Thursday, April 18, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ንግድ ባንክ የወሰዱበትን ገንዘብ ያልመለሱ 565 ግለሰቦች ስም ዝርዝር ይፋ አደረገ

ተዛማጅ ፅሁፎች

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በሲስተም ላይ በተፈጠረ ችግር ምክንያት ገንዘብ ወስደው ያልመለሱ 565 ግለሰቦችን ስም ዝርዝር በሒሳብ ቁጥራቸው ከቅርንጫፎቻቸው ጋር ይፋ ማድረግ ጀመረ፡፡

እስከ ቅዳሜ መጋቢት 21 ቀን 2016 ዓ.ም. ድረስ የወሰዱትን ገንዘብ ካልመለሱ ከእነ ፎቶግራፋቸው እንደሚታደኑ አስታውቋል፡፡

ባንኩ በቅርቡ የገጠመውን ችግር አስመልክቶ ማክሰኞ መጋቢት 17 ቀን 2016 ዓ.ም. በሰጠው መግለጫ፣ እስከ መጋቢት 16 ቀን 2016 ዓ.ም. በተለያዩ ዘዴዎች ማስመለስ የቻለው የገንዘብ መጠን 662 ሚሊዮን ብር ሲሆን፣ ይህም ተወስዶብኝ ነበር ካለው የገንዘብ መጠን 78 በመቶ ይሆናል ብሏል፡፡

የንግድ ባንክ ፕሬዚዳንት አቶ አቤ ሳኖ በሰጡት መግለጫ፣ ከባንኩ ያላግባብ የተወሰደው ወይም ሊወሰድ የነበረው የገንዘብ መጠን 801.4 ሚሊዮን ብር ነበረ ብለዋል፡፡

 ድርጊቱ በተፈጸመበት ዕለት የተጠቀሰውን ያህል ገንዘብ ያንቀሳቀሱ ደንበኞች ቁጥርም 25,761 መሆኑን፣ በተፈጠረው ክፍተት ተጠቅመው ገንዘብ ያላግባብ ወስደዋል ተብለው የተለዩት ከ15 ሺሕ በላይ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡ 

የገንዘብ አመላለሱን በተመለከተ በሰጡት ማብራሪያ ከ15 ሺሕ ደንበኞች ውስጥ ሙሉ በሙሉ ያላግባብ የወሰዱትን ገንዘብ የመለሱ ደንበኞች ቁጥር 9,281 እንደሆኑ፣ ካለባቸው ዕዳ የተወሰነውን የከፈሉት 5,160 መሆናቸውንና ደንበኞቹ ቀሪውን ለመመለስ መስማማታቸውን አስረድተዋል፡፡

ድርጊቱ በተፈጸመበት ምሽት ገንዘቡን ወስደዋል የተባሉ 25,761 ደንበኞች የፈጸሙት ግብይት ብዛት 238,293 እንደነበር አመልክተዋል፡፡ ይህ የግብይት መጠን በደንበኛ ሲካፈል በአማካይ 9.2 ጊዜ የሚደረግ ሲሆን፣ አንድ ደንበኛ በዚያ ሌሊት ከዘጠኝ ጊዜ በላይ ግብይት በመፈጸም ገንዘብ መውሰዱን ማረጋገጥ ተችሏል ብለዋል፡፡

ያልተመለሰው ቀሪ ገንዘብ በተመለከተን ከተሰጠው ማብራሪያ መረዳት እንደተቻለው፣ ወንጀሉ በተፈጸመበት ዕለት ወደ ሌሎች ባንኮች የተላለፈና ባንኮች እንዲያግዷቸው የተደረገ 118 ሚሊዮን ብር በመኖሩ ባንኮች በተጠየቁት መሠረት ገንዘቡን እንዲመልሱ ይጠበቃል ተብሏል፡፡ የንግድ ባንክ ሌሎች ባንኮች 118 ሚሊዮን ብር እንዲያግዱ በደብዳቤ የጠየቀ መሆኑን የገለጹት አቶ አቤ፣ ‹‹እስካሁን ምን ያህል እንደያዙልን ባይገለጽም መጠኑ ሲታወቅ ይህ ሲመጣ የሚፈለገው ገንዘብ ወደ 94 በመቶ አካባበቢ ተመላሽ ይሆናል ተብሎ ይጠበቃል፤›› ብለዋል፡፡

‹‹ግብይቱ የተካሄደው በዲጂታል ስለሆነና ማን እንዳካሄደው የሚታወቅ በመሆኑ፣ ገንዘቡን ይዞ መጥፋት አይችልም፡፡ ነገር ግን በዚያ ምሽት ከኤቲኤም የወጡ ገንዘቦች አሉ፡፡ በተለይ ግን በ567 ግለሰቦች የተወሰደን 9.8 ሚሊዮን ብር ግን የመመለሱ ነገር አጠራጣሪ ነው፤›› ብለዋል፡፡

ሙሉ ለሙሉ ገንዘብ እንዲመለስ እስከ መጨረሻው ጥረት እንደሚደረግ የተናገሩት ፕሬዚዳንቱ፣ 9.8 ሚሊዮን ብር የወሰዱ 567 ግለሰቦችን ግን ለባንኩ ሰጥተውት በነበረው አድራሻ ማግኘት አለመቻሉን ገልጸዋል፡፡

የግለሰቦቹን ስምና የሒሳብ ቁጥር ይፋ ማድረግ ገንዘብ ወሳጆቹ እንዲመልሱ የሚገፋ ይሆናል ተብሎ ታምኗል፡፡ ስማቸው ሲወጣ ወላጆችና ወዳጆቻቸው የሚከፍሉበት ዕድል ይኖራል ተብሎ ስለሚታሰብ፣ ይህ ዕርምጃ ቀሪውን ገንዘብ ለማስመለስ እንደሚያግዝ በንግድ ባንክ ታምኗል፡፡

‹‹በእኛ ግምት ግን በዚህ ሳምንት የተወሰደው ገንዘብ ሙሉ በሙሉ ይመለሳል የሚል እምነት አለን፤›› ያሉ አቶ አቤ፣ ሊቀር የሚችለው ገንዘብ ጥቂት ቢሆንም ይህም ቢሀን ምንም ዓይነት ገንዘብ እንዳይቀር ጥረት እንደሚደረግ ገልጸዋል፡

አሁን ባለው መረጃ የተወሰደው የገንዘብ መጠን በግል ብዙ የሚባል አለመሆኑን የገለጹት ፕሬዚዳንቱ፣ እስካሁን በግል ከተወሰደው ገንዘብ ውስጥ በአንድ ግለሰብ የተወሰደው ከፍተኛ የገንዘብ መጠን 304 ሺሕ ብር ነው ብለዋል፡፡

‹‹በተለይ ገንዘቡ የወጣበት መንገድ ጤናማ ባለመሆኑና እንደ የማይከፈል ብድር ስለማይታይ፣ አንድም ሳንቲም እንዲቀር ስለማንፈልግ ተከታትለን እንዲከፈል እናደርጋለን፤›› ብለዋል፡፡ እስካሁን ባለው የገንዘብ አመላለስ ሒደት የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ወላጆች በልጆቻቸው ተወስዷል የተባለውን ገንዘብ እየከፈሉ እንደሆነ ሳይጠቅሱ አላለፉም፡፡  

ባንኩ ያጋጠመው ችግር ሥራ ለማቀላጠፍ በተተገበረው አንድ ሶፍትዌር በትግበራው ሒደት በተፈጠረ ስህተት ስለመሆኑ ያስታወሱት አቶ አቤ፣ ይህም በወቅቱ ሲፈጸሙ የነበሩት ግብይቶችን በማባዛቱ ነው ብለዋል፡፡ ችግሩ እንዴትና ለምን ተከሰተ? እንዴት ሊሆን ቻለ? የሚለውን ጉዳይ በባንኩና ከውጭ በተቋቋመ ቡድን እየተመረመረ መሆኑን፣ ያልተገባቸውን ገንዘብ ለመውሰድ ተሳታፊ ናቸው ተብለው ከተለዩት ግለሰቦች ውስጥ 57 በመቶ የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች መሆናቸውን ማረጋገጥ መቻላቸውንም አቶ አቤ አብራርተዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች