Monday, April 15, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊዕውን የሆነው የኑክሌር ሕክምና ማዕከል

ዕውን የሆነው የኑክሌር ሕክምና ማዕከል

ቀን:

በየማነ ብርሃኑ

ፓዮኒር ዳያግኖስቲክ ማዕከል ከረዳት ኸልዝ ኬር ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር ጋር በኢትዮጵያ የግሉ የጤና ዘርፍ የመጀመርያ የሆነውን ኑክሌር ሕክምና ማዕከልን መጋቢት 14 ቀን 2016 ዓ.ም. አስመርቋል፡፡

ይህ ቴክኖሎጂ በሕክምና ዘርፍ ውሳኔዎችን ለመወሰን፣ በሽታን ቀድሞ በመለየት፣ የሰውነትን አሠራር ለመመርመርና ለማከም የሚረዳ መሆኑ በምረቃው ወቅት ተገልጿል፡፡ የኑክሌር ሕክምና ታካሚዎች ወደ ውጭ አገር መሄድ ሳይኖርባቸው አገልግሎቱን በአነስተኛ ዋጋ በአገር ውስጥ እንዲያገኙ ይረዳል፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

በዕለቱ የተገኙትም የጤና ሚኒስትር መቅደስ ዳባ (ዶ/ር) እንደተናገሩት፣ ሁለቱ ተቋማት የኑክሌር ሕክምና በአገር ውስጥ መስጠት መጀመራቸው የሚያስመሰግናቸው ነው፡፡ ሰዎች ለሕክምና ውጭ አገር ሄደው የሚያወጡትን ወጪና እንግልት ከማስቀረት አንፃር ትልቅ አስተዋጽኦ የሚያበረክት ነው ሲሉም ተናግረዋል፡፡

ተቋሙ በዚህ ዙሪያ የሕክምናና የመመርመሪያ አገልግሎት መስጠት ብቻ ሳይሆን ምርምሮችን በማካሄድ፣ ለአካዴሚክ ባለሙያዎች አቅማቸውን የሚያዳብሩበት ሥልጠና በመስጠትና ቴክኖሎጂውን በሳይንስ በመደገፍ ሕክምናውን ይበልጥ ማዘመን እንደሚኖርበት አስገንዝበዋል፡፡

ሚኒስትሯ አያይዘውም፣ በአሁኑ ወቅት የኑክሌር ሕክምናን በሦስት የመንግሥት የሕክምና ተቋማት ለማስጀመር እንቅስቃሴ እየተደረገ ይገኛል ብለዋል፡፡

በኢትዮጵያ ቴክኖሎጂ ባለሥልጣን የኖቲፊኬሽንና ኦትራይዜሽን ዳይሬክተር አቶ ስሩር ከድር እንደተናገሩት፣ በአገራችን የጨረርና የኑክሌር ቴክኖሎጂ ለተለያዩ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ግልጋሎቶች እየዋሉ ይገኛሉ፡፡ በሕክምናው ዘርፍ በሽታን ለመመርመርና ለማከም፣ በግብርናው ዘርፍ የእንስሳትና የዕፀዋት ዝርያዎችን ለማሻሻል፣ ለማራባትና ለማዳቀል ጉልህ አስተዋጽኦ ያበረክታል፡፡

ፓዮኒር የሕክምና ማዕከልም ለራዲዮሎጂ አገልግሎት የሚውሉ የሲቲ ስካንና የራጅ መሣሪያዎችን በማስመጣት ለአገልግሎት እንዲሰጡ ማድረጉ እየታየ ላለው የጨረር አመንጪዎች ሥርጭት ዕድገት ላይ ከፍተኛ ድርሻ ይኖረዋል፡፡

እንደ አቶ ሰሩር፣ ማዕከሉ የጨረር አመንጪዎች ሥርጭትና ትግበራ ለማከናወን ሲያቅድ የአገሪቱን ሕጎችና የባለሥልጣኑን የቁጥጥር መሥፈርቶች በማሟላት ነው፡፡

ካለው የሕዝብ ቁጥር አንፃር አሁን ያለው የሕክምና አገልግሎት በተለይም የራዲዮሎጂና የኑክሌር ሕክምና እጅግ አነስተኛ ነው ያሉት አቶ ሰሩር፣ በመንግሥት ብቻ ሊሸፈኑ የማይችሉ የጤና አገልግሎቶችን የግል የጤና ተቋማት የፓዮኒርን አርዓያ ተከትለው ሊሠሩበት እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡ መሥሪያ ቤታቸውም ይህን መሰል ሥራ ለሚሠሩ ተቋማት አስፈላጊውን ድጋፍና ዕገዛ እንደሚያደርግም ተናግረዋል፡፡

የፓዮኒር ዲያግኖስቲክና የረዳት ሄልዝኬር ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር መሥራች አቶ ብሩክ ፈቃዱ እንደተናገሩት፣ ከ18 ዓመት በፊት የተቋቋሙት ፓዮኒር ዳያግኖስቲክ ሴንተርና ኢንፍኒቲ አድቫንስ ቴክኖሎጂ ሶሉሽንስ ዓለም አቀፍ የጥራት ማረጋገጫ ሰርተፊኬት ያገኙና በየዘርፋቸው በኢትዮጵያ የመጀመሪያ የሆኑ ድርጅቶች ናቸው፡፡ ኢንፍኒቲ ከኢትዮጵያ ባሻገር በኬንያ ቅርንጫፍ በመክፈት ለ97 የመንግሥት ሆስፒታሎች የጥገና አገልግሎት መስጠት ጀምሯል፡፡

ከሁለት ዓመት በፊት የተቋቋመው ረዳት ሄልዝኬር ማዕከል በኢትዮጵያ የቴራዮፒክ ፕላዝማ አፓረስስ አገልግሎት መስጠት የቻለ ነው፡፡ ይህም ለተለያዩ በሽታዎች ፈውስ የሚሰጥ ሕክምና ሲሆን በተለይ ፓራላይዝ በሚያደርግ የነርቭ በሽታ ለተጠቁ ሕሙማን ፈውስ የሚሰጥ ነው፡፡

በፓዮኒር ዳያግኖስቲክ ማዕከል የኑክሌር ሜዲስን ስፔሻሊስት ናሆም ተስፋዬ (ዶክተር) እንደተናገሩት፣ በዓለም አቀፍ ደረጃ የኑክሌር ሜዲሲን ሕክምና ከ70 እስከ 80 ዓመት ዕድሜ ያስቆጠረ ነው፡፡

ሲቲ ስካን፣ ኤምአርዋይ፣ አልትራሳውንድ የሚባሉት የኢሜጅ ሞዳሊቲዎች ከመጀመራቸው በፊት አገልግሎቱ የነበረ ሲሆን፣ በኢትዮጵያ ከ1970 ዓ.ም. ጀምሮ በጥቁር አንበሳ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል መሠረታዊ በሚባል ደረጃ አገልግሎቱ ሲሰጥ ቆይቷል፡፡ ላለፉት አሥር ዓመታት ግን እንደ አገር ሕክምናው ተቋርጦ መቆየቱን ተናግረዋል፡፡

በኑክሌር ሜዲሲን ሕክምና ዘርፍ ከ17 በላይ ሐኪሞች ስፔሻላይዝ ማድረጋቸውን የተናገሩት ስፔሻሊስቱ፣ ፊዚስቶች፣ ቴክኖሎጂስቶችና ራዲዮ ፋርማሲስቶች በዚሁ ዘርፍ ሥልጠና ወስደው ይገኛሉ፡፡

ባለፉት ጥቂት ወራት ከ77 በላይ መሠረታዊ የኑክሌር ሕክምና የሚባሉትን የአጥንት፣ የታይሮይድ፣ የኩላሊትና የልብ ሕክምናዎችን በማዕከሉ መስጠቱን በአሁኑ ወቅትም ከ85 በላይ ታካሚዎች የታይሮይድ ካንሰር ሕክምና ተመዝግበው እየተጠባበቁ እንደሚገኙ ናሆም (ዶ/ር) ተናግረዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ቪር ጀነራል ትሬዲንግ ኃ/የተ/የግ/ማኀበር የጨረታ ማስታወቂያ

ቪር ጀነራል ትሬዲንግ ኃ/የተ/የግ/ማኀበር በገቢ እና በውጭ ንግድ እንዲሁም...

ያልተቃናው የልጆች የንባብ ክህሎት

አንብቦና አዳምጦ መረዳት፣ የተረዱትን ከሕይወት ጋር አዋህዶ የተቃና ሕይወት...

እንስተካከል!

ሰላም! ሰላም! ውድ ኢትዮጵያውያን ወገኖቼ እንዲሁም የሰው ዘር በሙሉ፣...

የሙዚቃ ምልክቱ ሙሉቀን መለሰ ስንብት

የኢትዮጵያ ዘመናዊ ሙዚቃ በ1950ዎቹ እና በ1960ዎቹ በኪነ ጥበባትም ሆነ...