የውሳኔ ሐሳብም 99 በመቶ በሚሆኑት ባለአክሲዮኖች ተደግፎ ፀድቋል። ባንኩ ካፒታሉን ወደ 20 ቢሊዮን ብር ለማሳደግ በወሰነው ውሳኔ መሠረት ተጨማሪውን አሥር ቢሊዮን ብር ባለአክሲዮኖች በምን ያህል ጊዜ ይክፈሉ የሚለው ጥያቄ ከሰኔ 30 ቀን 2016 ዓ.ም. በኋላ ውሳኔ እንዲሰጥበት ስምምነት ላይ ተደርሷል፡፡ 

በመሆኑም አዲሱ ቦርድ ያቀረባቸው ሦስቱም አጀንዳዎች ማለትም፣ የባንኩ የ2015 ሒሳብ ዓመት ትርፍ ሳይከፋፈል ለካፒታል ማሳደጊያ እንዲውል ያቀረበው የውሳኔ ሐሳብ፣ ቀደም ሲል የባንኩን ካፒታል ወደ አሥር ቢሊዮን ብር ለማሳደግ በተላለፈው ውሳኔ ላይ የቀመጠውን የጊዜ ገደብ ወደ ሰኔ 2016 በማሳጠር ያልተሸጡ ቀሪ አክሲዮኖች በተጠቀሰው ጊዜ ውስጥ ተሽጠው እንዲጠናቀቁ ያቀረበው የውሳኔ ሐሳብና የባንኩን ካፒታል ወደ 20 ቢሊዮን ብር ለማሳደግ ያቀረበው አዲስ የውሳኔ ሐሳብ በአብላጫ ድምፅ መፅደቃቸው ታውቋል።

በባንኩ ባለአክሲዮኖች ይሁንታ ያገኙት እነዚህ የውሳኔ ሐሳቦች ባንኩን ከገባበት ችግር ሊያላቅቁ ያስችላሉ ተብለው ከተያዙ መፍትሔ ሐሳቦች መካከል የተጠቀሱ ቢሆኑም የውሳኔ ሐሳቡ ከመፅደቁ በፊት ግን በባለአክሲዮኖች ከፍተኛ ክርክር ተደርጎባቸዋል፡፡ 

ባንኩ አሁን ካለበት ችግር አንጻር እነዚህን አጀንዳዎች ማፅደቅ አስፈላጊ ስለመሆኑ የአዲሱን ቦርድ ሐሳብ የደገፉ ቢኖሩም አንዳንድ ባለአክሲዮኖች ግን በተለይ የትርፍ ክፍፍሉ ለካፒታል ማሳደጊያ መዋል የለበትም ብለው ተሟግተዋል።

ከባንኩ የሚያገኙትን ዓመታዊ ትርፍ የሚተዳደሩበት ጭምር በመሆኑ የትርፍ ድርሻችን ለካፒታል ማሳደጊያ ቢውል እንጎዳለን በማለት ይህ አጀንዳ እንዳይጸድቅ ተከራክረዋል፡፡ ይህ አጀንዳ ቢፀድቅ መብታችን እንደተነካ ነው የምንቆጥረው ያሉም አሉ፡፡ 

እንዲህ ካለው አስተያየት ባሻገር ግን አጀንዳዎቹን ለማፅደቅ መጀመርያ ባንኩ ገጥሞት የነበረው ችግር በግልጽ ሊነገረን ይገባል በሚል የቀረቡ ጥያቄዎች ግን የብዙዎቹን ባለአክሲዮኖች ድጋፍ ያገኘ ነበር፡፡ 

በተለይ ባንኩ እዚህ ችግር ውስጥ የገባበት ምክንያትና ችግሩ ባንኩ ላይ ያስከተለውን ጉዳትም ማወቅ እንሻለን የሚል ጥያቄ ያቀረቡ ባለአክሲዮኖች በዕለቱ የቀረቡትን አጀንዳውን ለማፅደቅ መጀመርያ ባንኩ አጋጥሞታል በተባሉ ችግሮች ዙሪያ ዝርዝር ማብራሪያ ሊሰጠን ይገባል ብለዋል፡፡ 

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ በንብ ኢንተርናሽናል ባንክ ላይ ደረሰ ያለውን የጉዳት መጠን በተመለከተ ሐሳብ የሰነዘሩ አንድ ባለአክሲዮን፣ በተፈጠረው ችግር ባንኩ ላይ የደረሰው ጉዳት ምን ያህል እንደሆነ ይገለጽላቸው ዘንድ ጠይቀዋል፡፡ በተለይ ባንኩ ባጋጠመው ችግርና የአሠራር ግድፈት በኢትዮጵያ በብሔራዊ ባንክ ቅጣት እንደተጣለበት ጠቅሰው ይህ የቅጣት መጠን እንዲገለጽላቸው ጠይቀዋል፡፡ ሌላው አፅንኦት ሊሰጠው ይገባል ተብሎ ጥያቄና አስተያየት የተሰጠበት ጉዳይ ባንኩን ለቅጣትና አሁን ላለበት ችግር የዳረጉ የባንኩ አመራሮች መጠየቅ የለባቸውም ወይ? የሚል ነው፡፡ ይህ ጉዳይ በተለያዩ የጠቅላላ ጉባዔተኞች የተጠየቀ ሲሆን በዕለቱ የቀረቡትን የውሳኔ ሐሳብ ለማፅደቅም እንዲህ ላሉ ጥያቄዎች መልስ እንሻለን በማለት ሞግተዋል፡፡ 

ከባለአክሲዮኖች ለቀረቡት ለእነዚህና ለሌሎች ጥያቄዎች የባንኩ ዳይሬክተሮች ቦርድ አባላት ምላሽ የሰጡበት ሲሆን፣ በተለይ ባንኩ ገጥሞታል በተባለው ችግርና ለችግሩ መፈጠር ምክንያት ናቸው የተባሉ አመራሮች ጉዳይን በተመለከተ የዳይሬክተሮች ቦርድ ሰብሳቢው አቶ ሺሰማ ሸዋነካ በሰጡት ምላሽ ባንኩ ያገጠሙትን ሁሉንም ችግሮች በዝርዝር መግለጹ በተለያዩ ምክንያቶች ተገቢ አለመሆኑን አስረድተዋል፡፡ ሆኖም ባንኩ ለገጠመው ችግር ተጠያቂ ሊሆኑ የሚችሉ አካላትን ጉዳይ ግን በጥልቀት እየሠሩበት መሆኑንና ጉዳዩ የተዘነጋ እንዳልሆነ ገልጸዋል። ሕጋዊ ዕርምጃ መወሰዱ የማይቀር መሆኑን ማረጋገጫ ሰጥተዋል፡፡ 

ባንኩ ከፈጸመው የአሠራር ግድፈትና አጋጥሞት ከነበረው የአሠራር ክፍተት ጋር በተያያዘ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ 87 ሚሊዮን ብር ቅጣት እንደጣለበት አዲሶቹ የባንኩ አመራሮች ለባለአክሲዮኖች ገልጸዋል።

ይህም ቅጣት ባንኩ ከገንዘብ ማቀናነስ ጋር ተያይዞ በባንኩ በኩል ሊከፈሉ የሚገባቸውን ክፍያዎች መፈጸም ካለመቻሉ ጋር በተያያዘ የመጣ ስለመሆኑ ማብራሪያ ተሰጥቶበታል፡፡ እንዲህ ያሉና ሌሎች በርካታ አስተያየትና ጥያቄዎች የቀረቡበት አስቸኳይ ጠቅላላ ጉባዔ መጨረሻ ላይ የተሻለ የሚሆነው በዕለቱ የቀረቡ አጀንዳዎች ላይ ውሳኔ ማሳለፍ ነው የሚለው ሐሳብ በብዙኃኑ ተቀባይነት አግኝቶ ፀድቋል፡፡ ይህ ዕርምጃ ባንኩን ማዳንና ወደቀድሞው ከፍታው ለመመለስ የሚያስችል መሆኑን ስምምነት ላይ በመድረስ አጀንዳዎቹ ሊፀድቁ ችለዋል፡፡ 

አጀንዳዎቹ ከመፅደቃቸው ቀደም ብሎ አዲሱ ቦርድ ኃላፊነቱን ከተረከበ ጊዜ ወዲህ ያካሄዳቸው ሥራዎች በቦርድ ሊቀመንበሩ በኩል ሪፖርት ቀርቧል፡፡ በዚህም ሪፖርታቸው ባንካችን ባለፉት ወራት የገጠመውን ችግር መነሻ በማድረግ ታኅሳስ 18 ቀን 2016 ዓ.ም. በተካሄደው የባለክሲዮኖች ጠቅላላ ጉባዔ በብሔራዊ ባንክ አመቻችነት የተመረጠው አዲሱ ቦርድ የጣላችሁበትን አደራ በደንብ የሚረዳ መሆኑንና ባንካችን ከነበረበት ሁኔታ ወደ ተሻለና ከፍ ወዳለ ደረጃ ለማድረስ ቀን ከሌት እየሠራ መሆኑን ላረጋግጥላችሁ እወዳለሁ፤›› ብለዋል፡፡ 

አያይዘውም ‹‹በተለይም ምንም እንኳ ባአክሲዮኖች ብትሆኑም ባለፉት ጊዜያት ባጋጠመው ተግዳሮት ምክንያት ለደረሰባችሁ መጉላላትና ለተፈጠረባችሁ ቅሬታ ከልባችሁ ይቅር እንድትሉን እንጠይቃለን፤›› በማለት ባለአክሲዮኖችን ይቅርታ ብለዋል፡፡ አዲሱ ቦርድ ባንኩን ከገጠመው ችግር ለማላቀቅ ባለአክሲዮኖች ሲያደርጉ የነበረውን ድጋፍ እንዲቀጥሉም ጠይቀዋል፡፡ በተለይ እርሳቸው ወሳኝ ባሏቸው የአጭርና የረዥም ጊዜ ድጋፎች እንዲያደርጉላቸው በማሳሰብ ባለአክሲዮኑ ሊያደርግላቸው የሚገባቸውን በዝርዝር አቅርበዋል፡፡ ከእነዚህም መካከል የባንኩን ዕድገት ለማፋጠንና የውጤቱም ተቋዳሽ ለመሆን ከአሁን ጀምሮ፣ ከባንካችሁ ጋር ብቻ እንድትሠሩ የሚል ይገኝበታል፡፡ ከዚህም ሌላ ደንበኞቻቸው ጭምር ገቢያቸውን በንብ ብቻ እንዲያስገቡ፣ ሠራተኞችን በየቅርንጫፍ እየሄዳችሁ እንዲያበረታቱ፣ ባንኩ የጀመረውን የማርኬቲንግ ካምፔይን ዋነኛ አጋርና ተሳታፊ እንዲሆኑ ጥሪ አቅርበዋል፡፡ ባንኩ እያከናወነ ያለውን የለውጥ እንቅስቃሴ ሌሎች እንዲያውቁ ማድረግም የባለአክሲዮኖች ተግባር ሊሆን እንደሚገባም ጠቅሰዋል፡፡ ቼክ ክፍያዎች በባንኩ ብቻ እንዲያደርጉ ባለአክሲዮኖችን የጠየቁት የቦርድ ሊቀመንበሩ ከዚህ ጋር በተያያዘ ቼክ አይመነዘርም የሚል ሥጋት በፍጹም እንዳይገባችሁ፣ በማለት ቼክ ከመመንዘር ጋር የነበረው ችግር አሁን ስለመቀረፉ አረጋግጠዋል፡፡ ‹‹ባንካችን ለነጋዴው ማኅበረሰብና ለኮርፖሬት ተቋማት አለኝታ በመሆን ሲሠራ የቆየ ቢሆንም ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ በተለያዩ ምክንያቶች የገጠመው ተግዳሮት ቢኖርም ከባንካችን ጋር ያላችሁን የሥራ ግንኙነት አጠናክረው እንዲቀጥሉ ባለአክሲዮኖች የድርሻችሁን እንድትወጡ እንጠይቃለን፤›› በማለት ባንኩ ካለበት ችግር ለመወጣት የባለአክሲዮኖች ዕገዛ ከፍተኛ ነውም ብለዋል፡፡ 

የሁሉም ባለድርሻ አካላት ርብርብ ታክሎበት በአጭር ጊዜ ውስጥ ባንካቸው ወደ ቀድሞው መልካም ስምና ዝና፣ ለመመለስ ሌት ከቀን የሚሠሩ መሆኑን የገለጹት አቶ ሺሰማ በአሁኑ ወቅት ከገንዘብ እጥረት ጋር በተያያዘ የነበረው ችግር እየተቀረፈና ደንበኞች የጠየቁትን ክፍያ ወዲያው እንዲያገኙ እየተደረገ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡ በተለይ በመርካቶና በተለያዩ አካባቢዎች ያሉ ቅርንጫፎቻቸው ደንበኞች ተመልሰው የሚፈልጉትን አገልግሎት እያገኙ በመሆኑ በአጭር ጊዜ ውስጥ ባንኩን ወደ ቀደመ ከፍታው ይመለሳል የሚል እምነታቸውን ለባለአክሲዮኖቹ ገልጸዋል፡፡ 

ንብ ባንክ ከ1983 ዓ.ም. ወዲህ የባንክ ኢንዱስትሪውን ከተቀላቀሉ የግል ባንኮች መካከል አንዱ ነው፡፡ እስከ 2015 የሒሳብ ዓመት መጨረሻ ድረስ አጠቃላይ የሀብት መጠን ከ77 ቢሊዮን ብር በላይ ነው፡፡ 

በ2015 የሒሳብ ዓመት ከታክስ በፊት ሁለት ቢሊዮን ብር ያተረፈ መሆኑ አይዘነጋም፡፡ አጠቃላይ የብድር ክምችቱ ከ54 ቢሊዮን ብር በላይ የደረሰው ንብ ባንክ ባለፈው ዓመት ባንኩ አጋጥሞታል በተባለ ችግር የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ምርመራ በሚደረግ ባንኩ በተለይ ከጥሬ ገንዘብ እጥረት ጋር ያጋጠመን ችግር በዝርዝር በማቅረብ የችግሩ መነሻ ናቸው ያላቸውንም ባለአክሲዮኖች እንዲያውቁት ተደርጓል፡፡

ባደረገው ምርመራ ተጠያቂ ናቸው ያላቸውን የቀድሞ የባንኩን ዳይሬክተሮች ቦርድ አባላት በሙሉ ለስድስት ዓመታት በማንኛውም የፋይናንስ ተቋማት ውስጥ እንዳይሠሩ ማገዱ ይታወሳል፡፡ 

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች