Wednesday, April 17, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ልናገርፈርሰን ሳናልቅ እንድረስ - የሐኪም ወርቅነህ እሸቴ ቤት የዓለም አቀፍ ታሪካችን ሙዚየም...

ፈርሰን ሳናልቅ እንድረስ – የሐኪም ወርቅነህ እሸቴ ቤት የዓለም አቀፍ ታሪካችን ሙዚየም ነው

ቀን:

በሱራፌል ወንድሙ (ዶ/ር)

ኢትዮጵያን ለማዳን ሲባል በአውሮፓ ከታላላቅ የፓን አፍሪካ አስተሳሰብ ፈላስፎችና ታጋዮች ጋር ያደረጓቸው የቅርብ ትብብሮች (ለምሳሌ ሲኤልአር ጀምስን፣ ጆርጅ ፓድሞርንና ሲልቪያ ፓንክረስትን እንጠቅሳለን)፣ የፀረ ባርነት ትግል በኢትዮጵያ (በኪነ ጥበባት ጭምር) እና በዓለም አቀፍ መድረኮች፣ ኢትዮጵያ ከአፍሪካ አሜሪካውያን ጋር በሥራ ቅጥር የጀመረችውና እስከ ፀረ ፋሽስት ትግል ያደገው ዓለም አቀፋዊ ግንኙነት

(በህንድ ያደረጉትን የተማሩ ሰዎችን ወደ ኢትዮጵያ የማምጣት ሥራዎችን ጨምሮ)፣ የፀረ ቅኝ ግዛት ትግልን ለማካሄድ የተደረጉ ዓለም አቀፍ የጦር መሣሪያ የማግኘት ትግሎች፣ የዓባይ ግድብ መነሻ ታሪፈርሰን ሳናልቅ እንድረስ - የሐኪም ወርቅነህ እሸቴ ቤት የዓለም አቀፍ ታሪካችን ሙዚየም ነው | Ethiopian Reporter | ሪፖርተርካችን (የእንግሊዝንና የጣልያንን የመጋረጃ ጀርባ ሴራ ከአሜሪካ ጋር በመሆን ለማክሸፍ የተጣጣሩበት)፣ የባህር በር አስፈላጊነት ታሪክ (ኢትዮጵያ የባህር በር ለማግኘት ባደረገችው ትግል የነበራቸው ግንባር ቀደም ተሳትፎ)፣ የኢትዮ አሜሪካ የውጭ ግንኙነት በወጉ መጀመር ወይም መታደስ (አሜሪካ አያስፈልገንም ብላ የዘጋችውን ቆንስላ ከፕሬዚዳንቱ ጋር በአካል ተገናኝተው ዳግም የማስከፈት ትግል)፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

በኢትዮጵያ ታሪክ በተለይ በፀረ ቅኝ ግዛት ትግል ታሪካችን ዓለም አቀፋዊ መድረክ ላይ ጉልህ አስተዋጽኦ ያላቸውን ሰዎች ስንጠራ ከጥቂቶቹ ግንባር ቀደም ኢትዮጵያውያን መሀል የምናገኛቸው ሐኪም ወርቅነህ እሸቴን ነው። ይህም በራሳቸው በሐኪም ወርቅነህ እሸቴ የግል መዝገብም ሆነ በታሪክ ጥናት በአግባቡ ተመዝግቦ አለ (ብዙ ሊገለጡና ሊተነተኑ የሚገባቸው ታሪኮቻቸው ገና መጻፍ ቢኖርብንም)። አሁን ይህንን ታሪክ ስጽፍ የሐኪም ወርቅነህ እሸቴ ቤቶች (አንድ ፒያሳ ከአገር ፍቅር ቴዓትር ከፍ ብሎ ያለው ሦስት በባንኮ ዲ ሮማ አካባቢ የሚገኘው) ሕንፃዎች በከፊል መፍረስ ጀምረዋል። በአገር ፍቅር አካባቢ ያለው አጥሩ የፈረሰ ሲሆን፣ በባንኮ ዲ ሮማ አካባቢ ያለው ሌላኛው መኖሪያ ሕንፃቸው አንዱ ክንፉ ተቦርድሶ ሌላኛው ሊናድ ተሰናድቷል። እየተጣደፍኩ ነው የምጽፈው። ምክንያቱም ከመንግሥት ባለሥልጣናት የሚወጡት መግለጫዎች እርስ በርሳቸው ቢጋጩም፣ እንዲህ ያሉ ቅርሶች መፍረስ የማይቀርላቸው መሆኑን እያረዱን ስለሆነ። ሠፈሮች በፍጥነት እየፈራረሱ ስለሆነ። የከተማው አስተዳደር ቃል አቀባይዋ ቅርሶቹን በጥናት ላይ ተመሥርተን መዝግበናቸዋል፣ የሚፈርሱት ታሪካዊ ዋጋ የሌላቸው ዓይነቶቹ ናቸው ሲሉን፣ ሌላ የቅርስ ተቋም ኃላፊ “ምሁር” ነኝ የሚሉ ሰው በቅርስነት የተመዘገቡት ሁሉ ቅርሶች አይደሉምመ፣ ምክንያቱም መሥፈርቶቹ በጥናት የተደራጁ አይደሉም (ስለዚህም ይፈርሳሉ) እያሉን ነው።

ፈርሰን ሳናልቅ እንድረስ - የሐኪም ወርቅነህ እሸቴ ቤት የዓለም አቀፍ ታሪካችን ሙዚየም ነው | Ethiopian Reporter | ሪፖርተር

 እንኳንስ ጉዳዩን በቅርበት ለሚከታተሉና ሰዎች ይቅርና፣ ድንገት ጉዳዩን የሰማም ሰው ቢሆን ተራ ጥያቄዎችን ሊያነሳ ይችላል፡፡ የቅርስነት መሥፈርቶቹ በጥናት ካልተደራጁ፣ አጥንቶ መወሰን እያለ እያጣደፉ ቅርሶችን ማፍረሱ ለምን አስፈለገ? ዓምና ቅርስ የሆነን ዘንድሮ በጓሮ በር ቅርስ አይደለም የሚለው ነገር እንዴትና በነማን ለማን ሲባል ታሰበ? ይህንን መሰል ጥያቄዎችን የሚያቀርቡ ኃላፊነት የሚሰማቸውን ግለሰቦችና ማኅበራት ለምንድነው የመንግሥት ኃላፊዎች የሚያስፈራሯቸውና የሚያዋክቧቸው? በተቀናጀ ሁኔታ ቡል ዶዘሮች ተሰማርተው የሚካሄድን የቅርስ መናድ ተግባር ለምንድነው የአንድ መሥሪያ ቤት የተነጠለ ስህተት ለማስመሰል የሚሞከረው? ሌሎች ምሁራን ነን የሚሉ ጉልሃን እውነቱን አዕምሯቸው እያወቀ፣ እንደምን ታሪክን በመሸቀጠም ሆነ በዝምታ እያዩ በመተባበር ሒደት ውስጥ ተሳታፊዎች ሆኑ? እነዚህን የቅርስ ማጥፋት ዘመቻዎች ሰፊው ሕዝብ በከተማ ልማት ስም እየደረሰበት ካለው ጥፋት ጋር እንዴት ማስተሳሰር እንችላለን? እነዚህን ሁሉ ውጥንቅጦች ከአዳዲሶቹ ትርክቶችና ፖለቲካዊ ነውጦች፣ አገሪቱ በየአቅጣጫው ከገባችባችባቸው ጦርነቶች እንዲሁም ከወደሙትና እየወደሙ ካሉት የሰው ልጆች ሕይወት፣ ህሊናዊና የገላ ቁስሎች፣ ከንብረት ጥፋትና፣ ከህልውና ሥጋት ጋር እንዴት አያይዘን እንያቸው? ይህ ጽሑፍ እነዚህን ጥያቄዎች ወሳኝነታቸውን ቢያምንም እዚህ ለመመለስ ከመሞከር ይልቅ በአንድ ታሪክ መነሻነት ሕዝቡ የተለያዩ ሐሳቦችን እንዲያብላላ የሚጋብዝ ነው።  

ፈርሰን ሳናልቅ እንድረስ - የሐኪም ወርቅነህ እሸቴ ቤት የዓለም አቀፍ ታሪካችን ሙዚየም ነው | Ethiopian Reporter | ሪፖርተር

ጊዜው የጥድፊያ ሆኗል። ይናዳሉ። ቤቶች ይፈርሳሉ። ሕይወቶች ይደረመሳሉ። የትዝታ ማደሪያ ቁሶች ይሰባበራሉ። ሕዝብ ይተክዛል። መንግሥት ፕሮፓጋንዳ ያሠራጫል። አንዳንድ ነዋሪዎችና “አርቲስቶች” ነን የሚሉ ግለሰቦች የልማቱ “አርት” ውብ ሆኖ እየተከናወነ እንደሆነ ሊነግሩን ወደ ቴሌቪዥን መስኮት ይሳባሉ። አንዳንድ ነዋሪዎችም አዲስ በተሰጣቸው ሥፍራ ሕይወት ዓለም መሆን እንደ ጀመረች ተናገሩ ይባላሉ። ብዙዎች ያጉተመትማሉ። ውስጥ ውስጡን የረባ መኖሪያ እንዳልተሰጣቸው ይናገራሉ። ከትዝታዎቻቸውና ከማኅበራዊ ዓውዳቸው እንደተነቀሉ እንደተጓዙ ያስረዳሉ። ፒያሳን፣ አራት ኪሎን… ብታፈርሷቸውም ብጥስጣሽ ታሪኮቻችንን አትንዷቸውም እያሉ ትዝታዎቻቸውን የሙጥኝ ይላሉ። ሰው በሕንፃ ብቻ አይኖርም፣ በትውስታም እንጂ ይላሉ። የፖሊሶችን ማዋከብና እስር ችለው አፍራሾችንና ፈራሾችን በፎቶግራፍና በምሥለ ድምፅ ይቀርፃሉ። በልማት ስም የሚካሄድን ጥፋት ይመሰክራሉ። ይመዘግባሉ። በዋናዎቹ ሚዲያዎች የማንሰማቸውን ውይይቶች ያካሂዳሉ። ልማት ምንድነው? የልማት ተነሺ ወይስ በልማት ጠፊ? ያች ጦርነት የተካሄደባት የትግራዩዋ ዓድዋ ዙሪያዋን በጦርነት እሳት ተቃጥላ ባልዳነችበት በዚህ ወቅት፣ ይኼኛውን የፒያሳ የዓድዋ ሙዚየም እንዴት እንየው? የመጣልን መክሊት ነው ወይስ የመጣብን መዓት? ይላሉ… ይጠይቃሉ… መልስ የለም…  

ይህ ሰዓት በስብርባሪ ታሪክ ፊት ቆሞ እማኝነት መስጠትን ግድ ይላል። ከዘልማዱ የታሪክ አጻጻፍ በተለየ ሁኔታ፣ ጊዜ አልፎ ሁኔታዎች “ታሪክ” እስኪሆኑ ከመጠበቅ ተላቅቀን ዛሬን ከትላንት ጋር ማስተሳሰር ያሻናል። ታሪክ የትላንት ድርብርብ ጊዚያትና ሥፍራዎች እየታመቁባት እንደ እሳተ ገሞራ በየእግራችን ሥር በመፈንዳት፣ በዕለት ሕይወታችን ላይ እየቀለጠች የምትፈስ የዛሬ ጉዳይ ነች። እናም ይህ ጽሑፍ ዛሬ በአደባባይ ስለማኅበራዊ፣ ባህላዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ እውነት እንድንነጋገርና ውሳኔያችንን በጋራ ያማረ እንድናደርግ ለሁላችንም በተለይ ለመንግሥት የሚደረግ ጥሪ ነው። ይህንንም ተንተርሼ ስለሐኪም ወርቅነህ እሸቴ ቤት ታሪካዊነት እመሰክራለሁ።

ምክንያቱም ቤታቸው በቅርስነት ተመዝግቦ የነበረ ቢሆንም ዛሬ ቅርስነት የላቸውም ተብለው መፍረስ ከተፈረደባቸው መሀከል ሆኗል። ከ42 በቅርስነት የተመዘገቡ ሕንፃዎች ውስጥ 36ቱ ይፈርሳሉ የሚለው መርዶ ያስደነግጣል። ጥያቄው ደርሶ የመንገድና የሕንፃ፣ የቅርስና የቴክኖሎጂ ግንባታ ብቻ እንዳልሆነ፤ ይልቁንም በዚህ ዘመን ሰው መሆን ምንድነው ብለን እንድንጠይቅ ያሳስበናል። ሁኔታውን ሊረዱ የሚሹ ቀና ልቦች ካሉ በአክብሮት ተነጋግሮ ውሳኔን ለማስከለስ። ሁኔታውን ከቅርስም ባሻገር የነፃነት ጥያቄ አድርጎ በማየት፣ የአጠቃላይ የከተማ ልማትን ጉዳይ ከሥሩ እንዲጠራ ማድረግ መሠረታዊ ጉዳይ መሆኑን በማስመር ርዕሴን ተከትዬ ስለሐኪም ወርቅነህ እጽፋለሁ። ይህ ምስክርነት የግለሰቡን የዶ/ር ወርቅነህ እሸቴን ስም የማንቆለጳጰስ፣ የታላላቅ ሰዎችን የከፍተኛ መደብ ሕይወት የማስተጋባት፣ ወደ ትላንት ብቻ ከሚያነጉድ ትዝታ ጋር በፍቅር የመነሁለል ድሮ ናፋቂነት አይደለም። ታሪክን የምመለከትበት ዕይታ ከቶውኑም እዚያ እንድገኝ አይፈቅድልኝም። ይልቁንም በስተመጨረሻ የሐኪም ወርቅነህ እሸቴ ሕይወት የተቋጨባቸው መኖሪያ ቤቶቻቸው የኢትዮጵያን የዓለም አቀፍ ዲፕሎማሲ፣ የዓባይ ግድብና የባህር በር ታሪክ፣ የፀረ ባርነትና የፀረ ቅኝ ግዛት ትግልና የትምህርት ማስፋፋት ታሪኮችን አትመው ማቆየት የሚያስችሉ ሙዚየሞች ናቸው (ሊሆኑ ይገባቸዋል) ከሚል መነሻ ነው።

የሰውየውን የሕይወት ታሪክ ጠቅልሎ ከማቅረብ ይልቅ በመግቢያዬ ላይ ያሰፈርኳቸውን ዓውራ ነጥቦች የማፍታታት መስመርን ብከተልም፣ ሐኪም ወርቅነህ በእንግሊዝ ወታደሮች ከኢትዮጵያ ተነጥቀው ወደ ውጭ ይሰደዱ ዘንድ በልጅነታቸው የተፈረደባቸው መሆናቸውን በማውሳት ልጀምር። ወርቅነህ እሸቴ (አንድ ጸሐፊ የአባታቸው ስም እሸቱ ነው ይላሉ) ከእናታቸው ወ/ሮ ደስታ ወልደ ማሪርያምና ከአባታቸው ነጋድራስ እሸቴ ወልደ ማሪያም ጥቅምት 12፣ ቀን 1857 ዓ.ም. ነው ጎንደር ከተማ ወስጥ የተወለዱት። አፄ ቴዎድሮስን ‘የወጡበት ተራራ ድርሰ ወጥቼ አንበረከካለሁ’ ያለው የእንግሊዝ ጦር ከህንድ ተንስቶ መቅደላ ሲዘልቅ፤ የወርቅነህ እናትና አባት የግድ መቅደላ ተገኙ። ከሦስት ዓመት ከመንፈቅ ልጃቸው ከወርቅነህ ጋር። ነጭ ከጥቁር ሳንጃ ለሳንጃ ሲሞሻለቁ፣ የቴዎድሮስ ልጅ ልኡል ዓለማየሁና ወርቅነህ ቤተሰቦቻቸውን አጡ። እናም ሁለቱም ሕፃናት በእንግሊዝ ወታደሮች እጅ ወደቁ። ወርቅነህን መጀመርያ የወሰደው እንግሊዛዊ ወታደር ኮሎኔል ቻምበርሌይን ይባላል። በኋላ ኮሎኔል ቻርለስ ማርቲን ለተባለ ሌላ ወታደር አሳልፎ ሰጠው። ለዚያ ነው ሐኪም ወርቅነህ እሸቴ (ዶ/ር) ቻርለስ ማርቲን በሚልም ስም ሲጠሩ የኖሩት።

የእንግሊዙ ጦር አፄ ቴዎድሮስ የራሳቸውን ሕይወት ማጥፋታቸውን ካየ በኋላ ‘ሳያሸንፍ አሸንፎ’ ወደ መጣበት ሲመለስ ብላቴናው ወርቅነህ አብሮ ህንድ ገባ። ትንሹ ወርቅነህ በመጀመሪያ ራዋልፒንዲና አርሚስታር በተባሉ የሚሽን ትምህርት ቤቶች ከተማረ በኋላ በ1869 ዓ.ም. በላሆር ሜዲካል አካዳሚ ኮሌጅ ገብቶ ሕክምናን አጠና። ሐኪም ወርቅነህ በረዳት የቀዶ ጥገና ሐኪምነትም አንቱ መባል ጀመሩ። በኋላም ወደ ስኮትላንድ በመሄድ የሕክምና ትምህርታቸውን አሻሽለው በወርኃ ታኅሳስ 1883 ዓ.ም. በበርማ የሕክምና መኮንንና የቀዶ ጥገና ሐኪም በመሆን የእንግሊዝን ኢምፓየር አገለገሉ።  

በታሪካቸን የመጀመሪያው የሕክምና ዶክተር እየተባሉ የሚጠቀሱት ሐኪም ወርቅነህ ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ ኢትዮጵያ የተመለሱት በ1891 ዓ.ም. ነበር። (ከዚያ ቀድመው በዓድዋ ጦርነት ግድም ለአገራቸው የሚሆኑ የሕክምና ቁሳቁሶችን ይዘው ወደ ኢትዮጵያ ለመግባት በዘይላ ወደብ አካባቢ ሙከራ አድርገው ነበር። አልተሳካላቸውም እንጂ።) ከቤተሰቦቻቸውና ከአፄ ምኒልክ ጋር ተገናኝተው ለአንድ ዓመት ያህል ከቆዩ በኋላ ወደ ህንድ ተመልሰዋል። በሰባት ዓመታቸው አካባቢ ዳግም ወደ አዲሰ አበባ ሲመለሱ፣ የእንግሊዝ ለጋሲዮን የሕክምና ባለሙያ የነበረውን ዶ/ር ዌክማንን ተክተው ሠርተዋል። አፄ ምኒልክ ታመው አልጋ የዋሉበትና ቀድሞ ያክማቸው የነበረው ጀርመናዊው ሐኪም ዚንትግራፍ ከሥራው የተሰናበተበት ጊዜ ስለነበር፣ ሐኪም ወርቅነህ ንጉሱን ማከም ጀመሩ። በዚህ ቆይታቸው ወቅት ነበር ሐኪም ወርቅነህ እሸቴ ወ/ሮ ቀፀላ ቱሉን ያገቡት። በወቅቱ ታላቅ ከሚባሉት የጦር መሪ የሚወለዱት ወ/ሮ ቀፀላ ቱሉ ወደፊት ንግስት ሆነው ወደ ሥልጣን የሚመጡትን ወይዘሮ ዘውዲቱ ምኒልክን በደንገጡርነት ያገለግሉ ነበር።

አባታቸው ፊት አውራሪ ቱሉ ‘ልጄን ፈረንጅ ለሆነ ኢትዮጵያዊ’ አልሰጥም ብለው ያንገራገሩበት አንድ ምክንያት የቻርለስ ማርቲን (ወርቅነህ እሸቴ) በእንግሊዝ ኢምፓየር ባህል ውስጥ ማደግና ከኢትዮጵያ በቋንቋም ሆነ በሌሎች ነገሮች ራቅ ማለትን ተመልክተው ሊሆን ይችላል። ሐኪም ወርቅነህ ጋብቻው በመጨረሻ ተሳክቶላቸው ልጅም አፍርተው፣ አጼውን ለአራት ዓመታት ያህል ሲያክሙ ከቆዩ በኋላ፣ ንጉሡ ከመሞታቸው አንድ ዓመት በፊት ከባለቤታቸውና ዮሴፍ ከተባለው ልጃቸው ጋር ወደ በርማ አቀኑ፡፡ ወይዘሮ ቀፀላ በበርማ የነርሲንግ ትምህርትን ያጠኑ ሲሆን፣ ባለቤታቸውንም አማርኛና አፋን ኦሮሞን አስጠንተዋቸዋል።  

ብሔራዊ አገልግሎት፣ አስተዳደር፣ ትምህርትና የፀረ ባርነት ትግል

ሐኪም ወርቅነህ በርማ ከቤተሰባቸው ጋር ጥቂት ከኖሩ በኋላ በ1918 ዓ.ም. ወደ ኢትዮጵያ ተመለሱ። እሳቸው ወደ አገራቸው ሲመለሱ ያ ሶስተኛ ጊዜያቸው ነበር። ይህ ዘመናቸው በኢትዮጵያ በብዙ ዘርፎች ያገለገሉበት ነው። የመጀመሪያው የዳግማዊ ምኒልክ ሆስፒታል ሜዲካል ዳይሪክተር ሆኑ። በዓመቱ የፍል ውኃ አስተዳዳሪነትን ተሾሙ። በ1916 ዓ.ም. ተፈሪ መኮንን ትምህርት ቤት ሲከፈት ዋና ኃላፊ ሆነው ተመደቡ። ትምህርት ኢትዮጵያን ወደፊት የማራመድና ከድህነት እንድትላቀቅ የማድረግ ዓይነተኛ ሚና የነበረው መሆኑን ብቻ ሳይሆን፣ የአውሮፓን የቅኝ ግዛት ጥላ መግፈፊያ መሣሪያም እንዲሆን አበክረው ከወተወቱት፣ ከተናገሩትና ከጻፉት እንዲሁም በተግባር ከተፋለሙት ሰዎች መካከል አንዱ ነበሩ ሐኪም ወርቅነህ እሸቴ። በኋላም የጨርጨር አበጋዝነትን ተሹመው ከመሠረተ ልማት ግንባታ እስከ ባሪያ ንግድን የማስቆም እንቅስቃሴ፣ በርካታ ሥራዎችን ሠርተዋል። በዚያው ዘመን ማለትም በ1920 ዓ.ም. የዓለም ጂኦግራፊን ማስተማሪያ መጽሐፍ ደረሱ። የባሪያ ነፃነት አዋጅ በ1918 ዓ.ም. ሲታወጅ ከሌሎች ኃላፊነት ከሚሰማቸው የወቅቱ ልሂቃን ጋር የፍቅርና አገልግሎት ማኅበርን መሥርተው የባሪያ ንግድና ባርነት ይወገድ ዘንድ ቴዓትርን፣ ዲስኩርንና የአገር ውስጥና የውጭ ጋዜጣ ጽሑፎችን ለሕዝብ በማድረስ፣ እንዲሁም በዲፕሎማሲያዊ ሒደት ትግላቸውን አቀጣጠሉ።  

ከባርነት ነፃ ለወጡ ልጆችም ትምህርት ቤት መሥርተው የዕውቀትና የሙያ ክህሎት ለማስጨበጥ እልህ አስጨራሽ ትግል አደረጉ። ባሪያ ብለው በየቤታቸው የያዟቸውን ሰዎች አንለቅም፣ ነፃ አናወጣም የሚሉትን ባለሥልጣናት አዕምሮ ለመለወጥ፣ የነቁትም ባሪያ ብለው የያዟቸውን ነፃ እንዲያወጡ፣ ከባርነት እስራት የወጡትንም ለማቋቋም የገንዘብ መዋጮ እንዲያደርጉ ከባለቤታቸው ከነርስ ቀፀላ ቱሉና ከብዙ የቤተሰብና የወዳጅ ዘመድ እንዲሁም የጅበርተሰቡ አባላት ጋር አያሌ አስተዋጽኦ አበርክተዋል። ይህ ትግላቸው ባለ ሁለት ሰይፍ ነበር፡፡ በአገር ውስጥ የባርነት ቀንበርን ሲፋለሙ፣ በዓለም መድረክ ደግሞ ቅኝ ግዛትን እየታገሉ ነበር። እንዴት ቢባል ጣልያን ኢትዮጵያን ለመውረር እንደ አንድ ሰበብ ስትጠቀም የነበረው ‘ኢትዮጵያ ባርነትንና የባሪያ ሽያጭን ከአገሯ አላጠፋችም፣ ስለዚህ እኔ ሄጄ በቅኝ ግዛት ላሠለጥናት፣ ባርነትንም ላጠፋ ይገባኛል’ እያለች በዓለም አደባባይ ኢትዮጵያን እያሳጣች ስለነበር ነው።

በዚያ ላይ በአገር ውስጥ ያሉት ንጉሣውያን ቤተሰቦች፣ ባላባቶችና የጦር መሪዎች ባሮችን ነፃ ማውጣት ኢትዮጵያን በሰበብ አድርጎ ሊገዛት ከተነሳ የቅኝ ገዥ ኃይል መከላከል ነው ቢባሉም በጄ የማይሉ ጨካኞችም ስለነበሩ፣ ሐኪም ወርቅነህ አንዳንዴ እንደ አሜሪካ ላሉ አገሮች እባካችሁ የኢትዮጵያን መሪዎች ገስፁልኝ እስከ ማለት ርቀው ይሄዱም ነበር (እሳቸውም ሊኮነኑባቸው የሚገቡ ስህተቶች ቢኖሩባቸውም፣ እዚህ የማነሳቸው በመልካም ጎኑ ለአገራችንና ለሕዝቦቿ ያደረጓቸውን አበርክቶዎች ነው)።  

የዲፕሎማሲ ዘመቻ፣ የዓባይ ግድብና የጦር መሣሪያ አሰሳ

በ1919 ዓ.ም. አልጋ ወራሽ ተፈሪ መኮንን ሐኪም ወርቅነህ እሸቴን ድርብርብ የዲፕሎማሲ ተልዕኮ አስጨብጠው ነበር ወደ አሜሪካ የሸኟቸው (ምንም እንኳን በቅድሚያ በልጆቻቸው ትምህርት ቤት ጉዳይ በአገረ እንግሊዝ ማለፍ የነበረባቸው ቢሆንም)። ወደ አሜሪካ የተጓዙበት ታሪክ ውስብስብ ነበር። ነገሩ እንዲህ ነው። ጥር 13 ቀን 1918 ዓ.ም. ከአውሮፓ በእንግሊዝ ለጋሲዮን በኩል ኢትዮጵያ የሰማችው ዜና ጥሩ አልነበረም። ‘ከኢትዮጵያ ልናገኝ ይገባናል’ ስለሚሉት ጥቅም ሁለቱ አውሮፓውያን መንግሥታት እንግሊዝና ጣልያን መዋዋላቸውን ነበር በደብዳቤ “ነፃ” ነኝ ለምትለው ኢትዮጵያ ያሳወቋት። እንግሊዝ በዓባይ ወንዝ በተለይ በጣና ላይ ግድብ መገንባት ትፈልጋለች። ጣልያን በበኩሏ የባቡር ሃዲድ መገንባት ነው የምትፈልገው፣ ከኤርትራ አስመራ ተነስቶ ሉግ እስከ ተባለው የጣልያን ሶማሌላንድ ደቡባዊ ድንበር ድረስ የሚዘልቅ የቅኝ ግዛት ሃዲድ።

ዓድዋ ላይ ድል አድርጌ ነፃነቴን አውጃላሁ በምትለው ኢትዮጵያ ላይ እንዲህ የአውሮፓን ጥቅሞች የሚያስቀድሙ፣ እሷን የሚያገሉ ብቻ ሳይሆኑ የሚገድሉ ውሎችን መመልከቱ አንጀት የሚያቆስል እውነት ነበር። ለዚያ ነው ተፈሪና ወርቅነህ ተማክረው አሜሪካንን በዲፕሎማሲ ሽብልቅ አስገብተው የዓባይን ግድብ አንድም የፀረ ቅኝ ግዛት ፖለቲካ አንድም የልማት ጥያቄ አድርገው ለተግባሩ መንቀሳቀስ የያዙት። ኢትዮጵያ ጉዳዩን ወደ ሊግ ኦፍ ኔሽንስ ወስዳ የአፍታ ፋታ ብታገኝም፣ አይቡ ዳኛ ቅቤው መልከኛ በሆነባት አውሮፓ ለዘለቄታው ከመበላት እንደማትድን ገብቷታል። እናም የእንግሊዝ ሴራ እያደር እየተገለጠላቸው የሄዱትን ሐኪም ወርቅነህ እሸቴንና ከተፈሪ መኮንን ትምህርት ቤት የቴዓትር ዝግጅት እስከ ፍቅርና አገልግሎት ማኅበር የሐኪሙ ቅን ወዳጅና አገልጋይ የሆነውን መስፍን ቀለመወርቅን ወደ አሜሪካ ፕሬዚዳንት ካልቪን ኩሊጅ ዘንድ ላከቻቸው።  

ሐኪም ወርቅነህ ከዚያ በፊት የነበሯቸውን የግንኙነት ድሮች በመጠቀም ጭምር ከአሜሪካ ባለ ሥልጣናት ጋር እየተገናኙ በብዙ ጉዳዮች ላይ መክረዋል። በኋይት ሃውስ ተገኝተውም ከአልጋ ወራሽ ተፈሪ ለአሜሪካው ፕሬዚዳንት ኩሊጅ የተላከውን ደብዳቤና የወርቅ ጋሻ እንዲሁም የራሳቸውን ንግግር አቅርበዋል። የዓባይ ግድብን ለማካሄድ ምህንድስናና ለግድቡ የሚሆን የባንክ ብድር ማፈላለግ፣ የተማሩ አፍሪካ አሜሪካውያንን ለሥራ መመልመል፣ የጦር መሣሪያ ግዥ መፈጸምና ሌሎችም ዓላማዎቻቸውን በበጎ እንደሚያዩአቸውና የተሳኩም እንዲሆኑላቸው ፕሬዚዳንቱ ለሐኪም ወርቅነህ ተመኝተውላቸው ነበር። (አሜሪካ በወቅቱ በኢትዮጵያ ላይ የነበረውን የመሣሪያ ማዕቀብ ጉዳዬ አላለችውም ነበር)። ሐኪም ወርቅነህ ከዋሽንግተን ወደ ኒው ዮርክ ተመልሰው የዎል ስትሪት የባንክ ባለሙያዎችን እንዲሁም ጄጂ ኋይት ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን የተሰኘውን ኩባንያ ኃላፊዎች አነጋግረው የኢትዮጵያን ፍላጎት አስረድተዋል።

የብድሩ ነገር የማይሆን ቢመስልም፣ ከኋይት ኩባንያ ጋር የዓባይ ግድብን የተመለከት ውል አስረው ተለያዩ። (ያ ውል እነ እንግሊዝን አሳብዷቸው ነበር)። በተጨማሪም ኢትዮጵያ ለእኔ የትኩረት አገር አይደለችም በማለት ከዚያ ቀደም የነበራትን ተወካይ በማንሳቷ አዲስ አምባሳደር በኢትዮጵያ ትሾም ዘንድ አሜሪካንን ማግባባቱም የሐኪም ወርቅነህ የተሳካ ተልዕኮ ነበር።   

ሌላኛው ተልዕኳቸው ኢትዮጵያ ማዕቀብ ከጣለችባት አውሮፓ ገለል ብላ የጦር መሣሪያ ግዥ እንድትፈጽም ማስቻል ነበር። በዚህ ረገድ ሐኪም ወርቅነህ በአንድ የሃምብልተን አርምስ ኩባንያ ተወካይ በኩል ከዚያ ቀደም አዲስ አበባ ላይ ጀምረውት የነበረውን ድርድር ቀጥለው፣ መሣሪያውን ብቻ ሳይሆን ለመሣሪያውም መግዣ የሚሆን ብድር በማፈላለግ ጉዳይ ላይ ሲወያዩ ከረሙ። ሐኪሙ ዲፕሎማት ጎን ለጎንም የረሚንግተንና ቶምሰን የአውቶማቲክ ጠመንጃ አምራች ኩባንያን እያነጋገሩ ነበር።  ጣልያን፣ ፈረንሣይ፣ አሊያም እንግሊዝ መሣሪያዎቹን ከወደብ ቢወርሷቸውስ የሚለው ጥያቄ አስጨናቂ ነበር። ለዚያም ነው ሐኪም ወርቅነህ ከኒው ዮርክ ወደ ዋሽንግተን ተመልሰው ከአሜሪካ ባለስልጣናት ጋር ዳግም መነጋገር ግድ የሆነባቸው። ጣልያንና ኢትዮጵያ የጦር መሣሪያ ግዥ እንዳይፈጽሙ ማዕቀብ ቢጣልባቸውም፣ ጣልያን መሣሪያ አምራችም ወራሪ ለመሆን ያቆበቆበችም አገር ነችና እንደ ኢትዮጵያ ችግር ውስጥ አልነበረችም። ስለዚህ ያ ተልዕኮ ለሐኪም ወርቅነህ ወሳኝና ፈታኝ ነበር። የትልቁ የጦር መሣሪያ ግብይት ነገር ባይሆንላቸውም፣ ኢትዮጵያ የጦር መሣሪያ ከአሜሪካ ገዝታ ማስገባት መቻሏን ለመፈተን ጥቂት መሣሪያ ገዝተው ተመልሱ። (ወደ ኢትዮጵያ ሲመለሱም ከእንግሊዝ ጉያ ሆነው የቀጥታ ጠላትስ ምን ይላል ማለትን ለማየት ትንሽ ቁጥር ያለው መሣሪያ ጨምረው ገዙ)። ሆኖም ግን ማዕቀቡ መሣሪያዎቹን ከጂቡቲ ሊያስልካቸው አልቻለም። ኢትዮጵያ እግር ተወርች ታስራ እስከ አፍንጫዋ የታጠቀችውን ጣልያንን በሩዋ ተቆልፎባት፣ ሌጣዋን እንድትጠብቅ ተፈረደባት። ሆኖም ግን እነ ሐኪም ወርቅነህ አገራቸውንና ሕዝባቸውን ከጠላት ለማዳን ያልፈነቀሉት ድንጋይ እንዳልነበር ታሪካቸው ያስረዳናል።  

ዘይላ የባህር በር ማግኘት እንደ ፀረ ቅኝ ግዛት ታክቲክ       

በተጣለባት ፍትሐዊ ያልሆነ ዕቀባ የተነሳ ‘ከነጮቹ ብድር የማግኘቱ ነገር ባይሳካና ጠላትን የመፋለሚያው የጦር መሣሪያ ጉዳይ ለኢትዮጵያ የህልም እንጀራ እንደሆነባት የሚቀጥል ከሆነ ምን እናድርግ?’ በሚለው ሐሳብ ዙሪያ ወርቅነህ እሸቴ አንድ ዕቅድ ነበራቸው። እሱም ኢትዮጵያ ራሷ የምትቆጣጠረው ወደብ እንድታገኝ ማድረግ ነው። ወርቅነህ ኢትዮጵያን ከእንግሊዝ፣ ጣልያንና ፈረንሣይ ክልከላና ቁጥጥር እያደር ነፃ የሚያወጣ፣ የራሷ የባህር በር እንደሆነ ታይቷቸው ነበር። ያም ሐሳብ ይሳካ ዘንድ በኤደን ባህረ ሰላጤ የሚገኘውና ገና በፊት በ19ኛው ምዕተ ዓመት መገባደጃ ላይ አይናቸውን ሳይጥሉበት አይቀርም የሚባለው የዘይላ ወደብ ከፍተኛ ሚና አለው በሚል አቅደው ይንቀሳቀሱበት ነበር። የዘይላ ወደብ በወቅቱ በእንግሊዝ ሶማሊያ ግዛት ውስጥ በቅኝ ግዛት የነበረ ሲሆን፣ ሐኪም ወርቅነህ ከእንግሊዞች ጋር የሚደረገውን ድርድር ቀደም ብለው በእነ አምባሳደር ሲድኒ ባርተን በኩል ጀምረውት ነበር።

አፄ ኃይለ ሥላሴም ዘይላ ሁነኛ መተናፈሻ ወደብ እንደምትሆን ታይቷቸው ነበርና ወርቅነህ ከእንግሊዞች ጋር ድርድሩን አጠንክረው እንዲገፉት ይወተውቷቸው ነበር። ለዚያም ነው ሐኪም ወርቅነህ ከእንግሊዙ አምባሳደር ጋር በ1924 ዓ.ም. በኅዳር ወር በተከታታይ ሦስት ጊዜ አግኝተውት ዘይላን በእጃቸው ለማስገባት ረዥም ንግግሮችን ሲያደርጉ የነበሩት። ሰኔ 5 ቀን 1925 ዓ.ም. ደግመው ሥር ሲድኒን አገኙት። አምባሳደሩ በዘይላ አቅራቢያ እንግሊዝ ለኢትዮጵያ የባህር በር ልትሰጣት ፍላጎት እንዳላት ከመጥቀስ ባሻገር፣ ሐኪም ወርቅነህ ለእንግሊዙ ጠቅላይ ሚኒስትር ራምሴ ማክዶናልድ ኦፊሴላዊ ደብዳቤ እንዲፅፉ አበረታቷቸው ነበር። ያንንም ተከትሎ  አፄ ሃይለ ስላሴ በ1926 ምን ሰጥተን ዘይላን እንቀበል በሚለው ጉዳይ ከእንግሊዝ ባለ ሥልጣናት ጋር እየተነጋገሩበት ነበር። እንግሊዞቹም በዘይላ አካባቢ ለኢትዮጵያ ሊሰጡ የሚችሉ ሦስት መተላለፊያ መስመሮችን እንደ አማራጭ አቅርበው ነበር፡፡

አምባሳደር ባርተን ለወርቅነህ አስደሳች ዜና አብስረዋቸውም ነበር። የእንግሊዙ ጠቅላይ ሚኒስትር ከኢትዮጵያ ተከፍሎ በሚሰጣት መሬት ምትክ ለኢትዮጵያ የባህር በር ለመስጠት መስማማቱን የሚገልጽ ዜና ነበር። ወርቅነህ የዜናውን ተግባራዊነት በተስፋ በሚጠባበቁበት ጊዜ ግን ኃይለ ሥላሴ እንግሊዞቹ ቃላቸውን እንደበሉ ነገሯቸው። ሆኖም የኢትዮጵያ የባህር በር ፍላጎትና የዘይላ ጉዳይ በ1927 ዓ.ም. በነሐሴ ወር አጋማሽ በተከታታይ በእንግሊዝ፣ ፈረንሣይና ኢጣልያ የሴራ ንግግሮች ላይ መስተጋባቱ ቀጠለ። ሙሶሎኒ ኢትዮጵያ ዘይላን ሲያምርሽ ይቅር በሏት አለ። እንዲያም ሆኖ ጉዳዩ  በታኅሳስ ወር ዳግም ተነስቶ ነበር። ምንም እንኳን ጥያቄው ለረዥም ዘመን ተድበስብሶ ቢቀርም፣ እስከዚያ ጊዜ ድረስ ሐኪም ወርቅነህ እሸቴ ጉዳዩን የሙጥኝ ብለው ይዘውት ነበር።   

ኢትዮጵያውያንና አፍሪካ አሜሪካውያን

የሐኪም ወርቅነህ ተጨማሪ ሚና የእንግሊዝኛ ቋንቋ ተናጋሪ የሆኑ መምህራንና የሌሎች ሙያ ባለቤቶችን ከአሜሪካ በተለይም ከአፍሪካ አሜሪካውያን መካከል መመልመል ነበር። ያም ይሳካ ዘንድ በተለያዩ አካባቢዎች እየተዘዋወሩ ሐሳባቸውን በሕዝብ ፊት አስረድተዋል። ከሄዱባቸውም ቦታዎች መካከል በግንባር ቀደምነት የምትጠቀሰውና በጥቁሮች የነፃነት ባህልና ጥበብ አምባነቷ፣ ስመ ጥር የሆነችው ሃርለም ብቻ ሳትሆን ኒው ኮንኮርድ፣ ኒው ዮርክ፣ ፊላዴልፊያ፣ ተስኪጊና ዋሽንግተን ዲሲም ተጠቃሾች ናቸው።

በዓድዋ ድል ማግሥት በዓለም የተበተኑ ጥቁሮች አይኖቻቸውን በኢትዮጵያ ላይ መጣል የጀመሩበት ቢሆን፣ ኢትዮጵያ ደግሞ ከክልሏ ውጭ ስላሉ ጥቁር ሕዝቦች የማወቅ ጉጉቷ የጨመረው በሃያኛው ክፍለ ዘመን የመጀመሪያዎቹ አሥርታት ላይ ነው ማለት እንደምንችል የታሪክ ጸሐፍት ያስረዳሉ። ለዚህም አንድ ማስረጃ የሚሆነው ኢትዮጵያ በ1911 ዓ.ም. ሦስት ተወካዮቿን ማለትም ብላቴን ጌታ ህሩይ ወልደ ሥላሴን፣ ደጅ አዝማች ናደው አባ ወሎንና ከንቲባ ገብሩ ደስታን ወደ እንግሊዝ፣ ፈረንሣይና አሜሪካ መላኳ ነው። ምንም እንኳን ጉዞው በመጀመሪያው ዓለም ጦርነት በለስ የቀናቸውን ምዕራባውያንን እንኳን ደስ አላችሁ የማለት ቢመስልም፣ አብሮ የኢትዮጵያን በዓለም ፖለቲካ ንቁ ተሳትፎ የማድረግ ሕልም የሚያንፀባርቅም ነበር። በተለይ የአሜሪካ ጉዞ ለኢትዮጵያውያኑ ኦፊሴሊያዊ መልዕክተኞች አዲስ ነበር። አሜሪካኖቹ በ1905 ዓ.ም. ነበር አዲስ አበባ ላይ የነበራቸውን ኤምባሲ በወቅቱ ኢትዮጵያ የንግድም ሆነ የፖለቲካ ጥቅም የምናገኝባት አይደለችም ብለው የዘጉት።  

በቀደመው የ1911 ዓ.ም. ጉዞ በከንቲባ ገብሩ ለአፍሪካ አሜሪካውያን የተደረገውንና ‘እባካችሁ ወደ ኢትዮጵያ መጥታችሁ ሥሩ’ የሚለውን ጥሪ እንደ መልካም መነሻ ብናየውም፣ ኢትዮጵያን ወሳኝ የኢኮኖሚና የፖለቲካ ወዳጅ አድርጎ ግንኙነቱን በማደስ ረገድ ሐኪም ወርቅነህ እሸቴ ከፍተኛ ሚና ተጫውተዋል (የእነ ከንቲባ ገብሩን ቀጣይ ሚና ሳንዘነጋ)። ከዚህም በላይ ጥቁር አሜሪካውያን ባለሙያዎችን በመመልመል የተጀመረው ታሪካዊ ሒደት ወደ ፖለቲካዊ ትብብር ይለወጥ ዘንድ እርሾ የጣሉት ሐኪም ወርቅነህ ናቸው። እሳቸው በ1919 ዓ.ም. ወደ አሜሪካ ጉዞ ባደረጉ ወቅት በኦሃዮ ስቴት ተማሪ ለነበረውና በኋላም በአሜሪካ የመጀመሪያው ኢትዮጵያዊ የሕክምና ተመራቂ ዶ/ር ለነበረው መላኩ በያን የኢትዮጵያና የአፍሪካ አሜሪካውያን ትስስር እያደገ ይመጣ ዘንድ ውሉን አስጨብጠውታል። ሐኪም ወርቅነህ መላኩን እንዲህ ብለውት ነበር፡ ‹‹ለአገርህ የምትከውንላት ታላቁ አገልግሎት ከአሜሪካና ከካሪቢያን አገሮች በሺዎች የሚቆጠሩ ጥቁር ሕዝቦች ወደ ኢትዮጵያ መጥተው በልማት እንዲያግዙን ማድረግ ነው፤›› ይህንን ነበር መላኩ በልቡ ፅላት አትሞ እስከ ሕይወቱ ፍፃሜ ከአፍሪካ አሜሪካውያን ጋር ለኢትዮጵያ የሠራው።

ምንም እንኳን የመላኩ ታሪክ በራሱ ትልቅ ድርሳን የሚበቃው ባይሆንም፣ እዚህ ጋር ማለት የምንችለው፣ እሱ አገሩ በጣልያን ፋሽስት ቅኝ ገዥዎች በተወረረች ሰዓት በእናት ምድሩ በአካል ተገኝቶ ከማገዝ ባሻገር፣ ጥቁር አሜሪካውያን የኢኮኖሚ ድቀት ከፈታው መዓረባቸው ላይ እየከፈሉ፣ የሕክምና መርጃ መሣሪያዎችን፣ መድኃኒቶችንና ሌሎች ዕርዳታዎችን አስጭነው ወደ ኢትዮጵያ ይልኩ ዘንድ የላቀ ተጋድሎ አድርጓል። ጥቁር አሜሪካውያን ከዚያም ባሻገር በሠልፍ እየተመሙ ወደ ኢትዮጵያ ዘምተን ለኢትዮጵያ ውድ ሕይወታችንን እንሰጥላታለን እያሉ ተመዝግበዋል። ከዚያም በላይ መላኩ የጦር ጀት አብራሪዎቹን ጁሊያንና ጆን ሮቢንሰንን ጨምሮ መምህር የሆነውን ሲሪል ፕራይስን፣ የጤና ባለሙያዎቹን ሪዩበን ያንግንና ጆን ዌስትን እንዲሁም ሌሎች አፍሪካ አሜሪካውያንን ወደ ኢትዮጵያ በመላክ ረገድ ከፍተኛ አስተዋጽኦ አድርጓል።

መላኩ በወቅቱ ከፍተኛ የሚባለው የቤተሰብ ጋብቻ ኢትዮጵያዊት ሴት ቢያጭለትም፣ አፍሪካ አሜሪካዊቷን ዶሮቲ ኃድሌይን አግብቶ ከእሷና ከብዙ ጥቁር አሜሪካውያንና የካሪቢያን ሰዎች ጋር የፀረ ቅኝ ግዛትና የነጭ የበላይነትን ሥርዓት እስከለተ ሞቱ ታግሎ ህልፈቱ እዚያው አሜሪካ በጥቁር ወገኖቹ መሀል ሊሆን በቅቷል።   

ሐኪም ወርቅነህ በሎንዶን ዓለም አቀፍ የፓን አፍሪካ ትግል    

ሎንዶን የአውሮፓ አንድ አገዛዝ ማእከል የመሆኗን ያህል የፀረ ፋሽስት ቅኝ አገዛዝ ትግል መናኸሪያም ነበረች። ኢትዮጵያን ለማንበርከክ የነጮች መዶላቻ ብትሆንም፣ የፓን አፍሪካ እንቅስቃሴ ማካሄጃ ሥፍራም ነበረች። ለዚያም ነው እነ ሐኪም ወርቅነህና አማኑኤል አብርሃም የኢትዮጵያን ድምፅ በአውሮፓ አንድ ማዕከል ለማስተጋባት ሲታገሉ፣ ከካሪቢያን፣ ከአፍሪካና ከሌሎችም ሥፍራዎች የተሰባሰቡት ጥቁሮች ስለኢትዮጵያ ድምፃቸውን ከፍ አድርገው ለማሰማት ሲረባረቡ የነበረው። እነዚህ ጉልህ ድምፆች ይሰሙበት ከነበሩት የጥቁሮች ማኅበራት መካከል በእነ ሲኤልአር ጀምስ፣ ፒተር ሚሊያርድ (ዶ/ር) ቲ አልበርት ሜሪሾው፣ ጆሞ ኬንያታ፣ ኤሚ አሽውድ ጋርቪይ፣ ሞሐመድ ሰይድ፣ ሳሙኤል ማኒንግና ጆርጅ ፓድሞር የተመሠረተው የአቢሲኒያ ዓለም አቀፍ አፍሪካውያን ወዳጆች ማኅበር (The International African Friends of Abyssinia – IAFA) ተጠቃሽ ነው። ይህ ማኅበር በኋላም የዓለም አቀፍ አፍሪካውያን ሰርቪስ ቢሮ ተሰኝቶና ፓድሞር ሊቀ መንበርነቱን ከጀምስ ተረክቦ ለኢትዮጵያ የሚያደርገውን ትግል ቀጥሎ ነበር። ከዚያም ከዴንማርክ ወደ ሎንዶን ሄዶ የተቀላቀላቸው የጉያና ተወላጁ መኮንን ድርጅቱን በገንዘብ ማሰባሰብና በአመራር በኩል በእጅጉ አገልግሏል።  

በነፃነቷ ማግሥት የኬንያ መሪ የሆነው ታጋዩ ኬንያታ በረዳት ጸሐፊነት አስተዋጽኦውን ማበርከቱን ሲቀጥል፣ ዋላስ ጆንሰን በዋና ጸሐፊነት እንዲሁም የባርቤዶስ ሠራተኛ ማኅበር ታጋዩ ክሪስ ጆንስ አስተባባሪ ሆኖ ሁሉም ስለኢትዮጵያ ይረባረቡ ነበር። የጉያና ተወላጁ መኮንን በሎንዶን የኢትዮጵያ ኤምባሲ ያሉ ኃላፊዎች አብረውት በቅርቡ ይሠሩ እንደነበር ሲናገር፣ ሲኤልአር ጀምስ በተለይ እንደ አባት ይመለከቷቸው ስለነበሩት ስለሐኪም ወርቅነህ እሸቴ ምስክርነቱን ይሰጥ ነበር። እሱና የማኅበሩ አባላት በኢትዮጵያውያኑ ዲፕሎማቶች ዘወትር ዕገዛ ይደረግላቸው እንደነበርና የኢትዮጵያ ኤምባሲ ሁሌም ለእነሱ ክፍት እንደነበር ያስረዳም ነበር።

በተለይም ሐኪም ወርቅነህ ሁሌም በራቸውን ክፍት አድርገው እየተቀበሉት እንደሚወያዩ መስክሯል። በሎንዶን አደባባዮች ስለኢትዮጵያ ሲጮህ፣ ሲሰብክና ጥቁር ወገኖችን ለትግል ሲያነሳሳ የነበረው ጀምስ በኋላ ላይ የጻፈውና ዘ ብላክ ጃኮቢንስ የተሰኘው መጽሐፉ የሄይቲን አብዮት የተመለከተ እንደሆነ ይታወቃል። ያም መጽሐፍ እሰከ ዛሬ ድረስ በዓለም ዙሪያ ዓለም አቀፋዊ ታሪክን፣ አብዮትንና ሰብዓዊነትን ደግሞ በመተለም ረገድ ወሳኝ ሚና እንደተጫወተ አለ። ጀምስ ዘ ብላክ ጃኮቢንስን ከመጻፉ በፊት ያንን ታሪክ በቴዓትር ድርሰትነት ጽፎት ሎንዶን ላይ እንዲተወን ሲያደርገው፣ የኢትዮጵያ በፋሽስት ኢጣልያ መወረር ነበር በልቡ የሚጉላላው። ጀምስ መንፈሱ በኢትዮጵያውያን ሥቃይ ከመሰቃየቱ ብዛት ለኢትዮጵያ ተሠልፌ ካልተዋጋሁ ብሎ ጥያቄውን ለሐኪም ወርቅነህ አቅርቦላቸው ነበር። የሚከተለው የጀምስ ደብዳቤ ያንን ፅኑ ታሪክ ያስረዳናል፡፡

[ለኢትዮጵያ] ለመዋጋት የመሻቴን ጉዳይ እንዳብራራ ይፈቀድልኝ ዘንድ በትህትና እጠይቃለሁ[።]

በዚህ ዓመት መጀመሪያ ላይ በአፄ [ኃይለ ሥላሴ] ወታደራዊ ኃይል ውስጥ ወይም በሌላ በሚሰጠኝ ቦታ ላይ ሆኜ አገልግሎቴን ለማበርከት የኢትዮጵያ ኤምባሲን ጠይቄ ነበር። […]

የነበረኝ ምኞት ወታደራዊ ኃይሉን መቀላቀል ነበር። ያንን ዕድል ባገኝ ኖሮ ከኢትዮጵያውያንና ሌሎች አፍሪካውያን ሕዝቦች ጋር የመገናኘት ዕድል ብቻ ሳይሆን ከተራ ተርታው ሰው ጋር የዓለም አቀፉን የኅብረተሰባዊነት ጉዳይ የመጋራት መልካም አጋጣሚም አገኝ ነበር። በኢጣልያ [የቅኝ ገዥ] ወታደሮችም መካከል የፀረ ፋሽስት ፕሮፓጋንዳን በማሠራጨት ረገድ አበርክትዎ ይኖረኝም እንደነበር እምነቴ ነው። […]

እንዳለመታደል ሆኖ አምባሳደር ዶ/ር ማርቲን [ሐኪም ወርቅነህ] ከኢጣልያ ጋር የሚደረገውን ትግል በተመለከት የእኔ ዕገዛ በዓለም አቀፍ የኢትዮጵያ ወዳጆች ማኅበር በኩል የበለጠ ፍሬያማ እንደሚሆን አስረዱኝ።    

ስለሐኪም ወርቅነህ እሸቴ ታሪክ ስናወሳ እንዲህ ያለውን ዓለም አቀፍ ያፓን አፍሪካ ትግል ጭምር ነው የምናነሳው። ከዚህም ጋር ተያይዞ ሐኪም ወርቅነህ የመንግሥት ተሿሚ ፖለቲከኞችን ብቻ ሳይሆን የተራማጅ እንግሊዛውያንን ትብብር ለመሻትና ለማደራጀት፣ እንዲሁም የተጀመሩ እንቅስቃሴዎችን ለማገዝ ደከመኝና ሰለቸኝ ሳይሉ ንብረታቸውን በመሸጥ ጭምር ለዘመናት ታግለዋል። በዚህ ረገድ የኢትዮጵያ የቁርጥ ቀን ወዳጅ ከነበረችውና አገራችን አብዝታ ልታስታውሳት ከሚገባት ሲልቪያ ፓንክረስት ጋር አያሌ ቁም ነገሮችን ከውነዋል።

አገራችን በጣልያን በተወረረችበትና በፋሽስቶች ቀንበር ሥር በወደቀችበት ሰዓት፣ ከኢትዮጵያ ዜናዎችን አሰባስበው ለሲልቪያ ከማቀበል አንስተው፣ እያደር ጠንካራና መራራ የሆኑ (በተለይ እንግሊዝ ተምረው አገራችንን ከጠላት እንከላከላለን ሲሉ ወደ ኢትዮጵያ በመመለስ በኅቡዕ ይታገሉ የነበሩት ሁለቱ ልጆቻቸው ዮሴፍና ቢንያም በጣልያኖች መገረፍና መደብደብ ብቻ ሳይሆን በየካቲት 12 ጭፍጨፋ ወቅት በመገደላቸውም ጭምር) በተለያዩ ርዕሶች ላይ በኃይልና በጭካኔ የመጡብን ቅኝ ገዥዎች በኃይል ካልሆነ እንደማይመለሱ የሚያስረዱ ጽሑፎችን እያሰናዱ ለሲልቪያ ፓንክረስት ዝነኛ የጭቁኖች ድምፅ ኒውስ ኤንድ ቪውስ ያቀርቡ ነበር። ከዓለም ታጋዮች ጋር ሆነው ስለኢትዮጵያውያን ዓለምን ለመድረስ ይጣጣሩ ነበር።   

 እንዲህ ያሉና ተነግረው የማያልቁ ታሪኮችን የተሸከሙ ሰዎችንና ቤቶችን ነው በአሁኑ ሰዓት ባለ ሥልጣናት ቅርሶች አይደሉም የሚሉን። ይህንን የመሰለ ታሪክ በከተማው ማዘመን ሒደት ውስጥ ማካተት እንዴት ያለ ሀብት እንደሆነ እንዴት ልንገነዘበው አቃተን? ከዚያም ሲያልፍ ስለሰብዓዊነት ክብር በዓለም አቀፍ ደረጃ የተደረጉ ትግሎችን በቅርስና በትርክት እንዲሁም በቋሚ ኤግዚቢሽንነት ብናቆየው ቁሳዊም፣ ከቁስ በላይ የሆነም ትርፍ እንደምናገኝበት የት ቆመን በምን ፋታ እናስረዳ? ከላይ ያነበብናቸው ታሪኮች ከተሞቻችንንም ሆነ አገራችንን በማዘመን ሒደት ውስጥ ዋጋ የማይተመንላቸው ሀብቶች መሆናቸውን መመልከቱ ስለምን ተሳነን? የኪነ ሕንፃ ባለሙያዎች አሁን የተያዘው የኮሪዶር ልማት የሚሰኘው ፕሮጀክት የሐኪም ወርቅነህን የፒያሳ ቤት ትልቅ ማማ (Watching Tower) ሊገነባበት እንደሆነ ያስረዳሉ።

አያይዘውም ይህ ለማማ የታቀደ ሥፍራ በቀላሉ በዚያ “ከሕንፃ በላይ” በሆነ ቦታ ላይ ተስማምቶ ታሪክንም የሚያዩበት ሆኖ መሠራት እንደሚችል ይናገራሉ። ይህ የኪነ ሕንፃ መላ እንዳለ ሆኖ ጉዳዩን ስፋት ካለው ቅርስንና የዕለት ተዕለት ኑሮን እንዲሁም ማኅበራዊ ፍትሕን ባማከለ መልኩ ሁኔታዎቹን ቆም ብለን እናጢን። እባካችሁ ስሙን? እባካችሁ በአገር ውስጥም ሆነ በዓለም አቀፍ ደረጃ ቅርስን ለማዳን፣ ለማሰባሰብና ለመጠበቅ የሚፋለሙ ወገኖችን አዳምጡ? እባካችሁ ተቆርቋሪና ባለ መልካም ሕልም ባለሙያዎችን ስሙ? እባካችሁ ሕዝቡን አዳምጡ? ስለአጠቃላዩ ሕዝብ ሰብዓዊ ክብርና የዘለቄታ ነፃነት ከተራ ተርታው ሰው ጋር በዕርጋታ ምከሩ? ጥያቄዎቻችንን መልሱልን።

ልማት ማለት ምንድነው? የከተሜነት ሐሳብና የልማት ጥንስስ በእነማን ለምንና ለእነማን ነው የሚታሰበው? ስለከተማ ፅዳት ሲታሰብ “ቆሻሻ” የሚባሉ የኅብረተሰብ ክፍሎች አሉ? ብልጭልጩ ከተማ የእነማንን ሕይወት አጨልሞ ነው ሊንቦገቦግ የሚያስበው? (ዱባይን በምሳሌነት ማምጣትንስ ምን ይሉታል? በዚያ ላይ ዱባይ የንግድ ማዕከል ነኝ የማለቷን ያህል፣ የሺ ዘመናትን ሥልጣኔ የሚጠሩና የሚያስታውሱ፣ ታሪክ፣ ባህል፣ ቅርስና ትዝታዎቻቸውን ለመጠበቅ የሚረባረቡ ሰዎችም በብዙ ገንዘብና ሐሳብ የሚሠሯትስ ከተማ አይደለችም?) ማኅበራዊ ፍትሕ በነዚህ የከተማ ማዘመን ሥራዎች ውስጥ ቦታው ምንድነው? ከተማን ከ‘አላስፈላጊ’ ሰዎች አፅድቶ ለሕንፃና መንገድ ማስፋፊያ እንደሚዘጋጅ ባዶ ቦታ ማሰብ ምን ማለት ነው? ሰብዓዊነት ሥፍራዋ የት ነው? ዛሬን እየከፋን… ነገን ተማክረን በብዙ ሕልሞች ጥምረት እንድንሠራት ሳይደረግ ወይም እንዲያ የማድረግ መብታችንን በኃይልና በጥድፊያ ተነጥቀን ‘ወደፊት ትደሰቱበታላችሁ’ ብሎ ቋንቋ ምንድነው?   

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ሰላማዊ የፖለቲካ ትግልና ፈተናው

የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) የፖለቲካ ኦፊሰር የአቶ በቴ ኡርጌሳን...

አበጀህ ማንዴላ! አበጀሽ ደቡብ አፍሪካ!

በአየለ ት. የፍልስጤም ጉዳይ የዓለም አቀፍ ፖለቲካንም ሆነ የተባበሩት መንግሥታትን...

የውጭ ባለሀብቶች ለኢትዮጵያውያን ብቻ በተፈቀዱ የንግድ ዘርፎች እንዲገቡ የመወሰኑ ፋይዳና ሥጋቶች

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አዓመድ (ዶ/ር) የውጭ ኩባንያዎች በጅምላና ችርቻሮ...